በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች መብታቸው ተከበረ

ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች መብታቸው ተከበረ

 ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች መብታቸው ተከበረ

ግንቦት 3, 2007 ስትራዝቡር፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ በጆርጂያ ሪፑብሊክ ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ድምፅ ፈርዶላቸዋል። ፍርድ ቤቱ፣ በጆርጂያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ ግፍ እንደተፈጸመባቸውና የሃይማኖት ነፃነት የማግኘት መብታቸው እንደተጣሰ ገልጿል። ከዚህም በላይ የቀድሞውን የጆርጂያ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥቃት በፈጸሙት ወንጀለኞች ላይ እርምጃ ባለመውሰዱ ፍርድ ቤቱ አውግዞታል። ፍርድ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምን ነበር?

ጥቅምት 17, 1999 በጆርጂያ ዋና ከተማ በተብሊሲ የሚገኘው የግልዳኒ ጉባኤ 120 አባላት በሰላማዊ ሁኔታ አምልኳቸውን እያካሄዱ ነበር። በዚህ ጊዜ በመጥፎ ምግባሩ ምክንያት ከቅስና የወረደው ቫሲሊ ምካላቪሽቪሊ የተባለ የኦርቶዶክስ ቄስ የሚመራቸው 200 የሚያህሉ ዓመጸኞች ስብሰባው ወደሚካሄድበት ቦታ በድንገት ዘው ብለው ገቡ። ወፋፍራም ዱላዎችና የብረት መስቀሎች የያዙት እነዚህ ዓመጸኞች በስብሰባው ላይ የነበሩትን ሰዎች መደብደብ ጀመሩ፤ በበርካታ ተሰብሳቢዎች ላይ ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን አንዳንዶችም በጣም ተጎድተዋል። አንዲት ሴት በደረሰባት ድብደባ ምክንያት በዓይኗ ላይ ዘላቂ ጉዳት ደርሶባታል። ቢያንስ 16 ሰዎች የሕክምና እርዳታ አስፈልጓቸዋል። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ለማግኘት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄዱ በቦታው ያገኙት የፖሊስ አዛዥ፣ እሱ ቢሆን ኖሮ ከዚያ የባሰ ያደርግባቸው እንደነበረ ነገራቸው! እነዚህ ዓመጸኞች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ከዓመጸኞቹ አንዱ በቪዲዮ የቀረጸው ሲሆን ቆየት ብሎም በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ በመተላለፉ ጥቃት የሰነዘሩትን ሰዎች ማንነት በግልጽ መመልከት ይቻል ነበር። *

ጥቃት የደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ክስ ቢመሠርቱም በዓመጸኞቹ ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም። ጉዳዩን እንዲከታተል የተመደበው የፖሊስ መርማሪ ደግሞ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ በመሆኑ ሁኔታውን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ መመልከት እንደማይችል ገለጸ። ፖሊሶችም ሆኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው፣ ሃይማኖታዊ ጽንፈኞቹ ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ከመቶ በላይ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ አደፋፍሯቸዋል።

በመሆኑም ሰኔ 29, 2001 የይሖዋ ምሥክሮች ጉዳዩን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቀረቡ። * ፍርድ ቤቱም ግንቦት 3, 2007 የመጨረሻ ውሳኔ ያደረገ ሲሆን በዚህ ውሳኔ ላይ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት ከዘረዘረ በኋላ የጆርጂያን የመንግሥት ባለ ሥልጣናት እርምጃ ባለመውሰዳቸው አውግዟቸዋል። ፍርድ ቤቱ “ባለ ሥልጣናቱ [ጥቃቱን በተመለከተ የቀረበላቸውን] መረጃ ለማጣራት አፋጣኝ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ ነበረባቸው” ብሏል። ውሳኔው እንዲህ ይላል:- “ባለ ሥልጣናቱ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በቸልታ መመልከታቸው . . . ሕዝቡ፣ ሕጉ ፍትሐዊ ስለመሆኑና መንግሥት ሕጉን ተግባራዊ ስለማድረጉ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ከማድረግ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም።”

ፍርድ ቤቱ እንዲህ በማለት ደምድሟል:- “ክስ በመሠረቱት ሰዎች ላይ ጥቅምት 17, 1999 የደረሰው ጥቃት፣ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከተሰነዘሩት በርካታ ጥቃቶች የመጀመሪያው ሲሆን ባለ ሥልጣናቱ ጉዳዩን አጣርተው ወንጀለኞቹን አለመቅጣታቸው እነዚሁ ዓመጸኞች በሃይማኖት ሳቢያ የሚፈጽሙትን ጥቃት በመላው ጆርጂያ እንዲያስፋፉ አደፋፍሯቸዋል።”

ጥቃት የተሰነዘረባቸው ሰዎች በዚህ መንገድ መብታቸው የተከበረላቸው ከመሆኑም ሌላ የጆርጂያ መንግሥት ለግልዳኒ ጉባኤ አባላት የጉዳት ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም ለሕግ ነክ ጉዳዮች ያወጧቸውን ወጪዎች እንዲሸፍን ትእዛዝ ተላልፏል። በጆርጂያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ይፈጸምባቸው የነበረው ዓመጽና የጭካኔ ድርጊት በጣም መቀነሱ አስደስቷቸዋል፤ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ለአምልኮ በሰላም የመሰብሰብ መብታቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አስደስቷቸዋል። ለተገኘው ውጤት በሰማይ የሚገኘውን አባታቸውን፣ ይሖዋ አምላክን ከልብ ያመሰግኑታል፤ በደረሰባቸው መከራ ሁሉ የእሱ መመሪያና ጥበቃ አልተለያቸውም።—መዝሙር 23:4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የጥር 22, 2002 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 18-24 ተመልከት።

^ አን.5 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የአውሮፓ ምክር ቤት ክፍል ሲሆን በአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን ለማስከበር የተደረገው ስምምነት እንደተጣሰ የሚገልጹ ጉዳዮችን ይመለከታል። ጆርጂያ፣ ግንቦት 20, 1999 ይህን ስምምነት ስለተቀበለች በስምምነቱ ውስጥ የሰፈሩትን ደንቦች ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ ውስጥ ገብታለች።