በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አትታክቱ’

‘አትታክቱ’

“ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”ገላ. 6:9.

1, 2. በጽንፈ ዓለሙ የይሖዋ ድርጅት ላይ ማሰላሰላችን በድርጅቱ ይበልጥ እንድንተማመን የሚያደርገን እንዴት ነው?

በጣም ግዙፍ የሆነው አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት አባል መሆናችንን ማሰባችን በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት እንድንዋጥ ያደርገናል። በሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 እና በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ራእዮች ይሖዋ ዓላማውን ወደ ታላቅ ፍጻሜው ለማድረስ የተለያዩ ነገሮችን እንዴት እየመራ እንዳለ ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል። ኢየሱስ የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል እየመራ ነው፤ ድርጅቱ ዋነኛ ትኩረቱን ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ላይ እንዲያደርግ፣ ይህን ሥራ የሚያከናውኑትን በመንፈሳዊ እንዲንከባከብና እውነተኛውን የይሖዋ አምልኮ እንዲያስፋፋ ኢየሱስ አመራር በመስጠት ላይ ነው። ይህ በይሖዋ ድርጅት ላይ ጠንካራ እምነት እንዲያድርብን ያደርገናል!—ማቴ. 24:45

2 ታዲያ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ አስደናቂ ድርጅት ጋር እኩል እየተራመድን ነው? ለእውነት ያለን ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ? እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ራሳችንን ስንመረምር መታከት እንደጀመርን ምናልባትም ቅንዓታችን በተወሰነ ደረጃ እንደቀነሰ እናስተውል ይሆናል። ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ ቅንዓት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንዲያስቡ መምከር አስፈልጎት ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ማድረጋቸው ‘እንዳይደክሙና በነፍሳቸው እንዳይዝሉ’ እንደሚረዳቸው ገልጿል። (ዕብ. 12:3) እኛም በተመሳሳይ የይሖዋ ድርጅት ምን እያከናወነ እንዳለ የሚገልጸውን ከዚህ በፊት ያለውን ርዕስ በጥሞና መመርመራችን በቅንዓትና በጽናት ማገልገላችንን እንድንቀጥል በእጅጉ እንደሚረዳን ጥርጥር የለውም።

3. እንዳንታክት ምን ማድረግ ያስፈልገናል? በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንማራለን?

3 ይሁንና ጳውሎስ እንዳንታክት ልናደርገው የሚገባ ሌላም ነገር እንዳለ አመልክቷል። “መልካም ሥራ መሥራታችንን” መቀጠል እንዳለብን ገልጿል። (ገላ. 6:9) በመሆኑም እኛ በበኩላችን ልናከናውናቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። በአቋማችን ጸንተን እንድንኖርና ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመዳችንን እንድንቀጥል ሊረዱን የሚችሉ አምስት ነገሮችን እስቲ እንመልከት። ከዚያ በኋላ በግለሰብ ደረጃ እኛም ሆን ቤተሰባችን ይበልጥ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ይኖሩ እንደሆነና እንዳልሆነ መገምገም እንችላለን።

 ማበረታቻ ለማግኘትና ለአምልኮ ተሰብሰቡ

4. ስብሰባ የእውነተኛ አምልኮ ዋነኛ ክፍል ነው የምንለው ለምንድን ነው?

4 በየትኛውም ዘመን ቢሆን ስብሰባ በይሖዋ አገልጋዮች እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በዓይን በማይታየው የአጽናፈ ዓለም ክፍል የሚኖሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት በተገቢው ጊዜ በይሖዋ ፊት እንዲሰበሰቡ ይጠራሉ። (1 ነገ. 22:19፤ ኢዮብ 1:6፤ 2:1፤ ዳን. 7:10) በጥንቷ እስራኤል ሕዝቡ ‘ይሰሙና ይማሩ ዘንድ’ መሰብሰብ ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘዳ. 31:10-12) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማንበብ ወደ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበራቸው። (ሉቃስ 4:16፤ ሥራ 15:21) የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላም ለስብሰባ የሚሰጠው ልዩ ትኩረት አልቀነሰም፤ ዛሬም ቢሆን ስብሰባ የአምልኳችን ዋነኛ ክፍል ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች ለመነቃቃት አንዳቸው ለሌላው ትኩረት ይሰጣሉ።’ የይሖዋ ቀን “እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ” ልንበረታታ ይገባል።—ዕብ. 10:24, 25

5. በስብሰባዎቻችን ላይ አንዳችን ሌላውን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

5 አንዳችን ሌላውን ማበረታታት የምንችልበት አንዱ ዋነኛ መንገድ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ነው። ለአንቀጹ የቀረበውን ጥያቄ በመመለስ፣ አንድን ጥቅስ በማብራራት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ያለውን ጥቅም የሚያሳይ አጠር ያለ ተሞክሮ በመናገር ወይም በሌሎች መንገዶች እምነታችንን በሰዎች ፊት መግለጽ እንችላለን። (መዝ. 22:22፤ 40:9) ለበርካታ ዓመታት በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የቆየን ብንሆንም እንኳ ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች የሚሰጡትን ከልብ የመነጨ ሐሳብ መስማት ምንጊዜም የብርታት ምንጭ እንደሚሆንልን ምንም አያጠራጥርም።

6. ስብሰባዎቻችን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር የሚረዱን እንዴት ነው?

6 አምላካችን በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የገለጸባቸው ሌሎች ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የጉባኤም ሆኑ ትላልቅ ስብሰባዎቻችን በድፍረት እንድንሰብክና በክልላችን ውስጥ የሚያጋጥመንን ተቃውሞ ወይም ሰዎች የሚያሳዩትን የግድየለሽነት ስሜት መቋቋም እንድንችል ይረዱናል። (ሥራ 4:23, 31) በስብሰባዎቹ ላይ የሚቀርቡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች በእምነት እንድንጠነክርና እንድንጸና ያስችሉናል። (ሥራ 15:32፤ ሮም 1:11, 12) ለአምልኮ በምንሰበሰብበት ጊዜ የሚሰጠን ትምህርት እንዲሁም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን የምናገኘው ማበረታቻ እውነተኛ ደስታ እንዲሰማን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ‘ከመከራ ያሳርፈናል።’ (መዝ. 94:12, 13) የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ በምድር ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦችን ለማስተማር ሲባል ለሚዘጋጁት መንፈሳዊ ፕሮግራሞች በሙሉ አመራር ይሰጣል። በየሳምንቱ በስብሰባዎቻችን አማካኝነት ጠቃሚ ትምህርት እንድንማር ለተደረጉልን ዝግጅቶች ምንኛ አመስጋኞች ነን!

7, 8. (ሀ) የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚረዱህ እንዴት ነው?

7 ይሁንና በግላችን ከስብሰባ ከምናገኛቸው ጥቅሞች ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። የምንሰበሰብበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ለማምለክ ነው። (መዝሙር 95:6ን አንብብ።) ታላቁን አምላካችንን ማወደስ መቻላችን እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! (ቆላ. 3:16) በቲኦክራሲያዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ ለይሖዋ ሁልጊዜ አምልኮ ልናቀርብለት ይገባል። (ራእይ 4:11) እንግዲያው “አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል” እንዳንል ምክር መሰጠቱ ምንም አያስገርምም!—ዕብ. 10:25

8 ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ይሖዋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ እርምጃ እስከሚወስድበት ጊዜ ድረስ ጸንተን እንድንኖር እኛን ለመርዳት የተደረጉ ዝግጅቶች እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን? እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ሕይወታችን ውጥረት የበዛበት ቢሆንም እንኳ ስብሰባዎች ‘ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች’ መካከል እንደሚመደቡ በመገንዘብ አዘውትረን ለመገኘት ጥረት እናደርጋለን። (ፊልጵ. 1:10) ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካልገጠመን በስተቀር ከወንድሞቻችን ጋር ይሖዋን ለማምለክ የሚያስችለንን ይህን አጋጣሚ ምንም ነገር እንዲያሳጣን መፍቀድ አይኖርብንም።

 ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልጉ

9. የስብከቱ ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

9 በስብከቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረጋችንም ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እንድንራመድ ይረዳናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የስብከቱን ሥራ አስጀምሯል። (ማቴ. 28:19, 20) ከዚያን ጊዜ አንስቶ መላው የይሖዋ ድርጅት በዋነኛነት ትኩረቱን ያደረገው የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ተሞክሮዎች መላእክት ይህን ሥራችንን ከመደገፍም በተጨማሪ “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ወዳላቸው ሰዎች እየመሩን እንዳሉ በግልጽ ያሳያሉ። (ሥራ 13:48፤ ራእይ 14:6, 7) የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል የተቋቋመውና የተደራጀው ከምንም በላይ አስፈላጊ ለሆነው ለዚህ ሥራ ድጋፍ ለመስጠት ነው። አንተስ ለስብከቱም ሥራ ቅድሚያ እየሰጠህ ነው?

10. (ሀ) ለእውነት ያለንን ፍቅር መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተሞክሮውን ጠቅሰህ አብራራ። (ለ) አገልግሎት እንዳትዝል የረዳህ እንዴት ነው?

10 በአገልግሎት ቀናተኛ መሆናችን ለእውነት ያለንን ፍቅር ጠብቀን ለመኖር ያስችለናል። ለብዙ ዓመታት ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ ሆኖ ያገለገለው ሚቸል የተባለ ወንድም ምን አስተያየት እንደሰጠ ተመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “እውነትን ለሰዎች መናገር በጣም ያስደስተኛል። በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔት ላይ ስለወጣ አንድ አዲስ ርዕስ ሳስብ እያንዳንዱ እትም በውስጡ የያዘው ጥበብና ጥልቅ ማስተዋል እንዲሁም ሐሳቡ ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መቅረቡ እጅግ ያስገርመኛል። ሰዎች ምን ምላሽ እንደሚሰጡ እንዲሁም ፍላጎታቸውን እንዴት መቀስቀስ እንደምችል ለማየት ወደ  አገልግሎት መውጣት ያጓጓኛል። በአገልግሎት መካፈሌ ሚዛኔን እንድጠብቅ ይረዳኛል። ሌላውን ነገር ሁሉ ለአገልግሎት ከመደብኩት ጊዜ በፊት ወይም በኋላ ለማከናወን ጥረት አደርጋለሁ።” በተመሳሳይ እኛም ቅዱስ በሆነው አገልግሎታችን መጠመዳችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ጸንተን እንድንኖር ሊረዳን ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።

ከመንፈሳዊው ማዕድ ተቋደሱ

11. ይሖዋ የሚያቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ መመገብ ያለብን ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ እኛን ለማበርታት ሲል በጽሑፎች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል። አንድ ጽሑፍ ካነበብክ በኋላ ‘ለእኔ የሚያስፈልገኝ ትምህርት ይህ ነው! ይሖዋ ለእኔ ብሎ ያስጻፈው ያህል ነው!’ ያልክበት ጊዜ እንደሚኖር ጥርጥር የለውም። ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ይሖዋ በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት ያስተምረናል እንዲሁም ይመራናል። “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ” ሲል ተናግሯል። (መዝ. 32:8) የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ ሁሉ ለመመገብና በተማርነው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጥረት እናደርጋለን? እንዲህ ማድረጋችን አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች በመንፈሳዊ እንዳንጠወልግ ይልቁንም ፍሬ ማፍራታችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—መዝሙር 1:1-3ን፤ 35:28ን፤ 119:97ን አንብብ።

12. የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ አቅልለን እንዳንመለከት ምን ሊረዳን ይችላል?

12 ይህን ተስማሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ ማግኘት እንድንችል የሚከናወነውን ሥራ ማጤናችን ጠቃሚ ነው። የሚታተመውንም ሆነ በድረ ገጻችን ላይ የሚወጣውን እያንዳንዱን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምርምር ማድረግ፣ መጻፍ፣ ስህተቶችን ማረም፣ ሥዕላዊ መግለጫዎችን መጠቀምና መተርጎም ያስፈልጋል። የበላይ አካሉ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ይህን ሥራ በበላይነት የማካሄድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። የኅትመት ሥራውን የሚያካሂዱት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጽሑፎችን በተለያዩ አካባቢዎች ወዳሉ ጉባኤዎች ይልካሉ። ይህ ሁሉ ሥራ የሚከናወነው ለምንድን ነው? የይሖዋ ሕዝቦች በመንፈሳዊ በሚገባ እንዲመገቡ ነው። (ኢሳ. 65:13) በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት የምናገኘውን መንፈሳዊ ምግብ በሙሉ ለመመገብ ጥረት እናድርግ።—መዝ. 119:27

ድርጅቱ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ደግፉ

13, 14. በሰማይ ለይሖዋ ዝግጅት ድጋፍ የሚሰጡት እነማን ናቸው? እኛስ በምድር ላይ ተመሳሳይ ድጋፍ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

13 ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ ኢየሱስ በይሖዋ ላይ የሚያምፁትን ለማጥፋት ነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ሲጋልብ ታይቷል። (ራእይ 19:11-15) ኢየሱስን የሚከተሉ ታማኝ መላእክት እንዳሉ እንዲሁም ሰማያዊ ሽልማታቸውን የተቀበሉ ከምድር የተዋጁ ድል አድራጊ ቅቡዓን ከጎኑ እንደተሰለፉ ማወቁ ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ነው! (ራእይ 2:26, 27) ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች ድጋፍ በመስጠት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ይሆኑናል!

14 በተመሳሳይም እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ በምድር ላይ የሚገኙትና በአሁኑ ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ አመራር እየሰጡ ያሉት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች እያከናወኑት ያለውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ። (ዘካርያስ 8:23ን አንብብ።) ይሖዋ ላደረገልን ዝግጅቶች በግለሰብ ደረጃ ድጋፍ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጡን ወንድሞች በመገዛት ነው። (ዕብ. 13:7, 17) ይህ ደግሞ ከጉባኤያችን ይጀምራል። ስለ ሽማግሌዎች የምንናገረው ነገር ሌሎች እነሱንም ሆነ የኃላፊነት ቦታቸውን እንዲያከብሩ ያነሳሳል? ልጆቻችን እነዚህን ታማኝ ወንድሞች እንዲያከብሩና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር እንዲጠይቋቸው እናበረታታለን? በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ለሚካሄደው ሥራ መዋጮ በመስጠት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ስለምንችልበት መንገድ በቤተሰብ ደረጃ እንወያያለን? (ምሳሌ 3:9፤ 1 ቆሮ. 16:2፤ 2 ቆሮ. 8:12) የመንግሥት አዳራሹን በመንከባከቡ ሥራ የመካፈል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን? እንዲህ ያለ መከባበርና አንድነት ባለበት የይሖዋ መንፈስ በነፃነት ይፈሳል። ይህ መንፈስ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች እንዳንዝል ብርታት ይሰጠናል።—ኢሳ. 40:29-31

 ከምንሰብከው መልእክት ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሩ

15. ይሖዋ ካለው ታላቅ ዓላማ ጋር ተስማምተን ለመኖር የማያቋርጥ ፍልሚያ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

15 በመጨረሻም ለመጽናትና ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመዳችንን ለመቀጠል ምንጊዜም አኗኗራችን ከምንሰብከው መልእክት ጋር የሚስማማ መሆን አለበት፤ እንዲህ ለማድረግ ‘በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ መርምረን ማረጋገጥ’ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:10, 11) ፍጽምና የጎደለው ሥጋችን፣ ሰይጣንና ይህ ክፉ ዓለም ከሚያደርሱብን ጫና የተነሳ በሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብን ነገሮች ጋር ያለማቋረጥ እንታገላለን። ከተወደዳችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል አንዳንዶቻችሁ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ጠብቃችሁ ለመኖር በየዕለቱ ከፍተኛ ትግል ታደርጋላችሁ። ይህም በእሱ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ያደርጋችኋል። ተስፋ አትቁረጡ! ሕይወታችንን ከይሖዋ ዓላማ ጋር አስማምተን መምራታችን ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልናል፤ አምልኳችንም ከንቱ አይሆንም።—1 ቆሮ. 9:24-27

ሌሎች ሰዎች ግዙፍ የሆነው የይሖዋ ድርጅት አባል የመሆን አጋጣሚ እንዳላቸው መገንዘብ እንዲችሉ በትጋት እርዷቸው

16, 17. (ሀ) ከባድ ኃጢአት ብንፈጽም ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) የአን ምሳሌ እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?

16 ይሁንና ከባድ ኃጢአት ብንፈጽም ምን ማድረግ ይኖርብናል? ወዲያውኑ እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ። ጉዳዩን ለመሸሸግ መሞከር ችግሩን ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። ዳዊት ኃጢአቱን ለመደበቅ በሞከረ ጊዜ “ቀኑን ሙሉ ከመቃተቴ የተነሣ፣ . . . አጥንቶቼ ተበላሹ” በማለት እንደተናገረ አስታውስ። (መዝ. 32:3) አዎ፣ ኃጢአታችንን መደበቃችን ስሜታችን እንዲደቆስ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በመንፈሳዊ እንዝላለን፤ ኃጢአቱን “የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል።”—ምሳሌ 28:13

17 የአንን * ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አን በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ሳለች የዘወትር አቅኚ ሆና ታገለግል ነበር። ይሁንና ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር ጀመረች። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረባት። ሕሊናዋ ይወቅሳት ጀመር። “ደስታ ራቀኝ፤ ደግሞም በጭንቀት ተውጬ ነበር” በማለት ተናግራለች። በዚህ ጊዜ ምን አደረገች? አንድ ቀን በስብሰባ ላይ ያዕቆብ 5:14, 15 ሲብራራ ሰማች። አን እርዳታ እንደሚያስፈልጋት ስለተገነዘበች ወደ ሽማግሌዎች ሄደች። ያለፈውን ጊዜ መለስ ብላ ስታስብ እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ጥቅሶች መንፈሳዊ ፈውስ እንዳገኝ ይሖዋ ያዘዘልኝ መድኃኒቶች ናቸው። መድኃኒቱን መዋጥ ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ፈውስ ያስገኛል። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ያሉትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረጌ ጠቅሞኛል።” አን መንፈሷ ታድሶ በድጋሚ በንጹሕ ሕሊና ይሖዋን በቅንዓት ማገልገል ከጀመረች የተወሰኑ ዓመታት አልፈዋል።

18. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

18 በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ መኖርና አስደናቂ የሆነው የይሖዋ ድርጅት አባል መሆን እንዴት ያለ መብት ነው! ያገኘነውን መብት አቅልለን ላለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይልቁንም በቤተሰብ ደረጃ አዘውትረን ከጉባኤያችን ጋር ለአምልኮ ለመሰብሰብና በክልላችን የሚገኙ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በትጋት ለመፈለግ ጥረት እናድርግ፤ እንዲሁም በቋሚነት የምናገኛቸውን መንፈሳዊ ምግቦች በአድናቆት እንመልከት። በተጨማሪም ግንባር ቀደም ሆነው አመራር የሚሰጡንን ለመደገፍና ከምንሰብከው መልእክት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ጥረት እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል የምንራመድ ከመሆኑም ሌላ መልካም ነገር ለማድረግ ፈጽሞ አንታክትም!

^ စာပိုဒ်၊ 17 ስሟ ተቀይሯል።