በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነ አምላክ

ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነ አምላክ

ወደ አምላክ ቅረብ

ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነ አምላክ

ዮሐንስ 21:15-17

“ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ።” (መዝሙር 86:5) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ይህ አስደሳች ሐሳብ ይሖዋ አምላክ ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ተወዳዳሪ እንደማይገኝለት ያረጋግጣል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ያጋጠመው ነገር ይሖዋ ‘ይቅርታው ብዙ እንደሆነ’ በግልጽ ያሳያል።—ኢሳይያስ 55:7

ጴጥሮስ ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መካከል አንዱ ነበር። ያም ሆኖ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ በፍርሃት ተሸንፎ አንድ ከባድ ኃጢአት ፈጸመ። ይህ ሐዋርያ፣ ኢየሱስ በሐሰት ተከሶ ለፍርድ በቀረበበት ሸንጎ ግቢ ውስጥ ሳለ ኢየሱስን እንደማያውቀው ከአንዴም ሦስት ጊዜ ሽምጥጥ አድርጎ ካደ። ጴጥሮስ ኢየሱስን ፈጽሞ እንደማያውቀው በመናገር ለሦስተኛ ጊዜ ሲክደው ኢየሱስ ‘መለስ ብሎ ተመለከተው።’ (ሉቃስ 22:55-61) ይህ ሐዋርያ፣ ኢየሱስ ሲመለከተው ምን ተሰምቶት እንደነበር መገመት ትችላለህ? ጴጥሮስ፣ የፈጸመው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገነዘብ “ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።” (ማርቆስ 14:72) በጸጸት ስሜት የተዋጠው ይህ ሐዋርያ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ በመካዱ ከአምላክ ዘንድ ይቅርታ ማግኘት ይችል እንደሆነ እርግጠኛ አልነበረም።

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ከእሱ ጋር ያደረገው ውይይት ይቅርታ ስለማግኘቱ የነበረውን ጥርጣሬ እንዳስወገደለት ግልጽ ነው። ኢየሱስ አንድም መጥፎ ቃል አልተናገረውም፤ እንዲሁም አላወገዘውም። ከዚህ ይልቅ “ትወደኛለህን?” ሲል ጠየቀው። ጴጥሮስም “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት መለሰለት። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ ያንኑ ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ የጠየቀው ሲሆን ጴጥሮስም ተመሳሳይ መልስ ሰጠ፤ ምናልባት በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ስሜቱን ይበልጥ በሚገልጽ መንገድ መልስ ሰጥቶት ይሆናል። ኢየሱስም መልሶ “በጎቼን ጠብቅ” አለው። በመጨረሻም “ትወደኛለህን?” ሲል ለሦስተኛ ጊዜ በድጋሚ ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ዐዝኖ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ’” በማለት መለሰለት። ኢየሱስም “በጎቼን መግብ” አለው።—ዮሐንስ 21:15-17

ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚወደው እያወቀ የጠየቀው ለምን ነበር? ኢየሱስ ልብን ማንበብ ስለሚችል ጴጥሮስ እንደሚወደው ያውቅ ነበር። (ማርቆስ 2:8) ይሁን እንጂ ኢየሱስ እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቁ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ፍቅር ሦስት ጊዜ እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጥቶታል። ኢየሱስ “ጠቦቶቼን መግብ . . . በጎቼን ጠብቅ . . . በጎቼን መግብ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ንስሐ የገባው ሐዋርያ አሁንም እምነት የሚጣልበት ሰው እንደሆነ አረጋግጦለታል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ውድ ንብረቶቹን ማለትም በበግ የተመሰሉትን ተከታዮቹን እንዲንከባከብ ለጴጥሮስ መመሪያ እየሰጠው ነበር። (ዮሐንስ 10:14, 15) ጴጥሮስ፣ በኢየሱስ ዘንድ የነበረውን አመኔታ አሁንም ቢሆን እንዳላጣ ማወቁ እፎይታ እንዳስገኘለት ምንም ጥርጥር የለውም!

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ንስሐ የገባውን ይህን ሐዋርያ ይቅር ብሎታል። ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያትና መንገዶች ፍጹም በሆነ መንገድ ስላንጸባረቀ ይሖዋም ጴጥሮስን ይቅር እንዳለው በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። (ዮሐንስ 5:19) ይሖዋ ሰዎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው፤ እንዲያውም ንስሐ የሚገባን ኃጢአተኛ ‘ይቅር ለማለት’ ዝግጁ የሆነ መሐሪ አምላክ ነው። ታዲያ ይህ የሚያጽናና ሐሳብ አይደለም?