በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ጥበብ በፍጥረት ላይ ይንጸባረቃል

የአምላክ ጥበብ በፍጥረት ላይ ይንጸባረቃል

 የአምላክ ጥበብ በፍጥረት ላይ ይንጸባረቃል

“ከምድር እንስሳት ይልቅ የሚያስተምረን፣ ከሰማይ ወፎችም ይልቅ ጠቢባን የሚያደርገን፣ እርሱ [ነው]።”—ኢዮብ 35:11

አእዋፍ አስገራሚ ችሎታ አላቸው። እነዚህ ፍጥረታት በቀላሉ በአየር ላይ መንሳፈፍ መቻላቸው የአውሮፕላን ንድፍ አውጪዎችን ያስደምማል። አንዳንድ የአእዋፍ ዝርያዎች አቅጣጫን ለመለየት የሚያስችል ምንም ምልክት የሌለውን ሰፊ ውቅያኖስ አቋርጠው ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች በመጓዝ የሚፈልጉበት ቦታ ይደርሳሉ።

የፈጣሪያቸውን ጥበብ በግልጽ የሚያንጸባርቀው ሌላው የአእዋፍ አስደናቂ ችሎታ ደግሞ የተለያዩ ድምፆችን በማሰማትና በመዘመር መግባባት መቻላቸው ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

አእዋፍ የሚግባቡበት መንገድ

አንዳንድ የአእዋፍ ዝርያዎች መግባባት የሚጀምሩት ገና ሳይፈለፈሉ ነው። ለአብነት ያህል፣ ክዌል የተባለች የቆቅ ዝርያ ለስምንት ቀን ያህል በየቀኑ አንድ አንድ እንቁላል ትጥላለች። እያንዳንዱ እንቁላል ቀኑን ጠብቆ ቢፈለፈል ሁሉም ጫጩቶች እኩል አይፈለፈሉም። ይህ ከሆነ ደግሞ እናቲቱ ያልተፈለፈሉትን እንቁላሎች መታቀፍና የተፈለፈሉትን ጫጩቶች መንከባከብ ስለሚጠበቅባት ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደርግባታል። ይሁን እንጂ ስምንቱም እንቁላሎች የሚፈለፈሉት በስድስት ሰዓት ውስጥ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ፣ ጫጩቶቹ ገና በእንቁላል ውስጥ እያሉ እርስ በርስ መግባባት መቻላቸው ነው።

አእዋፍ ካደጉ በኋላ ብዙውን ጊዜ የሚዘምረው ወንዱ ነው። በተለይ ይህን የሚያደርገው በመራቢያው ወቅት ሲሆን የሚዘምረውም ክልሉን ለማስጠበቅ ወይም ተጓዳኙን ለመማረክ ነው። በሺህ የሚቆጠሩት የአእዋፍ ዝርያዎች እያንዳንዳቸው የራሳቸው “ቋንቋ” ያላቸው ሲሆን  ይህ ደግሞ እንስቶቹ የራሳቸው ዝርያ የሆኑ ተጓዳኞችን ለማግኘት ያስችላቸዋል።

ብዙውን ጊዜ አእዋፍ ማለዳ ላይና ጀንበር ስትጠልቅ የሚዘምሩበት በቂ ምክንያት አላቸው። በእነዚህ ጊዜያት አየሩ ጸጥ ያለ ሲሆን ጫጫታም አይሰማም። ማለዳ ላይ እንዲሁም ጀንበር ስትጠልቅ የሚሰማው የአእዋፍ ዝማሬ በቀኑ መሃል ከሚሰማው በ20 እጥፍ እንደሚበልጥ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

አብዛኛውን ጊዜ የሚዘምሩት ወንዶቹ ቢሆኑም ሁለቱም ጾታዎች የተለያየ መልእክት የሚያስተላልፉ ድምፆችን ያሰማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ቻፊንች የተባለው የወፍ ዝርያ ዘጠኝ ዓይነት ድሞፆችን ማውጣት ይችላል። አደጋ ሊያስከትልባቸው የሚችል እንደ ነጣቂ ወፍ ያለ ነገር በአየር ላይ ሲያንዣብብ ሲመለከቱ የሚያሰሙት ድምፅ ከመሬት አደጋ ሲያጋጥማቸው ከሚያወጡት ድምፅ ይለያል።

ከሁሉ የላቀ ስጦታ

በእርግጥም፣ አእዋፍ በተፈጥሮ ያገኙት ጥበብ አስደናቂ ነው። ይሁንና እርስ በርስ በመግባባት ችሎታ ረገድ ሰዎችን የሚተካከላቸው የለም። ኢዮብ 35:11 አምላክ ሰዎችን “ከሰማይ ወፎችም ይልቅ ጠቢባን” አድርጎ እንደሠራቸው ይናገራል። ሰዎችን የተለየ የሚያደርጋቸው በድምፅ ወይም በምልክት ውስብስብ የሆኑ ሐሳቦችን መግለጽ መቻላቸው ነው።

ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ የሰው ልጆች ውስብስብ ቋንቋዎችን የመማር ችሎታ ኖሯቸው ይወለዳሉ። አሜሪካን ሳይንቲስት የተባለ መጽሔት በኢንተርኔት ባስተላለፈው ዘገባ ላይ እንደሚከተለው ብሏል:- “ድክድክ የሚሉ ሕፃናት ወላጆቻቸው ሆን ብለው ባያስተምሯቸውም እንኳ መናገር ይችላሉ፤ ሌላው ቀርቶ መስማት የተሳናቸው ልጆች ቤታቸው ውስጥ የምልክት ቋንቋ የሚያስተምራቸው ሰው ባይኖርም የራሳቸውን የምልክት ቋንቋ ይፈጥራሉ።”

ሐሳባችንን እና ስሜታችንን በንግግር ወይም በምልክት መግለጽ መቻላችን በእርግጥም ግሩም የሆነ የአምላክ ስጦታ ነው። ለሰዎች የተሰጠው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ግን በጸሎት አማካኝነት ለአምላክ ሐሳባቸውን መግለጽ መቻላቸው ነው። እንዲያውም ይሖዋ አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ።”—ፊልጵስዩስ 4:6

ውሳኔ የሚጠይቅ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሰፈረልን ይህ ነው የማይባል ጥበብ ጥቅም እንድናገኝ ይፈልጋል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘውን ምክር በተግባር ልናውለው የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ የሆነው ያዕቆብ እንደሚከተለው ብሏል:- “ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል።”—ያዕቆብ 1:5

አንተስ ምን ይሰማሃል?

ማራኪ የሆነ የወፍ ዝማሬ ስታደምጥ ወይም አንድ ሕፃን ልጅ አፍ መፍታት ሲጀምር ምን ይሰማሃል? በፍጥረታት ላይ የአምላክ ጥበብ መንጸባረቁን አስተውለሃል?

መዝሙራዊው ዳዊት ስለ አፈጣጠሩ ካሰላሰለ በኋላ ወደ አምላክ እንዲህ በማለት ለመጸለይ ተገፋፍቷል:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።” (መዝሙር 139:14) በፍጥረት ላይ የተንጸባረቀውን የአምላክን ጥበብ በአድናቆት መመርመርህ ፈጣሪ አስተማማኝ መመሪያ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው ይበልጥ እርግጠኛ እንድትሆን ያደርግሃል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመግባባት ችሎታ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Dayton Wild/Visuals Unlimited