በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ

በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ

“ዳቦውን ከቆረሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ አከፋፈለ፤ እነሱ ደግሞ ለሕዝቡ አከፋፈሉ።”—ማቴ. 14:19

1-3. ኢየሱስ በቤተሳይዳ አቅራቢያ ብዙ ሕዝብ የመገበው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። (ማቴዎስ 14:14-21ን አንብብ።) ጊዜው በ32 ዓ.ም. ከተከበረው የማለፍ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። ሴቶችና ልጆች ሳይቆጠሩ 5,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰሜናዊው የገሊላ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው በቤተሳይዳ አቅራቢያ ባለ አንድ ራቅ ያለ አካባቢ ተሰባስበዋል።

2 ኢየሱስ ሕዝቡን ሲመለከት አዘነላቸው፤ ከዚያም ከእነሱ መካከል የታመሙትን ፈወሰ፤ እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ነገር አስተማራቸው። እየመሸ ሲሄድ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሰዎቹን እንዲያሰናብት ነገሩት፤ ይህንንም ያሉት ሰዎቹ በአቅራቢያው ወዳሉ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ አስበው ነው። ይሁንና ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የሚበሉት ነገር እናንተ ስጧቸው” አላቸው። ሆኖም የተናገረው ነገር ለደቀ መዛሙርቱ እንቆቅልሽ ሳይሆንባቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም በእጃቸው ያለው ምግብ አምስት ዳቦና ሁለት ዓሣ ብቻ ነበር።

3 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በርኅራኄ ተነሳስቶ አንድ ተአምር ፈጸመ፤ ይህ ደግሞ በአራቱም ወንጌሎች ውስጥ በመጠቀስ ረገድ ብቸኛው ተአምር ነው። (ማር. 6:35-44፤ ሉቃስ 9:10-17፤ ዮሐ. 6:1-13) ኢየሱስ ሕዝቡን መቶ መቶና፣ ሃምሳ ሃምሳ እያደረጉ በቡድን እንዲያስቀምጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ምግቡን ከባረከ በኋላ ዳቦውንና ዓሣውን መቆራረስ ጀመረ። ከዚያም ምግቡን በቀጥታ ለሕዝቡ ከመስጠት ይልቅ “ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው”፤ እነሱም ‘ለሕዝቡ አቀረቡ።’ የሚገርመው ነገር ሁሉም ከበሉ በኋላ ብዙ ምግብ ተረፈ! ኢየሱስ በጥቂቶች ማለትም በደቀ መዛሙርቱ ተጠቅሞ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መመገቡ ትኩረት የሚስብ ነው። *

4. (ሀ) ኢየሱስ ይበልጥ ያሳሰበው ምን ዓይነት ምግብ ማቅረብ ነበር? ለምንስ? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?

4 ኢየሱስ ይበልጥ ያሳሰበው ነገር ለተከታዮቹ መንፈሳዊ ምግብ ማቅረብ ነው። ምክንያቱም መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መረዳት የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ ያውቃል። (ዮሐ. 6:26, 27፤ 17:3) ኢየሱስ ርኅሩኅ መሆኑ ሕዝቡን ዳቦና ዓሣ ለመመገብ እንዳነሳሳው ሁሉ ይኸው ባሕርይው ተከታዮቹን ለረጅም ሰዓት እንዲያስተምራቸው አነሳስቶታል።  (ማር. 6:34) ይሁንና በምድር ላይ የሚያሳልፈው ጊዜ አጭር እንደሆነና ከዚያ በኋላ ወደ ሰማይ እንደሚመለስ ያውቅ ነበር። (ማቴ. 16:21፤ ዮሐ. 14:12) ታዲያ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ በደንብ እንዲመገቡ የሚያደርገው እንዴት ነው? ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን በመመገብ ነው። ታዲያ እነዚህ ጥቂቶች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? እስቲ በቅድሚያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙ ቅቡዓንን የመገበው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ከዚያም በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ሁላችንም ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባውን የሚከተለውን ጥያቄ እንመረምራለን፦ በዛሬው ጊዜ ክርስቶስ ብዙኃኑን ለመመገብ የሚጠቀምባቸው ጥቂቶች እነማን መሆናቸውን መለየት የምንችለው እንዴት ነው?

በጥቂቶች አማካኝነት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተመግበዋል (አንቀጽ 4ን ተመልከት)

ኢየሱስ ጥቂቶቹን መረጠ

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ፣ እሱ ከሞተ በኋላ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ በደንብ እንዲመገቡ ለማድረግ ሲል ምን ከባድ ውሳኔ አደረገ? (ለ) ኢየሱስ እሱ ከሞተ በኋላ ለሚኖራቸው ልዩ ሚና ሐዋርያቱን ቀደም ብሎ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?

5 ኃላፊነት የሚሰማው አንድ የቤተሰብ ራስ፣ እሱ ቢሞት ቤተሰቡ እንዳይቸገር አስቀድሞ ዝግጅት ያደርጋል። በተመሳሳይም የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ኢየሱስ፣ እሱ ከሞተ በኋላም ተከታዮቹ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እንዲያገኙ በማሰብ አስቀድሞ ዝግጅት አድርጓል። (ኤፌ. 1:22) ለምሳሌ ኢየሱስ ከመሞቱ ከሁለት ዓመታት በፊት አንድ ከባድ ውሳኔ አድርጎ ነበር። ብዙዎችን ለመመገብ የሚጠቀምባቸውን የመጀመሪያዎቹን ጥቂቶች መረጠ። እስቲ በወቅቱ የተከናወነውን ነገር እንመልከት።

6 ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ካደረ በኋላ በነጋታው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ ከመካከላቸው 12 ሐዋርያት መረጠ። (ሉቃስ 6:12-16) በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከ12ቱ ጋር ልዩ ቅርበት በመፍጠር እነሱን በቃልና ምሳሌ በመሆን ሲያስተምራቸው ቆየ። ብዙ መማር ያለባቸው ነገር እንዳለ ተገንዝቦ ነበር፤ እንዲያውም ሞቶ ከተነሳም በኋላ እንኳ “ደቀ መዛሙርት” ተብለው ተጠርተዋል። (ማቴ. 11:1፤ 20:17) በግለሰብ ደረጃ ጠቃሚ ምክር የለገሳቸው ከመሆኑም ሌላ በአገልግሎቱ ሰፊ ሥልጠና ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:1-42፤ 20:20-23፤ ሉቃስ 8:1፤ 9:52-55) እሱ ከሞተና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ለሚኖራቸው ልዩ ኃላፊነት ከወዲሁ እያዘጋጃቸው እንደነበረ ምንም አያጠያይቅም።

7. ኢየሱስ የሐዋርያቱ ዋነኛ ኃላፊነት ምን ሊሆን እንደሚገባው ፍንጭ የሰጠው እንዴት ነው?

7 ታዲያ የሐዋርያቱ ኃላፊነት ምንድን ነው? በ33 ዓ.ም. የሚከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ሐዋርያቱ “የበላይ ተመልካች” በመሆን እንደሚያገለግሉ ግልጽ ሆኖ ነበር። (ሥራ 1:20) ይሁንና ዋነኛ ኃላፊነታቸው ሊሆን የሚገባው ምንድን ነው? ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር ያደረገው ውይይት ፍንጭ ይሰጣል። (ዮሐንስ 21:1, 2, 15-17ን አንብብ።) የተወሰኑት ሐዋርያት በተገኙበት ኢየሱስ ጴጥሮስን “ግልገሎቼን መግብ” አለው። ኢየሱስ ለብዙኃኑ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ከሚጠቀምባቸው ጥቂቶች መካከል ሐዋርያቱ እንደሚገኙበት በዚህ መንገድ ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስ ‘ለግልገሎቹ’ ያለውን ስሜት በግልጽ የሚያሳይ እንዴት ያለ ልብ የሚነካ አነጋገር ነው! *

ከጴንጤቆስጤ አንስቶ ብዙኃኑን መመገብ

8. በጴንጤቆስጤ ወቅት አማኝ የሆኑት ሰዎች ክርስቶስ የሚጠቀምበት መስመር ማን እንደሆነ በሚገባ እንደተገነዘቡ ያሳዩት እንዴት ነው?

8 ከሞት የተነሳው ክርስቶስ በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል አንስቶ የተቀሩትን ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን ለመመገብ ሐዋርያቱን የሐሳብ ማስተላለፊያ መስመር አድርጎ መጠቀም ጀምሯል። (የሐዋርያት ሥራ 2:41, 42ን አንብብ።) በዚያን ዕለት ክርስትናን ተቀብለው በመንፈስ የተቀቡ አይሁዶች (ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብን ይጨምራል) ይህ መስመር ማን እንደሆነ በሚገባ ተገንዝበው ነበር። በመሆኑም ያለ ምንም ማቅማማት “[የሐዋርያቱን] ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ።” አንድ ምሁር እንደተናገሩት ከሆነ “በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ “አንድን ድርጊት በጽናትና ያለ ምንም ማወላወል በታማኝነት መደገፍ” የሚል ፍቺም ሊያስተላልፍ ይችላል። አዲሶቹ አማኞች መንፈሳዊ ምግብ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፤ ደግሞም ይህን ምግብ ከየት ማግኘት እንደሚችሉ  ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። በዝግጅቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ስለነበራቸው ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች አስመልክቶ እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ ሲፈልጉ ፊታቸውን የሚያዞሩት ወደ ሐዋርያቱ ነበር። *ሥራ 2:22-36

9. ሐዋርያቱ የኢየሱስን በጎች የመመገብ ኃላፊነታቸውን ትልቅ ቦታ ይሰጡት እንደነበረ ያሳዩት እንዴት ነው?

9 ሐዋርያቱ የኢየሱስን በጎች የመመገብ ኃላፊነታቸውን ትልቅ ቦታ ይሰጡት ነበር። በአዲሱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጥንቃቄ መያዝ የሚያስፈልገውና ወደ መከፋፈል ሊመራ የሚችል አንድ ጉዳይ ባጋጠማቸው ወቅት የወሰዱትን እርምጃ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የሚገርመው የተነሳው ጉዳይ ከምግብ ጋር የተያያዘ ነው፤ መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊ ምግብ። ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ መበለቶች በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ ቸል ተብለው ነበር፤ ዕብራይስጥ ተናጋሪ የሆኑት መበለቶች ግን በደንብ ይስተናገዱ ነበር። ሐዋርያቱ ጥንቃቄ የሚያሻውን ይህን ችግር የፈቱት እንዴት ነው? “አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት” ምግብ የማከፋፈሉን ይህን “አስፈላጊ ሥራ” በበላይነት እንዲከታተሉ ብቃት ያላቸውን ሰባት ወንድሞች ሾሙ። ኢየሱስ ሕዝቡን በተአምር በመገበበት ወቅት አብዛኞቹ ሐዋርያት ምግቡን በማከፋፈሉ ሥራ እንደተሳተፉ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ሐዋርያቱ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ ላይ ማተኮራቸው ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተዋል። በመሆኑም ‘ቃሉን ለማስተማሩ ሥራ’ ራሳቸውን ሰጥተው ነበር።—ሥራ 6:1-6

10. ክርስቶስ በኢየሩሳሌም የነበሩትን ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?

10 ከጊዜ በኋላ ከሐዋርያቱ መካከል አንዳንዶቹ ስለ ሞቱ፣ ብቃቱን ያሟሉ ጥቂት ሽማግሌዎች ከተቀሩት ሐዋርያት ጋር በመሆን ማገልገል ጀመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 15:1, 2ን አንብብ።) በዚህ ምክንያት በ49 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም የበላይ አካል ሆነው የሚያገለግሉ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች” ነበሩ። የጉባኤው ራስ የሆነው ክርስቶስ ብቃት ያለውን ይህን አነስተኛ ቡድን መሠረታዊ ከሆኑ ትምህርቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመፍታት ብሎም የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩንና የማስተማሩን ሥራ በበላይነት ለመምራት ተጠቅሞበታል።—ሥራ 15:6-29፤ 21:17-19፤ ቆላ. 1:18

11, 12. (ሀ) ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ጉባኤዎችን ለመመገብ የተጠቀመበትን ዝግጅት ይሖዋ እንደባረከው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ክርስቶስ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበት መስመር በግልጽ ተለይቶ እንዲታወቅ ያስቻለው ምንድን ነው?

11 ታዲያ ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ጉባኤዎች ለመመገብ ልጁ ኢየሱስ የተጠቀመበትን ዝግጅት ባርኮታል? ምንም ጥያቄ የለውም! እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተገኘውን ውጤት እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “[ሐዋርያው ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ] በየከተማዎቹ [ሲያልፉ] በዚያ ለሚያገኟቸው  ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ያሳውቋቸው ነበር። ስለሆነም ጉባኤዎቹ በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።” (ሥራ 16:4, 5) እነዚህ ጉባኤዎች እድገት እያደረጉ ሊሄዱ የቻሉት በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የበላይ አካል ጋር በታማኝነት በመተባበራቸው እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ታዲያ ይህ ሁኔታ ኢየሱስ ጉባኤዎችን ለመመገብ የተጠቀመበትን ዝግጅት ይሖዋ እንደባረከው የሚያሳይ አይደለም? እንግዲያው መንፈሳዊ እድገት የሚገኘው የይሖዋ በረከት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።—ምሳሌ 10:22፤ 1 ቆሮ. 3:6, 7

12 እስካሁን መመልከት እንደቻልነው ኢየሱስ ተከታዮቹን ለመመገብ የሚጠቀምበት አንድ መንገድ አለ፤ ይህም በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ ነው። መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበት መስመር ደግሞ በግልጽ ተለይቶ ይታወቅ ነበር። ለነገሩ የመጀመሪያዎቹ የበላይ አካል አባላት የሆኑት ሐዋርያት የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ የሚታይ ማስረጃ ማቅረብ ችለው ነበር። የሐዋርያት ሥራ 5:12 “ሐዋርያት በሕዝቡ መካከል ብዙ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች መፈጸማቸውን ቀጥለው ነበር” በማለት ይናገራል። * ስለሆነም በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች ‘ክርስቶስ በጎቹን ለመመገብ የሚጠቀመው በማን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱበት ምክንያት አልነበረም። ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ሁኔታዎች ተለዋወጡ።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን ለመመገብ የሚጠቀመው በማን እንደሆነ የሚጠቁም ግልጽ የሆነ ማስረጃ ነበር (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

እንክርዳዱ ብዙ፣ ስንዴው ጥቂት የነበረበት ወቅት

13, 14. (ሀ) ኢየሱስ በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) ጥቃቱ የሚመጣው ከየትኞቹ ሁለት አቅጣጫዎች ነው? (ተጨማሪ መረጃውን ተመልከት።)

13 ኢየሱስ በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ትንቢታዊ ምሳሌ ላይ አዲስ በተዘራው ስንዴ ይኸውም በቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል እንክርዳድ ማለትም አስመሳይ ክርስቲያኖች እንደሚዘሩ አስጠንቅቋል። ሁለቱም ቡድኖች ምንም ሳይነኩ እስከ መከሩ ማለትም እስከዚህ ‘ሥርዓት መደምደሚያ’ ድረስ አብረው እንደሚያድጉ ተናግሯል። (ማቴ. 13:24-30, 36-43) ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ፍጻሜውን ማግኘት ጀመረ። *

14 ከሃዲዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ላይ በተወሰነ መጠን ተጽዕኖ ማሳደር ጀምረው የነበረ ቢሆንም የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያት ጉባኤው በሐሰት ትምህርቶች እንዳይበከል ‘ማገድ’ ችለዋል። (2 ተሰ. 2:3, 6, 7) የመጨረሻው ሐዋርያ ሲሞት ግን ክህደት ሥር በመስደድ ማደግ ጀመረ፤ ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው የሚያድጉበት ጊዜም ለብዙ ዘመናት ቆየ። በተጨማሪም በዚህ ጊዜ ውስጥ እንክርዳዱ እየበዛ ሲሄድ ስንዴው ግን በጣም ጥቂት ነበር። መንፈሳዊ ምግብ በቋሚነት የሚያቀርብ የተደራጀ መስመር አልነበረም። ሆኖም ይህ ሁኔታ መቀየሩ አይቀርም። ጥያቄው ግን “መቼ” የሚለው ነው።

በመከር ወቅት ምግብ የሚያቀርበው ማን ነው?

15, 16. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ማጥናታቸው ምን ውጤት አስገኝቷል? የትኛው ጥያቄስ ይነሳል?

15 ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው የሚያድጉበት ወቅት እየተጠናቀቀ ሲመጣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብቅ ማለት ጀመሩ። በ1870ዎቹ ውስጥ ቅን ልብ ያላቸውና እውነት ፈላጊ የሆኑ ጥቂት ሰዎች ራሳቸውን ከእንክርዳዱ ይኸውም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ከሚገኙ አስመሳይ ክርስቲያኖች በመለየት አብረው ይሰበሰቡ እንደነበረ አስታውስ። ራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በማለት ይጠሩ የነበሩት እነዚህ ቅን ክርስቲያኖች ትሑት ልብ በመያዝና አእምሯቸውን ክፍት በማድረግ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጸሎት ታግዘው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር።—ማቴ. 11:25

16 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ማጥናታቸው አስደሳች ውጤት አስገኝቷል። እነዚህ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማተምና በማሰራጨት የሐሰት ትምህርቶችን አጋልጠዋል እንዲሁም መንፈሳዊ እውነቶችን ለብዙዎች አዳርሰዋል። እውነትን የተጠሙና የተራቡ በርካታ ሰዎች ተማሪዎቹ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልባቸውና አእምሯቸው ተማርኳል። አሁን  የሚነሳው ጥያቄ ‘ከ1914 በፊት ባሉት ዓመታት ክርስቶስ በጎቹን ለመመገብ የሚጠቀምበት መስመር እንዲሆን የሾመው እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበር?’ የሚለው ነው። መልሱ ‘አልነበረም’ ነው። እነዚህ ተማሪዎች የሚገኙት ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው በሚያድጉበት ወቅት ነበር፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብበት መስመር ገና አልተደራጀም ነበር። ስለሆነም በእንክርዳድ የተመሰሉት አስመሳይ ክርስቲያኖች በስንዴ ከተመሰሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚለዩበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር።

17. በ1914 ምን ወሳኝ ክንውኖች መፈጸም ጀመሩ?

17 ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የመከሩ ወቅት የጀመረው በ1914 ነው። በዚህ ዓመት ወሳኝ የሆኑ በርካታ ክንውኖች መፈጸም ጀመሩ። ኢየሱስ ንጉሥ በመሆን በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ የመጨረሻዎቹ ቀናትም ጀመሩ። (ራእይ 11:15) ከ1914 እስከ 1919 መባቻ ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ወሳኝ የሆነውን የምርመራና የማንጻት ሥራ ለማከናወን ከአባቱ ጋር በመሆን ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ መጥቷል። * (ሚል. 3:1-4) ከዚያም ከ1919 ጀምሮ ስንዴው መሰብሰብ ጀመረ። ታዲያ ክርስቶስ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበት አንድ የተደራጀ መስመር የሚሾምበት ጊዜ ደርሶ ነበር? እንዴታ!

18. ኢየሱስ ምን ዓይነት ሹመት እንደሚሰጥ አስቀድሞ ተናግሯል? የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ምን ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል?

18 ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን ትንቢት በተናገረበት ወቅት መንፈሳዊ ምግብ “በተገቢው ጊዜ” የሚሰጥ አንድ መስመር እንደሚሾም ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 24:45-47) ታዲያ ኢየሱስ በማን ይጠቀም ይሆን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ በመጨረሻዎቹ ቀናትም በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን እንደሚመግብ የታወቀ ነው። ይሁንና የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ በመሆኑ “ጥቂቶቹ እነማን ናቸው?” የሚል ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል። ይህም ሆነ ኢየሱስ ከተናገረው ትንቢት ጋር የተያያዙ ሌሎች ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ያገኛሉ።

 

^ አን.3 አንቀጽ 3፦ ኢየሱስ በሌላ ጊዜም ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ 4,000 ወንዶችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መግቦ የነበረ ሲሆን በዚህ ጊዜም ቢሆን ምግቡን “ለደቀ መዛሙርቱ [አከፋፈለ]፤ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ለሕዝቡ አከፋፈሉ።”—ማቴ. 15:32-38

^ አን.7 አንቀጽ 7፦ ጴጥሮስ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ‘ግልገሎቹ’ በሙሉ ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ነበሩ።

^ አን.8 አንቀጽ 8፦ አዲሶቹ አማኞች “[የሐዋርያቱን] ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ” መባሉ ሐዋርያት መደበኛ በሆነ መንገድ ያስተምሩ እንደነበረ ያሳያል። አንዳንዶቹ የሐዋርያት ትምህርቶች በመንፈስ መሪነት በተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ።

^ አን.12 አንቀጽ 12፦ ከሐዋርያት በተጨማሪ ሌሎች ክርስቲያኖችም ተአምራዊ ስጦታ የተቀበሉ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚሆነው በቀጥታ በሐዋርያቱ በኩል ወይም እነሱ በተገኙበት ነው።—ሥራ 8:14-18፤ 10:44, 45

^ አን.13 አንቀጽ 13፦ በሐዋርያት ሥራ 20:29, 30 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚጠቁመው የክርስቲያን ጉባኤ ጥቃት የሚሰነዘርበት ከሁለት አቅጣጫዎች ነው። የመጀመሪያው፣ አስመሳይ ክርስቲያኖች (“እንክርዳድ”) በእውነተኛ ክርስቲያኖች ‘መካከል መግባታቸው’ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች “መካከል” አንዳንዶች “ጠማማ ነገር” የሚናገሩ ከሃዲዎች መሆናቸው ነው።

^ አን.17 አንቀጽ 17፦ በዚህ እትም ውስጥ ከሚገኘው“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ከሚለው ርዕስ ላይ ገጽ 11 አንቀጽ 6ን ተመልከት።