በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀር ጦርነት”

“ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀር ጦርነት”

 “ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀር ጦርነት”

‘ይህ ጦርነት፣ ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀር የመጨረሻው ጦርነት እንደሚሆን ቃል እገባላችኋለሁ።’ —ውድሮ ዊልሰን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት (1913-1921)

90 ዓመታት ገደማ በፊት አንደኛው የዓለም ጦርነት ባበቃበት ወቅት ከላይ የሰፈረውን አስተያየት የተናገሩት መሪ በእርግጥም ጦርነቶች እንደሚቀሩ ትልቅ ተስፋ ነበራቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደው ይህ ጦርነት እጅግ አሰቃቂ ስለነበር በጦርነቱ ያሸነፉት አገራት የከፈሏቸው በርካታ መሥዋዕቶች ዘላቂ ጥቅሞችን እንደሚያመጡላቸው በእርግጠኝነት ማመን ይፈልጉ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎች ያካሄዷቸው ጦርነቶች ለችግሮች መፍትሔ ማስገኘት አልቻሉም፤ በተለይ ደግሞ ጦርነት ራሱ የሚያስከትለውን ሥር የሰደደ ችግር አላስወገዱም።

ፕሬዚዳንት ዊልሰን ከላይ በተገለጸው መንገድ ቸኩለው ቃል ከገቡ ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። በዚህ ጦርነት የጠፋው ሕይወትና የደረሰው ውድመት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በእጅጉ ይበልጥ ነበር። ሰዎች በሃያ ዓመታት ውስጥ በተገኘው የቴክኖሎጂ እድገት በመጠቀም ቀደም ሲል ከነበሯቸው የበለጡ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን መሥራት ችለው ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ የዓለም መሪዎች ጦርነት የመነሳቱ አጋጣሚ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሰፊ መሆኑን ተገነዘቡ።

የዩናይትድ ስቴትስ ጄኔራል የሆኑት ዳግላስ ማክአርተር በ1945 እንዲህ ብለው ነበር:- “ጦርነቶችን ለማስቀረት የነበረን የመጨረሻ አጋጣሚ አምልጦናል። ከበፊቱ የተሻለና ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ዘዴ ካልቀየስን በስተቀር አርማጌዶን መምጣቱ አይቀርም።”

ጄኔራል ማክአርተር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የመጨረሻ ቀናት በናጋሳኪና በሂሮሽማ ላይ የተጣሉት ሁለት አቶሚክ ቦምቦች ምን እንዳስከተሉ በሚገባ ያውቁ ነበር። በእነዚያ ሁለት የጃፓን ከተሞች ላይ የደረሰው ዘግናኝ እልቂት፣ “አርማጌዶን” ለሚለው ቃል አዲስ ፍቺ እንዲሰጡት ይኸውም ቃሉ የሰውን ዘር ከምድር ገጽ የሚያጠፋን ከፍተኛ የኑክሌር እልቂት የሚያመለክት እንደሆነ አድርገው እንዲገልጹት አድርጓቸዋል።

 የኑክሌር እልቂት ይፈጠር ይሆናል የሚለው ስጋት አሁንም ሰዎችን ያስጨንቃቸዋል። በ1960ዎቹ የዓለም ኃያላን መንግሥታት እርስ በርስ ላለመጠፋፋት ሲሉ ተፈራርተው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውን ሐሳብ አፈለቁ። ዓላማቸው ጦርነቱ ከየትኛውም ወገን ቢጀመር፣ 25 በመቶ የሚሆኑትን የጠላት ሰላማዊ ዜጎችና 50 በመቶ የሚሆነውን የኢንዱስትሪ አቅም ለመደምሰስ የሚያስችሉ በቂ ሚሳይሎችን ወይም የሚሳይል ማስወንጨፊያ መሣሪያዎችን ማከማቸት ነበር። ይሁን እንጂ በዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን ተብሎ በተነደፈው በዚህ ሐሳብ ብዙዎች አልተደሰቱም።

በዛሬው ጊዜ የኑክሌር መሣሪያዎች ቁጥር እያሻቀበ ከመሆኑም ሌላ በየቦታው የሚካሄዱ ጦርነቶች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ነው። የሰውን ዘር ከምድር ገጽ የሚያጠፋ የኑክሌር ጦርነት ይጀመር ይሆናል የሚለው ስጋት አሁንም አልተወገደም። ምንም እንኳ ሰዎች ጦርነት የሚቀርበትን ጊዜ በጉጉት ቢጠባበቁም ጦርነት አሊያም ማንኛውም ወታደራዊ ወይም ፖለቲካዊ ስልት እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ እንደሚያስችል የሚሰማቸው ጥቂቶች ናቸው።

የሆነ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ጦርነቶችን ሁሉ ስለሚያስወግድ አንድ ልዩ ጦርነት ይናገራል። ይህን ጦርነት “አርማጌዶን” በማለት የሚጠራው ሲሆን ይህን ቃል ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከኑክሌር እልቂት ጋር በማያያዝ ይጠቅሱታል። ታዲያ አርማጌዶን ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀረው እንዴት ነው? ቀጣዩ ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

DTRA Photo

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ናጋሳኪ፣ ጃፓን፣ 1945: USAF photo