በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 2

ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 2

“አባታችሁ . . . ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።”—ማቴ. 6:8

1-3. አንዲት እህት፣ ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያውቅ እርግጠኛ የሆነችው ለምንድን ነው?

ላና ጀርመን ውስጥ በ2012 አንድ ቀን ያጋጠማትን ነገር መቼም ቢሆን አትረሳውም። ሁለት ነገሮችን ለይታ በመጥቀስ ያቀረበችው ጸሎት ምላሽ እንዳገኘ ተሰምቷታል። የመጀመሪያውን ጸሎት ያቀረበችው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ለመሄድ በባቡር ባደረገችው ረጅም ጉዞ ላይ ነው። ምሥክርነት መስጠት እንድትችል አጋጣሚውን እንዲከፍትላት ይሖዋን ጠየቀችው። ሁለተኛውን ጸሎት ያቀረበችው ደግሞ አውሮፕላን ማረፊያው ደርሳ በረራው በአንድ ቀን እንደተራዘመ ስታውቅ ነው። ላና ከነበራት የአውሮፓ ገንዘብ የቀራት በጣም ትንሽ ሲሆን የምታርፍበት ቦታም አልነበራትም፤ በመሆኑም ይህን አስመልክታ ጸለየች።

2 ላና ሁለተኛውን ጸሎቷን ልክ እንደጨረሰች አንድ ሰው “ታዲያስ ላና፣ እዚህ ምን ትሠሪያለሽ?” አላት። ይህን ያላት አብሯት የተማረ አንድ ወጣት ነው። ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሄድ በመሆኑ እናቱና አያቱ ሊሸኙት አብረውት መጥተዋል። የወጣቱ እናት ኤልኬ፣ ላና ያጋጠማትን ሁኔታ ስታውቅ እነሱ ቤት እንድታርፍ በደግነት ጋበዘቻት። ኤልኬና እናቷ ላናን ጥሩ አድርገው ያስተናገዷት ሲሆን ስለ እምነቷና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ በመሆን ስለምታከናውነው ሥራ ብዙ ጥያቄዎች አቀረቡላት።

 3 በሚቀጥለው ቀን ላና ጥሩ ቁርስ ከበላች በኋላ ኤልኬና እናቷ ላነሷቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ሰጠቻቸው፤ ከዚያም ያስተናገዷትን እነዚህን ሰዎች ተከታትሎ የሚረዳቸው ሰው ለማመቻቸት ስትል አድራሻቸውን ወሰደች። ላና በሰላም ወደ ቤቷ ተመልሳ በአቅኚነት ማገልገሏን መቀጠል ችላለች። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ ነገሮችን እንዳሳካላት ይሰማታል።—መዝ. 65:2

4. ስለ የትኞቹ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንመረምራለን?

4 ድንገተኛ ችግር ሲያጋጥመን ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ አይከብደን ይሆናል፤ ይሖዋም ቢሆን ታማኞቹ የሚያቀርቡትን እንዲህ ያለውን ልመና መስማት ያስደስተዋል። (መዝ. 34:15፤ ምሳሌ 15:8) ይሁንና በጸሎት ናሙናው ላይ የምናሰላስል ከሆነ አንዳንድ ጊዜ በጸሎታችን የማንጠቅሳቸው ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ እናስተውል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በጸሎት ናሙናው ላይ በሚገኙት የመጨረሻዎቹ ሦስት ልመናዎች ላይ መንፈሳዊ ፍላጎታችን የተገለጸው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በሌላ በኩል ደግሞ ከዕለት ምግባችን ጋር ከተያያዘው ከአራተኛው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን?—ማቴዎስ 6:11-13ን አንብብ።

“የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን”

5, 6. በቂ ቁሳዊ ነገር ቢኖረንም እንኳ ይሖዋ የዕለት ምግባችንን እንዲሰጠን መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ይህን ልመና ስናቀርብ የዕለት “ምግቤን” ብቻ ሳይሆን የዕለት “ምግባችንን” ማለት እንዳለብን ልብ በል። በአፍሪካ የሚያገለግል ቪክቶር የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ የምንበላውን ምግብ ከየት እንደምናገኝ ወይም የቤት ኪራይ ማን እንደሚከፍልልን መጨነቅ ስለማያስፈልገን ይሖዋን ብዙ ጊዜ ከልቤ አመሰግነዋለሁ። ወንድሞቻችን የሚያስፈልገንን ነገር በየዕለቱ በደግነት ይሰጡናል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛን የሚንከባከቡን ወንድሞች የሚያጋጥሟቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች መቋቋም እንዲችሉ ይሖዋ እንዲረዳቸው እጸልያለሁ።”

6 እኛም ለብዙ ቀን የሚሆን ምግብ ይኖረን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ድሃ የሆኑ ወይም አደጋ በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ማሰብ አለብን። ስለ እነሱ ከመጸለይም አልፈን ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ ያለንን ነገር እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ማካፈል እንችላለን። በተጨማሪም ለዓለም አቀፉ ሥራ የምናደርገው መዋጮ እንደማይባክን እርግጠኛ በመሆን አዘውትረን የገንዘብ መዋጮ የማድረግ አጋጣሚ አለን።—1 ዮሐ. 3:17

7. ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ” የሚለውን ምክር ለማብራራት ምን ምሳሌ ተጠቀመ?

7 ኢየሱስ ስለ ዕለት ምግባችን ሲጠቅስ በየቀኑ ስለሚያስፈልገን ነገር መናገሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። አምላክ፣ አበቦችን እንደሚያለብስ ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? ስለዚህ . . . ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ።” ከዚያም “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ” የሚለውን ጠቃሚ ምክር በድጋሚ በመናገር ሐሳቡን ደመደመ። (ማቴ. 6:30-34) ይህም ለቁሳዊ ነገሮች ፍቅር ከማዳበር ይልቅ መሠረታዊ ስለሆኑት በየዕለቱ የሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ ማሰብ እንዳለብን ያሳያል። ከእነዚህ ፍላጎቶች መካከል ተስማሚ መኖሪያ፣ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር የሚያስችለን ሥራ እንዲሁም የጤና ችግሮችን ለመወጣት የሚረዳን ጥበብ ይገኙበታል። ይሁንና የምንጸልየው ከአካላዊ ፍላጎታችን ጋር ስለተያያዙት ስለ እነዚህ ነገሮች ብቻ ከሆነ ይህ ሚዛናዊ እንዳልሆንን የሚጠቁም ነው። ምክንያቱም ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ መንፈሳዊ ፍላጎት አለን።

8. ኢየሱስ የዕለት ምግብን መጥቀሱ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው ስለ የትኛው ፍላጎታችን እንድናስታውስ ሊያደርገን ይገባል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

8 ኢየሱስ የዕለት ምግባችንን መጥቀሱ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያስፈልገንም ሊያስታውሰን ይገባል። ጌታችን “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴ. 4:4) እንግዲያው ይሖዋ በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል ምንጊዜም ልንጸልይ ይገባል።

 “በደላችንን ይቅር በለን”

9. ኃጢአታችን እንደ “ዕዳ” ሊቆጠር የሚችለው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ የተጠቀመበት “በደላችን” ወይም “ኃጢአታችን” የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ዕዳችን” ማለት ነው፤ ኢየሱስ “ዕዳ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ማቴ. 6:12 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሉቃስ 11:4) ከ60 ዓመት በፊት በዚህ መጽሔት ላይ የሚከተለው ግሩም ማብራሪያ ወጥቶ ነበር፦ “የአምላክን ሕግ ስንተላለፍ የምንፈጽመው ኃጢአት የእሱ ባለዕዳዎች ያደርገናል። . . . አምላክ ለሠራነው ኃጢአት ሕይወታችንን ሊያስከፍለን ይችላል። . . . ሰላሙን ሊወስድብን በሌላ አባባል ከእኛ ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ሊያቋርጥ ይችላል። . . . ታዛዥ በመሆን የምንከፍለው የፍቅር ዕዳ አለብን፤ ኃጢአት በፈጸምን ቁጥር ደግሞ ለእሱ ያለብንን የፍቅር ዕዳ ሳንከፍል እንቀራለን፤ ምክንያቱም ኃጢአት መፈጸማችን ለአምላክ ያለን ፍቅር መቀነሱን ያሳያል።”—1 ዮሐ. 5:3

10. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር የሚለን ምንን መሠረት አድርጎ ነው? ይህን በተመለከተስ ምን ሊሰማን ይገባል?

10 በየዕለቱ ይቅርታ የሚያስፈልገን መሆኑ፣ አምላክ ኃጢአታችንን መሰረዝ የሚችልበት ብቸኛ ሕጋዊ መሠረት ይኸውም የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። ይህ ቤዛ የተከፈለው ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ቢሆንም ዛሬ እንደተቀበልነው ስጦታ በአድናቆት ልንመለከተው ይገባል። ለሕይወታችን የተከፈለው “የቤዛ ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ” ፍጹም ያልሆነ ማንኛውም ሰው ቤዛውን ለመክፈል ምንም ማድረግ አይችልም። (መዝሙር 49:7-9ን እና 1 ጴጥሮስ 1:18, 19ን አንብብ።) በእርግጥም ለዚህ ታላቅ ስጦታ ይሖዋን ሁልጊዜ ልናመሰግነው ይገባል። በተጨማሪም በጸሎቱ ላይ “በደሌን” ሳይሆን “በደላችንን” መባሉ የእምነት ቤተሰባችን አባላት በሙሉ ምሕረት የተንጸባረቀበት ይህ ዝግጅት እንደሚያስፈልጋቸው እንድናስታውስ ያደርገናል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ስለ ራሳችን መንፈሳዊ ደህንነት ብቻ ሳይሆን እንደበደሉን የሚሰማንን ሰዎች ጨምሮ ስለ ሌሎች መንፈሳዊ ፍላጎትም እንድናስብ ይፈልጋል። በእርግጥ ብዙውን ጊዜ የሚደርሱብን በደሎች ቀላል ናቸው፤ ሆኖም ወንድሞቻችንን ይቅር ስንላቸው፣ ከልብ እንደምንወዳቸውና መሐሪው አምላክ ይቅር እንዳለን ሁሉ እኛም እነሱን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆንን እናሳያለን።—ቆላ. 3:13

አምላክ ይቅር እንዲልህ ከፈለግህ ሌሎችን ይቅር በል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11. የይቅር ባይነት መንፈስ ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 የሚያሳዝነው ነገር፣ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች  በመሆናችን አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ላይ ቂም እንይዝ ይሆናል። (ዘሌ. 19:18) ስለ ጉዳዩ ለሌሎች የምናወራ ከሆነ አንዳንዶች ከእኛ ጋር እንዲወግኑና በጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር እናደርጋለን። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲቀጥል የምንፈቅድ ከሆነ ደግሞ ለአምላክ ምሕረትና ለቤዛው አድናቆት እንደጎደለን እናሳያለን። የይቅር ባይነት መንፈስ የማናሳይ ከሆነ አባታችን በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት እኛን ይቅር ማለቱን ይተዋል። (ማቴ. 18:35) ኢየሱስ የጸሎት ናሙናውን ካስተማረ በኋላ ወዲያውኑ ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:14, 15ን አንብብ።) በመጨረሻም አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን፣ በኃጢአት ጎዳና ላለመመላለስ ጥረት ማድረግ አለብን። ከኃጢአት ለመራቅ ያለን ፍላጎት ደግሞ የሚቀጥለውን ልመና ለማቅረብ ያነሳሳናል።—1 ዮሐ. 3:4, 6

“ወደ ፈተና አታግባን”

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ምን አጋጠመው? (ለ) በፈተና ብንወድቅ ጥፋቱ የራሳችን መሆኑን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? (ሐ) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆኑ ምን አረጋግጧል?

12 ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ያጋጠመውን ነገር መመልከታችን “ወደ ፈተና አታግባን” ብለን መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። የአምላክ መንፈስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ መራው። ለምን? ጥቅሱ “ዲያብሎስ ይፈትነው ዘንድ” ይላል። (ማቴ. 4:1፤ 6:13) ይህ ሊያስገርመን ይገባል? አምላክ፣ ልጁን ወደ ምድር የላከበትን ዋነኛ ምክንያት ካወቅን ይህ አያስገርመንም። ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው አዳምና ሔዋን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ሲያምፁ ለተነሳው ጥያቄ እልባት ለመስጠት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች አስነስቷል፦ አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ጉድለት ነበረው? ፍጹም የሆነ ሰው፣ “ክፉው” ተጽዕኖ ቢያሳድርበትም እንኳ የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፍ ይችል ነበር? ደግሞስ ሰይጣን እንዳለው የሰው ዘር ከአምላክ አገዛዝ ውጭ የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላል? (ዘፍ. 3:4, 5) እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ጊዜ ያስፈልጋል፤ ሆኖም ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘታቸው የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ አምላክ ሉዓላዊነቱን ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት ማየት እንዲችሉ ያደርጋል።

13 ይሖዋ ቅዱስ ነው፤ በመሆኑም ማንንም ክፉ እንዲያደርግ አይፈትንም። ከዚህ ይልቅ “ፈታኙ” ዲያብሎስ ነው። (ማቴ. 4:3) ዲያብሎስ ወደ ፈተና የሚመሩ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል። ሆኖም እያንዳንዱ ግለሰብ ፈተና ውስጥ መግባት አለመግባቱ በራሱ ላይ የተመካ ነው። (ያዕቆብ 1:13-15ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ሰይጣን ያቀረበለትን እያንዳንዱን ፈተና ከአምላክ ቃል ውስጥ ተስማሚ ጥቅስ በመጥቀስ ወዲያውኑ ተቃውሟል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የአምላክን ሉዓላዊነት ደግፏል። ሰይጣን ግን ተስፋ አልቆረጠም። “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ” ጠበቀ። (ሉቃስ 4:13) ኢየሱስም ቢሆን ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ሰይጣን ባደረገበት ተጽዕኖ አልተሸነፈም። ክርስቶስ፣ የይሖዋ ሉዓላዊነት በጽድቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያረጋገጠ ከመሆኑም ሌላ አንድ ፍጹም ሰው ከምንም በላይ ከባድ የሆነ ፈተና ቢያጋጥመውም እንኳ ታማኝ መሆን እንደሚችል አሳይቷል። ያም ቢሆን ሰይጣን አንተን ጨምሮ የኢየሱስን ተከታዮች ለማጥመድ ጥረት ያደርጋል።

14. ወደ ፈተና እንዳንገባ ምን ማድረግ አለብን?

14 ከአምላክ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ መልስ ስላላገኘ ፈታኙ በዚህ ዓለም ተጠቅሞ እንዲፈትነን ይሖዋ ፈቅዶለታል። ወደ ፈተና የሚያስገባን አምላክ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ በእኛ የሚተማመን ከመሆኑም ሌላ ሊረዳን ይፈልጋል። ይሁንና ይሖዋ የመምረጥ ነፃነታችንን ሊጋፋ ስለማይፈልግ ወደ ፈተና እንዳንገባ አይከለክለንም። እኛ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይኸውም በመንፈሳዊ ንቁ መሆንና በጸሎት መጽናት አለብን። ታዲያ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው?

መንፈሳዊነታችሁንና ለአገልግሎቱ ያላችሁን ቅንዓት ጠብቃችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15, 16. (ሀ) ልንቋቋማቸው የሚገቡ አንዳንድ ፈተናዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) አንድ ሰው በፈተና ቢወድቅ ተጠያቂው ማን ነው?

15 ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ያለውን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጥንካሬ እንድናገኝና ፈተናን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። በተጨማሪም አምላክ  ልንርቃቸው ስለሚገቡ ሁኔታዎች በቃሉና በጉባኤው አማካኝነት አስቀድሞ ያስጠነቅቀናል፤ ከማስጠንቀቂያዎቹ መካከል እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ማጥፋትን አስመልክቶ የሚሰጠን ምክር ይገኝበታል። ኢስፔንና ያኒ የሚኖሩት በአውሮፓ በሚገኝ አንድ የበለጸገ አገር ነው። እነዚህ ባልና ሚስት በአገራቸው ውስጥ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለብዙ ዓመታት በዘወትር አቅኚነት አገልግለዋል። የመጀመሪያ ልጃቸው ሲወለድ አቅኚነትን ለማቆም ተገደዱ፤ አሁን ሁለተኛ ልጅ ወልደዋል። ኢስፔን እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል እናደርገው እንደነበረው አሁን በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ አንችልም፤ በመሆኑም ፈተና ውስጥ እንዳንወድቅ አዘውትረን ወደ ይሖዋ እንጸልያለን። መንፈሳዊነታችንንና ለአገልግሎቱ ያለንን ቅንዓት ጠብቀን ለመኖር እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቀዋለን።”

16 በዘመናችን የተስፋፋው ሌላው ፈተና ደግሞ ፖርኖግራፊ ማየት ነው። እንዲህ ባለው ፈተና ከወደቅን በሰይጣን ልናሳብብ አንችልም። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም የማንፈልገውን ነገር እንድናደርግ ሊያስገድዱን አይችሉም። አንዳንዶች፣ መጥፎ በሆኑ ነገሮች ላይ በማሰላሰላቸው በዚህ ፈተና ወድቀዋል። ሆኖም በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እንዳደረጉት እኛም ይህን ፈተና መቋቋም እንችላለን።—1 ቆሮ. 10:12, 13

“ከክፉው አድነን”

17. (ሀ) ከክፉው እንዲያድነን ከምናቀርበው ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በቅርቡ ምን እፎይታ እናገኛለን?

17 “ከክፉው አድነን” ከሚለው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ከፈለግን፣ የሰይጣን ‘ዓለም ክፍል ላለመሆን’ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ እንዲሁም የሰይጣንን ‘ዓለምም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች መውደድ’ የለብንም። (ዮሐ. 15:19፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ይህን ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ትግል ይጠይቃል። ይሖዋ፣ ሰይጣንንም ሆነ የእሱን ክፉ ዓለም በማጥፋት ለዚህ ልመና ምላሽ ሲሰጠን እንዴት ያለ እፎይታ እናገኛለን! ይሁንና ሰይጣን ከሰማይ ሲወረወር፣ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ እንደነበር ማስታወስ አለብን። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን እንድናጎድፍ ለማድረግ የተቻለውን ያህል ይፍጨረጨራል። እንግዲያው ይሖዋ ከእሱ እንዲያድነን ሁልጊዜ መጸለይ ይኖርብናል።—ራእይ 12:12, 17

18. የሰይጣን ዓለም ሲጠፋ ለመትረፍ ምን ማድረጋችንን መቀጠል አለብን?

18 እንዲህ ባለው አስደሳች ጊዜ መኖር ትፈልጋለህ? እንግዲያው የአምላክ መንግሥት፣ የእሱን ስም እንዲያስቀድስና ፈቃዱን በምድር ላይ እንዲፈጽም መጸለይህን ቀጥል። መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎትህን እንዲያሟላልህ ይሖዋን ጠይቀው። አዎን፣ ከጸሎት ናሙናው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።