በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል

በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል

 በእምነታቸው ምሰሏቸው

በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል

ኤልያስ ብቻውን ሆኖ በሰማይ ወደሚገኘው አባቱ መጸለይ ፈልጎ ነበር። ሆኖም ይህ እውነተኛ ነቢይ እሳት ከሰማይ ሲያወርድ የተመለከቱ ብዙ ሰዎች በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስለፈለጉ ከበውት ነበር። ኤልያስ ገላጣ ወደሆነው የቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ በመውጣት ለይሖዋ ከመጸለዩ በፊት ደስ የሚያሰኘው ባይሆንም ንጉሥ አክዓብን ማናገር ነበረበት።

አክዓብና ኤልያስ ፈጽሞ የተለያዩ ሰዎች ነበሩ። በምርጥ የንጉሥ ልብስ የተንቆጠቆጠው አክዓብ ስግብግብ ከመሆኑም ሌላ ደካማ አስተሳሰብ ያለው ከሃዲ ሰው ነበር። ምናልባትም ከእንስሳት ቆዳ አሊያም ከግመል ወይም ከፍየል ፀጉር የተሠራ ተራ የነቢይ ልብስ የለበሰው ኤልያስ ደግሞ በጣም ደፋር፣ ጽኑ አቋምና እምነት ያለው ሰው ነበር። በመገባደድ ላይ የነበረው ቀን የሁለቱ ሰዎች ማንነት ይበልጥ ቁልጭ ብሎ እንዲታይ አድርጓል። *

ዕለቱ አክዓብም ሆነ ሌሎች የበኣል አምላኪዎች የኀፍረት ማቅ የተከናነቡበት ቀን ነበር። አክዓብና ሚስቱ ንግሥት ኤልዛቤል አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያስፋፉት የነበረው አረማዊ እምነት ሐሰት መሆኑ ተረጋግጧል። በኣል አታላይ መሆኑ ተጋልጧል። ይህ በድን የሆነ አምላክ፣ ነቢያቱ እጅግ በመጨነቅ ልመና ቢያቀርቡም፣ ቢጨፍሩም እንዲሁም እንደ ልማዳቸው ሰውነታቸውን ቢያቆስሉም ብልጭታ እሳት እንኳ በመፍጠር ምላሽ መስጠት አልቻለም። በኣል፣ 450 ነቢያቱ የሚገባቸውን ቅጣት ከማግኘት ሊታደጋቸው አልቻለም። ይሁንና ይህ ሐሰተኛ የሆነ አምላክ በአንድ ሌላ ጉዳይም ከንቱ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይፋ ይሆናል። የበኣል ነቢያት ምድሪቱን ያጠቃውን ድርቅ እንዲያቆም ከሦስት ዓመት በላይ አምላካቸውን ሲለማመኑ ቆይተዋል፤ በኣል ግን ለጥያቄያቸው መልስ መስጠት አልቻለም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ድርቁ እንዲቆም በማድረግ እውነተኛው አምላክ እሱ መሆኑን በቅርቡ ያሳያል።—1 ነገሥት 16:30 እስከ 17:1፤ 18:1-40

ይሁንና ይሖዋ ይህን የሚያደርገው መቼ ነው? እስከዚያው ድረስ ኤልያስ እንዴት ያለ ባሕርይ በማሳየት ይመላለስ ይሆን? ከዚህ የእምነት ሰው ምን ትምህርት እናገኛለን? በ1 ነገሥት 18:41-46 ላይ ያለውን ዘገባ ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

የጸሎተኝነት መንፈስ

ኤልያስ ወደ አክዓብ ሄዶ፣ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማልና ሂድና ብላ፤ ጠጣም” አለው። (ቁጥር 41) ይህ ክፉ ንጉሥ በዕለቱ ከተከናወኑት ነገሮች ያገኘው ትምህርት ይኖር ይሆን? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ በቀጥታ አይናገርም፤ ሆኖም አክዓብ ንስሐ እንደገባ የሚያሳይ አንድም ቃል የለም፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ምሕረት ለማግኘት የነቢዩን እርዳታ እንደጠየቀ የሚናገር ምንም ሐሳብ አናገኝም። ዘገባው፣ አክዓብ “ሊበላና ሊጠጣ ሄደ” ስለሚል ከዚህ ውጭ ያደረገው ነገር የለም። (ቁጥር 42) ኤልያስስ ምን አድርጎ ይሆን?

“ኤልያስ ግን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።” አክዓብ ሆዱን ለመሙላት ሲሄድ ኤልያስ ግን ወደ አባቱ የመጸለይ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ኤልያስ ፊቱ ጉልበቱ ጋ እስኪደርስ ድረስ በትሕትና ራሱን እንዴት ዝቅ እንዳደረገ ልብ በል። ኤልያስ የሚጸልየው ስለ ምን ጉዳይ ነበር? ስለ ምን እንደጸለየ መገመት አያዳግትም። መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 5:18 ላይ ኤልያስ ድርቁ እንዲቆም እንደጸለየ ይነግረናል። በቀርሜሎስ ተራራ አናት ላይ ሆኖ እንዲህ ያለውን ጸሎት እያቀረበ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።

 ቀደም ሲል ይሖዋ “በምድሪቱ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (1 ነገሥት 18:1) ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለ ጸሎት ካስተማረበት መንገድ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ኤልያስ ከላይ የተገለጸው የአባቱ ፈቃድ እንዲፈጸም ጸልዮአል።—ማቴዎስ 6:9, 10

ኤልያስ የተወው ምሳሌ ስለ ጸሎት ብዙ ነገር ያስተምረናል። ከምንም በላይ ኤልያስን የሚያሳስበው የአባቱ ፈቃድ መፈጸም ነበር። እኛም በምንጸልይበት ጊዜ፣ ‘ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እንደሚሰማን’ ማስታወሳችን ጥሩ ነው። (1 ዮሐንስ 5:14) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ተቀባይነት ባለው መንገድ ለመጸለይ እንድንችል የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል፤ ለዚህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሕይወታችን ክፍል እንዲሆን ማድረጋችን ተገቢ መሆኑን እናያለን። ኤልያስ ድርቁ እንዲቆም የጸለየበት ሌላው ምክንያት በትውልድ አገሩ የሚኖሩ ሰዎች የሚደርስባቸው መከራ ስላሳሰበው እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። በዚያን ዕለት ይሖዋ ያደረገውን ተአምር ሲመለከት ልቡ በአመስጋኝነት ስሜት እንደተሞላ ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም፣ ስለ ሌሎች ደህንነት መጸለይ እንዲሁም ስለተደረገልን ነገር ከልብ ማመስገን ይገባናል።—2 ቆሮንቶስ 1:11፤ ፊልጵስዩስ 4:6

ጠንካራ እምነትና ነቅቶ የመጠበቅ ዝንባሌ ነበረው

ኤልያስ፣ ይሖዋ ድርቁን ለማቆም እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ የነበረ ቢሆንም መቼ እንደሚያቆመው ግን የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ታዲያ ነቢዩ በዚህ መሃል ምን አደረገ? ቁጥር 43 ምን እንደሚል ልብ በል:- “አገልጋዩንም፣ ‘ውጣና ወደ ባሕሩ ተመልከት’ አለው። አገልጋዩም ሄዶ ተመለከተና፤ ‘በዚያ ምንም የለም’ አለው። ኤልያስ ሰባት ጊዜ ‘እንደ ገና ሂድ’ አለው።” ከኤልያስ ምሳሌ ቢያንስ ሁለት ትምህርቶችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ነቢዩ ያሳየው ጠንካራ እምነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይሆናል ተብሎ የተነገረውን ነገር በንቃት መጠባበቁ ነው።

ኤልያስ፣ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መድረሱን የሚያሳይ አንድ የሆነ ፍንጭ ለማየት ጓጉቶ ነበር። በመሆኑም አገልጋዩን ምቹ ወደሆነ አንድ ከፍታ ላይ በመውጣት እንደሚዘንብ የሚጠቁም ምልክት መኖር አለመኖሩን እንዲያይ ላከው። አገልጋዩ፣ “በዚያ ምንም የለም” የሚል ተስፋ አስቆራጭ ሪፖርት ይዞ ተመለሰ። አድማሱ የጠራ ከመሆኑም በላይ በግልጽ እንደሚታየው በሰማይም ላይ ምንም ደመና አልነበረም። ጥያቄ የሚፈጥር አንድ ነገር እንዳለ አስተዋልክ? ኤልያስ ለአክዓብ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማል” ብሎት እንደነበር አስታውስ። ነቢዩ የዝናብ ደመና ባልታየበት ሁኔታ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሊናገር ቻለ?

ኤልያስ፣ ይሖዋ የገባውን ቃል ያውቃል። የይሖዋ ነቢይና ወኪል እንደመሆኑ መጠን አምላኩ ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ነበር። ኤልያስ በይሖዋ ይተማመን ስለነበር ከባድ ዝናብ መጣል የጀመረ ያህል ተሰምቶት ነበር። ይህ ታሪክ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቊጠር በሐሳቡ ጸና” በማለት ስለ ሙሴ የተናገረውን አባባል ያስታውሰን ይሆናል። አምላክ ለአንተ ይህን ያህል እውን ነው? ይሖዋ፣ በእሱና በገባቸው ተስፋዎች ላይ እንዲህ ያለ እምነት እንድንጥል የሚያደርግ በቂ ማስረጃ ሰጥቶናል።—ዕብራውያን 11:1, 27

በመቀጠል ኤልያስ ይመጣል የተባለውን ነገር ምን ያህል በንቃት ይጠብቅ እንደነበር ልብ በል። አገልጋዩን አንዴ ወይም ሁለቴ ሳይሆን ሰባት ጊዜ ተመልሶ እንዲሄድ ልኮታል! አገልጋዩ አሁንም አሁንም ሲላክ ምን ያህል  ድካም ሊሰማው እንደሚችል መገመት ትችላለህ፤ ሆኖም ኤልያስ አንድ ምልክት ለማየት ጓጉቶ ስለነበር ተስፋ አልቆረጠም። በመጨረሻም አገልጋዩ ለሰባተኛ ጊዜ ከሄደ በኋላ ለኤልያስ፣ “እነሆ፤ የሰው እጅ የምታህል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለው። (ቁጥር 44) አገልጋዩ፣ የእጁን መዳፍ በማሳየት ከታላቁ ባሕር * የወጣችውን የትንሿን ደመና መጠን ለመግለጽ ሲሞክር በዓይነ ሕሊናህ ማየት ትችላለህ? አገልጋዩ ይህች ትንሽ ደመና ያን ያህል ለውጥ እንደማታመጣ አስቦ ሊሆን ይችላል። ለኤልያስ ግን ይህች ደመና ትልቅ ትርጉም ነበራት። በዚህ ጊዜ ኤልያስ አገልጋዩን በአስቸኳይ “ሂድና አክዓብን፣ ‘ዝናቡ ሳያግድህ፣ ሠረገላህን ጭነህ ውረድ’ ብለህ ንገረው” የሚል መመሪያ ሰጠው።

በዚህ ረገድም ቢሆን ኤልያስ ትልቅ ምሳሌ ይሆነናል። እኛም ብንሆን አምላክ የገለጻቸው ዓላማዎች በቅርቡ ፍጻሜ በሚያገኙበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ኤልያስ ድርቁ የሚያበቃበትን ጊዜ በትዕግሥት ጠብቋል፤ ዛሬም ቢሆን የአምላክ አገልጋዮች ይህ ብልሹ ዓለም የሚጠፋበትን ጊዜ በትዕግሥት እየተጠባበቁ ነው። (1 ዮሐንስ 2:17) ይሖዋ አምላክ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ልክ እንደ ኤልያስ ንቁ ሆነን መጠበቅ ይኖርብናል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 24:42) ሆኖም ኢየሱስ ይህን ሲል ተከታዮቹ የመጨረሻው ጊዜ መድረሱን ጨርሶ አያውቁም ማለቱ ነበር? በፍጹም፤ ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የዓለም ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። እያንዳንዳችን “የዓለም መጨረሻ” ምልክት ስለሆኑት ስለ እነዚህ  ዝርዝር ጉዳዮች ማወቅ እንችላለን።—ማቴዎስ 24:3-7 *

እያንዳንዱ የምልክቱ ገጽታ ጠንካራና አሳማኝ ማስረጃ ይዟል። እንዲህ ያለው ማስረጃ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ በቂ ሆኖ አግኝተነዋል? ኤልያስ ከአድማስ ማዶ የወጣችውን አንዲት ትንሽ ደመና ማየቱ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መድረሱን ለማመን በቂው ነበረች። ይህ ታማኝ ነቢይ የጠበቀው ነገር ሳይፈጸም ቀርቶ አዝኖ ይሆን?

ይሖዋ እፎይታና በረከት አስገኝቶለታል

ዘገባው በመቀጠል፣ “ወዲያውኑም ሰማዩ በጥቍር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱ ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብ ጣለ፤ አክዓብም በሠረገላ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ” ይላል። (ቁጥር 45) ሁኔታዎቹ በሚያስገርም ፍጥነት መከናወን ጀመሩ። የኤልያስ አገልጋይ፣ የነቢዩን መልእክት ለአክዓብ በማድረስ ላይ ሳለ ያቺ ትንሽ ደመና ብዙ እየሆነች በመሄዷ ሰማዩ እየተሸፈነና እየጠቆረ መጣ፤ ከባድ ነፋስም ነፈሰ። በመጨረሻም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በእስራኤል ምድር ላይ ዝናብ ጣለ። * ደርቆ የተሰነጣጠቀው መሬት በዝናቡ ራሰ። ኃይለኛ ዶፍ በሚጥልበት ጊዜ መሙላት የጀመረው የቂሶን ወንዝ በዚያ የታረዱትን የበኣል ነቢያት ደም ጠራርጎ እንደወሰደ ሁሉ አስቸጋሪ የነበሩት እስራኤላውያንም አስጸያፊ የሆነውን የበኣል አምልኮ ከምድሪቱ ሙሉ በሙሉ እንዲያስወግዱ አጋጣሚ ተሰጥቷቸው ነበር።

ኤልያስ ይህ በእርግጠኝነት እንደሚፈጸም ተስፋ አድርጎ ነበር! አክዓብ ንስሐ በመግባት ምድሪቱን በበኣል አምልኮ ከመበከል ተቆጥቦ ይሆን? በዕለቱ የተከናወኑት ነገሮች እንዲህ የመሰለ ለውጥ እንዲያደርግ ሊገፋፉት ይገባ ነበር። እርግጥ ነው፣ በወቅቱ አክዓብ ምን ያስብ እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ዘገባው በአጭሩ፣ “አክዓብም በሠረገላ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ” በማለት ይነግረናል። ከተከናወኑት ነገሮች ትምህርት አግኝቶ ይሆን? አካሄዱንስ ለመለወጥ ቆርጦ ይሆን? ቆየት ብለው የተከናወኑት ነገሮች እንደሚያሳዩት ከሆነ መልሱ በፍጹም የሚል ነው። አሁንም ቢሆን የአክዓብም ሆነ የኤልያስ ውሎ ገና አልተጠናቀቀም።

የይሖዋ ነቢይ፣ አክዓብ የሄደበትን መንገድ ተከትሎ መጓዝ ጀመረ። ረጅም፣ በጨለማ የተዋጠና የጨቀየ መንገድ ይጠብቀዋል። ሆኖም በመቀጠል አንድ ያልተለመደ ነገር ተከሰተ።

“የእግዚአብሔርም ኀይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን ከፍ አድርጎ በቀበቶው ካጠበቀ በኋላ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ በአክዓብ ፊት ሮጠ።” (ቁጥር 46) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ‘የእግዚአብሔር ኀይል’ በኤልያስ ላይ ከሰው አቅም በላይ በሆነ መንገድ እየሠራ ነበር። ኢይዝራኤል የምትገኘው 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ ሲሆን ኤልያስ ደግሞ ዕድሜው ገፍቷል። * ይህ ነቢይ ረጅሙን መጎናጸፊያ ለብሶ፣ እግሮቹን እንደ ልብ ለማንሳት እንዲያመቸው ልብሶቹን ሰብሰብ አድርጎ ወገቡ ላይ በቀበቶ ሸብ በማድረግ በጨቀየው መንገድ ላይ ሲሮጥ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የቤተ መንግሥቱ ሠረገላ ላይ ለመድረስ አልፎ ተርፎም ቀድሞት ለመሄድ በከፍተኛ ፍጥነት እየሮጠ ነው!

ይህ ለኤልያስ እንዴት ያለ በረከት ነበር! እንዲህ የመሰለ ምናልባትም በወጣትነት ጊዜው ተሰምቶት የማያውቀው ዓይነት ኃይል፣ ጥንካሬና ብርታት ሲሰማው ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይህ ሁኔታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ጤንነትና ብርታት እንደሚያገኙ ዋስትና የሚሰጡትን ትንቢቶች ሳያስታውሰን አልቀረም። (ኢሳይያስ 35:6፤ ሉቃስ 23:43) ኤልያስ በዚያ በጨቀየ መንገድ ላይ ሲሮጥ፣ ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን የአባቱን የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘ ተገንዝቦ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በረከት ለመስጠት ይጓጓል። እነዚህን በረከቶች ለማግኘት መጣራችን የሚያስቆጭ አይደለም። እንደ ኤልያስ ሁሉ እኛም፣ ይሖዋ በዚህ አደገኛና አጣዳፊ በሆነ ጊዜ ውስጥ እርምጃ የሚወስድበት ቀን መድረሱን የሚያሳዩ ጠንካራ ማስረጃዎችን በጥንቃቄ በመመርመር ነቅተን መጠበቅ ያስፈልገናል። እኛም እንደ ኤልያስ “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አሉን።—መዝሙር 31:5

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.16 በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ባሕር ሜድትራንያን በመባል ይታወቃል።

^ አን.17 ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜያቸውን በማግኘት ላይ ስለመሆናቸው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።

^ አን.20 አንዳንዶች ‘ድርቁ የቆየበትን ዘመን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሐሳብ እርስ በርሱ ይጋጫል?’ ብለው ይጠይቃሉ። በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.23 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ኤልሳዕን እንዲያሠለጥነው ለኤልያስ ኃላፊነት ሰጠው። ኤልሳዕ ከዚህ ቀደም “የኤልያስን እጅ ያስታጥብ” እንደነበር ተጠቅሷል። (2 ነገሥት 3:11) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኤልሳዕ፣ አረጋዊውን ኤልያስን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ በማድረግ አገልጋዩ ሆኖ ሠርቷል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በኤልያስ ዘመን ተከስቶ የነበረው ድርቅ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

የይሖዋ ነቢይ የነበረው ኤልያስ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ድርቅ በቅርቡ እንደሚያበቃ ለንጉሥ አክዓብ አሳውቆት ነበር። ድርቁ ያቆመው “በሦስተኛው ዓመት” ላይ ሲሆን ዓመቱ መቆጠር የጀመረው ኤልያስ ስለ ድርቁ ከተናገረበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ እንደሚሆን ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (1 ነገሥት 18:1) ኤልያስ፣ ዝናብ እንደሚጥል ከተናገረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋ እንዲዘንብ አደረገ። ከዚህ በመነሳት አንዳንዶች ድርቁ ያቆመው በሦስተኛው ዓመት ላይ ስለሆነ የቆየው ከሦስት ዓመት ላነሰ ጊዜ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሱ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስና ያዕቆብ ድርቁ እስከ “ሦስት ዓመት ተኩል” እንደቆየ ይነግሩናል። (ሉቃስ 4:25፤ ያዕቆብ 5:17) ታዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል?

በፍጹም አይጋጭም። የጥንቷ እስራኤል የበጋ ወራት በጣም ረጅም ሲሆን እስከ ስድስት ወር ድረስ ይዘልቃል። ኤልያስ ለአክዓብ ስለ ድርቁ ሊነግረው የመጣው የበጋው ወራት ከመጠን በላይ እንደረዘመና ከባድ እየሆነ እንደመጣ በግልጽ መታየት ከጀመረ በኋላ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው የድርቁ ዘመን በትክክል የጀመረው ኤልያስ ለአክዓብ ስለ ድርቁ ሊነግረው ከመምጣቱ ከስድስት ወር ገደማ ቀደም ብሎ ነው ለማለት ይቻላል። በመሆኑም ኤልያስ ድርቁ ማብቃቱን ያሳወቀው ቀደም ሲል ስለ ድርቁ በተናገረ “በሦስተኛው ዓመት” ላይ ቢሆንም ድርቁ በአጠቃላይ የቆየው ወደ ሦስት ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የቀረበውን ታላቅ ፈተና ለማየት በተሰበሰቡ ጊዜ ‘የሦስት ዓመት ተኩሉ’ ጊዜ አልፎ ነበር።

ኤልያስ ለመጀመሪያ ጊዜ አክዓብን ለማነጋገር ሲሄድ ሕዝቡ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደነበር ተመልከት። ሕዝቡ፣ በኣል የበጋውን ወራት በማሳለፍ ዝናብ የሚያመጣ “ደመና ጋላቢ” አምላክ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የበጋው ወራት ከተለመደው በላይ ሲረዝም ‘በኣል የት አለ? ዝናቡ እንዲጥል የሚያደርገው መቼ ነው?’ በማለት ሳይጠይቁ አልቀሩም። ኤልያስ፣ እሱ ይሆናል እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ዝናብም ሆነ ጠል እንደማይኖር መናገሩ የበኣል አምላኪዎችን ሳያበሳጫቸው አልቀረም።—1 ነገሥት 17:1

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልያስ ያቀረባቸው ጸሎቶች የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያሉ