በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ መንግሥት መሥዋዕትነት ትከፍላላችሁ?

ለአምላክ መንግሥት መሥዋዕትነት ትከፍላላችሁ?

“አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው [ይወዳል]።”—2 ቆሮ. 9:7

1. ብዙ ሰዎች ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ይከፍላሉ? ለምንስ?

ሰዎች፣ ትልቅ ቦታ ለሚሰጧቸው ነገሮች መሥዋዕትነት መክፈል ያስደስታቸዋል። ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሲሉ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እንዲሁም ጉልበታቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ። በኦሎምፒክ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ ወጣት አትሌቶች፣ እንደ እኩዮቻቸው ከመዝናናት ይልቅ በየቀኑ ለበርካታ ሰዓታት አድካሚ ሥልጠናና ልምምድ ያደርጋሉ። ኢየሱስም ትልቅ ቦታ ለሚሰጣቸው ነገሮች ሲል መሥዋዕትነት ከፍሏል። የተንደላቀቀ ሕይወት ለመምራት ወይም ልጅ ወልዶ ለመሳም አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ትኩረት ያደረገው የመንግሥቱን ፍላጎት በማራመድ ላይ ነው። (ማቴ. 4:17፤ ሉቃስ 9:58) ተከታዮቹም እንዲሁ የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ ሲሉ ብዙ ነገሮችን ትተዋል። በዋነኝነት ትኩረት ያደረጉት ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማከናወን ላይ ሲሆን መንግሥቱን ለመደገፍ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ሲሉ በርካታ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል። (ማቴ. 4:18-22፤ 19:27) እኛም ‘በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር ምንድን ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።

2. (ሀ) ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መሥዋዕት እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል? (ለ) አንዳንዶች ምን ተጨማሪ መሥዋዕቶችን መክፈል ችለዋል?

2 ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረትና ይህን ዝምድናቸውን ጠብቀው ለመኖር ከፈለጉ የግድ ሊከፍሏቸው የሚገቡ አንዳንድ መሥዋዕቶች አሉ። ለምሳሌ ለጸሎት፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ ለቤተሰብ አምልኮ፣ ለስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት ስንል ጊዜያችንንና ጉልበታችንን መሥዋዕት ማድረግ ይኖርብናል። * (ኢያሱ 1:8፤ ማቴ. 28:19, 20፤ ዕብ. 10:24, 25) በስብከቱ ሥራ የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ ስለባረከው ሥራው እየተፋጠነ ሲሆን ብዙዎች ‘ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ’ መጉረፋቸውን ቀጥለዋል። (ኢሳ. 2:2) በርካታ ሰዎች የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ሲሉ በሌሎች መንገዶችም መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። አንዳንዶች በቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ያገለግላሉ፤ ሌሎች ደግሞ  የመንግሥት አዳራሾችንና ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን በመገንባት፣ ትላልቅ ስብሰባዎችን በማደራጀት ወይም የተፈጥሮ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ በመስጠት ጠቃሚ ሥራዎችን ያከናውናሉ። እነዚህ ተጨማሪ ሥራዎች ሕይወት ለማግኘት የግድ አስፈላጊ ባይሆኑም የአምላክን መንግሥት በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

3. (ሀ) ለመንግሥቱ ብለን መሥዋዕት ስንከፍል ምን ጥቅም እናገኛለን? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል?

3 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ብዙዎች ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ በፈቃደኝነት መሥዋዕት ሲከፍሉ ማየት ምንኛ ያስደስታል! (መዝሙር 54:6ን አንብብ።) የአምላክን መንግሥት መምጣት እየተጠባበቅን ባለንበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ የልግስና መንፈስ ማሳየታችን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (ዘዳ. 16:15፤ ሥራ 20:35) ይሁንና እያንዳንዳችን ራሳችንን በሚገባ መመርመር አለብን። የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ ስንል ተጨማሪ መሥዋዕት መክፈል የምንችልባቸው መንገዶች አሉ? ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንን እንዲሁም ችሎታዎቻችንን እንዴት እየተጠቀምንባቸው ነው? መሥዋዕት ከመክፈል ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ልናደርግበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? በፈቃደኝነት መሥዋዕት ማቅረባችን ይበልጥ ደስተኛ እንድንሆን ይረዳናል፤ በዚህ ረገድ ልንኮርጃቸው የምንችል አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

በጥንቷ እስራኤል ይቀርቡ የነበሩ መሥዋዕቶች

4. እስራኤላውያን መሥዋዕት ማቅረባቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸው ነበር?

4 በጥንቷ እስራኤል፣ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት መሥዋዕት ማቅረብ የግድ አስፈላጊ ነበር። ሕዝቡ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። እስራኤላውያን አንዳንድ መሥዋዕቶችን እንዲያቀርቡ ሕጉ የሚያዝዝ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የፈቃደኝነት ስጦታ ይሰጡ ነበር። (ዘሌ. 23:37, 38) እስራኤላውያን ለይሖዋ በበጎ ፈቃድ ከሚያቀርቧቸው መሥዋዕቶች ወይም ስጦታዎች መካከል የሚቃጠል መሥዋዕት ይገኝበታል። በሰለሞን ዘመን ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምልኮ በተወሰነበት ወቅት የተከናወነው ነገር ለአምላክ መሥዋዕት በማቅረብ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።—2 ዜና 7:4-6

5. ይሖዋ ድሃ ለሆኑ እስራኤላውያን ምን ዝግጅት አድርጎ ነበር?

5 አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ መጠን ያለው መሥዋዕት ማቅረብ እንደማይችል ስለሚያውቅ እያንዳንዱ ሰው የአቅሙን ያህል እንዲሰጥ አዝዞ ነበር። የይሖዋ ሕግ፣ መሥዋዕት የሚሆነው እንስሳ ደሙ እንዲፈስ ያዝዛል፤ ይህም በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” ነበር። (ዕብ. 10:1-4) ይሁን እንጂ ይሖዋ ከዚህ ሕግ ጋር በተያያዘ ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ አንድ ሰው በሬ፣ ላም፣ በግ ወይም  ፍየል ማቅረብ ካልቻለ ዋኖሶችን እንዲያቀርብ ይሖዋ ፈቅዶ ነበር። በመሆኑም ድሃ የሆኑ ሰዎች እንኳ ለይሖዋ በደስታ መሥዋዕት ማቅረብ ይችሉ ነበር። (ዘሌ. 1:3, 10, 14፤ 5:7) ይሁንና በፈቃደኝነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው፣ የሚያቀርበው እንስሳ ምንም ይሁን ምን ሊያሟላቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች ነበሩ።

6. መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ምን ይጠበቅበታል? እነዚህ ብቃቶች መሟላታቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነበር?

6 በመጀመሪያ ደረጃ፣ እያንዳንዱ ሰው ምርጡን መስጠት ነበረበት። ይሖዋ፣ ሕዝቡ የሚያቀርቡት መሥዋዕት “ተቀባይነት” እንዲኖረው እንከን የሌለበት ሊሆን እንደሚገባ ነግሯቸው ነበር። (ዘሌ. 22:18-20) እንስሳው እንከን ያለበት ከሆነ ይሖዋ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጎ አይመለከተውም። ሁለተኛ፣ መሥዋዕቱን የሚያመጣው ሰው ንጹሕና ያልረከሰ መሆን ነበረበት። በሆነ ምክንያት የረከሰ ሰው የሚያቀርበው የበጎ ፈቃድ ስጦታ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ግለሰቡ አስቀድሞ የኃጢአት ወይም የበደል መሥዋዕት በማቅረብ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ማድረግ ነበረበት። (ዘሌ. 5:5, 6, 15) ይህ በቀላሉ የሚታይ ነገር አልነበረም። አንድ የረከሰ ሰው፣ በበጎ ፈቃድ ከሚቀርቡት መሥዋዕቶች መካከል አንዱ ከሆነው ከኅብረት መሥዋዕት ከበላ ከሕዝቡ ተለይቶ መጥፋት እንዳለበት ይሖዋ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘሌ. 7:20, 21) በሌላ በኩል ደግሞ መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም ያለው ከሆነ እንዲሁም እንከን የሌለበት መሥዋዕት ካቀረበ ግለሰቡ እንዲህ በማድረጉ ሊደሰት ይችላል።—1 ዜና መዋዕል 29:9ን አንብብ።

በዛሬው ጊዜ የሚቀርብ መሥዋዕት

7, 8. (ሀ) ብዙዎች ለመንግሥቱ ሲሉ መሥዋዕት መክፈላቸው ምን ዓይነት ደስታ አስገኝቶላቸዋል? (ለ) ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገን ልናቀርባቸው የምንችላቸው ምን ነገሮች አሉን?

7 በዛሬው ጊዜም ብዙዎች በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሲሆን ይሖዋም በዚህ ይደሰታል። ወንድሞቻችንን የሚጠቅም ነገር ማከናወን የሚክስ ነው። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን በመርዳቱ ሥራ የሚካፈል አንድ ወንድም በዚህ ዓይነት አገልግሎት በመካፈሉ ያገኘውን እርካታ በቃላት መግለጽ እንደሚያዳግተው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች፣ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሲያገኙ ወይም በተፈጥሮ አደጋ ወቅት እርዳታ ሲደረግላቸው በፊታቸው ላይ የሚነበበውን የደስታና የአድናቆት ስሜት ስንመለከት ያከናወንነው ከባድ ሥራና ጥረታችን ሁሉ የሚክስ እንደሆነ ይሰማናል።”

ብዙዎቹ መሥዋዕቶች በፈቃደኝነት የሚቀርቡ ነበሩ፤ ዛሬም በፈቃደኝነት የምናቀርበው መሥዋዕት አለ (አንቀጽ 7-13ን ተመልከት)

8 በዛሬው ጊዜ፣ የይሖዋ ድርጅት መንግሥቱን ለመደገፍ የሚቻልባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት ይከታተላል። ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1904 እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ ገንዘቡንና የመሳሰሉትን በሚገባ እንዲይዝ በጌታ እንደተሾመ አድርጎ ራሱን መቁጠር አለበት፤  እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው እነዚህን ተሰጥኦዎቹን አቅሙ በፈቀደለት መጠን ጌታን ለማክበር ሊጠቀምባቸው መጣር አለበት።” ለይሖዋ መሥዋዕት ስናቀርብ የምንከፍለው ነገር ቢኖርም ብዙ በረከቶችን እናጭዳለን። (2 ሳሙ. 24:21-24) ታዲያ ያሉንን ነገሮች ተጠቅመን አሁን ከምናቀርበው መሥዋዕት የበለጠ ማቅረብ እንችል ይሆን?

በአውስትራሊያ የሚገኙ ቤቴላውያን

9. ከጊዜ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ኢየሱስ በሉቃስ 10:2-4 ላይ የሰጠውን የትኛውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ አለብን?

9 ጊዜያችን። ጽሑፎቻችንን ለመተርጎምና ለማተም፣ የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት፣ ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማደራጀት፣ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ ለመስጠት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎችን ለማከናወን ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። በቀኑ ውስጥ ያለው ጊዜ ደግሞ ውስን ነው። ኢየሱስ በዚህ ረገድ ሊረዳን የሚችል መመሪያ ሰጥቷል። ደቀ መዛሙርቱን ወደ መስክ ሲልካቸው “በመንገድ ላይም ቆማችሁ ከማንም ጋር ሰላምታ አትለዋወጡ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 10:2-4) ኢየሱስ እንዲህ ያለ መመሪያ የሰጣቸው ለምንድን ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “በሩቅ ምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች ሰላምታ የሚለዋወጡት እኛ እንደምናደርገው በትንሹ አንገትን ሰበር በማድረግ ወይም በመጨባበጥ ሳይሆን ደጋግሞ በመተቃቀፍና ለጥ ብሎ እጅ በመንሳት አልፎ ተርፎም በመስገድ ጭምር ነበር። ይህ ሁሉ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ነበር።” ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ለሚያገኟቸው ሰዎች አክብሮት እንዳይኖራቸው እያበረታታ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ፣ ያላቸው ጊዜ ውስን ስለሆነ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ማከናወን እንዲችሉ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው እያስገነዘባቸው ነበር። (ኤፌ. 5:16) እኛስ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን የሚያስችለን ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት እንድንችል ይህን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?

አስፋፊዎች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ኬንያ፣ አፍሪካ

10, 11. (ሀ) ዓለም አቀፉን ሥራ በገንዘብ ለመደገፍ የምናደርገው መዋጮ ጥቅም ላይ የሚውልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በ1 ቆሮንቶስ 16:1, 2 ላይ የሚገኘውን የትኛውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው?

10 ገንዘባችን። የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያስፈልጋል። በየዓመቱ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ የልዩ አቅኚዎችንና የሚስዮናውያንን ወጪ ለመሸፈን በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ይወጣል። የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ ከ1999 ወዲህ ከ24,500 በላይ የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ወደ 6,400 የሚጠጉ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። በየወሩ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ይታተማሉ። ይህ ሁሉ ሥራ የሚከናወነው እናንተ በምታደርጉት የፈቃደኝነት መዋጮ ነው።

11 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ መዋጮ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ልንከተለው የሚገባ መመሪያ አስፍሮልናል። (1 ቆሮንቶስ 16:1, 2ን አንብብ።) በቆሮንቶስ የሚገኙ ወንድሞቹ፣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተረፋቸውን ነገር ከመስጠት ይልቅ ገና በሳምንቱ መጀመሪያ እንደ አቅማቸው መስጠት የሚችሉትን ያህል እንዲያስቀምጡ በመንፈስ መሪነት ጽፎላቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም እንደ አቅማቸው በልግስና ለመስጠት አስቀድመው እቅድ ያወጣሉ። (ሉቃስ 21:1-4፤ ሥራ 4:32-35) ይሖዋ እንዲህ ያለውን የልግስና መንፈስ ያደንቃል።

የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግል ወንድም፣ ተክሲዶ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

12, 13. አንዳንዶች ጉልበታቸውንና ችሎታቸውን ለይሖዋ ከመስጠት ወደኋላ እንዲሉ የሚያደርጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ይሖዋ የሚያግዛቸውስ እንዴት ነው?

12 ጉልበታችንና ችሎታችን። ጉልበታችንንና ችሎታችንን ለመንግሥቱ ሥራ ለመጠቀም ጥረት ስናደርግ ይሖዋ ይደግፈናል። ስንዝል እንደሚያበረታን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 40:29-31) ሥራውን ለመደገፍ ብቁ እንዳልሆንን ይሰማን ይሆን? ሌሎች ከእኛ የተሻለ ሥራውን እንደሚያከናውኑት እናስባለን? ይሖዋ ለባስልኤልና ለኤልያብ እንዳደረገው፣ ሁላችንም ችሎታችንን በተሻለ ሁኔታ እንድንጠቀምበት ሊረዳን ይችላል።—ዘፀ. 31:1-6፤ በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።

13 ይሖዋ፣ ያለንን ምንም ሳንቆጥብ ምርጣችንን እንድንሰጥ ይጠብቅብናል። (ምሳሌ 3:27) ቤተ መቅደሱ እንደገና በተገነባበት ወቅት ይሖዋ፣ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አይሁዳውያን የግንባታውን ሥራ ለመደገፍ ምን እያደረጉ እንዳሉ ቆም ብለው እንዲያስቡ ነግሯቸዋል። (ሐጌ 1:2-5) ሕዝቡ፣ ትኩረታቸው  ከመከፋፈሉም ሌላ ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቅድሚያ አልሰጡም ነበር። እኛም፣ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮች ይሖዋ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ቆም ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በመንግሥቱ ሥራ የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ ‘መንገዳችንን ልብ ማለት’ እንችል ይሆን?

እንደ አቅማችን መሥዋዕት ማቅረብ

14, 15. (ሀ) የገንዘብ አቅማቸው ውስን የሆነ ወንድሞቻችን ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል? (ለ) ሁላችንም ምን ማድረግ እንፈልጋለን?

14 ብዙዎች በየቀኑ ከድህነትና ከሌሎች ችግሮች ጋር ይታገላሉ። የይሖዋ ድርጅት፣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ባሉባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞችን ጉድለት ‘ለመሸፈን’ ሌሎች ወንድሞች በሚያዋጡት ገንዘብ ይጠቀማል። (2 ቆሮ. 8:14) ይሁንና የገንዘብ አቅማቸው ውስን የሆነ ወንድሞችም ልግስና የማሳየት መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ድሃ የሆኑ ወንድሞች በደስታ መስጠታቸው ይሖዋን ያስደስተዋል።—2 ቆሮ. 9:7

15 በጣም ድሃ በሆነ አንድ የአፍሪካ አገር የሚኖሩ አንዳንድ ወንድሞች ከማሳቸው የተወሰነውን ክፍል ከለዩ በኋላ ከዚያ የሚያገኙትን ምርት በመሸጥ ገቢውን የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ያውሉታል። በዚሁ አገር የመንግሥት አዳራሽ በጣም ያስፈልግ ስለነበር ግንባታውን ለማከናወን እቅድ ወጣ። በአካባቢው ያሉ ወንድሞችና እህቶች በግንባታው ሥራ እገዛ ለማድረግ ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ ግንባታው የሚከናወነው ዘር በሚዘሩበት ወቅት ላይ ሆነ። እነዚህ ወንድሞች በግንባታው ሥራ ለመካፈል በጣም ስለፈለጉ ቀን ቀን የመንግሥት አዳራሽ ግንባታውን ሲያግዙ ይውሉና ምሽት ላይ ወደ ማሳቸው ሄደው ይሠራሉ። ይህ እንዴት ያለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ነው! እነዚህ ወንድሞች፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በመቄዶንያ የነበሩ ወንድሞችን ያስታውሱናል። የመቄዶንያ ወንድሞች “ከባድ ድህነት” ውስጥ የነበሩ ቢሆንም ወንድሞቻቸውን የመርዳት መብት ለማግኘት ይለምኑ ነበር። (2 ቆሮ. 8:1-4) እኛም በተመሳሳይ ‘እግዚአብሔር በባረከን መጠን እንደ ችሎታችን እንስጥ።’ዘዳግም 16:17ን አንብብ።

16. የምናቀርበው መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ልናደርግበት የሚገባ ጉዳይ አለ። እንደ ጥንቶቹ እስራኤላውያን ሁሉ እኛም በፈቃደኝነት የምናቀርበው መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሊሆን ይገባል። ሚዛናዊ በመሆን ከምንም ነገር በላይ ለቤተሰብ ኃላፊነታችንና ለይሖዋ ለምናቀርበው አምልኮ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። ጊዜያችንን እና ንብረታችንን መሥዋዕት በማድረግ ሌሎችን ስንረዳ የቤተሰባችንን መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎት ችላ እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል። አለዚያ በሌለን መጠን እንደ መስጠት ይሆንብናል። (2 ቆሮንቶስ 8:12ን አንብብ።) በተጨማሪም መንፈሳዊነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 9:26, 27) ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ ለይሖዋ የምናቀርበው መሥዋዕት ከፍተኛ ደስታና እርካታ እንደሚያስገኝልን እንዲሁም በይሖዋ ዘንድ “ይበልጥ ተቀባይነት” እንደሚኖረው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

የምናቀርበው መሥዋዕት ትልቅ ዋጋ አለው

17, 18. ለመንግሥቱ ሲሉ መሥዋዕት ለሚከፍሉ ሁሉ ምን ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል? ሁላችንም ልናስብበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?

17 ብዙ ወንድሞችና እህቶች መንግሥቱን ለመደገፍ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን በማከናወን ራሳቸውን “እንደ መጠጥ መሥዋዕት [እያፈሰሱ]” ነው። (ፊልጵ. 2:17) እንዲህ ያለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የሚያሳዩ ክርስቲያኖችን ከልብ እናደንቃቸዋለን። አንዳንድ ወንድሞች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነው ያከናውናሉ፤ የእነዚህ ወንድሞች ሚስቶችና ልጆችም ለሚያሳዩት የልግስናና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ሊመሰገኑ ይገባል።

18 ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመደገፍ ብዙ የሚከናወን ነገር አለ። ሁላችንም በዚህ ረገድ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት ስለምንችልበት መንገድ በቁም ነገር እንዲሁም በጸሎት ልናስብበት ይገባል። እንዲህ ማድረጋችን ዛሬ ታላቅ ሽልማት፣ “በሚመጣው ሥርዓት” ደግሞ ከዚያ የላቀ በረከት እንደሚያስገኝልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማር. 10:28-30

^ አን.2 በጥር 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21-25 ላይ የሚገኘውን “ለይሖዋ የሙሉ ነፍስ መሥዋዕት ማቅረብ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።