በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኖኅ የጥፋት ውኃ በእርግጥ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ነበረው?

የኖኅ የጥፋት ውኃ በእርግጥ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ነበረው?

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የኖኅ የጥፋት ውኃ በእርግጥ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ነበረው?

የኖኅ የጥፋት ውኃ ከተከሰተ ከ4,000 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በመሆኑም ስለ ሁኔታው ሊነግረን የሚችል ከጥፋቱ የተረፈ ሰው የለም። ይሁንና የጥፋት ውኃው በዘመኑ ረጅም የነበረውን ተራራ እንደሸፈነ የሚገልጽ በጽሑፍ የሰፈረ ዘገባ ይገኛል።

የታሪክ ዘገባው እንዲህ ይላል:- “የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ . . . ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ [ሄደ፤] . . . ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ 7 ሜትር ያህል ከፍ አለ።”—ዘፍጥረት 7:17-20

አንዳንድ ሰዎች የጥፋት ውኃ መላውን ምድር እንደሸፈነ የሚገልጸው ሐሳብ የፈጠራ ታሪክ አሊያም የተጋነነ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ሐቁ ግን ከዚህ የተለየ ነው! እንዲያውም አሁንም ቢሆን ምድር በውኃ የተጥለቀለቀች ነች ሊባል ይችላል፤ ሰባ አንድ በመቶ የሚሆነው የምድር ክፍል በውቅያኖስ የተሸፈነ ነው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ ምድርን ያጥለቀለቃት ውኃ አሁንም አለ። በተጨማሪም በተራሮች አናት ላይም ሆነ በዋልታዎች አካባቢ የሚገኘው የበረዶ ግግር ቢቀልጥ ውኃው ኒው ዮርክንና ቶኪዮን የመሳሰሉ ከተሞችን ሊውጥ ይችላል።

የሰሜን ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስን መልክዓ ምድር የሚያጠኑ የሥነ ምድር ተመራማሪዎች፣ ቀደም ባሉት ዘመናት በተለያዩ ጊዜያት 100 የሚያህሉ የውኃ መጥለቅለቅ አደጋዎች በዚህ አካባቢ ተከስተው እንደነበረ ያምናሉ። ከእነዚህ የውኃ መጥለቅለቅ አደጋዎች አንዱ 600 ሜትር የሚደርስ ከፍታ የነበረው ሲሆን በሰዓትም 105 ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር። ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር ኩብ መጠን ያለው ይህ ውኃ ከሁለት ትሪሊዮን ቶን በላይ ይመዝናል። እንዲህ ያሉት ግኝቶች በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ውኃ ምድርን አጥለቅልቋት ሊሆን ይችላል ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርገዋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች ግን የጥፋት ውኃው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደነበረው ፈጽሞ አይጠራጠሩም። ኢየሱስ ወደ አምላክ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” መሆኑን ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ታዲያ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች የፈጠራ ታሪኮች ከሆኑ ጳውሎስ ለኢየሱስ ተከታዮች ሃይማኖታዊ እውነቶችን እንዴት ሊያስተምራቸው ይችላል?

ኢየሱስ የጥፋት ውኃ እንደተከሰተ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደነበረው ጭምር ያምን ነበር። ኢየሱስ፣ ሥልጣን በሚይዝበትና የዓለም መጨረሻ በሚቀርብበት ወቅት የሚኖሩት ሁኔታዎች በኖኅ ዘመን ከነበሩት ጋር እንደሚመሳሰሉ ትንቢት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:37-39) በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ “በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ” በማለት በኖኅ ዘመን ስለተከሰተው የጥፋት ውኃ ጽፏል።—2 ጴጥሮስ 3:6

ስለ ኖኅም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለተከሰተው የጥፋት ውኃ የሚናገረው ዘገባ የፈጠራ ታሪክ ቢሆን ኖሮ ጴጥሮስና ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች የሰጡት ማስጠንቀቂያ ትርጉም አይኖረውም ነበር። የጥፋት ውኃው የፈጠራ ታሪክ ነው የሚለው አመለካከት አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ማስጠንቀቂያዎች በተመለከተ ግራ እንዲጋባ ያደርገዋል። እንዲሁም በቅርቡ ከሚመጣውና ከኖኅ የጥፋት ውኃ የበለጠ ጥፋት ከሚያስከትለው መከራ የመዳን አጋጣሚውን አደጋ ላይ ይጥለዋል።—2 ጴጥሮስ 3:1-7

አምላክ ለሕዝቦቹ ምሕረት እንደሚያሳይ ሲገልጽ ‘የኖኅ ውሃ ምድርን ዳግመኛ እንዳያጥለቀልቃት ምያለሁ፤ አሁንም እናንተን ዳግም እንዳልቈጣ፣ እንዳልገሥጻችሁም ምያለሁ’ በማለት ተናግሮ ነበር። የጥፋት ውኃው ምድርን ማጥለቅለቁ እውነት እንደሆነ ሁሉ አምላክ በእሱ ለሚታመኑ ሰዎችም ፍቅራዊ ደግነቱን እንደሚያሳይ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳይያስ 54:9