በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በ2013 ተሻሽሎ የወጣው እንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም

በ2013 ተሻሽሎ የወጣው እንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም

አዲስ ዓለም ትርጉም በተለያዩ ጊዜያት ማሻሻያ የተደረገበት ቢሆንም በ2013 የተደረገው ማሻሻያ እስካሁን ከተደረጉት አንጻር ብዙ ነገሮችን የሚዳስስ ነው። ለምሳሌ በዚህ ትርጉም ውስጥ ያሉት ቃላት ብዛት ከቀድሞው 10 በመቶ ገደማ ቀንሷል። አንዳንድ ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ተለውጠዋል። አንዳንድ ምዕራፎች በግጥም መልክ የተቀመጡ ሲሆን ሐሳቦቹን ግልጽ የሚያደርጉ የግርጌ ማስታወሻዎችም ተጨምረዋል። የተደረጉትን ማሻሻያዎች ሁሉ በዚህ ርዕስ ውስጥ መዘርዘር አይቻልም፤ ሆኖም ዋና ዋና ከሚባሉት ለውጦች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።

የተለወጡት ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የትኞቹ ናቸው? ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው “ሲኦል፣” “ሐዲስ” እና “ነፍስ” የሚሉት ቃላት የተተረጎሙበት መንገድ ተቀይሯል። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አገላለጾችም ተሻሽለዋል።

“ብልግና” የሚለው ቃል፣ የግሪክኛው ቃል የሚያስተላልፈውን የንቀት ዝንባሌ ጥሩ አድርጎ በሚገልጸው “ዓይን ያወጣ ምግባር” በሚለው ሐረግ ተተክቷል። “ዝሙት” የሚለው ቃል በብዙ ቦታዎች ላይ “የፆታ ብልግና” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ይህም በአሁኑ ጊዜ ለመረዳት ይበልጥ ቀላል የሆነ አገላለጽ ነው። (ገላ. 5:19-22) “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው አገላለጽ ደግሞ “ታማኝ ፍቅር” ተብሎ በትክክል ተተርጉሟል። ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ “ታማኝነት” (ፌዝፉልነስ) ተብሎ የሚተረጎመውን ቃል አካቶ የያዘ ነው።—መዝ. 36:5፤ 89:1

በሁሉም ቦታዎች ላይ በተመሳሳይ መንገድ ይተረጎሙ የነበሩ አንዳንድ ቃላት አሁን እንደየአገባባቸው ተተርጉመዋል። ለምሳሌ ኦህላም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ቀደም ሲል የተሠራበት ረጅም ጊዜን ለማመልከት ነበር፤ ይሁንና ይህ ቃል “ዘላለም” የሚል መልእክትም ሊያስተላልፍ ይችላል። የቃሉ የተለያዩ ትርጉሞች እንደ መዝሙር 90:2 እና ሚክያስ 5:2 ባሉ ጥቅሶች ላይ እንዴት እንደተሠራባቸው ተመልከት።

“ዘር” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ ከእህልም ሆነ ከሰዎች አንጻር ተሠርቶባቸዋል። ከዚህ ቀደም የነበሩት የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ዘፍጥረት 3:15ን ጨምሮ በሁሉም ቦታዎች ላይ “ዘር” (ይኸውም ሲድ) የሚለውን ቃል ይጠቀሙ ነበር። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ዘር” የሚለውን ቃል ከሰዎች አንጻር መጠቀም የተለመደ አይደለም፤ በመሆኑም የተሻሻለው እንግሊዝኛ እትም በዘፍጥረት 3:15 እና ከዚያ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ጥቅሶች ላይ ሌላ ቃል (ይኸውም ኦፍስፕሪንግ) ይጠቀማል። (ዘፍ. 22:17, 18፤ ራእይ 12:17) በሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ ቃሉ እንደየአገባቡ ተተርጉሟል።—ዘፍ. 1:11፤ መዝ. 22:30፤ ኢሳ. 57:3

ቃል በቃል ተተርጉመው የነበሩ አገላለጾች ማስተካከያ የተደረገባቸው ለምንድን ነው? በ2013 የተሻሻለው እትም ተጨማሪ መረጃ ሀ1 ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ላይ ያለው ቃል ወይም ሐረግ በቀጥታ በሚተረጎምበት ወቅት ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት የሚያዛባ ወይም የሚያድበሰብስ ከሆነ የቃሉን ወይም የሐረጉን ትክክለኛ መንፈስ ለማስተላለፍ [እንደሚጥር]” ይናገራል። መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ የሚገኙ ዘይቤያዊ አነጋገሮች በሌሎች ቋንቋዎችም የተፈለገውን መልእክት የሚያስተላልፉ ከሆነ ቃል በቃል ይተረጎማሉ። ከዚህ አንጻር ሲታይ በራእይ 2:23 ላይ ያለው ‘ልብን መመርመር’ የሚለው አገላለጽ በብዙ ቋንቋዎች ግልጽ ነው። ይሁንና በዚያው ጥቅስ ላይ ያለው ‘ኩላሊትን መመርመር’ የሚለው ሐረግ ለመረዳት አስቸጋሪ ስለሆነ “ኩላሊት” ከማለት ይልቅ “የውስጥ ሐሳብ” ተብሏል፤ ይህ አተረጓጎም ደግሞ በኩረ ጽሑፉ የሚያስተላልፈውን መልእክት ይዟል። በተመሳሳይም ዘዳግም 32:14 ላይ የሚገኘው “ከስንዴው ኩላሊት ስብ” የሚለው አገላለጽ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን “ከምርጥ ስንዴ” በሚለው ሐረግ ተተክቷል። በብዙ ቋንቋዎች፣ “ከንፈሮቼ ያልተገረዙ” የሚለው አገላለጽም ቢሆን “የመናገር ችግር ያለብኝ” የሚለውን ያህል ግልጽ አይደለም።—ዘፀ. 6:12

“የእስራኤል ወንዶች ልጆች” እና ‘አባት የሌለው ወንድ ልጅ’ የሚሉት አገላለጾች “እስራኤላውያን” እና ‘አባት የሌለው ልጅ’ በሚሉት ሐረጎች የተተኩት ለምንድን ነው? የዕብራይስጥ ቋንቋ ተባዕታይና አንስታይ ፆታን ለመለየት የሚያስችል አገላለጽ ስላለው ሐሳቡ ስለ ወንድ ይሁን ስለ ሴት መለየት አያስቸግርም። ሆኖም አንዳንድ በተባዕት ፆታ የተቀመጡ አገላለጾች ለወንድም ሆነ ለሴት ሊሠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ከአንዳንድ ጥቅሶች አውድ መረዳት እንደሚቻለው “የእስራኤል ወንዶች ልጆች” የሚለው አገላለጽ ለወንዶችም ለሴቶችም ይሠራል፤ በመሆኑም ይህ ሐረግ “እስራኤላውያን” በሚለው ተተክቷል።—ዘፀ. 1:7፤ 35:29፤ 2 ነገ. 8:12

በዘፍጥረት 3:16 ላይ የሚገኘው “ወንዶች ልጆች” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ቀደም ባሉት የአዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ላይ “ልጆች” ተብሏል። በተሻሻለው የእንግሊዝኛ እትም ላይም ይኸው ቃል በዘፀአት 22:24 ላይ “ልጆቻችሁ [በዕብራይስጥ “ወንዶች ልጆቻችሁ”] አባት የሌላቸው ልጆች ይሆናሉ” ተብሎ ተተርጉሟል። ይህንን አካሄድ በመከተል በሌሎች ቦታዎችም ላይ አባት የሌለው ወንድ ልጅ’ የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ‘አባት የሌለው ልጅ’ ወይም ‘ወላጅ አልባ ልጅ’ በሚለው ተተክቷል። (ዘዳ. 10:18፤ ኢዮብ 6:27) ይህም የግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ከተተረጎመበት መንገድ ጋር ይመሳሰላል።

የአብዛኞቹ የዕብራይስጥ ግሶች ትርጉም ቀላል እንዲሆን የተደረገው ለምንድን ነው? በዕብራይስጥ ቋንቋ ሁለት ዋና ዋና የግስ ዓይነቶች አሉ፤ አንደኛው ቀጣይ የሆነን ድርጊት የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የተጠናቀቀን ድርጊት የሚያመለክት ነው። ቀደም ሲል የነበሩት የአዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ቀጣይ የሆነ ድርጊትን የሚያሳዩ የዕብራይስጥ ግሶችን ሲተረጉሙ ድርጊቱ ቀጣይ እንደሆነ የሚያሳዩ ሐረጎችን ከግሱ ጋር ይጠቀሙ ነበር። * ድርጊቱ የተጠናቀቀ መሆኑን የሚያሳይ ግስ እንዳለ ለመጠቆም ደግሞ “በእርግጥ” እንደሚለው ያሉ አጽንኦትን የሚገልጹ ቃላት ይጨምሩ ነበር።

በ2013 የወጣው የተሻሻለው እትም፣ በትርጉሙ ላይ ለውጥ እስካላመጣ ድረስ እንደዚህ ያሉ ተጨማሪ መግለጫዎችን አይጠቀምም። ለምሳሌ አምላክ “ብርሃን ይሁን” በማለት የተናገረው በተደጋጋሚ እንደሆነ መግለጽ አስፈላጊ ስላልሆነ “አለ” የሚለው ግስ ቀጣይነትን በሚያሳይ መንገድ አልተተረጎመም። (ዘፍ. 1:3) ይሁንና ይሖዋ አዳምን ደጋግሞ እንደጠራው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ በመሆኑም ይህንን ሐሳብ ለማስተላለፍ ዘፍጥረት 3:9 ላይ “በተደጋጋሚ በመጣራት” የሚለው ሐረግ ገብቷል። በጥቅሉ ሲታይ ትኩረት የተደረገው ግሶቹን ቀለል ባለ መንገድ በማስቀመጥ ላይ እንጂ የዕብራይስጡን ግስ ቀጣይነት በማሳየት ላይ አይደለም። ይህ ደግሞ ልክ እንደ ዕብራይስጡ መልእክቱን ቅልብጭ ባለ መንገድ ለማስቀመጥ አስችሏል።

መጀመሪያ የተጻፉበትን ይዘት ለመጠበቅ ሲባል ተጨማሪ ምዕራፎች በግጥም መልክ እንዲቀመጡ ተደርጓል

ተጨማሪ ምዕራፎች በግጥም መልክ የተቀመጡት ለምንድን ነው? በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መጀመሪያ የተጻፉት በግጥም መልክ ነው። በአሁኑ ጊዜ ባሉ አብዛኞቹ ቋንቋዎች አንድን ጽሑፍ ግጥም የሚያሰኘው ቤት መምታቱ ነው፤ በዕብራይስጥ ቋንቋ ግን ዋናው የግጥም መለያ፣ ተመሳሳይ ወይም ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን በንጽጽር ማስቀመጥ ነው። በዕብራይስጥ ቋንቋ አንድ ግጥም ቤት መታ የሚባለው የስንኙ አጨራረስ ተመሳሳይ በመሆኑ ሳይሆን ሐሳቡ ትርጉም በሚሰጥ ቅደም ተከተል በመቀመጡ ነው።

ቀደም ሲል በተዘጋጁት የአዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ላይ የኢዮብና የመዝሙር መጻሕፍት የተቀመጡት በግጥም መልክ ነው፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ሐሳቦቹ መጀመሪያውኑም ቢሆን የተዘጋጁት እንዲዘመሩ ወይም በቃል እንዲደገሙ ታስቦ እንደሆነ ለማሳየት ነው። ይህ ዓይነቱ አቀማመጥ ስንኞቹን አጉልቶ የሚያወጣ ከመሆኑም ሌላ መልእክቱን ለማስታወስ ይረዳል። በ2013 በወጣው እትም ላይ ምሳሌና መኃልየ መኃልይ እንዲሁም በነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ያሉ በርካታ ምዕራፎችም በግጥም መልክ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፤ ይህም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መጀመሪያ በግጥም መልክ እንደተጻፉ ብሎም ተመሳሳይ ወይም ተቃራኒ የሆኑ ስንኞችን እንደያዙ ለማጉላት ያስችላል። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ 24:2 ላይ እያንዳንዱ መስመር በንጽጽር ተቀምጧል። ይህ ጥቅስ የተጻፈው አንዱ ሐሳብ ወደ ሌላው እንዲመራ ተደርጎ ሲሆን ከአምላክ ፍርድ የሚያመልጥ ማንም እንደሌለ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። እንዲህ ያሉ ዘገባዎች በግጥም መልክ መጻፋቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው አንድን ሐሳብ እየደጋገመ ሳይሆን የአምላክን መልዕክት ጎላ አድርጎ ለመግለጽ የግጥም የአጻጻፍ ስልት እየተጠቀመ እንደሆነ ያሳያል።

በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀ ስድ ንባብንና ግጥምን ሁልጊዜ በቀላሉ መለየት ስለማይቻል አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በግጥም መልክ ያስቀመጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሌሎቹ በስድ ንባብ መልክ ያስቀምጡታል። በግጥም መልክ መጻፍ ያለባቸው የትኞቹ ክፍሎች እንደሆኑ የሚወስኑት ተርጓሚዎቹ ናቸው። አንዳንዶቹ ዘገባዎች በስድ ንባብ መልክ ቢቀመጡም ሐሳቡን ለማጉላት ሥዕላዊና ቅኔያዊ አገላለጾችን እንዲሁም ንጽጽሮችን ስለሚጠቀሙ የግጥም ይዘት አላቸው።

በተሻሻለው እትም ላይ “የመጽሐፉ ይዘት” የሚባል አዲስ ገጽታ አለ፤ በተለይ ጥንታዊ የግጥም መጽሐፍ በሆነው መኃልየ መኃልይ ላይ ተናጋሪዎቹ ቶሎ ቶሎ ስለሚቀያየሩ ይህ ገጽታ መኖሩ ማን እየተናገረ እንዳለ በቀላሉ ለመለየት ያስችላል።

በእጅ በተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ የተደረገው ጥናት ለዚህ እትም ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? የመጀመሪያው የአዲስ ዓለም ትርጉም እትም መሠረት ያደረገው የዕብራይስጡን የማሶሬቶች ጽሑፍ እንዲሁም በዌስትኮትና ሆርት የተዘጋጀውን ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ የግሪክኛ ጽሑፍ ነው። በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ የሚደረገው ጥናት አዳዲስ መረጃዎችን ማስገኘቱን ቀጥሏል፤ ይህም ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር በተያያዘ አዲስ ግንዛቤ አስገኝቷል። በአሁኑ ጊዜ የሙት ባሕር ጥቅልሎችን ቅጂ ማግኘት ይቻላል። በግሪክኛ በተዘጋጁ ተጨማሪ ጥንታዊ ቅጂዎችም ላይ ጥናት ተደርጓል። እነዚህ አዳዲስ ጥንታዊ ቅጂዎች ኮምፒውተር ላይ ስለገቡ በቅጂዎቹ መካከል ያለውን ልዩነት በቀላሉ ማወዳደር ይቻላል፤ ይህ ደግሞ የትኛው የዕብራይስጥ ወይም የግሪክ ጽሑፍ ብዙ ድጋፍ እንዳለው ለማወቅ ይረዳል። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ እነዚህን መረጃዎች በመመርመር በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ የተወሰነ ማሻሻያ አድርጓል።

ለምሳሌ በ2 ሳሙኤል 13:21 ላይ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም “ሆኖም አምኖን የበኩር ልጁ በመሆኑ በጣም ይወደው ስለነበር ሊያስቀይመው አልፈለገም” የሚል ሐሳብ ይዟል። ይህ ሐሳብ በማሶሬቶች ቅጂዎች ላይ ስለማይገኝ ቀደም ሲል በነበሩት የአዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ላይ አልተካተተም። ይሁንና ይህ የጥቅሱ ክፍል በሙት ባሕር ጥቅልሎች ላይ ስለሚገኝ በ2013 በወጣው የተሻሻለ ትርጉም ውስጥ ተካትቷል። የአምላክ ስም በአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ አምስት ቦታዎች ላይ የተጨመረውም በዚሁ ምክንያት ነው። በጥንታዊ ግሪክኛ ቅጂዎች ላይ የተደረገው ጥናት በማቴዎስ 21:29-31 ላይ ያሉት ሐሳቦች ቅደም ተከተልም እንዲለወጥ አድርጓል። በመሆኑም አንዳንዶቹ ለውጦች የተደረጉት አንድን ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂ በጥብቅ ከመከተል ይልቅ አብዛኞቹ ቅጂዎች ላይ ያለውን ሐሳብ ለማንጸባረቅ ሲባል ነው።

በ2013 የተዘጋጀው የእንግሊዝኛው እትም ለማንበብ የሚጋብዝና ለመረዳት ቀላል እንዲሆን ካደረጉት ለውጦች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በእርግጥም ብዙዎች አዲስ ዓለም ትርጉምን አምላክ ሐሳቡን ለእኛ ለመግለጽ የተጠቀመበት ልዩ ስጦታ እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው የሚያስገርም አይደለም።

^ አን.10 ባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ተጨማሪ መረጃ 3C ላይ የሚገኘውን “ቀጣይ ድርጊት የሚያመለክቱ የዕብራይስጥ ግሶች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።