የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?
የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?
የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለው አመለካከት በዛሬ አኗኗሩ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ብሩህ ተስፋ የማይታያቸው ሰዎች “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል አመለካከት ሊያዳብሩ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:32) እንዲህ ያለው ዝንባሌ አብዛኛውን ጊዜ ከልክ በላይ ወደ መብላትና ወደ መጠጣት ይመራል። እንዲሁም ጭንቀትን ያስከትላል እንጂ እውነተኛ የአእምሮ ሰላም አያስገኝም።
የወደፊቱ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የተመካው የሰው ልጆች በሚያደርጉት ጥረት ላይ ቢሆን ኖሮ ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀን ነገር ተስፋ ቢስ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የምድራችን አየር፣ ውኃ እንዲሁም አፈር ከዚህ ቀደም ሆኖ በማያውቅ መጠን እየተበከለ ይገኛል። የኑክሌር ጦርነት ይፈነዳ ይሆናል አሊያም ሽብርተኞች ጥቃት ይሰነዝሩ ይሆናል የሚለው ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታና በድህነት እየማቀቁ ነው። ይሁንና ተስፋ እንድናደርግ የሚያስችል ጠንካራ ምክንያት አለን።
ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት ትክክለኛ ትንቢት መናገር የማይችሉ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ አምላክ ግን “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:10) ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ምን ብሏል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ይሖዋ፣ ምድርም ሆነች በውስጧ ያለው ሕይወት መታደስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ድረስ እንዲበላሹ አይፈቅድም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፏትን እንደሚያጠፋ’ ይናገራል። (ራእይ 11:18) ይሖዋ በሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት ክፋትን ከምድር ላይ በማጥፋት የመጀመሪያ ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። (ዘፍጥረት 1:26-31፤ 2:8, 9፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ከዚህ በታች ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በምድር ላይ የሚኖረውን እያንዳንዱን ግለሰብ የሚነኩ ምን ነገሮች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ በመግለጽ የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ ይጠቁሙናል።
መዝሙር 46:8, 9:- “ኑና የእግዚአብሔርን ሥራ፣ ምድርንም እንዴት ባድማ እንዳደረጋት እዩ። ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።”
ኢሳይያስ 35:5, 6:- “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል፤ ውሃ ከበረሓ ይወጣል፤ ምንጮችም ከምድረ በዳ ይፈልቃሉ።”
ኢሳይያስ 65:21, 22:- “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም።”
ዳንኤል 2:44:- “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”
ዮሐንስ 5:28, 29:- “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል።”
ራእይ 21:3, 4:- “[አምላክ] ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ እውነተኛ የአእምሮ ሰላም የሚያስገኘው እንዴት ነው?
መጀመሪያ ላይ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ይፈጸማሉ ብሎ ማመን ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚህን ተስፋዎች የሰጠው ሰው ሳይሆን አምላክ ነው። ይሖዋ አምላክ ደግሞ ‘አይዋሽም።’—ቲቶ 1:2
አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች የምትተማመንና በሕጎቹ የምትመራ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙህ ጊዜም እንኳ የአእምሮ ሰላምህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ። ጦርነት፣ ድህነት፣ በሽታ ሌላው ቀርቶ በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚከሰቱ አንዳንድ ችግሮች ወይም ከነገ ዛሬ እሞታለሁ የሚለው ስጋት እንኳ ያለህን የአእምሮ ሰላም ለዘለቄታው ሊያጠፉት አይችሉም። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እነዚህ ችግሮች ያስከተሏቸውን ጠባሳዎች ጭምር እንደምታስወግድ እርግጠኛ ስለምትሆን ነው።
የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እንዲህ ያለ ጠንካራ ተስፋ ሊኖርህ የሚችለው እንዴት ነው? ‘አእምሮህን ማደስ’ እንዲሁም ‘መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነው የአምላክ ፈቃድ’ ምን እንደሆነ መርምረህ ማረጋገጥ ይኖርብሃል። (ሮሜ 12:2) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸው ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ማስረጃዎች ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ ያለውን ምርምር ማድረግ ምንም ያህል አድካሚ ቢሆን ከጥቅሙ አንጻር ሲታይ የሚያስቆጭ አይደለም። በሕይወትህ ውስጥ የዚህን ያህል የአእምሮ ሰላም የሚያስገኝልህ ነገር አይኖርም።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ ቃል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይላል?