ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችሉ አዳራሾችን መገንባት
ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችሉ አዳራሾችን መገንባት
“ዓይኔን ማመን አልቻልኩም። አንድ ላይ ለመሰብሰብና ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችል እንዲህ ያለ ውብ አዳራሽ ይኖረናል ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። የተሰማኝ ደስታ በዋጋ ልትተምኑት ከምትችሉት በላይ ነው!”—ማሪያ፣ ሜክሲኮ
የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቃል ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር አንድ ላይ መሰብሰብ ያስደስታቸዋል። (መዝሙር 27:4፤ ዕብራውያን 10:23-25) በተለይ ደግሞ አምልኮ ለማቅረብ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ መሰብሰብ ሲችሉ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ይሆናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገሮች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የአምልኮ ቦታዎችን የገነቡ ሲሆን እነዚህን የአምልኮ ቦታዎችም የመንግሥት አዳራሾች ብለው ይጠሯቸዋል።
ይህ ሁሉ የግንባታ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? ሥራውን የሚያከናውኑትስ እነማን ናቸው? ይህ ሥራ ግንባታውን በሚያከናውኑ ሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እንድትችል በሜክሲኮና በቤሊዝ ምን እየተካሄደ እንዳለ ተመልከት።
በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ!
ባለፉት ጊዜያት በሜክሲኮ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ የሚሰበሰቡት በጓሯቸው እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶቻቸው፣ በመጋዘኖች፣ በመኪና ማቆሚያዎቻቸው ወይም በተከራዩአቸው አዳራሾች ውስጥ ነበር። እነዚህ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የራሳቸው የሆኑ የመንግሥት አዳራሾች መገንባት ቢችሉ በጣም የተሻለ እንደሚሆን ያስቡ ነበር።
በ1994 ሜክሲኮ ውስጥ 388,000 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በዚያው ዓመት የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸው በሆነ የአምልኮ ቦታ መሰብሰብ እንዲችሉ 3,300 አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች መገንባት ነበረባቸው። እንዴት ያለ መጠነ ሰፊ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር!
በዚያ ወቅት አቅማቸው የሚፈቅድላቸው አንዳንድ ጉባኤዎች የራሳቸውን የመንግሥት አዳራሽ እየገነቡ ነበር። ይሁን እንጂ የሚያስፈልጉትን ያህል የመንግሥት አዳራሾች ለማግኘት ተጨማሪ አዳራሾችን በፍጥነት መገንባት እንደሚኖርብን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ግልጽ ሆነ። ታዲያ ይህን ሥራ ማከናወን የተቻለው እንዴት ነው?
በሙያው የተካኑ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፉ ተጓዥ ቡድኖች
በ1999 አዲስ የግንባታ መርሃ ግብር ተዘረጋ። በመላው ሜክሲኮ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች መቋቋም ጀመሩ። በአገሪቱ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ አስደሳች ሥራ ለመካፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹ፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የግንባታ ሙያ ነበራቸው። በአሁኑ ጊዜ በሜክሲኮ ለዚህ ዓላማ የተደራጁ 35 ቡድኖች የሚገኙ ሲሆን በቤሊዝ ደግሞ አንድ ቡድን ተቋቁሟል።
አብዛኛውን ጊዜ በእያንዳንዱ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድን ውስጥ ያለ ደሞዝ በቋሚነት የሚሠሩ ስምንት የሚያህሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ይገኛሉ፤ በቡድኑ ውስጥ ወንዶችም ሴቶችም አሉ። ደስተኛ የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፉት እነዚህ ቡድኖች በግንባታ ሥራዎች ላይ በፈቃደኝነት ለሚካፈሉ ሌሎች ሰዎች አመራር ለመስጠት በመላ አገሪቱ ከቦታ
ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። እያንዳንዱ ፈቃደኛ ሠራተኛ ከሰኞ እስከ ዓርብ እንዲሁም በየሁለት ሳምንቱ አንድ ቅዳሜ በቀን ስምንት ሰዓት ይሠራል። ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት ላይ የዕለት ጥቅስ የሚያነብቡ ሲሆን ከዚያም ቁርሳቸውን ይበላሉ። ሁሉም የታዘዙትን ማንኛውንም ሥራ በፈቃደኝነት ይሠራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሴቶች ግድግዳ መለሰንን፣ ጡብ መደርደርንና ቀለም መቀባትን የመሳሰሉ ሥራዎችን ከወንዶች እኩል ይሠራሉ።የመንግሥት አዳራሹ የሚገነባለት ጉባኤ ከቦታ ቦታ ለሚንቀሳቀሱት ፈቃደኛ ሠራተኞች ማረፊያና ምግብ በማዘጋጀት እንዲሁም ልብሶቻቸውን በማጠብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞችና በአካባቢው የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች፣ አዳራሹን አብረው በመገንባት ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት እንቅስቃሴ በመካፈል እርስ በርስ ይቀራረባሉ።
ፈቃደኛ ሠራተኛ መሆን የሚያስገኛቸው በረከቶች
እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ስለሚያከናውኑት ሥራ ምን ይሰማቸዋል? ከሦስት ዓመታት በላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ በመሆን ያገለገለው ዳንየል እንዲህ ብሏል:- “በሙቀትም ሆነ በብርድ ወቅት ተግተን እንደምንሠራ፣ ከዚህ በፊት ተመግበናቸው የማናውቃቸውን ምግቦች እንደምንበላ፣ በየጊዜው ከቦታ ቦታ እንደምንዘዋወር፣ ከቤተሰብ ርቀን እንደምንኖርና ብዙውን ጊዜም የተመቻቸ ሁኔታ እንደማናገኝ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የሚያጋጥሙን ችግሮች ካገኘናቸው በረከቶች ጋር ሲወዳደሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም።”
እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ካገኟቸው በረከቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? አብዛኞቹ ሠራተኞች አዳዲስ የግንባታ ሙያዎችን ከሌሎች መማር ችለዋል። ትልልቅ ከሆኑት ቡድኖች መካከል አንዱን በበላይነት የሚከታተለው ካርሎስ የተባለ ፈቃደኛ ሠራተኛ፣ ካገኛቸው በረከቶች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው በመካከላቸው ላለው ግንኙነት እንደሆነ ተናግሯል። ካርሎስ እንዲህ ብሏል:- “ሃያ አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ ሆነናል። የምንመገበው፣ የምንሠራው፣ የምናጠናውም ሆነ የምንጸልየው አንድ ላይ ነው። በመካከላችን በጣም ጠንካራ የሆነ ወዳጅነት አለ።”
ከዚህ በተጨማሪ የግንባታ ቡድኖቹ፣ አዳራሹን ከሚገነቡላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ችለዋል። ከ100 በሚበልጡ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎች ላይ የተካፈለው ሆሴ እንዲህ ብሏል:- “አዳራሽ የተሠራላቸው የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ለማግኘት የነበራቸው ምኞት እውን በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታና አድናቆት ፊታቸው ላይ በሚታየው ፈገግታና በእንባ ሲገልጹ መመልከት በጣም ያስደስታል። ንጹሑን አምልኮ ለማካሄድ የሚያስችል አዳራሽ በተሳካ ሁኔታ በመገንባቱ ሥራ ላይ በምናበረክተው አነስተኛ አስተዋጽኦ እንኳ የሌሎች እምነት እንደሚጠናከር ማወቃችን ያስደስተናል።”
አስገራሚ ውጤት!
እነዚህ የአምልኮ ቦታዎች እጅግ ያጌጡ ወይም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ተብለው የተገነቡ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የመንግሥት አዳራሾቹን ለመገንባት የሚያገለግለው ንድፍ ያልተወሳሰበ ነው፤ ይህ ደግሞ አዳራሾቹን በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅና ብዙ ገንዘብ ለመቆጠብ አስችሏል። ሠራተኞቹ፣ ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ሁሉ በአካባቢው የሚሠራባቸውን ዘዴዎችና የግንባታ ቁሳቁሶች ይጠቀማሉ። በዚህ መንገድ አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ከስድስት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሠርቶ ማጠናቀቅ ይቻላል!
በ2007 በቤሊዝ የሚገኙ ጉባኤዎች በሙሉ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ማግኘት ችለዋል፤ በቤሊዝ በአጠቃላይ 17 የመንግሥት አዳራሾች አሉ። በሜክሲኮ ደግሞ ከ1999 ወዲህ ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ1,400 በላይ የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል!
ማቴዎስ 9:37) በአሁኑ ጊዜ በሜክሲኮ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ600,000 በላይ የደረሰ ሲሆን እነዚህ ሁሉ ከአምላክ ቃል ለመማር በሳምንት ሦስት ጊዜ ይሰበሰባሉ። በመሆኑም ወደ 2,000 ገደማ የሚሆኑ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች አሁንም ያስፈልጋሉ። በፈቃደኝነት የሚከናወነው ይህ የግንባታ ሥራ ሰዎች በሚያደርጉት ጥረት ላይ ብቻ የተመካ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ግብ ላይ መድረስ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው በይሖዋ አምላክ እርዳታ “ሁሉም ነገር ይቻላል።”—ማቴዎስ 19:26
በርካታ ሥራዎችን ማከናወን የተቻለ ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ የሚሠራ አለ። ([በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“የተናገሩትን ያደርጋሉ”
የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራው በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድረው በአካባቢው የሚገኘው ጉባኤ አባላት በሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በቤሊዝ አንድ የመንግሥት አዳራሽ በመገንባት ላይ ሳለ የጰንጠቆስጤ ሃይማኖት ተከታይ የሆነች ሚስት ያለችው አንድ ሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮች “ቤተ ክርስቲያናቸውን” ሠርተው ሲጨርሱ አብሯቸው መሰብሰብ እንደሚፈልግ ለባለቤቱ ነገራት። ይህ ሰው በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የፈለገው ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል:- “አምላክ ከእነሱ ጋር እንዳለ መመልከት ችያለሁ። አብረው ሲሠሩ በመካከላቸው ጠብ የሚባል ነገር የለም፤ ደግሞም የተናገሩትን ያደርጋሉ።”
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኦሬንጅ ዎክ፣ ቤሊዝ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ የሚደረግ እንቅስቃሴ
የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች በ120 አገሮች ውስጥ ይገኛሉ። ፈቃደኛ ሠራተኞች ይህን ሥራ በደስታ ከሚያከናውኑባቸው አገሮች መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል:-
ሆንግ ኮንግ፣ ላይቤሪያ፣ ሕንድ፣ ሞልዶቫ፣ ሩዋንዳ፣ ቦሊቪያ፣ ቱቫሉ፣ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ኢትዮጵያ፣ ካዛክስታን፣ ክሮኤሺያ፣ ዛምቢያ፣ ዩክሬን፣ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ፣ ጃማይካ፣ ጋና፣ ፊጂ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ቬነዝዌላ።
[ሥዕሎች]
በአካፑልኮ፣ ሜክሲኮ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ
በሜክሲኮ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድን አባላት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትላክስካላ፣ ሜክሲኮ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ