በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

 ይህን ያውቁ ኖሯል?

የሃይማኖት መሪዎች፣ ‘ራሱን የአምላክ ልጅ አድርጓል’ ብለው ኢየሱስን በከሰሱት ጊዜ ጳንጥዮስ ጲላጦስ የፈራው ለምን ነበር?ዮሐንስ 19:7

የሮም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ጁሊየስ ቄሳር ከሞተ በኋላ የአምላክነት ማዕረግ ሰጥቶት ነበር። የጁሊየስ ቄሳር የማደጎ ልጅና አልጋ ወራሽ የነበረው ኦክታቪያን ደግሞ ዲቪ ፊልየስ ማለትም “የመለኮት ልጅ” ወይም “የአምላክ ልጅ” የሚለው መጠሪያ ተሰጠው። ከዚያም ይህ የላቲን ስያሜ ሮማውያን ነገሥታት ብቻ የሚጠሩበት የማዕረግ ስም ሆነ። ሮማውያን በሠሯቸው መሠዊያዎች፣ ቤተ መቅደሶች፣ ሐውልቶችና ሳንቲሞች ላይ የተቀረጹ በርካታ ጽሑፎች ይህ ሐሳብ እውነት መሆኑን ያረጋግጣሉ። በመሆኑም አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ ራሱን ‘የአምላክ ልጅ’ አድርጓል ሲሉ የነገሥታቱን የማዕረግ ስም ለራሱ ወስዷል ብለው የከሰሱት ያህል ነበር፤ ይህ ደግሞ ከክህደት ተለይቶ የሚታይ አልነበረም።

ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ጢባሪዮስ፣ ዲቪ ፊልየስ የሚለውን የማዕረግ ስም ወርሶ ነበር። ጢባሪዮስ፣ ጠላቶቹ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሰዎች ከመግደል ወደኋላ የማይል ጨካኝ ንጉሥ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። በመሆኑም ጲላጦስ፣ ኢየሱስን አለማውገዙ ለቄሳር ታማኝ እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚያስቆጥረው አይሁዳውያን በተዘዋዋሪ መንገድ በተናገሩ ጊዜ ይህ ሮማዊ ገዥ “የባሰውኑ ፈራ።” በመጨረሻም በተጽዕኗቸው በመሸነፍ ኢየሱስ እንዲገደል ትእዛዝ አስተላለፈ።—ዮሐንስ 19:8, 12-16

ዘካርያስ፣ ጢሮስ በባቢሎናውያን ከጠፋች ከረጅም ጊዜ በኋላ ከተማዋ እንደምትጠፋ ትንቢት የተናገረው ለምን ነበር?

በሜድትራንያን ጠረፍ ላይ የምትገኘው የጥንቷ ጢሮስ ሁለት ቦታዎችን ታመለክት ነበር። አንደኛው በየብስ ሌላኛው ደግሞ በደሴት ላይ ይገኝ ነበር።

በአንድ ወቅት የጢሮስ ነዋሪዎች የእስራኤላውያን ወዳጆች ነበሩ። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ጢሮስ እየበለጸገች ስትሄድ በይሖዋ አምላክ ላይ ዓመጸች፤ እንዲያውም የእስራኤላውያንን ወርቅና ብር እስከ መዝረፍ ብሎም ሕዝቡን ለባርነት እስከ መሸጥ ደረሰች። (ኢዩኤል 3:4-6) ይህ ደግሞ የይሖዋን የቅጣት ፍርድ አስከትሎባታል። ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት ጢሮስ፣ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ እንደምትወድቅ ትንቢት አስነገረ። ይህ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ካጠፋ በኋላ ሠራዊቱን ይዞ ወደ ጢሮስ አመራ።—ኢሳይያስ 23:13, 14፤ ኤርምያስ 27:2-7፤ ሕዝቅኤል 28:1-19

ሽንፈት የገጠማቸው የጢሮስ ነዋሪዎች ንብረታቸውን ይዘው በደሴቲቱ ላይ ወደምትገኘው ጢሮስ ሸሹ። ባቢሎናውያን በየብስ ላይ ትገኝ የነበረችውን ከተማ የፍርስራሽ ክምር አደረጓት። ከ100 ዓመታት ገደማ በኋላ፣ ይሖዋ በጢሮስ ላይ የሚወስደውን የሚከተለውን የፍርድ እርምጃ እንዲናገር ነቢዩ ዘካርያስን በመንፈሱ አነሳሳው:- “ጌታ ግን ሀብቷን ይወስዳል፤ በባሕር ያላትንም ኀይል ይደ[መ]ስሳል፤ እርሷም በእሳት ፈጽማ ትጠፋለች።”—ዘካርያስ 9:3, 4

በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ታላቁ እስክንድር በደሴቲቱ ላይ የምትገኘውን ከተማ ባጠፋ ጊዜ የዘካርያስ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። እስክንድር ይህን ለማድረግ ቀደም ሲል ከጠፋችው የጢሮስ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ድንጋይና እንጨት በማምጣት ወደ ደሴቲቱ የሚወስድ 800 ሜትር ርዝመት ያለው መተላለፊያ ሠራ። ሕዝቅኤልም ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።—ሕዝቅኤል 26:4, 12

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የጢሮስ ወረራ”

[ምንጭ]

Drawing by Andre Castaigne (1898-1899)