በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ቢብልዮማንሲ ምንድን ነው? ክርስቲያኖችስ እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?

ቢብልዮማንሲ ማለት መጽሐፍ ቅዱስን የሆነ ቦታ ላይ እንዳመጣለት ከፍቶ መጀመሪያ ላይ ዓይን ውስጥ የገባውን ጥቅስ ማንበቡ አስፈላጊውን መመሪያ ያስገኛል የሚል እምነት ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በጥንቆላ አይካፈሉም። ከዚህ ይልቅ ትክክለኛ እውቀትና መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ።—12/15 ገጽ 3

እንደሚጠፋ የተገለጸው “ዓለም” ምንድን ነው?

እንደሚጠፋ የተገለጸው “ዓለም” ከአምላክ ፈቃድ ጋር በማይስማማ መንገድ የሚኖሩትን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች የሚያመለክት ነው። (1 ዮሐ. 2:17) ምድርና ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከጥፋቱ ይተርፋሉ።—1/1 ገጽ 5-7

አቤል ቢሞትም እንኳ አሁንም የሚናገረው እንዴት ነው? (ዕብ. 11:4)

በእምነቱ አማካኝነት ነው። ከእሱ እምነት ትምህርት መውሰድና ምሳሌውን መከተል እንችላለን። እሱ የተወው ምሳሌ ታላቅና ሕያው ነው።—1/1 ገጽ 12

ከአምላክ ሊያርቁን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፦ ሥራችን፣ የምንመርጣቸው መዝናኛዎች፣ ከተወገደ ዘመዳችን ጋር መቀራረብ፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምንጠቀምበት መንገድ፣ ስለ ጤና መጨነቅ፣ ለገንዘብ የተሳሳተ አመለካከት መያዝ እና ለራሳችን ወይም ላለን ቦታ ከልክ ያለፈ ትኩረት መስጠት።—1/15 ከገጽ 12-21

ሙሴ ካሳየው ትሕትና ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

ሙሴ ሥልጣን እንዲያስታብየው አልፈቀደም፤ እንዲሁም በራሱ ሳይሆን በአምላክ ታምኗል። እኛም ኃይል፣ ሥልጣን ወይም የተፈጥሮ ችሎታ እንዲያስታብየን ከመፍቀድ ይልቅ በይሖዋ እንታመናለን። (ምሳሌ 3:5, 6)—2/1 ገጽ 5

ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች የሚኖሩት የት ነው?

ጥቂቶች ማለትም 144,000 ሰዎች በሰማይ ይኖራሉ። አብዛኞቹ ሰዎች ግን የሚነሱት በምድር ላይ ለመኖር ነው። እነዚህ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል።—3/1 ገጽ 6

እስራኤላውያን “ልባቸው አልተገረዘም” ነበር ሲባል ምን ማለት ነው? (ኤር. 9:26)

ልባቸው እልኸኛና ዓመፀኛ ነበር፤ በመሆኑም ልባቸው ደንዳና እንዲሆን ያደረገውን ነገር ይኸውም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረነውን አስተሳሰባቸውን፣ ፍላጎታቸውን ወይም ዝንባሌያቸውን ማስወገድ ያስፈልጋቸው ነበር። (ኤር. 5:23, 24)—3/15 ከገጽ 9-10

ኢየሱስ ትርጉም ያለው ሕይወት በመምራት ረገድ ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው?

ዋነኛ ዓላማው የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ነበር። ለአባቱ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ሲሆን ሰዎችንም ይወድ ነበር። በመሆኑም አባቱ እንደሚወደውና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው እርግጠኛ ነበር። እነዚህ ነገሮች ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ቁልፍ ናቸው።—4/1 ከገጽ 4-5

የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል እነማንን ይጨምራል?

የበላይ አካሉን፣ ቅርንጫፍ ኮሚቴዎችን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ የሽማግሌዎች አካላትን፣ ጉባኤዎችን እና አስፋፊዎችን በግለሰብ ደረጃ ያጠቃልላል።—4/15 ገጽ 29

አምላክ የወሰዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ጨካኝ እንደሆነ አያሳዩም የምንለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ በክፉዎች ሞት አይደሰትም። (ሕዝ. 33:11) በቀድሞ ዘመን ከወሰዳቸው እርምጃዎች ማየት እንደሚቻለው የጥፋት ፍርድ ከማምጣቱ በፊት በፍቅሩ ተነሳስቶ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ይህ ደግሞ ከሚመጣው ጥፋት መትረፍ እንደምንችል ተስፋ ይፈነጥቅልናል።—5/1 ከገጽ 5-6

እስራኤላውያን፣ ወንጀለኞችን ግንድ ላይ በመስቀል በሞት ይቀጡ ነበር?

በፍጹም። በጥንት ጊዜ የነበሩ ብሔራት እንዲህ የማድረግ ልማድ ቢኖራቸውም እስራኤላውያን ይህን አያደርጉም ነበር። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በተጻፉበት ወቅት ክፉ አድራጊዎች በድንጋይ ተወግረው ወይም በሌላ መንገድ እንዲሞቱ ይደረግ ነበር። (ዘሌ. 20:2, 27) ከዚያም ለሌሎች ማስጠንቀቂያ እንዲሆን ሲባል አስከሬኑ በእንጨት ላይ ሊሰቀል ይችላል።——5/15 ገጽ 13

ዓለም አቀፍ ሰላም የሕልም እንጀራ ሆኖ የቀረው ለምንድን ነው?

የሰው ልጆች ብዙ ነገሮችን ያከናወኑ ቢሆንም ራሳቸውን የመምራት ችሎታ የላቸውም። (ኤር. 10:23) ዓለምን የሚቆጣጠረው ሰይጣን ስለሆነ በሰዎች ጥረት ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማግኘት አይቻልም። (1 ዮሐ. 5:19)—6/1 ገጽ 16.