የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?
የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?
የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የሰው ልጆችን በጣም ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች መካከል፣ ሕይወት ትርጉም ወይም ዓላማ የለውም የሚለው ሐሳብ ይገኝበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በሕይወቱ ውስጥ ግልጽ ዓላማ ያለው ሰው መጥፎ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት መቋቋም የሚችል ከመሆኑም በላይ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ብዙ ጊዜ አይፈጅበትም። ከናዚ እልቂት በሕይወት የተረፉት ቪክቶር ፍራንክል የተባሉ ኒውሮሎጂስት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ሕይወት ትርጉም እንዳለው የማወቅን ያህል በጣም አስከፊ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ኃይል የለም ለማለት እደፍራለሁ።”
ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ በርካታ አመለካከቶች አሉ። ብዙ ሰዎች አንድ ሰው ሕይወቱን ዓላማ እንዲኖረው የማድረጉ ኃላፊነት የራሱ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በተቃራኒው ግን በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች ሕይወት ይህ ነው የሚባል ዓላማ የለውም በማለት ያስተምራሉ።
የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ ሕይወት ሰጪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ከመማር የተሻለ መንገድ የለም። በዚህ ረገድ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል እስቲ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በፈጠረበት ወቅት እነሱ እንዲያከናውኑት ያሰበው ግልጽ ዓላማ እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከዚህ በታች ያለውን መመሪያ ሰጣቸው:-
ዘፍጥረት 1:28:- “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።”
አምላክ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ልጆቻቸው መላውን ምድር ገነት እንዲያደርጉ ዓላማው ነበር። ሰዎች እንዲያረጁና እንዲሞቱ እንዲሁም ምድርን እንዲያበላሹ ዓላማው አልነበረም። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ባደረጉት የተሳሳተ ምርጫ ሁላችንም ኃጢአትና ሞትን ወርሰናል። (ዘፍጥረት 3:2-6፤ ሮሜ 5:12) ሆኖም የይሖዋ ዓላማ አልተለወጠም። በቅርቡ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች።—ኢሳይያስ 55:10, 11
ይሖዋ የፈጠረን የእሱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ችሎታ እንዲኖረን አድርጎ ነበር። ያለ እሱ እርዳታ እንድንኖር ተደርገን አልተፈጠርንም። በቀጣዮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ እንዴት እንደተገለጸ ልብ በል።
መክብብ 12:13:- “እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።”
ሚክያስ 6:8:- “እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?”
ማቴዎስ 22:37-39:- “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ እውነተኛ የአእምሮ ሰላም የሚያስገኘው እንዴት ነው?
ውስብስብ የሆነ አንድ ማሽን በትክክል እንዲሠራ ከተፈለገ፣ ለተፈለሰፈበት ዓላማ መዋል እንዲሁም ሠሪው ባቀደው መንገድ አገልግሎት መስጠት አለበት። እኛም በተመሳሳይ በራሳችን ላይ መንፈሳዊ፣ አእምሯዊ፣ ስሜታዊ ወይም አካላዊ ጉዳት እንዳናመጣ ሕይወታችንን ፈጣሪያችን ባቀደው መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል። የአምላክን ዓላማ
ማወቃችን ከታች ከተዘረዘሩት የሕይወት ዘርፎች አንጻር የአእምሮ ሰላም ሊያስገኝልን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ነገሮች አንጻር:- በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው በዋነኝነት ያተኮረው ሀብት በማካበት ላይ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
በሌላ በኩል ግን ከገንዘብ ይልቅ አምላክን መውደድ እንዳለባቸው የተማሩ ሰዎች እርካታ የሚገኝበት ምስጢር ምን እንደሆነ አውቀዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) ጠንክሮ መሥራት ያለውን ጠቀሜታ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። (ኤፌሶን 4:28) በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል የተናገራቸውን የማስጠንቀቂያ ቃላት በቁም ነገር ይመለከቷቸዋል:- “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።”—ማቴዎስ 6:24
ስለዚህ አምላክን የሚወዱ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት ለሰብዓዊ ሥራቸው ወይም ሀብት ለማካበት ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ነው። በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ የሚሰጡ ከሆነ ይሖዋ አምላክ እንደማይተዋቸው ያውቃሉ። ይሖዋም እነሱን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለበት ይሰማዋል።—ማቴዎስ 6:25-33
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት:- በርካታ ሰዎች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ራሳቸውን ማስቀደም ይቀናቸዋል። በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ሰላም የለም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ብዙ ሰዎች ‘ራሳቸውን የሚወዱና ፍቅር የሌላቸው’ መሆናቸው ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3) አንድ ሰው ቢያበሳጫቸው አሊያም ከእነሱ አመለካከት ጋር ባይስማማ ስሜታቸውን የሚገልጹት ‘በቁጣና በንዴት እንዲሁም በጭቅጭቅና በስድብ’ ነው። (ኤፌሶን 4:31) እንዲህ ያለው ራስን ያለመግዛት ባሕርይ የአእምሮ ሰላም ከማምጣት ይልቅ “ጠብ ያነሣሣል።”—ምሳሌ 15:18
ከዚህ በተቃራኒ ግን ሌሎችን እንደራሳቸው አድርገው እንዲወዱ የሚናገረውን የአምላክን ሕግ የሚታዘዙ ሰዎች ‘እርስ በርስ ይቅር የሚባባሉ፣ ቸሮችና ርኅሩኆች’ ናቸው። (ኤፌሶን 4:32፤ ቈላስይስ 3:13) ሌላው ቀርቶ ሰዎች ደግነት የጎደለው ድርጊት ቢፈጽሙባቸው እንኳ ሲሰድቡት ‘መልሶ ያልተሳደበውን’ ኢየሱስን ለመኮረጅ ይጥራሉ። (1 ጴጥሮስ 2:23) ሰዎች ለተደረገላቸው ነገር ባያመሰግኗቸውም እንኳ ልክ እንደ ኢየሱስ ሌሎችን ማገልገል እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ ተረድተዋል። (ማቴዎስ 20:25-28፤ ዮሐንስ 13:14, 15፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35) ይሖዋ አምላክ ልጁን ለመምሰል ለሚጥሩት መንፈሱን ይሰጣቸዋል። ይህ መንፈስ ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ ሰላም እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።—ገላትያ 5:22
ይሁን እንጂ፣ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ያለህ አመለካከት ከአእምሮ ሰላም ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ ዓላማ ሊኖረው ይገባል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የአእምሮ ሰላም እንዴት ማግኘት እንደምንችል አስተምሮናል