በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ኪንግዝሊ ከቻለ እኔም እችላለሁ!”

“ኪንግዝሊ ከቻለ እኔም እችላለሁ!”

ኪንግዝሊ ትከሻውን ነካ በማድረግ ምልክት ሲሰጠው በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ክፍሉን ማቅረብ ጀመረ፤ ክፍሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ነው። አንድም ፊደል ሳይገድፍ እያንዳንዷን ቃል ጥርት አድርጎ አነበበ። እንዴ! መጽሐፍ ቅዱሱን እያየ የማያነበው ለምንድን ነው?

በስሪ ላንካ የሚኖረው ኪንግዝሊ ዓይነ ስውር ነው። በተጨማሪም የመስማት ችግር ያለበት ሲሆን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ወንበር ያስፈልገዋል። ለመሆኑ ይህ ሰው ስለ ይሖዋ መማርና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቃቱን ማሟላት የቻለው እንዴት ነው? እስቲ ታሪኩን ላጫውታችሁ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከኪንግዝሊ ጋር ስንገናኝ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረው ጥማት አስደንቆኝ ነበር። ከዚያ በፊት ከተለያዩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና ሲሆን በብሬይል የተዘጋጀው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፉ ብዙ ከማገልገሉ የተነሳ አርጅቷል። * ኪንግዝሊ ጥናቱን እንዲቀጥል ያቀረብኩለትን ግብዣ ተቀበለ፤ ይሁን እንጂ ሁለት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጠሙን።

አንደኛ፣ ኪንግዝሊ የሚኖረው ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች በተዘጋጀ ቤት ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር ነው። በአካባቢው ጫጫታ ከመኖሩም ሌላ የኪንግዝሊ የመስማት ችሎታ ደካማ በመሆኑ ድምፄን ከፍ አድርጌ መናገር ነበረብኝ። በመሆኑም  እዚያ የነበረ ሰው ሁሉ በየሳምንቱ ስናጠና መስማት ይችላል!

ሁለተኛ ደግሞ፣ ኪንግዝሊ በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ማንበብና መረዳት የሚችለው አዲስ ሐሳብ ትንሽ ነው። የጥናት ጊዜያችንን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንድንችል ኪንግዝሊ በትጋት ይዘጋጅ ነበር። የሚጠናውን ነገር በቅድሚያ ደግሞ ደጋግሞ ያነበዋል፤ ጥቅሶቹንም በብሬይል መጽሐፍ ቅዱሱ ላይ አውጥቶ ያነብባል፤ ከዚያም የጥያቄዎቹን መልስ በአእምሮው ይዘጋጃል። ይህ ዘዴ በጣም ውጤታማ ነው። ኪንግዝሊ በጥናታችን ወቅት በምንጣፉ ላይ እግሮቹን አጣምሮ ይቀመጥና የተማረውን ነገር ድምፁን ከፍ አድርጎ ይገልጽልኛል፤ ይህን የሚያደርገው በደስታ ወለሉን እየቆረቆረ ነው። ብዙም ሳይቆይ በሳምንት ሁለት ጊዜ ማጥናት ጀመርን፤ እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ ሁለት ሰዓት ይወስድ ነበር!

በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ

ኪንግዝሊና ፖል

ኪንግዝሊ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጉጉት ቢኖረውም ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ለመቀመጥና ለመነሳት እንዲሁም ወደ መኪና ብሎም ወደ መንግሥት አዳራሹ ለመግባትና ለመውጣት እርዳታ ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ በጉባኤው ውስጥ ብዙዎች እሱን መርዳት መብት እንደሆነ ስለሚሰማቸው በየተራ ይህን ያደርጉ ነበር። ስብሰባዎች በሚደረጉበት ወቅት ኪንግዝሊ የድምፅ ማጉያ አጠገብ ተቀምጦ በትኩረት ያዳምጣል፤ አልፎ ተርፎም ሐሳብ ይሰጣል!

ኪንግዝሊ ለተወሰነ ጊዜ ካጠና በኋላ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመመዝገብ ወሰነ። የመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡን ሊያቀርብ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ልምምድ እያደረገ እንደሆነ ጠየቅሁት። እሱም በልበ ሙሉነት “አዎ ወንድም፣ 30 ጊዜ ያህል ተለማምጄዋለሁ” አለኝ። ላደረገው ጥረት አመሰገንኩትና ንባቡን እንዲያሰማኝ ጠየቅሁት። እሱም መጽሐፍ ቅዱሱን ከገለጠ በኋላ እጆቹን ብሬይሉ ላይ አሳርፎ ማንበብ ጀመረ። ይሁን እንጂ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው ጣቶቹ የሚያነበውን መስመር ተከትለው እንደማይንቀሳቀሱ አስተዋልኩ። ለካስ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡን ሙሉውን ሸምድዶታል!

በዚህ ጊዜ እንባዬ በጉንጬ ላይ ይወርድ ጀመር፤ ያየሁትን ማመን ስላቃተኝ፣ ንባቡን 30 ጊዜ ብቻ በመለማመድ እንዴት በቃሉ ሊይዘው እንደቻለ ኪንግዝሊን ጠየቅሁት። እሱም “በየቀኑ 30 ጊዜ ያህል ተለማምጄዋለሁ ማለቴ ነው” አለኝ። ኪንግዝሊ ክፍሉን በቃሉ እስኪይዘው ድረስ ምንጣፉ ላይ ተቀምጦ ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜ ደግሞ ደጋግሞ ሲያነበው ቆይቷል።

ከዚያም ክፍሉን በመንግሥት አዳራሹ የሚያቀርብበት ቀን ደረሰ። ኪንግዝሊ ንባቡን አቅርቦ ሲጨርስ አዳራሹ በጭብጨባ አስተጋባ፤ እንዲሁም ብዙዎች ይህ አዲስ ተማሪ ያሳየው ቆራጥነት ልባቸውን ስለነካው አለቀሱ። በፍርሃት ምክንያት በትምህርት ቤቱ ክፍል ማቅረቧን አቋርጣ የነበረች አንዲት አስፋፊ እንደገና ለመመዝገብ ጠየቀች። ለምን? “ኪንግዝሊ ከቻለ እኔም እችላለሁ!” ብላለች።

ኪንግዝሊ መጽሐፍ ቅዱስን ለሦስት ዓመታት ካጠና በኋላ ሕይወቱን ለይሖዋ መወሰኑን ለማሳየት መስከረም 6 ቀን 2008 ተጠመቀ። ግንቦት 13 ቀን 2014 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ የቆየው ኪንግዝሊ፣ ምድር ገነት ስትሆን የተሟላ ጥንካሬና ፍጹም ጤንነት አግኝቶ ይሖዋን ማገልገሉን እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነበር። (ኢሳ. 35:5, 6)—ፖል ማክማነስ እንደተናገረው

^ አን.4 በ1995 የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።