በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤው አምላክ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ . . . ይራቅ” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 34:10) ታዲያ አሁን ላለው መከራ ዋነኛው መንስኤ ማን ነው?

ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 14:30) እርግጥ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ይሖዋ ነው፤ ይህን ሥልጣኑን ለማንም አሳልፎ አይሰጥም። ሆኖም አምላክ፣ ሰይጣን ለተወሰነ ጊዜ አብዛኛውን የሰው ዘር እንዲገዛ ፈቅዶለታል።—1 ዮሐንስ 5:19

ሰይጣን ምን ዓይነት ገዢ ነው? ሰይጣን ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይና ውሸታም መሆኑ ታይቷል። ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። ኢየሱስ፣ “እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው” በማለት የሰይጣንን ማንነት አጋልጧል። (ዮሐንስ 8:44) በተጨማሪም ኢየሱስ ሊገድሉት ይፈልጉ የነበሩት ሰዎች፣ የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ የሰይጣን ልጆች መሆናቸውን ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች የሰይጣንን ተግባር በመኮረጅ ራሳቸውን የእሱ ልጆች አድርገዋል። ልጆች አባታቸውን መምሰላቸው ደግሞ ያለ ነገር ነው።

ሰይጣን በአሁኑ ጊዜም እንኳ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የመግደል ዝንባሌ እንዲሰርጽ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው የሐዋይ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩት ሩዶልፍ ራሜል፣ የተለያዩ መንግሥታት ከ1900 እስከ 1987 ባሉት ዓመታት በፖለቲካዊ አለመግባባቶች፣ በዘር ማጥፋት ዘመቻዎች እንዲሁም በጅምላ ጭፍጨፋዎች ወቅት 169,198,000 ሰዎችን እንደገደሉ ተናግረዋል። ይህ ቁጥር በተመሳሳይ ወቅት በጦር ሜዳ ላይ የተገደሉ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አይጨምርም።

ታዲያ መከራን ያመጣው አምላክ ካልሆነ ሰዎች ሲሠቃዩ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው? ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ከረጅም ጊዜ በፊት ተነስተው የነበሩት ጽንፈ ዓለማዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ስላለባቸው ነው። እስቲ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱን ብቻ እንመልከት።

በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን ሰይጣንን ወግነው የአምላክን አገዛዝ አንቀበልም በማለት ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መረጡ። ይህ ውሳኔያቸው ደግሞ በዲያብሎስ አገዛዝ ሥር እንዲወድቁ አድርጓቸዋል።—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9

ይሖዋ ለፍትሕ ያለው ስሜት ለጉዳዩ የሚያስፈልገውን መረጃ ለማሰባሰብ ጊዜ እንዲሰጥ አነሳስቶታል። ታዲያ ጊዜ መፈቀዱ ምን ግልጽ የሆነ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አስችሏል? በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ያለው የሰው አገዛዝ መከራ ከማምጣት ውጪ የፈየደው ነገር የለም። በእርግጥም ጊዜ መፈቀዱ ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለሰው ልጆች ነው። እንዴት? ማስረጃውን ያገናዘቡና በዚያ ላይ እምነት ያሳደሩ ሁሉ በአምላክ ለመገዛት ፈቃደኞች መሆናቸውን የማሳየት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ተምረው በእነሱ የሚመሩ ሁሉ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—ዮሐንስ 17:3፤ 1 ዮሐንስ 2:17

በአሁን ጊዜ፣ ዓለም በክፉው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር መውደቁ እሙን ነው። ሆኖም ሁኔታው በዚህ መልኩ አይቀጥልም። በቅርቡ ይሖዋ፣ በልጁ አማካኝነት ‘የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሳል።’ (1 ዮሐንስ 3:8) ኢየሱስ፣ በአምላክ አመራር ሥር በመሆን የተሰበሩ ልቦችን ይጠግናል እንዲሁም የተመሰቃቀለውን የሰው ልጆች ሕይወት ያስተካክላል። ባለፉት መቶ ዘመናት መከራ ደርሶባቸው የሞቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችንም ከሞት ያስነሳል።—ዮሐንስ 11:25

የኢየሱስ ከሞት መነሳት አምላክ በዲያብሎስ ሥራ ላይ ድል መቀዳጀቱን የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ሲሆን ይህም የአምላክን አገዛዝ የሚመርጡ የሰው ልጆች ወደፊት ምን እንደሚጠብቃቸው የሚጠቁም ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:31) መጽሐፍ ቅዱስ በሚከተሉት አጽናኝ ቃላት አማካኝነት አእምሯችን በመጪው ጊዜ ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል:- “እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4