በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ሜክሲኮ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ሜክሲኮ

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን ለማስፋት አኗኗራቸውን ቀላል ሲያደርጉ ማየት የሚያስደስት ነገር ነው። (ማቴ. 6:22) ምን ለውጦች አድርገዋል? ምን እንቅፋቶችስ ያጋጥሟቸዋል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በአሁኑ ጊዜ በሜክሲኮ እያገለገሉ ካሉት መካከል ጥቂቶቹ ምን እያደረጉ እንዳሉ እንመልከት።

“ለውጥ ማድረግ እንዳለብን ተረዳን”

ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡት ደስቲን እና ጄሰ የተጋቡት ጥር 2007 ነበር። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለረጅም ጊዜ ሲያልሙት የኖሩትን ነገር ይኸውም በነፋስ የሚንቀሳቀስ ጀልባ ገዝተው ዓመቱን ሙሉ በዚያ ላይ ለመኖር የነበራቸውን ምኞት ማሳካት ችለው ነበር። ጀልባቸው የታሰረችው በደን በተሸፈኑ ኮረብታዎችና በበረዶ በተሸፈኑ ተራራዎች በተከበበችው በዩናይትድ ስቴትስ የምትገኝ አስቶሪያ የተባለች ውብ የሆነች የኦሪገን ከተማ አቅራቢያ ነበር፤ ይህ ቦታ የሚገኘው ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጥቂት ርቀት ላይ ነው። ደስቲን “ወደየትኛውም አቅጣጫ ብትመለከቱ የአካባቢው ውበት ልባችሁን ያጠፋዋል!” በማለት ተናግሯል። ባልና ሚስቱ በይሖዋ ታምነው ቀላል ኑሮ እየኖሩ እንዳሉ ይሰማቸው ነበር። ‘የምንኖረው 7.9 ሜትር ርዝመት ባላት ጀልባ ላይ ሲሆን የምንሠራው የተወሰነ ሰዓት ነው። በውጭ አገር ቋንቋ የሚካሄድ ጉባኤ እንረዳለን፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ረዳት አቅኚ ሆነን እናገለግላለን’ ብለው ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሳቸውን እያታለሉ እንደሆነ ተገነዘቡ። ደስቲን እንዲህ ብሏል፦ “ጉባኤውን በመርዳት ፋንታ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋው ጀልባችንን በመጠገን ነበር። በሕይወታችን ውስጥ  በእርግጥ ይሖዋን ማስቀደም ከፈለግን ለውጥ ማድረግ እንዳለብን ተረዳን።”

ጄሰ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ከማግባቴ በፊት በሜክሲኮ እኖር የነበረ ሲሆን በእንግሊዝኛ ጉባኤ አገለግል ነበር። እዚያ ማገልገል ደስ ይለኝ ስለነበረ ወደዚያ የመመለስ ምኞት ነበረኝ።” ደስቲንና ጄሰ በውጭ አገር ለማገልገል ያላቸውን ምኞት ለማጠናከር ሲሉ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ፣ የደረሰ አዝመራ ወደሚገኝባቸው አገሮች ስለተዛወሩ ወንድሞችና እህቶች የሚገልጹ የሕይወት ታሪኮችን ማንበብ ጀመሩ። (ዮሐ. 4:35) “እኛም እንዲህ ያለ ደስታ ለማግኘት ፍላጎት አደረብን” ሲል ደስቲን ተናግሯል። በሜክሲኮ የሚኖሩ ጓደኞቻቸው እርዳታ የሚያስፈልገው አንድ አዲስ ቡድን እንደተቋቋመ ሲነግሯቸው ደስቲንና ጄሰ ወደዚያ ለመሄድ ወሰኑ። ሥራቸውን ከለቀቁና ጀልባቸውን ከሸጡ በኋላ ወደ ሜክሲኮ ተዛወሩ።

“እስከ ዛሬ ካገኘነው ነገር ሁሉ የላቀ ነው”

አሁንም ደስቲንና ጄሰ በፓስፊክ ውቅያኖስ አቅራቢያ በምትገኝ ቴኮማን በምትባል ከተማ ውስጥ መኖር የጀመሩ ቢሆንም ከተማዋ የምትገኘው ከአስቶሪያ በስተ ደቡብ 4,345 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ደስቲን እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “አሁን የምንኖረው ነፋሻማ አየርና የሚያማምሩ ተራሮች ባሉበት ቦታ ሳይሆን ኃይለኛ ሙቀት ባለባትና ለዓይን እስኪታክት ድረስ የሎሚ ዛፎች በሚታዩባት ከተማ ነው።” መጀመሪያ ላይ ሥራ ማግኘት አልቻሉም ነበር። ገንዘብ ስላለቀባቸው ከሳምንት እስከ ሳምንት በቀን ሁለት ጊዜ ሩዝና ቦሎቄ ለመብላት ተገደዱ። ጄሰ “የምንበላው ምግብ እየሰለቸን ሲመጣ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ማንጎ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ከረጢት ሙሉ ሎሚ ይሰጡን ጀመር!” ብላለች። ከጊዜ በኋላ፣ መቀመጫውን በታይዋን ያደረገ በኢንተርኔት አማካኝነት የቋንቋ ትምህርት የሚሰጥ አንድ ድርጅት ባልና ሚስቱን ቀጠራቸው። አሁን ከዚያ ሥራ የሚያገኙት ገቢ ዕለታዊ ወጪያቸውን በበቂ መጠን ይሸፍንላቸዋል።

ታዲያ ደስቲንና ጄሰ አኗኗራቸውን በመለወጣቸው ምን ይሰማቸዋል? እንዲህ ይላሉ፦ “ወደዚህ መዛወራችን እስከ ዛሬ ካገኘነው ነገር ሁሉ የላቀ ነው። ከይሖዋ ጋርም ሆነ እርስ በርሳችን ያለን ዝምድና ከምንገምተው በላይ እጅግ ተጠናክሯል። በየቀኑ ብዙ ነገሮችን አብረን እንሠራለን፤ ወደ መስክ አገልግሎት የምንሄደው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን እንዴት መርዳት እንደምንችል የምንወያየው፣ ለስብሰባዎች የምንዘጋጀው አንድ ላይ ነው። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያጋጥሙን ከነበሩት የኑሮ ጫናዎች ተገላግለናል።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ቀደም ሲል ሙሉ በሙሉ ያልተረዳነውን ነገር ይኸውም ‘[ይሖዋ] ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ’ የሚለውን በመዝሙር 34:8 ላይ የሚገኘውን የተስፋ ቃል እውነተኝነት አሁን በሚገባ መረዳት ችለናል።”

በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞችን እንዲህ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?

አብዛኞቹ በ20ዎቹና በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ፣ ያገቡና ያላገቡ ከ2,900 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አሁንም ድረስ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በጣም ወደሚያስፈልጉባቸው በሜክሲኮ የሚገኙ ክልሎች ሄደው ለማገልገል ወደዚያ ተዛውረዋል። እነዚህ ሁሉ ምሥክሮች ይህን ተፈታታኝ ሥራ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑት ለምንድን ነው? ከእነሱ መካከል የተወሰኑት ይህ ጥያቄ ሲቀርብላቸው  ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶችን ጠቅሰዋል። እነዚህ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ሌቲስያ እና ኤርሚሎ

ለይሖዋና ለሰዎች ያለንን ፍቅር ለመግለጽ። ሌቲስያ የተጠመቀችው በ18 ዓመቷ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ሕይወቴን ለይሖዋ ስወስን በሙሉ ልቤና በሙሉ ነፍሴ እሱን ማገልገል እንደሚጠይቅብኝ ተረድቼ ነበር። ስለዚህ ይሖዋን በሙሉ ልቤ እንደምወደው ለማሳየት አብዛኛውን ጊዜዬንና ጉልበቴን ለእሱ አገልግሎት የማዋል ፍላጎት አደረብኝ።” (ማር. 12:30) አሁን ከሌቲስያ ጋር ትዳር መሥርቶ የሚኖረው ኤርሚሎ ተጨማሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲዛወር በ20ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ይገኝ ነበር። እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንዲያረኩ መርዳት ለሰዎች ያለኝን ፍቅር ማሳየት የምችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ እንደሆነ ተገነዘብኩ።” (ማር. 12:31) ስለዚህ በባንክ እየሠራ በምቾት ይኖርባት የነበረችውን ሞንተሬ የተባለች የበለጸገች ከተማ ትቶ ወደ አንዲት አነስተኛ ከተማ ተዛወረ።

ኤስሊ

እውነተኛና ዘላቂ ደስታ ለማግኘት። ሌቲስያ ከተጠመቀች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተሞክሮ ካላት አቅኚ እህት ጋር ራቅ ብላ ወደምትገኝ አንዲት ከተማ በመሄድ ለአንድ ወር ያህል አብረው አገለገሉ። ሌቲስያ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ሁኔታው በጣም ገረመኝ። ሰዎቹ ለምናካፍላቸው የመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ መስጠታቸው በጣም አስደሰተኝ። በወሩ መጨረሻ ላይ ‘ሕይወቴን ልጠቀምበት የሚገባው በዚህ መንገድ ነው!’ ብዬ አሰብኩ።” በተመሳሳይም አሁን በ20ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ኤስሊ የምትባል ነጠላ እህት ይህን አገልግሎት እንድትወደው ያደረጋት በሌሎች ላይ የተመለከተችው ደስታ ነበር። ገና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለች የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ካገለገሉ ብዙ ቀናተኛ ምሥክሮች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ነበራት። እንዲህ ብላለች፦ “በእነዚያ ወንድሞችና እህቶች ፊት ላይ የሚነበበውን ደስታ ማየቴ እኔም የእነሱን ዓይነት ሕይወት እንድመኝ አድርጎኛል።” ብዙ እህቶች የኤስሊ ዓይነት ምላሽ ሰጥተዋል። እንዲያውም በሜክሲኮ ከ680 የሚበልጡ ነጠላ እህቶች የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ለወጣቶችም ሆነ ለአረጋውያን ግሩም ምሳሌ ናቸው!

ዓላማ ያለውና አርኪ ሕይወት ለመኖር። ኤስሊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንደጨረሰች ነፃ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ዕድል አገኘች። እኩዮቿ ያገኘችውን ነፃ የትምህርት ዕድል እንድትቀበልና እንደ ማንኛውም ሰው “የተለመደውን ሕይወት” እንድትመራ ይኸውም ዲግሪ እንድትይዝ፣ ተቀጥራ እንድትሠራ፣ መኪና እንድትገዛና እረፍት እየወሰደች አገር እንድትጎበኝ አበረታቷት። እሷ ግን የእነሱን ምክር አልተከተለችም። ኤስሊ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ክርስቲያን ጓደኞቼ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሲሆን ለመንፈሳዊ ግቦች ቅድሚያ መስጠት እንዳቆሙ ተመልክቻለሁ። እንዲሁም በዚህ ዓለም ጉዳዮች ይበልጥ እየተጠላለፉ በሄዱ መጠን በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ለተስፋ መቁረጥ ሲዳረጉ አስተውያለሁ። እኔ በበኩሌ ወጣትነቴን ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ልጠቀምበት ወሰንኩ።”

ራኬል እና ፊሊፕ

ኤስሊ አቅኚ ሆና በምታገለግልበት ጊዜ ራሷን ለመደገፍ የሚያስችሏትን አንዳንድ ተጨማሪ ኮርሶች ወሰደችና የመንግሥቱ  አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛወረች። ከዚህም በላይ የኦቶሚ እና የትላፐኔኮ ሕዝቦች የሚናገሯቸውን ቋንቋዎች ለመማር ብዙ ጥረት አደረገች። አሁን በገለልተኛ ክልሎች በመስበክ ያሳለፈቻቸውን ሦስት ዓመታት መለስ ብላ ስታስብ እንዲህ ትላለች፦ “የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገሌ እርካታ ያስገኘልኝ ከመሆኑም ሌላ ሕይወቴ እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው አስችሏል። ከሁሉ በላይ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና አጠናክሮልኛል።” ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡት በ30ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ፊሊፕ እና ራኬል የሚባሉ ባልና ሚስት ኤስሊ በተናገረችው ሐሳብ ይስማማሉ። “ዓለም በፍጥነት እየተለዋወጠ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው የተረጋጋ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚያዳምጡ በርካታ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ማገልገላችን ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ረድቶናል። አገልግሎቱ በጣም አስደሳች ነው!”

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

ቬሮኒካ

እርግጥ ነው፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገል የራሱ የሆኑ ፈታኝ ሁኔታዎች አሉት። ከእነዚህ ችግሮች አንዱ ራሳችሁን ለመደገፍ የሚያስችላችሁን የገቢ ምንጭ ማግኘት ነው። ከአካባቢው ሁኔታዎች ጋር ለመላመድ ፈቃደኛ መሆናችሁ በዚህ ረገድ ይረዳችኋል። የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ያላት ቬሮኒካ የምትባል አቅኚ እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “በአንድ ቦታ ሳገለግል በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡ ምግቦችን እያዘጋጀሁ እሸጥ ነበር። በሌላ ቦታ ደግሞ ልብስ በመሸጥና ፀጉር በማስተካከል እተዳደር ነበር። በአሁኑ ጊዜ ቤት የማጽዳት እንዲሁም በቅርቡ ልጅ የወለዱ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዴት የሐሳብ ግንኙነት እንደሚያደርጉ የማስተማር ሥራ በማከናወን ላይ እገኛለሁ።”

በተለይ የአካባቢው ተወላጅ የሆነ ሕዝብ በሚኖርበት ገለልተኛ ክልል በምትኖሩበት ጊዜ ከማታውቁት ባሕልና ልማድ ጋር መላመድ በጣም ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ፊሊፕና ራኬል በናዋትል ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ ሲያገለግሉ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ፊሊፕ “በመካከላችን ያለው የባሕል ልዩነት ከፍተኛ ነው” ሲል ተናግሯል። ታዲያ መላመድ እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው? “የናዋትል ሕዝቦች ባላቸው መልካም ጎን ላይ ትኩረት አደረግን። በቤተሰባቸው መካከል የጠበቀ ትስስር ያለ ከመሆኑም ሌላ እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት በቅንነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ደግሞም ለጋስ ናቸው።” ራኬልም እንዲህ በማለት አክላ ተናግራለች፦ “በሕዝቡ መካከል በመኖርና የክልሉ ተወላጅ ከሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን በማገልገል ብዙ ነገር ተምረናል።”

ራሳችሁን ማዘጋጀት የምትችሉበት መንገድ

እርዳታ ወደሚያስፈልግባቸው ገለልተኛ ክልሎች ሄዳችሁ ማገልገል የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁን ለማዘጋጀት አሁን ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ይላሉ፦ ተዛውራችሁ ከመሄዳችሁ በፊት ኑሯችሁን ማቅለል መጀመርና ባላችሁ ነገር መርካትን መማር ያስፈልጋችኋል። (ፊልጵ. 4:11, 12) ሌላስ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ሌቲስያ እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች፦ “በአንድ ቦታ ረዘም ያለ ጊዜ እንድቆይ የሚያስገድዱኝን የሥራ ዓይነቶች ከመያዝ እቆጠብ ነበር። በፈለግኩበት ጊዜ ወደተፈለገው ቦታ ለመዛወር በሚያስችል ሁኔታ ለመኖር ጥረት አደርጋለሁ።” ኤርሚሎ “ምግብ መሥራት፣ ልብስ ማጠብና መተኮስ ተማርኩ” ሲል ተናግሯል። ቬሮኒካ እንዲህ ብላለች፦ “ከወላጆቼ እንዲሁም ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር በምኖርበት ጊዜ ቤት አጸዳ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ገንቢ ምግቦችን አዘጋጅ ነበር። በተጨማሪም ገንዘብ መቆጠብ ተምሬያለሁ።”

አሚሊያ እና ሊቫይ

ከተጋቡ ስምንት ዓመት የሆናቸው ሊቫይ እና አሚሊያ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሜክሲኮ ሄደው ለማገልገል ሲዘጋጁ ጸሎት እንዴት እንደረዳቸው ተናግረዋል። ሊቫይ እንዲህ ብሏል፦ “ለአንድ ዓመት ያህል በውጭ አገር ለማገልገል ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልገን አሰላንና ይህን ገንዘብ ሠርተን እንድናገኝ ይሖዋ እንዲረዳን በጸሎት ጠየቅነው።” በጥቂት ወራት ውስጥ በጸሎታቸው ላይ የጠቀሱትን ያህል ገንዘብ ማጠራቀም ስለቻሉ ዛሬ ነገ ሳይሉ ወደ ሜክሲኮ ሄዱ። ሊቫይ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ጠቅሰን ያቀረብነውን ጸሎት ስለመለሰልን እኛ ደግሞ የበኩላችንን ማድረግ ነበረብን።” አሚሊያ እንዲህ በማለት አክላ ተናግራለች፦ “ለአንድ ዓመት ብቻ ለመቆየት አስበን የነበረ ቢሆንም አሁን ሰባት ዓመት ሆኖናል፤ ደግሞም የመመለስ ሐሳብ የለንም! እዚህ መኖራችን የይሖዋን እርዳታ በቀጥታ እንድናገኝ አስችሎናል። በየዕለቱ የእሱን ደግነት በተግባር እናያለን።”

አዳም እና ጄኒፈር

ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሜክሲኮ ሄደው እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ባሉበት መስክ በማገልገል ላይ የሚገኙት አዳም እና ጄኒፈር የተባሉ ባልና ሚስትም ጸሎት በእጅጉ እንደረዳቸው ገልጸዋል። እንዲህ በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ እስኪመቻቹ ድረስ አትጠብቁ። ወደ ውጭ አገር ሄዳችሁ ለማገልገል ያላችሁን ምኞት ጠቅሳችሁ ጸልዩ፤ ከዚያም ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ። ኑሯችሁን ቀላል አድርጉ፤ ማገልገል በምትፈልጉበት አገር ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ተጻጻፉ፤ እንዲሁም ወጪያችሁን ካሰላችሁ በኋላ ወዳሰባችሁት አገር ሂዱ!” * እንዲህ ካደረጋችሁ ሕይወታችሁ አስደሳች ይሆናል፤ በመንፈሳዊም ትባረካላችሁ።

^ စာပိုဒ်၊ 21 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በነሐሴ 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ የወጣውን “‘ወደ መቄዶንያ መሻገር’ ትችላለህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።