በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሕይወት ታሪክ

የትም ብንመደብ ጉጉታችን ይሖዋን ማገልገል ነው

የትም ብንመደብ ጉጉታችን ይሖዋን ማገልገል ነው

ብቻዬን ሰብኬ አላውቅም ነበር። አገልግሎት በወጣሁ ቁጥር በጣም ከመፍራቴ የተነሳ እግሮቼ ይብረከረኩ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ በማገለግልበት ክልል ውስጥ ያሉት ሰዎች መልእክቱን ለመስማት ፈጽሞ ፈቃደኞች አልነበሩም። እንዲያውም አንዳንዶቹ በጣም ቁጡ ከመሆናቸውም ሌላ እንደሚደበድቡኝ ይዝቱብኝ ነበር። በአቅኚነት ባሳለፍኩት የመጀመሪያው ወር ላይ ያበረከትኩት አንድ ቡክሌት ብቻ ነበር!—ማርከስ

ይህ የሆነው ከ60 ዓመታት በፊት በ1949 ነው፤ ታሪኬ የሚጀምረው ግን ከዚያ ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ ነው። አባቴ ሄንድሪክ፣ በኔዘርላንድ ውስጥ በሰሜናዊ ድሬንት በምትገኝ ዶንደረን በተባለች ትንሽ መንደር ውስጥ ጫማ በመሥራትና በአትክልተኝነት ይተዳደር ነበር። እኔም የተወለድኩት በ1927 በዚህ ቦታ ሲሆን ከሰባት ልጆች አራተኛ ነኝ። የምንኖርበት አካባቢ የገጠር ወረዳ ነው፤ ቤታችን የሚገኘው መንገድ ዳር ሲሆን መንገዱ አቧራማ ነበር። አብዛኞቹ የአካባቢው ሰዎች ገበሬዎች ነበሩ፤ እኔም የግብርና ሕይወት በጣም ያስደስተኛል። በ1947 የ19 ዓመት ልጅ ሳለሁ ቴሁኒስ ባን ከተባለ ጎረቤታችን እውነትን ሰማሁ። መጀመሪያ ላይ ቴሁኒስን አልወደውም ነበር፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ግን የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በዚህ ጊዜ ከበፊቱ ይበልጥ ለሰዎች ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት እንደ ጀመረ አስተዋልኩ። ያደረገው የባሕርይ ለውጥ በጣም ስለነካኝ አምላክ ወደፊት ምድርን ገነት ለማድረግ ቃል እንደገባ ሲነግረኝ እሱን ለማዳመጥ ተነሳሳሁ። እውነትን ወዲያው የተቀበልኩ ሲሆን ከዚያ በኋላ ከቴሁኒስ ጋር የዕድሜ ልክ ወዳጆች ሆንን። *

አገልግሎት የጀመርኩት ግንቦት 1948 ነው፤ በወሩ ማለትም ሰኔ 20 ላይ በዩትሬክት በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቅኩ። ጥር 1, 1949 አቅኚ በመሆን በምሥራቅ ኔዘርላንድ ውስጥ ቦርኮሎ በተባለ መንደር በሚገኝ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ ተመድቤ ማገልገል ጀመርኩ። መንደሩ የሚገኘው 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመሆኑ በብስክሌት ለመጓዝ ወሰንኩ። ጉዞው 6 ሰዓት ብቻ እንደሚወስድብኝ አስቤ ነበር፤ ነገር ግን በጣለው ከባድ ዝናብና በነፋሱ ምክንያት 12 ሰዓታት ፈጀብኝ፤ ለዚያውም የመጨረሻዎቹን  90 ኪሎ ሜትሮች የተጓዝኩት በባቡር ነበር! በእንግድነት የተቀበለኝ ቤተሰብ ጋ ስደርስ በጣም መሽቶ ነበር፤ በዚያ አካባቢ በአቅኚነት ባገለገልኩባቸው ጊዜያት ሁሉ የኖርኩት ከዚህ ቤተሰብ ጋር ነው።

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ባሉት ዓመታት ሰዎች ብዙ ንብረት አልነበራቸውም። እኔም የነበረኝ አንድ ሙሉ ልብስና አንድ ሱሪ ብቻ ነበር፤ በዚያ ላይ ሙሉ ልብሱ በጣም ሰፊ፣ ሱሪው ደግሞ በጣም አጭር ነበር! መግቢያዬ ላይ እንደነገርኳችሁ በቦርኮሎ ያሳለፍኩት የመጀመሪያው ወር በጣም ፈታኝ ነበር፤ ይሖዋ ግን በርካታ ጥናቶችን በመስጠት ባርኮኛል። ከዘጠኝ ወራት በኋላ አምስተርዳም ተመደብኩ።

ከገጠር ወደ ከተማ

ያደግኩት በገጠራማ አካባቢ ከመሆኑ አንጻር የኔዘርላንድ ትልቋ ከተማ በሆነችው በአምስተርዳም መኖር ለእኔ ትልቅ ለውጥ ነበር። አገልግሎቱ በጣም ፍሬያማ ነበር። በዚህ ከተማ ባገለገልኩበት የመጀመሪያ ወር ላይ ያበረከትኩት ጽሑፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ካበረከትኩት የበለጠ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ስምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመርኩ። የቡድን አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ሆኜ ከተሾምኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር እንዳቀርብ ተመደብኩ። ነገር ግን ንግግሩን የማቀርብበት ቀን ሊደርስ ሲል ወደ ሌላ ጉባኤ ተቀየርኩ፤ በጣም ፈርቼ ስለነበር በመቀየሬ ታላቅ እፎይታ ተሰማኝ። የሚገርመው ግን በቀጣዮቹ ዓመታት ከ5,000 የሚበልጡ ንግግሮች እሰጣለሁ ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር!

ከላይ፦ ማርከስ (በስተ ቀኝ) በ1950 አምስተርዳም አቅራቢያ መንገድ ላይ ስናገለግል

ግንቦት 1950 ሐርለም እንዳገለግል ተመደብኩ። ከዚያም የወረዳ ሥራ እንድሠራ ግብዣ ቀረበልኝ። ከመደንገጤ የተነሳ ለሦስት ቀን እንቅልፍ አልወሰደኝም። በቅርንጫፍ ቢሮው ከሚያገለግሉት ወንድሞች አንዱ ለሆነው ለሮበርት ዊንክለር ለዚህ መብት ብቁ እንደሆንኩ እንደማይሰማኝ ነገርኩት፤ እሱ ግን “ብቻ አንተ ቅጹን ሙላ፤ እየተማርክ ትሄዳለህ” አለኝ። ብዙም ሳይቆይ ለአንድ ወር ሥልጠና ተሰጠኝና የወረዳ አገልጋይ (የበላይ ተመልካች) ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። አንድ ጉባኤ ስጎበኝ ያኒ ታትከን ከተባለች ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ካላትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ካላት አንዲት ደስተኛ ወጣት አቅኚ ጋር ተዋወቅኩ። በኋላም በ1955 ተጋባን። ታሪኬን ከመቀጠሌ በፊት ግን ያኒ እንዴት አቅኚ እንደሆነችና የተገናኘነው እንዴት እንደሆነ ታጫውታችሁ።

ትዳር ከመሠረትን በኋላ ያለው አገልግሎት

ያኒ፦ እናቴ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው በ1945 ሲሆን በወቅቱ የ11 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከዚያም እናቴ ወዲያውኑ ሦስት ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረች፤ ነገር ግን አባቴ እውነትን ስለሚቃወም የምታስጠናን እሱ ቤት በማይኖርበት ጊዜ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁበት ስብሰባ በ1950 በሄግ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ነበር። ከሳምንት በኋላ ደግሞ በአሰን (ድሬንት) በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘሁ። በወቅቱ አባቴ በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ ከቤት አባረረኝ። እናቴም “የት መሄድ እንደምትችይ ታውቂያለሽ” አለችኝ። ስለ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ እየተናገረች እንደሆነ ገባኝ። በመጀመሪያ በአቅራቢያችን ካለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመርኩ፤ ያም ቢሆን አባቴ በጣም ስላስቸገረኝ 95 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በዴቨንተር (ኦቨርአይሰል)  ወዳለ ጉባኤ ተዛወርኩ። በወቅቱ ለአቅመ ሔዋን አልደረስኩም ነበር፤ በመሆኑም አባቴ እኔን ከቤት ማባረሩን የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለደረሱበት ችግር ውስጥ ገባ። በዚህ የተነሳ ወደ ቤት መመለስ እንደምችል ነገረኝ። አባቴ እስከ መጨረሻው እውነትን ባይቀበልም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እንድገኝና አገልግሎት እንድወጣ ከጊዜ በኋላ ፈቀደልኝ።

ከታች፦ ያኒ (በስተ ቀኝ ጫፍ ላይ) በ1952 ረዳት አቅኚ ሆነን ስናገለግል

ወደ ቤት ከተመለስኩ ብዙም ሳይቆይ እናቴ በጠና ስለታመመች የቤቱን ሥራ ሁሉ እኔ መሥራት ነበረብኝ። ያም ሆኖ በመንፈሳዊ እድገት በማድረግ በ1951 በ17 ዓመቴ ተጠመቅኩ። በ1952 እናቴ ከሕመሟ ስታገግም ከሦስት አቅኚ እህቶች ጋር በመሆን ለሁለት ወራት በረዳት አቅኚነት አገለገልኩ። እንደ ቤትም ሆኖ በሚያገለግል ጀልባ ውስጥ እየኖርን ድሬንት ውስጥ በሚገኙ ሁለት ከተሞች ሰብከናል። ከዚያም በ1953 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ አንድ ወጣት የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ ጉባኤያችንን ሊጎበኝ መጣ። ይህ የወረዳ የበላይ ተመልካች ማርከስ ነበር። እናም ግንቦት 1955 ከማርከስ ጋር ተጋባን፤ አብረን ይሖዋን በተሻለ ሁኔታ ማገልገል እንደምንችል ተሰማን።—መክ. 4:9-12

በስተ ቀኝ፦ በ1955 የሠርጋችን ዕለት

ማርከስ፦ ከተጋባን በኋላ መጀመሪያ ላይ ቪንዳም (ግሮኒንገን) ውስጥ በአቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። የምንኖረው ሁለት በሦስት በሆነች ጠባብ ቤት ውስጥ ነበር። ያም ሆኖ ያኒ ክፍሉን ጥሩ አድርጋ ስለያዘችው በጣም ያምር ነበር። ማታ ማታ ታጣፊ አልጋችንን ለመዘርጋት ጠረጴዛውንና ሁለቱን ወንበሮቻችንን ማነሳሳት ነበረብን።

ከስድስት ወር በኋላ ቤልጂየም ውስጥ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። በ1955 በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት አስፋፊዎች 4,000 ገደማ ብቻ ነበሩ። አሁን ግን ቁጥሩ በስድስት እጥፍ ጨምሯል! ሰሜን ቤልጂየም በምትገኘው በፍላንደርዝ የሚኖሩ ሰዎች የሚናገሩት ቋንቋ በኔዘርላንድ ከሚነገረው ጋር ይመሳሰላል። ይሁንና የአነጋገር ቅላጼያቸው ለየት ያለ ነው፤ በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ይህን ችግር መቋቋም ነበረብን።

ያኒ፦ የወረዳ ሥራ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየትን ይጠይቃል። ጉባኤዎችን ለመጎብኘት የምንጓዘው በብስክሌት ሲሆን የምናርፈውም ወንድሞችና እህቶች ቤት ነበር። አንድን ጉባኤ ጎብኝተን ከጨረስን በኋላ ወደ ሌላው ከመሄዳችን በፊት የምናርፍበት የራሳችን ቤት ስላልነበረን እስከ ሰኞ ድረስ እዚያው እንቆይና ማክሰኞ ጠዋት ወደ ቀጣዩ ጉባኤ እንጓዛለን። ያም ቢሆን አገልግሎታችንን የምንመለከተው ከይሖዋ እንዳገኘነው በረከት አድርገን ነበር።

ማርከስ፦ በምንሄድበት ጉባኤ ውስጥ መጀመሪያ ላይ የምናውቃቸው ወንድሞችና እህቶች አልነበሩም፤ ያም ሆኖ ሁሉም በጣም ደጎችና እንግዳ ተቀባዮች ነበሩ። (ዕብ. 13:2) በቀጣዮቹ ዓመታት ቤልጅየም ውስጥ በደች ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን በሙሉ በተደጋጋሚ ጎብኝተናል። ይህም ብዙ በረከት አስገኝቶልናል። ለምሳሌ ያህል፣ በደች ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን ባቀፈው አውራጃ ውስጥ ከሚገኙት ከሁሉም ወንድሞችና እህቶች ጋር ማለት ይቻላል መተዋወቅ ችለናል፤ እንዲሁም እነዚህን ወንድሞች በጣም እንወዳቸዋለን። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ፣ ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ለመንግሥቱ ቅድሚያ ሲሰጡ ለመመልከት በቅተናል። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማርተው ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ መመልከትም በጣም የሚያስደስት ነው።  (3 ዮሐ. 4) በዚህ መንገድ ‘እርስ በርስ መበረታታታችን’ በተመደብንበት ቦታ፣ ምንጊዜም በሙሉ ልባችን እንድናገለግል ረድቶናል።—ሮም 1:12

ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመንም በእጅጉ ተባርከናል

ማርከስ፦ ከተጋባንበት ጊዜ ጀምሮ ጊልያድ ገብተን የመሠልጠን ምኞት ነበረን። በየቀኑ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል እንግሊዝኛ እናጠና ነበር። ይሁንና መጻሕፍት በማንበብ ብቻ እንግሊዝኛ ማወቅ ከባድ ነው፤ በመሆኑም በእረፍት ጊዜያችን ወደ እንግሊዝ በመሄድ እያገለገልን ቋንቋውን ለማጥናት ወሰንን። በመጨረሻም በ1963 ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት አንድ ፖስታ ደረሰን። ፖስታው ሁለት ደብዳቤ ይዟል፤ አንዱ ለእኔ ሌላኛው ደግሞ ለያኒ የተላከ ነበር። የእኔ ደብዳቤ በጊልያድ ለአሥር ወር የሚቆይ ልዩ ሥልጠና እንድወስድ የተጋበዝኩ መሆኑን የሚገልጽ ነበር። ሥልጠናው በአብዛኛው የሚያተኩረው ወንድሞችን በማሠልጠንና ድርጅታዊ መመሪያዎችን በመስጠት ላይ ነበር። በመሆኑም በዚያ ሥልጠና ላይ ከተካፈሉት 100 ተማሪዎች መካከል 82ቱ ወንድሞች ነበሩ።

ያኒ፦ ለእኔ የደረሰኝ ደብዳቤ፣ ማርከስ በጊልያድ በሚማርበት ወቅት እኔ ቤልጅየም መቆየት እችል እንደሆነ በጸሎት እንዳስብበት የሚጠይቅ ነበር። መጀመሪያ ላይ በጣም ከፍቶኝ እንደነበር አልክድም። እኔ ወደ ጊልያድ ለመሄድ ያደረኩትን ጥረት ይሖዋ እንዳልባረከው ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ማርከስ በጊልያድ ትምህርት ቤት ገብቶ መማሩ ጥቅም እንደሚያስገኝለትና የትምህርት ቤቱን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ እንደሚያስችለው በማስታወስ ራሴን አጽናናሁ። ስለዚህ በቤልጅየም ለመቆየት ተስማማሁ፤ ከዚያም ጀንት በተባለች የቤልጅየም ከተማ ውስጥ አና እና ማሪያ ከተባሉ ተሞክሮ ያላቸው ልዩ አቅኚዎች ጋር እንዳገለግል ተመደብኩ።

ማርከስ፦ እንግሊዝኛዬን ማሻሻል ስለነበረብኝ ትምህርት ቤቱ ከመጀመሩ ከአምስት ወራት በፊት ወደ ብሩክሊን አቀናሁ። እዚያም በጽሑፍ መላኪያ ክፍልና በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ሠራሁ። በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ ማገልገሌ እንዲሁም ወደ እስያ፣ አውሮፓና ደቡብ አሜሪካ የሚላኩ ጽሑፎችን በማዘጋጀቱ ሥራ ተሳትፎ ማድረጌ ስለ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበራችን ያለኝ ግንዛቤ እንዲጨምር አድርጓል። በተለይ ደግሞ በወንድም ራስል ዘመን ፒልግሪም (ተጓዥ የበላይ ተመልካች) በመሆን ያገለገለውን ወንድም ማክሚላንን ፈጽሞ አልረሳውም። እኔ በሄድኩበት ጊዜ በጣም አርጅቶ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የመስማት ችግር ነበረበት፤ ያም ቢሆን በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኝ ነበር። ይህም በእኔ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በፍጹም አቅልለን መመልከት እንደሌለብንም አስተምሮኛል።—ዕብ. 10:24, 25

ያኒ፦ እኔና ማርከስ በሳምንት ውስጥ ብዙ ጊዜ እንጻጻፍ ነበር። በጣም ተነፋፍቀን ነበር! ያም ሆኖ ማርከስ በጊልያድ የሚወስደውን ሥልጠና ወዶት ነበር፤ እኔም ብሆን በአገልግሎቴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ማርከስ ከዩናይትድ ስቴትስ በተመለሰበት ወቅት 17 ጥናቶች ነበሩኝ! ለአንድ ዓመት ከሦስት ወራት መለያየታችን በጣም ፈታኝ ቢሆንብንም ይሖዋ የከፈልነውን መሥዋዕትነት እንደባረከው ተመልክቻለሁ። ማርከስ የመጣበት አውሮፕላን የደረሰው ረጅም ሰዓት ዘግይቶ ነበር፤ በመጨረሻ አውሮፕላኑ ደርሶ ስንገናኝ ተቃቅፈን ተላቀስን። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ተለያይተን አናውቅም።

ላገኘናቸው መብቶች በሙሉ አመስጋኞች ነን

ማርከስ፦ ታኅሣሥ 1964 ከጊልያድ እንደተመለስኩ በቤቴል እንድናገለግል ተመደብን። በወቅቱ በቋሚነት ቤቴል የምንቆይ መስሎን ነበር። ይሁን እንጂ ከሦስት ወራት በኋላ ፍላንደርዝ ውስጥ በአውራጃ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። አልዘን እና ኤልስ ቨከርስማ የተባሉ ሚስዮናውያን ወደ ቤልጅየም ሲመጡ በአውራጃ ሥራ እንዲያገለግሉ ተመደቡ፤ እኛ ደግሞ በቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። በዚያም በአገልግሎት  ዘርፍ ማገልገል ጀመርኩ። ከ1968 እስከ 1980 ባሉት ዓመታት በርካታ ጊዜያት አንዴ ቤቴል አንዴ የወረዳ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል። ከ1980 እስከ 2005 ግን በቋሚነት በአውራጃ የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ።

የአገልግሎት ምድባችን በየጊዜው ቢለዋወጥም ራሳችንን የወሰንነው ይሖዋን በሙሉ ልባችን ለማገልገል መሆኑን ለአፍታም ቢሆን አልዘነጋንም። ከምድባችን ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ለውጥ ቢደረግ ይህ የሆነበት ምክንያት የመንግሥቱን ሥራ ለማስፋፋት እንደሆነ ስለምንተማመን የሚሰጠንን ማንኛውንም ኃላፊነት በደስታ እንወጣ ነበር።

ያኒ፦ በተለይ ማርከስ በ1977 በብሩክሊን እንዲሁም በ1997 በፓተርሰን ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት የተዘጋጀውን ተጨማሪ ሥልጠና እንዲወስድ በተጠራበት ጊዜ ከእሱ ጋር የመሄድ አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያውቃል

ማርከስ፦ በ1982 ያኒ ቀዶ ሕክምና አደረገች፤ ያም ሆኖ በደንብ ማገገም ቻለች። ከሦስት ዓመት በኋላ በሉቫን የሚገኘው ጉባኤ በመንግሥት አዳራሹ ፎቅ ላይ ያለውን መኖሪያ ቤት እንድንጠቀምበት በመስጠት ደግነት አሳየን። ከ30 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳችን የሆነ ትንሽ ማረፊያ ቤት አገኘን። ማክሰኞ ማክሰኞ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት ስንነሳ ጓዛችንን ለማውረድ 54ቱን የቤታችንን ደረጃዎች በርካታ ጊዜ መውጣትና ወውረድ ነበረብኝ! ደስ የሚለው በ2002 ምድር ቤት እንድንኖር ዝግጅት ተደረገልን። ሰባ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ልዩ አቅኚ ሆነን እንድናገለግል ሎከረን የተባለ ከተማ ተመደብን። በዚህ መንገድ በማገልገላችንና በየቀኑ አገልግሎት መውጣት በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን።

“ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የምናገለግለው ማንን ነው የሚለው ጉዳይ እንጂ የምናገለግልበት ቦታ ወይም የተሰጠን ኃላፊነት እንዳልሆነ ጠንካራ እምነት አለን”

ያኒ፦ ሁለታችን በአንድነት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍነው ጊዜ ከ120 ዓመታት ይበልጣል! ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት የገባው ቃል በእኛ ሕይወት ፍጻሜውን ሲያገኝ መመልከት ችለናል፤ በተጨማሪም እሱን በታማኝነት እስካገለገልን ድረስ ‘አንዳች ነገር እንደማያሳጣን’ የሰጠው ተስፋ እውን ሲሆን በገዛ ሕይወታችን ተመልክተናል።—ዕብ. 13:5፤ ዘዳ. 2:7

ማርከስ፦ ሕይወታችንን ለይሖዋ የወሰነው ወጣቶች እያለን ነው። ለራሳችን ታላቅ ነገርን ለመፈለግ ፈጽሞ አልሞከርንም። ምንም ዓይነት የአገልግሎት ምድብ ቢሰጠን ለመቀበል ፈቃደኞች ነን፤ ምክንያቱም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የምናገለግለው ማንን ነው የሚለው ጉዳይ እንጂ የምናገለግልበት ቦታ ወይም የተሰጠን ኃላፊነት እንዳልሆነ ጠንካራ እምነት አለን።

^ አን.5 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አባቴና እናቴ እንዲሁም ታላቅ እህቴና ሁለት ወንድሞቼ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።