በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 1

ከጸሎት ናሙናው ጋር ተስማምቶ መኖር—ክፍል 1

“ስምህ ይቀደስ።”—ማቴ. 6:9

1. በማቴዎስ 6:9-13 ላይ የሚገኘውን ጸሎት በአገልግሎታችን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?

ብዙ ሰዎች የጌታን ጸሎት በቃላቸው መድገም ይችላሉ። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር እንደሆነና በምድር ላይ አስደናቂ የሆኑ ለውጦችን እንደሚያመጣ ለሰዎች ለማስረዳት ብዙውን ጊዜ ይህን ጸሎት እንጠቅሳለን። አሊያም ደግሞ አምላክ የግል ስም እንዳለውና ይህ ስም መቀደስ ወይም ‘ብሩክ መሆን’ እንዳለበት ለማጉላት በጸሎቱ ላይ ያለውን የመጀመሪያ ልመና አውጥተን እናሳያቸው ይሆናል።—ማቴ. 6:9 የግርጌ ማስታወሻ

2. ኢየሱስ የጸሎት ናሙናውን ያስተማረን በጸለይን ቁጥር ቃል በቃል እንድንደግመው አስቦ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

2 ኢየሱስ ይህን ጸሎት ያስተማረን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በርካታ ሰዎች እንደሚያደርጉት በጸለይን ቁጥር ቃል በቃል እንድንደግመው አስቦ ነው? በፍጹም። ኢየሱስ ይህን ናሙና ከማስተማሩ በፊት “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 6:7) ከጊዜ በኋላም ይህን ጸሎት በድጋሚ ሲያስተምር ለየት ያለ አገላለጽ ተጠቅሟል። (ሉቃስ 11:1-4) ኢየሱስ፣ ስለ የትኞቹ ነገሮች መለመን እንዳለብንና በጸሎታችን ላይ ቅድሚያ መስጠት የሚገባን ለምን ነገሮች እንደሆነ አስገንዝቦናል።  ይህ ጸሎት፣ የጸሎት ናሙና ተብሎ የሚጠራውም ለዚህ ነው።

3. የጸሎት ናሙናውን ስንመረምር በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል እንችላለን?

3 በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን የጸሎት ናሙና አንድ በአንድ እንመረምራለን። ይህን ስናደርግ ‘ይህ ናሙና፣ የጸሎቴን ይዘት ለማሻሻል የሚረዳኝ እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከዚህ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖርኩ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ”

4. “አባታችን ሆይ” የሚለው አገላለጽ ምን ያስታውሰናል? ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ይሖዋን “አባት” ብለው መጥራት የሚችሉት ከምን አንጻር ነው?

4 በጸሎት ናሙናው ላይ “አባቴ ሆይ” ሳይሆን “አባታችን ሆይ” መባሉ እርስ በርስ ከልብ በሚዋደድ “የወንድማማች ማኅበር” ውስጥ እንደታቀፍን ያስታውሰናል። (1 ጴጥ. 2:17) ይህ እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸውና ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋን “አባት” ብለው የመጥራት ልዩ የሆነ መብት አላቸው። (ሮም 8:15-17) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ይሖዋን “አባት” ብለው መጥራት ይችላሉ። ይሖዋ ሕይወት ሰጪያቸው ከመሆኑም ሌላ ለሁሉም እውነተኛ አምላኪዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በፍቅር ተነሳስቶ ያቀርብላቸዋል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ፍጽምና ደረጃ ላይ ከደረሱና በመጨረሻው ፈተና ታማኝ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ “የአምላክ ልጆች” ተብለው ይጠራሉ።—ሮም 8:21፤ ራእይ 20:7, 8

5, 6. ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጡ የሚችሉት ግሩም ስጦታ ምንድን ነው? እያንዳንዱ ልጅ ይህን ስጦታ እንዴት ሊይዘው ይገባል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

5 ወላጆች ልጆቻቸውን መጸለይ ሲያስተምሯቸውና ይሖዋን እንደ አፍቃሪ ሰማያዊ አባታቸው አድርገው እንዲመለከቱት ሲረዷቸው ትልቅ ስጦታ እየሰጧቸው ነው። በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሴቶች ልጆቻችን ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ፣ ቤት እስካለሁ ድረስ ሁልጊዜ ማታ ማታ አብሬያቸው እጸልይ ነበር። ልጆቻችን፣ ምሽት ላይ በምናደርገው ጸሎት ላይ ምን እጠቅስ እንደነበር በትክክል እንደማያስታውሱ ብዙ ጊዜ ይነግሩኛል። ይሁንና በጸሎቱ ወቅት የነበረውን መንፈስ፣ ከአባታችን ከይሖዋ ጋር በጸሎት መነጋገር ቅዱስ ነገር መሆኑን ይገነዘቡ እንደነበር እንዲሁም የሚያድርባቸውን የመረጋጋትና የደኅንነት ስሜት ያስታውሳሉ። ልጆቻችን መጸለይ የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ፣ ለይሖዋ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ሲገልጹ ለመስማት ስል ጮክ ብለው እንዲጸልዩ አበረታታቸው ነበር። ይህም በልባቸው ውስጥ ያለው ነገር በተወሰነ መጠን ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶልኛል። ከዚያም ጸሎታቸው ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያስችሉ ከጸሎት ናሙናው ላይ የተወሰዱ አስፈላጊ ነጥቦችን እንዲያካትቱ በደግነት እረዳቸዋለሁ።”

6 የዚህ ወንድም ሴቶች ልጆች ግሩም መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸው የሚያስገርም አይደለም። በአሁኑ ወቅት አስደሳች ትዳር ያላቸው ሲሆን ከባሎቻቸው ጋር ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመሳተፍ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ነው። ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሊሰጧቸው ከሚችሉት ስጦታ ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር የቀረበና የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት ነው። እርግጥ ነው፣ ይህን ውድ ዝምድና ጠብቆ ማቆየት የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ነው። ይህ ደግሞ የአምላክን ስም መውደድን ማለትም ለስሙ ጥልቅ አክብሮት ማዳበርን ይጨምራል።—መዝ. 5:11, 12፤ 91:14

“ስምህ ይቀደስ”

7. የአምላክ ሕዝቦች ምን መብት አለን? ይህስ ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል?

7 የአምላክን የግል ስም ከማወቅም አልፈን “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” በመሆን በስሙ መጠራታችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው። (ሥራ 15:14፤ ኢሳ. 43:10) በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን “ስምህ ይቀደስ” ብለን እንለምነዋለን። እንዲህ ያለ ልመና ማቅረብህ፣ ቅዱስ የሆነውን የይሖዋን ስም  የሚያስነቅፍ ነገር ላለመናገር ወይም ላለማድረግ እንዲረዳህ እሱን ለመጠየቅ ሊያነሳሳህ ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ ያላደረጉ ክርስቲያኖች መሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእናንተ ምክንያት የአምላክ ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” በማለት ጽፎላቸዋል።—ሮም 2:21-24

8, 9. የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ማድረጋቸው የሚያሳስባቸውን ክርስቲያኖች ይሖዋ እንዴት እንደሚባርክ የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

8 የአምላክ ስም እንዲቀደስ ማድረግ እንፈልጋለን። በኖርዌይ የምትኖር አንዲት እህት ባሏ ሲሞት ከሁለት ዓመት ልጇ ጋር ብቻዋን ቀረች። “በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከባድ ወቅት ነበር” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ስሜታዊ ሆኜ ሚዛኔን እንዳልስት ይሖዋ ጥንካሬ እንዲሰጠኝ በየዕለቱ እንዲያውም በየሰዓቱ እጸልይ ነበር፤ ይህንንም የማደርገው ጥበብ የጎደለው ውሳኔ በመወሰኔ ወይም ታማኝነቴን በማጉደሌ ሰይጣን ይሖዋን የሚነቅፍበት ነገር እንዳያገኝ ስል ነው። የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ልጄም አባቱን በገነት እንዲያገኝ እመኛለሁ።”—ምሳሌ 27:11

9 ይሖዋ እንዲህ ላሉ ከራስ ወዳድነት ነፃ ለሆኑ ጸሎቶች ምላሽ ይሰጣል? በሚገባ። ይህች እህት አሳቢ ከሆኑ የእምነት ባልንጀሮቿ ጋር አዘውትራ ጊዜ በማሳለፏ ድጋፍ ማግኘት ችላለች። ከአምስት ዓመት በኋላ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አገባች። አሁን ልጇ 20 ዓመቱ ሲሆን የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ነው። “ባለቤቴ ልጄን ሳሳድግ ስላገዘኝ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች።

10. የአምላክ ስም ሙሉ በሙሉ እንዲቀደስ ምን ያስፈልጋል?

10 የአምላክ ስም ሙሉ በሙሉ እንዲቀደስና ከደረሰበት ነቀፋ ሁሉ ነፃ እንዲሆን ምን ያስፈልጋል? ይሖዋ የእሱን ሉዓላዊነት ሆን ብለው የሚቃወሙትን ሁሉ ማጥፋት ያስፈልገዋል። (ሕዝቅኤል 38:22, 23ን አንብብ።) ከዚያም የሰው ዘር ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ይደርሳል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ የይሖዋን ስም የሚያስቀድሱበትን ጊዜ ለማየት ምንኛ እንጓጓለን! በመጨረሻም አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል።—1 ቆሮ. 15:28

“መንግሥትህ ይምጣ”

11, 12. በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ማስተዋል አገኙ?

11 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ሐዋርያቱ “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ፣ የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀመርበትን ወቅት የሚያውቁበት ጊዜ እንዳልደረሰ የሚያሳይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ሊያከናውኑት በሚገባው አስፈላጊ ሥራ ይኸውም በስብከቱ ተልእኮ ላይ እንዲያተኩሩ ነገራቸው። (የሐዋርያት ሥራ 1:6-8ን አንብብ።) ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንዲጠባበቁ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። በመሆኑም ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች ይህ መንግሥት እንዲመጣ ሲጸልዩ ኖረዋል።

12 ኢየሱስ የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት ከሰማይ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ሲደርስ፣ ይሖዋ ነገሮች የሚከናወኑበትን ጊዜ እንዲያውቁ ሕዝቡን ረድቷቸዋል። በ1876 ቻርልስ ቴዝ ራስል የጻፈው አንድ ርዕስ ባይብል ኤግዛሚነር በተባለ መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር። “የአሕዛብ ዘመናት የሚያበቁት መቼ ነው?” የሚል ጭብጥ ያለው ይህ ርዕስ 1914 ልዩ ዓመት መሆኑን ጠቁሞ ነበር። በዳንኤል ትንቢት ላይ የተገለጹት “ሰባት ዘመናት” ኢየሱስ ከጠቀሳቸው “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በዚህ ርዕስ ላይ ተብራርቷል። *ዳን. 4:16፤ ሉቃስ 21:24

13. በ1914 ምን ተከናወነ? ከዚያ ወዲህ በዓለም ላይ የተፈጸሙ ሁኔታዎችስ ምን ያረጋግጣሉ?

13 በ1914 በአውሮፓ በሚገኙ አገራት መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ ጦርነቱም በመስፋፋቱ በመላው  ዓለም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በ1918 ጦርነቱ ሲያበቃ ከባድ የምግብ እጥረት ተከሰተ፤ ቀጥሎም በጦርነቱ ከሞቱት የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች የጨረሰ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ተነሳ። በመሆኑም ኢየሱስ የምድር አዲሱ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን እንደሚጠቁም የሚያሳየው “ምልክት” መፈጸም ጀመረ። (ማቴ. 24:3-8፤ ሉቃስ 21:10, 11) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አክሊል የተሰጠው’ በ1914 መሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አለ። “እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።” (ራእይ 6:2) ኢየሱስ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ጦርነት በማወጅ ሰማይን ያጸዳ ሲሆን እነሱንም ወደ ምድር አካባቢ ወረወራቸው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጆች፣ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ እውነተኝነት እየተመለከቱ ነው።—ራእይ 12:7-12

14. (ሀ) አሁንም ቢሆን የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ምን የማድረግ መብት ተሰጥቶናል?

14 በራእይ 12:7-12 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ የአምላክ መንግሥት የተወለደበትና በሰው ልጆች ላይ አሁንም ድረስ ሥቃይ እያስከተሉ ያሉት ክንውኖች የጀመሩበት ወቅት ተመሳሳይ ጊዜ ላይ የዋለው ለምን እንደሆነ ያብራራል። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ፣ መግዛት የጀመረው በጠላቶቹ መካከል ነው። ኢየሱስ ድሉን እስኪያጠናቅቅና በምድር ላይ ያለውን ክፋት ጨርሶ እስኪያስወግድ ድረስ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያችንን እንቀጥላለን። እስከዚያው ግን አስገራሚ የሆነው ‘የምልክቱ’ ገጽታ ፍጻሜውን  እንዲያገኝ የበኩላችንን በማድረግ ከጸሎታችን ጋር በሚስማማ መንገድ ልንኖር ይገባል። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴ. 24:14

“ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም”

15, 16. የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከምናቀርበው ልመና ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

15 ከዛሬ 6,000 ዓመታት ገደማ በፊት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተፈጽሞ ነበር። ይሖዋ፣ ለሰዎች ሁሉን ነገር ካመቻቸላቸው በኋላ ሁኔታውን ተመልክቶ “እጅግ መልካም ነበር” ያለው ለዚህ ነው። (ዘፍ. 1:31) ይሁንና ሰይጣን ዓመፀ፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአምላክን ፈቃድ በምድር ላይ ያደረጉት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ነው። በዛሬው ጊዜ ግን ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከመጸለይ አልፈው ከዚህ ጸሎት ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት እያደረጉ ነው፤ በእርግጥም በዚህ ዘመን በመኖራችን ታድለናል። እነዚህ ሰዎች በአኗኗራቸው እንዲሁም ደቀ መዛሙርት በማፍራቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ከጸሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚኖሩ ያሳያሉ።

ወላጆች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከሚቀርበው ልመና ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ልጆቻችሁን እየረዳችኋቸው ነው? (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

16 ለምሳሌ ያህል፣ በ1948 የተጠመቁና በአፍሪካ ያገለግሉ የነበሩ አንዲት ሚስዮናዊት እንዲህ ብለዋል፦ “የጸሎት ናሙናው ክፍል ከሆነው ከዚህ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ፣ በግ መሰል ሰዎች ሁሉ ጊዜው ከማለቁ በፊት እንዲገኙና ይሖዋን ለማወቅ የሚያስችላቸው እርዳታ እንዲደረግላቸው ብዙ ጊዜ እጸልያለሁ። በተጨማሪም ለአንድ ሰው ከመመሥከሬ በፊት የግለሰቡን ልብ መንካት እንድችል ጥበብ እንዲሰጠኝ ይሖዋን እጠይቀዋለሁ። የተገኙትን በግ መሰል ሰዎች በተመለከተ ደግሞ ይሖዋ እነሱን ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት እንዲባርከው እጸልያለሁ።” እኚህ የ80 ዓመት አረጋዊት በአገልግሎት ስኬታማ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም፤ ከሌሎች ጋር አብረው በመሥራት ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር እንዲሆኑ ረድተዋል። አንተም የዕድሜ መግፋት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ተቋቁመው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን መሥዋዕት ያደረጉ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ክርስቲያኖችን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም።ፊልጵስዩስ 2:17ን አንብብ።

17. ይሖዋ፣ ፈቃዱ በምድር እንዲፈጸም ለምናቀርበው ጸሎት ምላሽ ለመስጠት ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር ምን ይሰማሃል?

17 የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ከምድር እስኪወገዱ ድረስ፣ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም መጸለያችንን እንቀጥላለን። ከዚያም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ይበልጥ በተሟላ መንገድ ሲፈጸም እንመለከታለን። ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ [ድምፄን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” ብሏል፤ እነዚህ ሰዎች ከመቃብር “ይወጣሉ።” (ዮሐ. 5:28, 29) በሕይወት ኖረን፣ በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎች መቀበል መቻል እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! አምላክ “እንባን ሁሉ [ከዓይናችን] ያብሳል።” (ራእይ 21:4) ከሞት የሚነሱት አብዛኞቹ ሰዎች “ዓመፀኞች” ይኸውም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ እውነቱን የማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ግለሰቦች ናቸው። ከሞት ለተነሱ ሰዎች ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ በማስተማር “የዘላለም ሕይወት” ለማግኘት እንዲበቁ መርዳት ትልቅ መብት ነው።—ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 17:3

18. የሰው ልጅ ከምንም በላይ የሚያስፈልጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

18 በአጽናፈ ዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ስም በመቀደሱ ላይ የተመካ ነው። በመሆኑም በጸሎት ናሙናው ላይ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ልመናዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ሲያገኙ የሰው ልጆች ከምንም በላይ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይሟላሉ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ለማግኘት የምንፈልጋቸው ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች አሉ፤ እነዚህም ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ በጠቀሳቸው አራት ልመናዎች ላይ ተገልጸዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ እነዚህ ልመናዎች እንመረምራለን።

^ አን.12 ይህ ትንቢት በ1914 የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ሲወለድ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 215-218 ተመልከት።