በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ መጠጊያችን ነው

ይሖዋ መጠጊያችን ነው

“እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መጠጊያችን ሆንህልን።”—መዝ. 90:1

1, 2. የአምላክ አገልጋዮች ይህን ሥርዓት በተመለከተ ያላቸው ስሜት ምንድን ነው? መጠጊያ ወይም ቤት አላቸው ሊባል የሚችለውስ ከምን አንጻር ነው?

 በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ስትኖር በቤትህ ያለህ ያህል የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት ይሰማሃል? እንዲህ ዓይነት ስሜት የማይሰማህ ከሆነ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ያላቸው ዓይነት ስሜት አለህ ማለት ነው። ባለፉት የታሪክ ዘመናት፣ ይሖዋን አጥብቀው የሚወዱ ሰዎች በሙሉ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሲኖሩ ራሳቸውን እንደ እንግዳ ወይም መጻተኛ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በከነዓን ምድር ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ ሲኖሩ “እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን በይፋ [ተናግረዋል]።”—ዕብ. 11:13

2 በተመሳሳይም “የሰማይ ዜጎች” የሆኑት የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሲኖሩ ራሳቸውን እንደ “መጻተኞችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች” አድርገው ይቆጥራሉ። (ፊልጵ. 3:20፤ 1 ጴጥ. 2:11) የክርስቶስ ‘ሌሎች በጎችም’ ቢሆኑ ‘ኢየሱስ የዓለም ክፍል እንዳልነበረ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።’ (ዮሐ. 10:16፤ 17:16) ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች መጠጊያ ወይም ቤት የላቸውም ማለት አይደለም። እንዲያውም ከየትኛውም መኖሪያ ይበልጥ አስተማማኝ ጥበቃ የምናገኝበትና ፍቅር የሰፈነበት በእምነት ዓይን የሚታይ ቤት አለን። ሙሴ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መጠጊያችን ሆንህልን” በማለት ጽፏል። * (መዝ. 90:1) ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩት ታማኝ አገልጋዮቹ “መጠጊያ” ወይም መኖሪያ የሆነው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜስ በስሙ ለተጠሩ ሕዝቦቹ “መጠጊያ” የሆነው እንዴት ነው? ደግሞስ ወደፊት ብቸኛው አስተማማኝ መጠጊያ የሚሆነው እንዴት ነው?

ይሖዋ በጥንት ጊዜ ለነበሩት አገልጋዮቹ “መጠጊያ” ሆኗል

3. በመዝሙር 90:1 ላይ ምን ርዕሰ ጉዳይ፣ ምስልና ተመሳሳይነት ተጠቅሶ እናገኛለን?

3 መዝሙር 90:1 ላይ ያለው ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኙት በርካታ ዘይቤያዊ አነጋገሮች ርዕሰ ጉዳይና ለማነጻጸር  የገባ ምስል ያለው ከመሆኑም ሌላ በሁለት ነገሮች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ይገልጻል። ርዕሰ ጉዳዩ ይሖዋ ነው። ምስሉ መጠጊያ ወይም የመኖሪያ ቦታ ነው። ይሖዋ ከመኖሪያ ቦታ ጋር በብዙ መንገድ ይመሳሰላል። ለምሳሌ ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት ነው ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (1 ዮሐ. 4:8) በተጨማሪም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ “ያለ ሥጋት” እንዲኖሩ የሚያደርግ የሰላም አምላክ ነው። (መዝ. 4:8) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ከነበሩት ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የነበረውን ግንኙነት እስቲ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

4, 5. አምላክ ለአብርሃም “መጠጊያ” የሆነው እንዴት ነው?

4 በወቅቱ አብራም ተብሎ ይጠራ የነበረው አብርሃም፣ ይሖዋ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ” ባለው ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በዚህ ጊዜ አብርሃም ሁኔታው አስጨንቆት ከነበረ ይሖዋ ቀጥሎ የተናገራቸውን ቃላት ሲሰማ ተበረታትቶ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፦ “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ . . . የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህን እረግማለሁ።”—ዘፍ. 12:1-3

5 ይሖዋ እነዚህን ቃላት በመናገር ለአብርሃምና ለዘሮቹ አስተማማኝ መኖሪያ እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘፍ. 26:1-6) ደግሞም የገባውን ቃል ፈጽሟል። ለምሳሌ ያህል የግብፁ ፈርዖንና የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ ሣራን ለመውሰድና አብርሃምን ለመግደል በሞከሩ ጊዜ ጣልቃ ገብቶ አስጥሏቸዋል። ይስሐቅንና ርብቃንም ተመሳሳይ የሆነ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። (ዘፍ. 12:14-20፤ 20:1-14፤ 26:6-11) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ] ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሠጸ፤ ‘የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።’”—መዝ. 105:14, 15

“አልተውህም”

6. ይስሐቅ ያዕቆብን ምን አለው? በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል?

6 ከእነዚህ ነቢያት መካከል የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ይገኝበታል። ያዕቆብ የሚያገባበት ዕድሜ ላይ በደረሰ ጊዜ አባቱ ይስሐቅ እንዲህ አለው፦ “ምንም ቢሆን ከነዓናዊት ሴት አታግባ። አሁኑኑ ተነሥተህ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ እዚያም ከአጎትህ ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዲቷን አግባ።” (ዘፍ. 28:1, 2) ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ እንዳለው አደረገ። በከነዓን ምድር ከሚኖረው ቤተሰቡ ተለይቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ ካራን ተጓዘ፤ ወደዚያ የተጓዘው ብቻውን ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍ. 28:10) ምናልባትም ‘እዚያ ምን ያህል እቆይ እሆን? አጎቴ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ አምላክን የምትፈራ ሚስት ይድርልኝ ይሆን?’ ብሎ አስቦ ይሆናል። ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ተጨንቆ ከነበረ ከቤርሳቤህ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወዳለችው ሎዛ የተባለች ስፍራ ሲደርስ ተበረታትቶ መሆን አለበት። በሎዛ ያጋጠመው ነገር ምን ነበር?

7. አምላክ በሕልም ተገልጦ ያዕቆብን ያበረታታው እንዴት ነው?

 7 በሎዛ ይሖዋ ለያዕቆብ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።” (ዘፍ. 28:15) አሳቢነት የተሞላባቸው እነዚህ ቃላት ያዕቆብን ምንኛ አበረታተውትና አጽናንተውት ይሆን! ከዚያ በኋላ ያዕቆብ አምላክ የገባውን ቃል ሲፈጽም ለማየት በመጓጓት በፍጥነት ወደፊት ሲገሰግስ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ! አንተም ምናልባት በሌላ አገር ለማገልገል መኖሪያህን ለቀህ ሄደህ ከሆነ ያዕቆብ የተሰማውን ስሜት ትረዳ ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ተንከባክቦህ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

8, 9. ይሖዋ ለያዕቆብ “መጠጊያ” የሆነለት በምን መንገዶች ነው? እኛስ ከዚህ ምን መማር እንችላለን?

8 ያዕቆብ ካራን ሲደርስ አጎቱ ላባ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረገለት ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ልያንና ራሔልን ዳረለት። ይሁንና ውሎ አድሮ ላባ የያዕቆብን ደሞዝ አሥር ጊዜ በመለዋወጥ ጉልበቱን አላግባብ ለመበዝበዝ ሞክሯል። (ዘፍ. 31:41, 42) ያም ሆኖ ያዕቆብ ይሖዋ እሱን መንከባከቡን እንደማይተው በመተማመን የደረሰበትን ግፍ ችሎ ኖሯል፤ ደግሞም ይሖዋ ተንከባክቦታል። አምላክ ወደ ከነዓን ምድር እንዲመለስ በነገረው ጊዜ ያዕቆብ “የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት” ሆኖ ነበር። (ዘፍ. 30:43) ያዕቆብ ይሖዋ ያደረገለትን ነገር በእጅጉ በማድነቅ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ።”—ዘፍ. 32:10

9 ሙሴ በጉዳዩ ላይ በማሰላሰል “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መጠጊያችን ሆንህልን” ሲል ያቀረበው ጸሎት ምንኛ እውነት ነው! (መዝ. 90:1) ዛሬም ቢሆን የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት እየተመለከትን ነው፤ ይሖዋ ‘ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ ስለማይለዋወጥ’ ለታማኝ አገልጋዮቹ ፍቅር የሰፈነበት አስተማማኝ መኖሪያ ሆኖላቸዋል። (ያዕ. 1:17) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በዛሬው ጊዜም ይሖዋ “መጠጊያችን” ነው

10. ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ለአገልጋዮቹ አስተማማኝ መጠጊያ ይሆናል ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

10 በዓለም ዙሪያ በሚንቀሳቀስ አንድ ወንጀለኛ ድርጅት ላይ የምሥክርነት ቃል እንድትሰጥ ፍርድ ቤት ቀርበሃል እንበል። የድርጅቱ መሪ በጣም ብልጥ፣ ኃይለኛና ምንም ዓይነት ርኅራኄ የሌለው ውሸታም ብሎም ነፍሰ ገዳይ ነው። የምሥክርነት ቃልህን ከሰጠህ በኋላ ፍርድ ቤቱን ለቀህ ስትወጣ የደህንነት ስሜት ይሰማሃል? በፍጹም! ይልቁንም ጥበቃ እንዲደረግልህ ትጠይቃለህ። ይህ ምሳሌ በድፍረት ለይሖዋ የሚመሠክሩትን እንዲሁም ጨካኝና የአምላክ ቀንደኛ ባላጋራ የሆነውን ሰይጣንን ያላንዳች ፍርሃት የሚያጋልጡትን የይሖዋ አገልጋዮች ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል! (ራእይ 12:17ን አንብብ።) ይሁንና ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች አፍ ማዘጋት ችሏል? በፍጹም! እንዲያውም በመንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ እንገኛለን፤ ይህ ደግሞ ይሖዋ በተለይ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች “መጠጊያ” ወይም መኖሪያ እንደሆነልን የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው። (ኢሳይያስ 54:14, 17ን አንብብ።) ይሁንና ሰይጣን አታሎ ከመኖሪያችን እንዲያስወጣን ከፈቀድንለት ይሖዋ አስተማማኝ መጠጊያ ሊሆንልን አይችልም።

የአምላክ መላእክት አገልጋዮቹን ይረዳሉ እንዲሁም ይጠብቃሉ

11. ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

11 ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ የምናገኘውን ሌላ ትምህርት ደግሞ እስቲ እንመልከት። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች በከነዓን ምድር ይኖሩ የነበረ ቢሆንም በምድሪቱ ላይ ከነበሩት ሰዎች የተለዩ ነበሩ፤ ደግሞም መጥፎና ብልሹ የሆነውን ሥነ ምግባራቸውን ይጠሉ ነበር። (ዘፍ. 27:46) በዝርዝር በሰፈረ ሕግና ደንብ ሳይሆን በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመሩ ሰዎች ነበሩ። ስለ ይሖዋና ስለ ባሕርያቱ የነበራቸው እውቀት ለእነሱ በቂ ነበር። ይሖዋ መኖሪያ ሆኖላቸው ስለነበር የሚችሉትን ያህል ወደ ዓለም ለመቅረብ አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ  በተቻለ መጠን ከዓለም ርቀው ለመኖር ጥረት አድርገዋል። ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! በጓደኛም ሆነ በመዝናኛ ምርጫ ረገድ እነዚህን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለመምሰል ጥረት ታደርጋለህ? የሚያሳዝነው ነገር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንዶች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሰይጣን ዓለም ተመችቷቸው እየኖሩ ያሉ ይመስላሉ። በመጠኑም ቢሆን እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ይህ ዓለም የሰይጣን መሆኑን አትዘንጋ። ደግሞም የሰይጣንን ርኅራኄ የጎደለው የራስ ወዳድነት መንፈስ ያንጸባርቃል።—2 ቆሮ. 4:4፤ ኤፌ. 2:1, 2

12. (ሀ) ይሖዋ ለመንፈሳዊ ቤተሰቦቹ ምን ዝግጅቶች አድርጓል? (ለ) ስለ እነዚህ ዝግጅቶች ምን ይሰማሃል?

12 የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች ለመቋቋም ይሖዋ ለእምነት ቤተሰቦቹ ይኸውም እሱን መኖሪያቸው ላደረጉ ሰዎች በሚያዘጋጃቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል። ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ የቤተሰብ አምልኮ እንዲሁም ‘የወንዶች ስጦታዎች’ ማለትም በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙን ፈታኝ ሁኔታዎች ጋር በምንታገልበት ጊዜ የሚያጽናኑንና የሚደግፉን በአምላክ የተሾሙ እረኞች ይገኙበታል። (ኤፌ. 4:8-12) ለበርካታ ዓመታት የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ “[በአምላክ ሕዝብ] መካከል ስሆን ቤቴ ውስጥ ከቤተሰቤ ጋር እንዳለሁ አልፎ ተርፎም በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንደሆንኩ ይሰማኛል” በማለት ጽፏል። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል?

13. ከዕብራውያን 11:13 ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

13 ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ልንኮርጀው የሚገባው ሌላው ግሩም ባሕርይ ደግሞ በዙሪያቸው ከነበሩት ሰዎች የተለዩ ሆነው ለመኖር ፈቃደኞች መሆናቸው ነው።  አንቀጽ 1 ላይ እንደተመለከትነው “በምድሩም ላይ እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን በይፋ [ተናግረዋል]።” (ዕብ. 11:13) በዓለም ካሉት ሰዎች የተለየህ ሆነህ ለመኖር ቆርጠሃል? እርግጥ ነው፣ እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ሆኖም በአምላክ እርዳታና በእምነት ባልንጀሮችህ ድጋፍ ይህን ማድረግ ትችላለህ። አንተ ብቻ ሳትሆን ይሖዋን ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ እንዲህ ያለ ትግል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስታውስ! (ኤፌ. 6:12) ይሁንና በይሖዋ የምንታመንና እሱን መጠጊያችን የምናደርገው ከሆነ በዚህ ትግል አሸናፊዎች መሆን እንችላለን።

14. የይሖዋ አገልጋዮች የትኛዋን “ከተማ” ይጠባበቁ ነበር?

14 በተጨማሪም ዓይንህ ሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ አብርሃም የተወውን ምሳሌ መከተልህ በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮ. 4:18) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አብርሃም “አምላክ የገነባትንና የሠራትን እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 11:10) ይህች “ከተማ” መሲሐዊውን መንግሥት ታመለክታለች። በእርግጥም አብርሃም ይህችን “ከተማ” መጠባበቅ አስፈልጎት ነበር። በአንድ በኩል ሲታይ እኛ ይህችን ከተማ እየተጠባበቅን አይደለም ሊባል ይችላል።  ምክንያቱም ይህ መንግሥት አሁን በሰማይ እየገዛ ነው። በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ ውስጥ መላዋን ምድር እንደሚቆጣጠር በርካታ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ይህ መንግሥት ለአንተ እውን ነው? ስለ ሕይወትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ስላለው ዓለም ባለህ አመለካከት ላይ እንዲሁም ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ በጎ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?—2 ጴጥሮስ 3:11, 12ን አንብብ።

መጨረሻው በቀረበ መጠን ይሖዋ “መጠጊያችን” ይሆናል

15. በዚህ ዓለም የሚታመኑ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል?

15 የሰይጣን ዓለም መጨረሻው እየቀረበ ሲሄድ ‘የምጥ ጣሩ’ የዚያኑ ያህል እየከፋ ይሄዳል። (ማቴ. 24:7, 8) በታላቁ መከራ ወቅት ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱ ጥርጥር የለውም። የመሠረተ ልማት አውታሮች ይፈራርሳሉ፤ ሰዎችም ቢሆኑ ለሕይወታቸው መስጋታቸው አይቀርም። (ዕን. 3:16, 17) የሚያደርጉት ጠፍቷቸው በምሳሌያዊ ሁኔታ “በዋሻዎች ውስጥና በተራራ ዐለቶች ውስጥ” መሸሸጊያ ይሻሉ። (ራእይ 6:15-17) ይሁንና ቃል በቃል በምድር ውስጥ ያሉ ዋሻዎችም ሆኑ እንደ ተራራ ያሉ የፖለቲካና የንግድ ድርጅቶች ጥበቃ ሊያስገኙላቸው አይችሉም።

16. ለጉባኤ ስብሰባዎች ምን አመለካከት አለህ? ለምንስ?

16 ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦች በዚያን ጊዜም ቢሆን ‘መጠጊያቸው’ በሆነው በይሖዋ አምላክ ጥበቃ ያገኛሉ። እንደ ነቢዩ ዕንባቆም ‘በእግዚአብሔር ደስ ይላቸዋል፤ በድነታቸው አምላክ ሐሤት ያደርጋሉ።’ (ዕን. 3:18) በዚያ ቀውጢ የሆነ ወቅት ይሖዋ “መጠጊያ” የሚሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይህ ጊዜ የሚያሳየን ነገር ይሆናል። ይሁንና ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ ‘እጅግ ብዙ ሕዝብም’ በተደራጀ ሁኔታ በመንቀሳቀስ የሚሰጣቸውን መለኮታዊ መመሪያ በንቃት መጠባበቃቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 7:9፤ ዘፀአት 13:18ን አንብብ።) መመሪያው የሚተላለፈው ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ ምናልባትም በጉባኤ አማካኝነት ሊሆን ይችላል። በዓለም ዙሪያ ያሉት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጉባኤዎች በኢሳይያስ 26:20 ላይ በትንቢት ከተነገረው ጥበቃ የሚገኝበት “ቤት” ጋር ዝምድና ያላቸው ይመስላሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) የጉባኤ ስብሰባዎችን ከፍ አድርገህ ትመለከታለህ? ይሖዋ በጉባኤ አማካኝነት የሚሰጠውን መመሪያ ወዲያውኑ ተግባራዊ ታደርጋለህ?—ዕብ. 13:17

17. ይሖዋ በሞት ላንቀላፉት ታማኝ አገልጋዮቹም እንኳ “መጠጊያ” የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

17 ይሖዋ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ በሞት ለሚያንቀላፉ አገልጋዮቹም እንኳ አስተማማኝ “መጠጊያ” ይሆንላቸዋል። እንዴት? ይሖዋ የጥንት ታማኝ አገልጋዮቹ ከሞቱ ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ ሙሴን “እኔ . . . የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” ብሎት ነበር። (ዘፀ. 3:6) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ከጠቀሰ በኋላ “እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ምክንያቱም በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 20:38) አዎ፣ ይሖዋ ለእሱ ታማኝ ሆነው የሞቱ አገልጋዮቹ በእሱ ፊት በሕይወት ያሉ ያህል ናቸው፤ ከሞት እንደሚነሱ የተረጋገጠ ነው።—መክ. 7:1

18. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ልዩ በሆነ መንገድ “መጠጊያ” የሚሆነው እንዴት ነው?

18 ከፊታችን በሚጠብቀን አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋ በሌላም መንገድ ለሕዝቡ “መጠጊያ” ይሆናል። ራእይ 21:3 “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል” ይላል። መጀመሪያ ላይ ይሖዋ በምድር ላይ ካሉት ተገዢዎቹ ጋር የሚኖረው ወኪሉ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ነው። በሺህ ዓመቱ ማብቂያ ላይ ኢየሱስ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለአባቱ ያስረክባል። (1 ቆሮ. 15:28) ከዚያ በኋላ ፍጹም የሆኑት የሰው ልጆች የኢየሱስ አማላጅነት አያስፈልጋቸውም፤ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ይሆናል። ከፊታችን እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ይጠብቀናል! እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ይሖዋን “መጠጊያችን” ወይም መኖሪያችን በማድረግ የጥንቶቹን ታማኝ አገልጋዮች ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናድርግ።

^ စာပိုဒ်၊ 2 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን መዝሙር 90:1ን “ጌታችን ሆይ፣ በትውልዶች ሁሉ አንተ ቤታችን ሆነሃል” በማለት ተርጉሞታል።