ስለ አንተ የሚያስብ እረኛ
ወደ አምላክ ቅረብ
ስለ አንተ የሚያስብ እረኛ
‘አምላክ ስለ እኔ ያስባል?’ ይህንን ጥያቄ አንስተህ የምታውቅ ከሆነ እንዲህ ብለህ የጠየቅኸው አንተ ብቻ አይደለህም። አብዛኞቻችን በሕይወት ውስጥ መከራና ችግር አጋጥሞን ያውቃል፤ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የዚህ ግዙፍ ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ ስለ እኛ ያስብ እንደሆነ እንጠይቃለን። ‘ይሖዋ አምላክ በግለሰብ ደረጃ ስለ እኛ ያስባል?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት እንፈልጋለን። ይሖዋን ከማንም በላይ የሚያውቀው ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የተናገረው ምሳሌ ለዚህ ጥያቄ የሚያረካ መልስ ይሰጠናል።
ኢየሱስ፣ ለበጎቹ የሚያስብ እረኛን ሕይወት እንደ ምሳሌ በመውሰድ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋውን በግ ሲያገኝ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በዚያ በተገኘው ደስ ይለዋል። እንደዚሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።” (ማቴዎስ 18:12-14) ይሖዋ፣ እሱን ለሚያመልኩ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብ ኢየሱስ እንዴት እንደገለጸ እስቲ እንመልከት።
እረኛው ስለ እያንዳንዱ በግ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማዋል። አንድ በግ ከመንጋው ርቆ ቢሄድ እረኛው የትኛው በግ እንደጠፋ ያውቃል። እያንዳንዱን በግ ራሱ ባወጣለት ስም ለይቶ ያውቀዋል። (ዮሐንስ 10:3) ይህ አሳቢ እረኛ የባዘነው በግ ተመልሶ ከመንጋው ጋር እስኪቀላቀል ድረስ ፍለጋውን አያቋርጥም። እረኛው የባዘነውን በግ ለመፈለግ ሲሄድ የቀሩትን 99 በጎች ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ አይተዋቸውም። እረኞች ብዙውን ጊዜ አብረው ስለሚሆኑ መንጎቻቸውን ይቀላቅላሉ። * ስለዚህ የባዘነውን በግ ለመፈለግ የሚሄደው እረኛ፣ የቀሩትን በጎች ሌሎች እረኞች ለጊዜው እንዲጠብቁለት ትቶላቸው ሊሄድ ይችላል። እረኛው የጠፋውን በግ አደጋ ሳይደርስበት ሲያገኘው ይደሰታል። የበረገገውን በግ በትከሻው ላይ ተሸክሞ ወደ መንጋው በመውሰድ ከአደጋ እንዲጠበቅ ያደርገዋል።—ሉቃስ 15:5, 6
ኢየሱስ ምሳሌውን ሲያብራራ፣ አምላክ “ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ” እንደማይፈልግ ተናግሯል። ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ “[በእሱ] ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን” እንዳያሰናክሉ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ማቴዎስ 18:6) ታዲያ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ፣ ‘ታናናሾቹን’ በጎች ማለትም ዓለም እምብዛም ትኩረት የማይሰጣቸውን ጨምሮ ስለ እያንዳንዱ በግ በጥልቅ የሚያስብ እረኛ ነው። አዎን፣ አምላክ እያንዳንዱን አገልጋዩን ልዩና ውድ አድርጎ ይመለከተዋል።
አምላክ ውድ እንደሆንክ አድርጎ እንደሚመለከትህ እርግጠኛ ለመሆን ከፈለግህ፣ ታላቁ እረኛ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲሁም ወደ እሱ እንዴት መቅረብ እንደምትችል ለምን አትማርም? እንዲህ ካደረግህ ኢየሱስ ስለጠፋው በግ ምሳሌ ሲናገር ሰምቶ ሊሆን እንደሚችለው እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ዓይነት የመተማመን ስሜት ሊኖርህ ይችላል። ጴጥሮስ “[አምላክ] ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 5:7
[የግርጌ ማስታወሻ]