በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ማንኛውንም አምልኮ ይቀበላል?

አምላክ ማንኛውንም አምልኮ ይቀበላል?

 አምላክ ማንኛውንም አምልኮ ይቀበላል?

ፕሮፌሰር አለስተር ሃርዲ፣ ዘ ስፒሪቹዋል ኔቸር ኦቭ ማን በተባለው መጽሐፍ ላይ “ሃይማኖት በሰው ልጆች ደም ውስጥ የሰረጸ ነገር ነው” በማለት ተናግረዋል። በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናትም ይህን ሐሳብ ይደግፋል። ጥናቱ፣ 86 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የራሱ ሃይማኖት እንዳለው ዘግቧል።

በተጨማሪም ይህ ጥናት እነዚህ ሰዎች የሚከተሏቸው እምነቶች በ19 ዋና ዋና ሃይማኖቶች ውስጥ እንደሚፈረጁ ገልጿል፤ ከእነዚህም መካከል ክርስቲያን ነን የሚሉት በ37,000 የክርስትና እምነት ድርጅቶች ውስጥ እንደታቀፉ ጠቁሟል። ይህንን ማወቅህ ‘እነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጥርብህ ይሆናል። በእርግጥ አምላክን በፈለግነው መንገድ ብናመልከው ችግር አለው?

በጣም አስፈላጊ የሆነውን ይህን ጥያቄ በራሳችን አመለካከት ተመርኩዘን ወይም በስሜት ተነሳስተን መመለስ አንችልም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ማወቃችን አስፈላጊ ነው። የአምላክን አመለካከት ለማወቅ ደግሞ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:17) ታማኝ የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስም “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት . . . ይጠቅማሉ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሁሉም የአምልኮ ዓይነቶች እንዳልሆኑ ይናገራል። ከዚህም በላይ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስለነበራቸውና በእሱ ዘንድ ስለተወገዙ የአምልኮ ዓይነቶች የሚናገሩ ምሳሌዎችን ይዟል። እነዚህን ምሳሌዎች በጥንቃቄ መመርመራችን አምላክን የሚያስደስት አምልኮ በማቅረብ ረገድ ምን ማድረግ እንዳለብንና እንደሌለብን እንድናውቅ ያስችለናል።

ጥንታዊ ምሳሌ

ይሖዋ አምላክ፣ እስራኤላውያን እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ በርካታ ሕጎችን በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል። እስራኤላውያን በተለምዶ የሙሴ ሕግ ተብለው የሚጠሩትን እነዚህን ሕጎች ሲታዘዙ አምላክ፣ ሕዝቦቹ አድርጎ የሚቀበላቸው ከመሆኑም በላይ ይባርካቸው ነበር። (ዘፀአት 19:5, 6) እነዚህ ሕዝቦች የአምላክን በረከት የማግኘት አጋጣሚ ቢኖራቸውም ተቀባይነት ባለው መንገድ እሱን ማምለካቸውን አልቀጠሉም። እንዲያውም በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝቦች ሃይማኖታዊ ልማድ በመከተል በተደጋጋሚ ለይሖዋ ጀርባቸውን ሰጥተዋል።

በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በነቢዩ ሕዝቅኤልና በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን በርካታ እስራኤላውያን የአምላክን ሕግ ችላ በማለት በዙሪያቸው ካሉት ብሔራት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተው ነበር። እስራኤላውያን የእነዚህን ብሔራት ልማድ በመከተልና በበዓላቸው ላይ በመካፈል አምልኮ መቀላቀል ጀመሩ። አብዛኞቹ እስራኤላውያን “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” ይሉ ነበር። (ሕዝቅኤል 20:32፤ ኤርምያስ 2:28) ለይሖዋ አምልኮ እንደሚያቀርቡ ቢናገሩም ‘ጣዖታትንም’ ያመልኩ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ልጆቻቸውን እንኳ ለጣዖታት እስከ መሠዋት ደርሰው ነበር።—ሕዝቅኤል 23:37-39፤ ኤርምያስ 19:3-5

አርኪኦሎጂስቶች እንዲህ ዓይነቱ አምልኮ፣ ሃይማኖትን መቀላቀል ማለትም የተለያዩ አማልክትን በአንድ ጊዜ ማምለክ እንደሆነ ይናገራሉ። በርካታ ሰዎች፣ የተለያዩ እምነቶች ባሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ ሃይማኖትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለመቀበል ሰፋ ያለ አመለካከት ሊኖረን ይገባል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች አምላክን ደስ ባላቸው መንገድ ቢያመልኩት ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማቸዋል። ይህ በእርግጥ ትክክል ነው? የእነሱን አመለካከት የማይቀበል ሰው ጠባብ አስተሳሰብ አለው ማለት ነው? ታማኝ ያልነበሩት እስራኤላውያን ሃይማኖትን በመቀላቀል የፈጠሩት እምነት ምን ገጽታዎች እንደነበሩትና ምን እንዳስከተለባቸው እስቲ እንመልከት።

 እስራኤላውያን አምልኮ መቀላቀል ጀመሩ

እስራኤላውያን፣ ቅልቅል አምልኮ በዋነኝነት የሚያቀርቡት ‘በኰረብቶች’ ወይም በአካባቢያቸው በሚገኙ ቅዱስ ሥፍራዎች ሲሆን በእነዚህ ቦታዎችም መሠዊያዎች፣ ማጠኛዎችና የድንጋይ አምዶች ይገኙ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከእንጨት የተሠሩ የማምለኪያ አምዶች የነበሩ ሲሆን እነዚህም የከነዓናውያን የመራባት አምላክ በሆነችው በአሼራ ምስል የተቀረጹ ሳይሆኑ አይቀሩም። በይሁዳ እንዲህ ያሉ የመስገጃ ኮረብቶች በብዛት ይገኙ ነበር። ሁለተኛ ነገሥት 23:5, 8 እንደሚገልጸው ‘በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ የሚገኙት ኰረብቶች ከጌባ [ከሰሜናዊው ድንበር] እስከ ቤርሳቤህ [ደቡባዊው ድንበር] ድረስ’ ተስፋፍተው ነበር።

እስራኤላውያን በእነዚህ የመስገጃ ኰረብቶች ላይ “ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት [ያጥኑ]” ነበር። “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን” የሚያስተናግዱ ክፍሎች የነበሯቸው ሲሆን ልጆቻቸውንም “ለሞሎክ በእሳት” ይሠዉ ነበር።—2 ነገሥት 23:4-10

አርኪኦሎጂስቶች በሰው መልክ የተሠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሸክላ ቅርጻ ቅርጾችን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አግኝተዋል፤ በተለይ ደግሞ እነዚህን ቅርጻ ቅርጾች ያገኙት በመኖሪያ ቤቶች ፍርስራሽ ውስጥ ነው። አብዛኞቹ ምስሎች ትልልቅ ጡቶች ባሏት እርቃኗን በሆነች ሴት ቅርጽ የተሠሩ ናቸው። ምሑራን፣ እነዚህ ቅርጻ ቅርጾች የመራባት አምላክ የሆኑት የአስታሮት እና የአሼራ ምስሎች እንደሆኑ ገልጸዋል። እነዚህ ምስሎች “ሴቶች እንዲጸንሱና ልጆች እንዲወልዱ እንደሚያስችሉ” ይታመናል።

እስራኤላውያን ቅልቅል አምልኮ የሚያካሂዱባቸውን እነዚህን የመስገጃ ኰረብቶች እንዴት ይመለከቷቸው ነበር? የሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ስተርን፣ አብዛኞቹ የመስገጃ ኰረብቶች “ለያህዌህ [ለይሖዋ] የተወሰኑ” ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ተናግረዋል። አርኪኦሎጂስቶች ቁፋሮ ባካሄዱባቸው ቦታዎች የተገኙት ጽሑፎችም ይህን ሐሳብ የሚደግፉ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛው ጽሑፍ “በሰማርያው ያህዌህና የእሱ በሆነችው አሼራ [ስም] እባርክሃለሁ” የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “በቴማኑ ያህዌህና የእሱ በሆነችው አሼራ [ስም] እባርክሃለሁ!” ይላል።

እነዚህ ምሳሌዎች፣ እስራኤላውያን የይሖዋ አምላክን ንጹሕ አምልኮ አስነዋሪ ከሆነው አረማዊ አምልኮ ጋር እንዴት እንደቀላቀሉት ያሳያሉ። ይህ ደግሞ እስራኤላውያን በሥነ ምግባር እንዲረክሱና በመንፈሳዊ ጨለማ እንዲዋጡ አድርጓቸዋል። ታዲያ አምላክ እንዲህ ያለውን ወራዳ አምልኮ እንዴት ተመለከተው?

ይሖዋ አምልኮን በቀላቀሉ ሰዎች ላይ የወሰደው እርምጃ

አምላክ፣ እስራኤላውያን ባቀረቡት ወራዳ አምልኮ ምክንያት አውግዟቸዋል፤ ድርጊታቸው ምን ያህል እንዳስቆጣው በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ።” (ሕዝቅኤል  6:6) ይሖዋ እንዲህ ያለውን አምልኮ ፈጽሞ እንደማይቀበለው ብሎም እንደሚጸየፈው ምንም ጥርጥር የለውም።

ይሖዋ አምላክ እነዚህን ሰዎች እንዴት እንደሚያጠፋቸው ትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ . . . በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ . . . አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች።” (ኤርምያስ 25:9-11) በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ባቢሎናውያን በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አወደሙ።

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፕሮፌሰር ስተርን፣ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “[አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶቹ] ቤቶችና ቅጥሮች ስለመውደማቸው፣ በእሳት ስለመጋየታቸው እንዲሁም ስለመፈራረሳቸው የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ (2 ነገሥት 25:8፤ 2 ዜና መዋዕል 36:18, 19) ትክክል መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “በኢየሩሳሌም ታሪክ ውስጥ የተፈጸመውን ይህን ክስተት በሚመለከት የተገኘው አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ . . . በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሌሎች አካባቢዎች ከተገኙት በጣም አስገራሚ ግኝቶች ውስጥ የሚካተት ነው።”

ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ከዚህ አንድ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን፤ ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከሌላ የሃይማኖት ቀኖና፣ ወግና ልማድ ጋር በመቀላቀል የሚቀርቡ አምልኮዎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በሚገባ ተረድቶ ነበር። ይህ ሰው ፈሪሳዊ የነበረ ሲሆን የአይሁድ እምነት ሕጎችን በሚገባ ተምሮ ነበር። ታዲያ ጳውሎስ፣ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን ሲያውቅ ምን አደረገ? “ይጠቅመኝ የነበረውን ሁሉ አሁን ለክርስቶስ ስል እንደ ጒድለት ቈጥሬዋለሁ” በማለት ተናግሯል። ጳውሎስ፣ ቀደም ሲል ይከተለው የነበረውን አካሄድ እርግፍ አድርጎ በመተው ቀናተኛ የክርስቶስ ተከታይ ሆኗል።—ፊልጵስዩስ 3:5-7

ጳውሎስ ተጓዥ ሚስዮናዊ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ሰዎችን ሃይማኖታዊ ልማድና በፍልስፍና ላይ የተመሠረቱ እምነቶች ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። በመሆኑም በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን ስምምነት አለው? የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ኅብረት አለው? የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው? . . . ‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡ፤ ለእኔም የተለያችሁ ሁኑ፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ።’”—2 ቆሮንቶስ 6:14-17

አምላክን በፈለግነው መንገድ ማምለክ እንደማንችል ተገንዝበናል፤ በመሆኑም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘አምላክ የሚቀበለው አምልኮ ምን ዓይነት ነው? ወደ አምላክ መቅረብ የምችለውስ እንዴት ነው? አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’

የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህም ሆነ ለሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። በአካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበህ እንድታነጋግር እንጋብዝሃለን። ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በሚመችህ ጊዜና ቦታ በነፃ ማጥናት የምትፈልግ ከሆነ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ እናበረታታሃለን።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴል አራድ፣ እስራኤል የሚገኘው ጥንታዊ የጣዖት አምልኮ ሥፍራ

[ምንጭ]

Garo Nalbandian

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንት የአይሁዳውያን ቤቶች ውስጥ የተገኙ የአስታሮት ምስሎች

[ምንጭ]

Photograph © Israel Museum, Jerusalem; courtesy of Israel Antiquities Authority