በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በተራሮች ጥላ ከልሏቸዋል

ይሖዋ በተራሮች ጥላ ከልሏቸዋል

አንዲት ሴት ጠዋት በማለዳ ወደ ደጅ ስትወጣ በደጃፏ ላይ አንድ የታሸገ ነገር ተመለከተች። ዕቃውን አነሳችውና ዙሪያዋን ቃኘች፤ መንገዱ ላይ ግን የሚታይ ሰው የለም። አንድ ሰው በሌሊት መጥቶ ትቶት ሄዶ መሆን አለበት። ሴትየዋ እሽጉን በከፊል ከፈት አድርጋ ካየችው በኋላ በፍጥነት ወደ ቤቷ ገብታ በሩን ዘጋች። ይህን ማድረጓ ምንም አያስገርምም! ምክንያቱም ያገኘችው እሽግ እገዳ የተጣለበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ነው! እሽጉን እንደያዘች ድምፅዋን ሳታሰማ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ላገኘችው ውድ መንፈሳዊ ምግብ ምስጋና አቀረበች።

በ1930ዎቹ ዓመታት በጀርመን የነበረው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር። ናዚዎች በ1933 ሥልጣን ሲይዙ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ታገደ። አሁን ዕድሜው ከ100 ዓመት በላይ የሆነው ሪቻርድ ሩዶልፍ * “ስለ ይሖዋና ስለ ስሙ የማወጁ ሥራ፣ ሰዎች በሚጥሉት በዚህ ዓይነቱ ማዕቀብ ሊቆም እንደማይችል እርግጠኞች ነበርን” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጥናት የምናደርግባቸው እንዲሁም በአገልግሎት ላይ የምንጠቀምባቸው አስፈላጊ መሣሪያዎቻችን ነበሩ። ይሁን እንጂ በእገዳው ምክንያት እነዚህን ጽሑፎች በቀላሉ ማግኘት አልተቻለም። ሥራው እንዴት እንደሚቀጥል ግራ ገብቶን ነበር።” ሪቻርድ፣ ጽሑፎች ወንድሞች እጅ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ወዲያውኑ ተገነዘበ፤ እርግጥ ጽሑፎቹ የሚገኙበት መንገድ ያልተለመደ ነበር። ይህን ማድረግ የሚቻለው የተራሮቹን ጥላ ተገን በማድረግ ነበር።—መሳ. 9:36

የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች መንገድ

የኤልባን (ወይም የላቤ) ወንዝ ተከትለህ ወደ መነሻው እየተጓዝክ ነው እንበል። የተወሰነ መንገድ እንደተጓዝክ በአሁኑ የቼክ ሪፑብሊክና የፖላንድ ድንበር ላይ ወደሚገኙት ጃይንት ማውንቴንስ (ክርከኖሼ) ወደሚባሉት ተራሮች ትደርሳለህ። የተራሮቹ ከፍታ ከባሕር ጠለል በላይ 1,600 ሜትር ብቻ ቢሆንም በአውሮፓ መካከል ያለው የአርክቲክ ደሴት ተብለው ይጠራሉ። የተራራ ሰንሰለቶቹ ለስድስት ወር ያህል እስከ 3 ሜትር ከፍታ ባለው በረዶ ይሸፈናሉ። የአየሩ ጠባይ ተለዋዋጭ ስለሆነ ጥሩ የሚባለው የአየር ጠባይ እንኳ በድንገት ተቀይሮ የተራሮቹ አናት ጥቅጥቅ ባለ ጉም ሊሸፈን ይችላል።

ባለፉት መቶ ዘመናት፣ ይህ የተራሮች ሰንሰለት በክፍላተ አገሮችና በአገሮች መካከል ተፈጥሯዊ ድንበር ሆኖ አገልግሏል። መልክአ ምድሩ አካባቢውን ለቁጥጥር አስቸጋሪ ያደርገዋል፤ በመሆኑም በቀድሞ ጊዜ ብዙ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በእነዚህ  ተራሮች ላይ ሸቀጦቻቸውን ያሳልፉ ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት ጃይንት ማውንቴንስ፣ የቼኮስሎቫኪያና የጀርመን ድንበር ሆኑ፤ በዚህ ጊዜ ደፋር የይሖዋ ምሥክሮች፣ የቀድሞ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች መመላለሻ የነበሩ መንገዶችን መጠቀም ጀመሩ። ምን ለማድረግ? ውድ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንደ ልብ ከሚገኙበት ቦታ ተቀብለው ለማጓጓዝ ነበር። ወጣቱ ሪቻርድ እንዲህ ያደርጉ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ነበር።

ወንድሞችና እህቶች ልክ እንደ ተራራ ወጪዎች በመልበስ ጃይንት ማውንቴንስ የተባሉትን ተራሮች አቋርጠው ጽሑፎችን ወደ ጀርመን ያስገቡ ነበር

አደገኛ “የተራራ ጉዞዎች”

“በሳምንቱ የመጨረሻ ቀኖች ላይ ሰባት ወይም ከዚያ በላይ ወጣት ወንድሞች በቡድን እንሆንና ተራራ እንደሚወጡ ሰዎች ለብሰን ወደ ተራሮቹ እንሄድ ነበር” በማለት ሪቻርድ ያስታውሳል። “ከጀርመን ተነስተን፣ ተራሮቹን አቋርጠን በቼክ ግዛት ውስጥ ወደሚገኘው ሽፒንደልሩቭ ሚሊን የተባለ የመዝናኛ ቦታ ለመድረስ 16.5 ኪሎ ሜትር ያህል እንጓዝ ነበር፤ ጉዞው ሦስት ሰዓት ገደማ ይፈጅብናል። በወቅቱ ብዙ ጀርመናውያን በዚያ አካባቢ ይኖሩ ነበር። ከእነዚህ ጀርመናውያን መካከል አንድ ገበሬ ከወንድሞች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ሆነ። ይህ ገበሬ፣ ቱሪስቶችን ለማጓጓዝ በሚያገለግል በፈረስ የሚጎተት ጋሪ በመጠቀም በጽሑፎች የተሞሉ ሣጥኖችን ጭኖ ይመጣ ነበር፤ ገበሬው ከፕራግ በባቡር የሚመጡ ጽሑፎችን የሚያገኘው በአቅራቢያው ካለ አንድ መንደር ነው። ከዚያም ሣጥኖቹን ወደ እርሻው ይዞ ይመጣና ጽሑፎቹን ወደ ጀርመን የሚወስዷቸው ሰዎች እስኪመጡ ድረስ በሣር ክምር ውስጥ ይደብቃቸዋል።

ሪቻርድ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “ወደዚያ እርሻ ስንደርስ፣ ብዙ ነገር መያዝ እንዲችሉ ተብለው በተዘጋጁ በጀርባ የሚታዘሉ ቦርሳዎቻችን ውስጥ ጽሑፎቹን እንሞላለን። እያንዳንዳችን 50 ኪሎ ግራም ያህል እንሸከም ነበር።” ወንድሞች፣ መንገድ ላይ እንዳይያዙ በመፍራት የሚጓዙት በጨለማ ነው፤ ጉዟቸውን ጀምበር ስትጠልቅ ይጀምሩና ፀሐይ ሳትወጣ በፊት ቤታቸው ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ በጀርመን የወረዳ የበላይ ተመልካች የነበረው ኧርነስት ቪስነር ወንድሞች ሌሎችን ለማስጠንቀቅ የሚጠቀሙበትን ዘዴ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “ሁለት ወንድሞች ቀድመው ይሄዱና መንገድ ላይ ሰው ሲያገኙ ወዲያውኑ በእጅ ባትሪያቸው ምልክት ይሰጣሉ። ከእነዚህ ወንድሞች ኋላ 100 ሜትር በሚያህል ርቀት ላይ ሆነው ከባድ ቦርሳ አዝለው የሚከተሉ ሌሎች ወንድሞች ይህን ምልክት ሲያዩ በጫካው ውስጥ ይደበቃሉ፤ እነዚህ ወንድሞች፣ ከፊት ያሉት ወንድሞች መጥተው የሚስጥር ኮድ በመጠቀም እስከሚጠሯቸው ድረስ በተደበቁበት ይቆያሉ፤ ይህ የሚስጥር ኮድ በየሳምንቱ ይቀያየራል።” ይሁን እንጂ እነዚህ ወንድሞች የሚፈሩት ሰማያዊ የደንብ ልብስ የሚለብሱት የጀርመን ፖሊሶች እንዳያገኟቸው ብቻ አልነበረም።

ሪቻርድ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “አንድ ቀን አምሽቼ መሥራት ስለነበረብኝ ወደ ቼክ ለመሄድ መንገድ የጀመርኩት ከሌሎቹ  ወንድሞች ዘግይቼ ነው። አካባቢውን ጨለማና ጭጋግ የዋጠው ከመሆኑም ሌላ ዝናብ ይዘንብ ስለነበር ብርዱ ያንቀጠቅጣል። በአጫጭር የፓይን ዛፎች መካከል ስጓዝ መንገድ ስቼ ስለጠፋሁ ለብዙ ሰዓታት ብማስንም ትክክለኛውን መንገድ ማግኘት አልቻልኩም። ተራራ የሚወጡ ብዙ ሰዎች መንገድ በመሳታቸው ምክንያት ሞተዋል። ከወንድሞች ጋር መገናኘት የቻልኩት ጠዋት በማለዳ ከጉዟቸው ተመልሰው ሲመጡ ነበር።”

ደፋር የሆኑት እነዚያ ጥቂት ወንድሞች፣ ለሦስት ዓመት ያህል በየሳምንቱ ወደ ተራሮቹ ይሄዱ ነበር። በክረምት ወቅት ውድ የሆኑ ጽሑፎችን የሚያጓጉዙት በበረዶ መንሸራተቻ በመጠቀም ነበር። አልፎ አልፎ፣ እስከ 20 የሚሆኑ ወንድሞችን የያዙ የተለያዩ ቡድኖች ቀን ላይ ተራራ ወጪዎች በሚጠቀሙበት መንገድ ይጓዙ ነበር። ዓላማቸው ተራራ መውጣት ብቻ እንደሆነ ለማስመሰል አንዳንድ እህቶች አብረዋቸው ይሄዱ ነበር። አንዳንዶቹ ወደፊት ቀድመው የሚሄዱ ሲሆን የሚያሰጋ ነገር መኖሩን ከጠረጠሩ ባርኔጣዎቻቸውን ወደ ላይ በመወርወር ምልክት ይሰጣሉ።

ጃይንት ማውንቴንስ የተባሉት ተራሮች አናታቸው በበረዶ የተሸፈነ በመሆኑ በዚህ አካባቢ መጓዝ አደገኛ ነበር

ወንድሞች ሌሊቱን ተጉዘው ጽሑፉን ካመጡ በኋላስ ምን ይደረጋል? ጽሑፎቹን ወዲያውኑ ለማከፋፈል ዝግጅት ይደረጋል። እንዴት? ጽሑፎቹ እንደ ሣሙና ተጠቅልለው በሂርሽበርክ ወዳለው ባቡር ጣቢያ ይወሰዳሉ። ከዚያም የታሸጉት ጥቅልሎች ወደተለያዩ የጀርመን ግዛቶች ይላካሉ፤ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ወንድሞችና እህቶች ለእምነት አጋሮቻቸው ጽሑፎቹን በድብቅ ያደርሱላቸዋል። ወንድሞች ተቀናጅተው በድብቅ የሚያከናውኑትን ይህን ሥራ በጥንቃቄ መሥራታቸው አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው አንዱ ቢጋለጥ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። አንድ ቀን፣ ያልታሰበ ነገር አጋጠማቸው።

በ1936 በበርሊን አቅራቢያ የነበረ አንድ የጽሑፍ ማከማቻ ተደረሰበት። እዚያ ከተቀመጡት ነገሮች መካከል፣ በሂርሽበርክ ከሚገኝ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው የተላኩ ሦስት ጥቅልሎች ይገኙበታል። ፖሊሶች፣ የእጅ ጽሑፉን በመመርመር ጽሑፎችን በድብቅ ከሚያስገቡት መካከል ቁልፍ ቦታ የነበረውን ወንድም ማወቅ ቻሉ፤ ከዚያም አሰሩት። ብዙም ሳይቆይ ሪቻርድ ሩዶልፍን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ታሰሩ። ወንድሞች ለተከሰሱበት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን ስለወሰዱ እያደር አደገኛ እየሆነ የመጣውን ይህን ሥራ ሌሎች ለተወሰነ ጊዜ ያህል መቀጠል ችለዋል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

በጀርመን የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በዋነኝነት የሚያገኙት ጽሑፎችን በጀርባቸው አዝለው ጃይንት ማውንቴንስን በሚያቋርጡ ወንድሞች አማካኝነት ነበር። ይሁን እንጂ ጽሑፎች ወደ ጀርመን የሚገቡት በዚህ መንገድ ብቻ አልነበረም። የጀርመን ሠራዊት ቼኮስሎቫኪያን እስከያዘበት እስከ 1939 ድረስ ከቼኮስሎቫኪያ ወደ ጀርመን ጽሑፎች የሚገቡባቸው ሌሎች መንገዶችም ነበሩ። እንደ ስዊዘርላንድ፣ ኔዘርላንድስና ፈረንሳይ ባሉ ሌሎች የጀርመን አዋሳኝ አገሮች የሚኖሩም ሆኑ በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በስደት ላይ ለነበሩ የእምነት አጋሮቻቸው መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ሲሉ ከባድ ችግሮችን ለመጋፈጥ ቆርጠው ነበር።

በዛሬው ጊዜ፣ አብዛኞቻችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንደ ልብ ማግኘት እንችላለን፤ እነዚህን ጽሑፎች ታትመው ብቻ ሳይሆን በኤሌክትሮኒክ ፎርማት እንዲሁም በድምፅና በቪዲዮ ማግኘት ይቻላል። ታዲያ አንድን አዲስ ጽሑፍ ከመንግሥት አዳራሽ ስትወስድ ወይም jw.org ከተባለው ድረ ገጽ ላይ ስታወርድ፣ ይህን ጽሑፍ እንድታገኝ ምን ያህል ጥረት እንደተደረገ ቆም ብለህ ታስባለህ? በእርግጥ፣ ጽሑፎቹ እጅህ እንዲገቡ ማድረግ በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮችን በሌሊት ማቋረጥን አይጠይቅ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ተነሳስተው የሚያገለግሉን ብዙ የእምነት አጋሮቻችን ጽሑፍ ለእኛ እንዲደርስ ለማድረግ በጣም እንደደከሙ ምንም ጥርጥር የለውም።

^ አን.3 ሪቻርድ፣ በሳይሌዥያ ባለው በሂርሽበርክ ጉባኤ አገልግሏል። የሂርሽበርክ ከተማ አሁን የምትገኘው በደቡባዊ ምዕራብ ፖላንድ ሲሆን ዬሌንያ ጉራ ተብላለች።