በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበቃ ከምታገኙበት ከይሖዋ ሸለቆ አትውጡ

ጥበቃ ከምታገኙበት ከይሖዋ ሸለቆ አትውጡ

“[“ይሖዋም፣” NW] በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል።”—ዘካ. 14:3

1, 2. በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት የጦርነት ዳመና እያንዣበበ ነው? የይሖዋ አገልጋዮች በዚያ ወቅት ምን ማድረግ አያስፈልጋቸውም?

ጥቅምት 30, 1938 በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቲያትሮች ላይ ተመሥርቶ የሚቀርብ ተወዳጅ የሬዲዮ ፕሮግራም ያዳምጡ ነበር። በዚያ ምሽት ይተላለፍ የነበረው ፕሮግራም የዓለማት ጦርነት በተባለው ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ ዜና አንባቢ ሆነው የሚተውኑት ተዋናዮች፣ ከማርስ ወራሪ ኃይሎች እንደመጡና መላዋን ምድር ሊያጠፏት እንደሆነ የሚገልጽ ዜና አቀረቡ። ፕሮግራሙ በቲያትር ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስቀድሞ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ብዙ አድማጮች ጥቃቱ የእውነት ስለመሰላቸው በፍርሃት ተሸበሩ። እንዲያውም ምናብ የፈጠራቸው ከሌላ ዓለም የመጡ ወራሪዎች ከሚሰነዝሩት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል አንዳንድ እርምጃዎችን የወሰዱም ነበሩ።

2 በዛሬው ጊዜ ግን በልብ ወለድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን እውነተኛ የጦርነት ዳመና እያንዣበበ ነው። ይሁንና ሰዎች ጦርነቱ እየተቃረበ መሆኑን አላስተዋሉም። ይህ ጦርነት እንደሚመጣ ያወቅነው በሳይንሳዊ ልብ ወለድ ላይ ተመሥርተን ሳይሆን አምላክ በመንፈሱ መሪነት ባስጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ ስለተናገረ ነው። አርማጌዶን ተብሎ በሚጠራው በዚህ ጦርነት አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት ያጠፋዋል። (ራእይ 16:14-16) በዚህ ጦርነት ወቅት በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ከሌላ ፕላኔት ይመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ ፍጥረታት ከሚሰነዝሩት ጥቃት ራሳቸውን መከላከል አያስፈልጋቸውም። ያም ቢሆን በዚያ ወቅት በሚፈጸሙት አስደናቂ ክንውኖችና የአምላክ ኃይል በሚገለጥባቸው አስፈሪ ሁኔታዎች እጅግ መደመማቸው አይቀርም።

3. የትኛውን ትንቢት እንመረምራለን? ትንቢቱ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

3 በዘካርያስ ምዕራፍ 14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ስለ አርማጌዶን ጦርነት ይነግረናል። ይህ ትንቢት የተጻፈው ከ2,500 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም ሕይወታችንን የሚነካ ሐሳብ ይዟል። (ሮም 15:4) በዚህ ትንቢት ላይ  የሚገኘው አብዛኛው ሐሳብ በ1914 መሲሐዊው መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመ ወዲህ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ ስለሚኖራቸው ሁኔታዎች እንዲሁም በቅርቡ ስለሚፈጸሙ አስደናቂ ክንውኖች የሚያወሳ ነው። በዚህ ትንቢት ውስጥ ጎላ ብለው ከሚታዩት ገጽታዎች መካከል የአንድ “ታላቅ ሸለቆ” መፈጠርና “የሕይወት ውሃ” መፍለቅ ይገኙበታል። (ዘካ. 14:4, 8) ይህ ሸለቆ ለይሖዋ አምላኪዎች ጥበቃ በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም የሕይወት ውሃ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታችን ይህን ውሃ የመጠጣትን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ብቻ ሳይሆን ይህን የማድረግ ጉጉት እንዲያድርብንም ያደርገናል። በእርግጥም ይህን ትንቢት ትኩረት ሰጥተን መመርመራችን ጠቃሚ ነው።—2 ጴጥ. 1:19, 20

‘የይሖዋ ቀን’ ጀመረ

4. (ሀ) ‘የይሖዋ ቀን’ የጀመረው መቼ ነው? (ለ) የይሖዋ ቀን በ1914 ከመጀመሩ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት የይሖዋ አምላኪዎች ምን እያወጁ ነበር? የዓለም መሪዎችስ ምን ምላሽ ሰጡ?

4 ዘካርያስ ምዕራፍ 14 መጀመሪያ ላይ ስለ ‘ይሖዋ ቀን’ የሚናገር ሐሳብ እናገኛለን። (ዘካርያስ 14:1, 2ን አንብብ።) ይህ ቀን ምን ያመለክታል? ‘የጌታን ቀን’ የሚያመለክት ሲሆን የጀመረውም “የዓለም መንግሥት የጌታችንና የመሲሑ መንግሥት” በሆነበት ጊዜ ነው። (ራእይ 1:10፤ 11:15) በሌላ አባባል ይህ ቀን የጀመረው መሲሐዊው መንግሥት በሰማይ በተቋቋመበት ጊዜ ይኸውም በ1914 ነው። ይህ ከመሆኑ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት የይሖዋ አምላኪዎች “የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 እንደሚያበቁና ታይቶ የማይታወቅ የመከራ ጊዜ በዚህ ወቅት እንደሚጀምር ሲያውጁ ነበር። (ሉቃስ 21:24) ታዲያ ብሔራት ምን ምላሽ ሰጡ? ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መሪዎች ይህን ወቅታዊ ማስጠንቀቂያ ከመስማት ይልቅ መልእክቱን በሚያውጁት በመንፈስ የተቀቡ ቀናተኛ ወንጌላውያን ላይ ማፌዝና እነሱን ማሳደድ ጀመሩ። የዓለም መሪዎች በእነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ወንጌላውያን ላይ ሲያፌዙ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ላይ ያፌዙ ያህል ነው፤ ምክንያቱም የመንግሥቱ አምባሳደሮች የሚወክሉት ‘ሰማያዊቱን ኢየሩሳሌም’ ይኸውም መሲሐዊውን መንግሥት ከመሆኑም ሌላ የዚህ መንግሥት ወራሾች ናቸው።—ዕብ. 12:22, 28

5, 6. (ሀ) በትንቢት በተነገረው መሠረት ብሔራት ‘በከተማዪቱ’ እና ‘በዜጎቿ’ ላይ ምን እርምጃ ወስደዋል? (ለ) “የሚቀረው ሕዝብ” የተባሉት እነማን ናቸው?

5 ዘካርያስ፣ ብሔራት ምን እርምጃ እንደሚወስዱ ትንቢት ሲናገር “ከተማዪቱ [ኢየሩሳሌም] ትያዛለች” ብሏል። “ከተማዪቱ” ለአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ተምሳሌት ናት። ይህች ከተማ በምድር ላይ የምትወከለው ደግሞ ‘በዜጎቿ’ ማለትም በቅቡዓን ቀሪዎች ነው። (ፊልጵ. 3:20) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ ሥራውን በበላይነት ይከታተሉ የነበሩ ወንድሞች ‘ተይዘው’ በአትላንታ፣ ጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ ወኅኒ ቤት ታሰሩ። “ቤቶች ይበዘበዛሉ” የሚለው ትንቢት ደግሞ በእነዚህና በሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ላይ የተፈጸመውን ከፍተኛ ግፍና ጭካኔ ያመለክታል። በእርግጥም ወራሪዎቹ የእነዚህን ቅቡዓን ቀሪዎች ጽሑፎች በማገድና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው እንዳይሠሩ በመከልከል ቅቡዓኑ የሚያከናውኑትን ሥራ ለማስቆም ሞክረዋል፤ በዚህ መንገድ ሀብታቸውን በዝብዘዋል።

6 የአምላክ ሕዝቦች ከወራሪዎቻቸው በቁጥር እጅግ የሚያንሱ ከመሆኑም ሌላ ስማቸው ጎድፎ እንዲሁም ተቃውሞና ስደት ደርሶባቸው ነበር፤ ያም ሆኖ እውነተኛው አምልኮ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። በከተማይቱ ውስጥ ‘የሚቀር ሕዝብ’ እንደሚኖር ተነግሮ ነበር፤ በሌላ አባባል ‘ከከተማይቱ ለመወሰድ’ ወይም ለመውጣት ፈቃደኛ ባለመሆን በታማኝነት የጸኑ ቅቡዓን ቀሪዎች ነበሩ።

7. የይሖዋ ቅቡዓን ምሥክሮች ታማኝነት በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

7 በዘካርያስ ትንቢት ፍፃሜ መሠረት ብሔራት በአምላክ አገልጋዮች ላይ ስደት ያደረሱት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብቻ ነው? አይደለም። ብሔራት በቅቡዓን ቀሪዎች እንዲሁም ምድራዊ ተስፋ ባላቸው ታማኝ አጋሮቻቸው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት በዚህ ብቻ አላቆመም። (ራእይ 12: 17) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተከሰተው ነገር ለዚህ ማረጋገጫ ይሆናል። ታማኝ የሆኑ የአምላክ ቅቡዓን ምሥክሮች ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ የተዉት ምሳሌ፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም ከማያምኑ ዘመዶችና ከሥራ ባልደረቦች የሚደርስባቸውን ተቃውሞ ወይም አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች የሚሰነዝሩባቸውን ፌዝ ጨምሮ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና እንዲቋቋሙ ያበረታታቸዋል። (1 ጴጥ. 1:6, 7) በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ‘በጠላቶቻቸው ከመሸበር’ ይልቅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ‘በአንድ መንፈስ ጸንተው ለመቆም’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። (ፊልጵ. 1:27, 28) ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች አጥብቆ በሚጠላቸው ዓለም ውስጥ እያሉ ጥበቃ ማግኘት የሚችሉት ከየት ነው?—ዮሐ. 15:17-19

ይሖዋ “ታላቅ ሸለቆ” አዘጋጀ

8. (ሀ) ተራሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ያመለክታሉ? (ለ) ‘የደብረ ዘይት ተራራ’ ምን ያመለክታል?

8 “ከተማዪቱ” ማለትም ኢየሩሳሌም የምታመለክተው ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም እንደሆነ ሁሉ “ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ” የሚገኘው “የደብረ ዘይት ተራራም” ምሳሌያዊ ሊሆን ይገባል። ይህ ተራራ ምን ያመለክታል? ተራራው ‘ለሁለት ተከፍሎ’ ሁለት ተራሮች የሚሆነው እንዴት ነው? ይሖዋ እነዚህን ተራሮች “ተራሮቼ” (NW) ያላቸው ለምንድን ነው? (ዘካርያስ 14:3-5ን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተራሮች አገዛዝን ወይም መንግሥታትን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ተራራ በረከት እንዲሁም ደህንነት እንደሚገኝበት ቦታ ተደርጎ ተገልጿል። (መዝ. 72:3፤ ኢሳ. 25:6, 7) ከዚህ አንጻር፣ ከምድራዊቷ ኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ የሚገኘው አምላክ የቆመበት የደብረ ዘይት ተራራ የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ወይም የበላይ ገዥነቱን ያመለክታል።

9. ‘የደብረ ዘይት ተራራ’ ለሁለት ተከፈለ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

9 የደብረ ዘይት ተራራ መከፈሉ ምን ያመለክታል? ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ የሚገኘው ተራራ ለሁለት መከፈሉ ይሖዋ በእሱ አገዛዝ ሥር ያለ ሌላ መስተዳድር እንደሚያቋቁም የሚያሳይ ነው። ይህ ሁለተኛ መስተዳድር በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው መሲሐዊው መንግሥት ነው። ይሖዋ “የደብረ ዘይት ተራራ” ሲከፈል የተገኙትን ሁለት ተራሮች “ተራሮቼ” በማለት የጠራቸው ለዚህ ነው። (ዘካ. 14:4) ሁለቱም ተራሮች የእሱ ናቸው።

10. በሁለቱ ተራሮች መካከል የተፈጠረው እጅግ “ታላቅ ሸለቆ” ምን ያመለክታል?

10 ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ይህ ተራራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ሲከፈል የይሖዋ እግሮች በሁለቱም ተራሮች ላይ ይቆማሉ። ተራራው ሲከፈል ከይሖዋ እግሮች በታች እጅግ “ታላቅ ሸለቆ” ይፈጠራል። ይህ ምሳሌያዊ ሸለቆ የይሖዋ አገልጋዮች በእሱ አጽናፈ ዓለማዊ አገዛዝ እንዲሁም በልጁ መሲሐዊ መንግሥት አስተዳደር ሥር መለኮታዊ ጥበቃ የሚያገኙበትን ዝግጅት ያመለክታል። ይሖዋ መቼም ቢሆን እውነተኛው አምልኮ ጨርሶ እንዲጠፋ አይፈቅድም። ታዲያ የደብረ ዘይት ተራራ ለሁለት የተከፈለው መቼ ነው? “የአሕዛብ ዘመናት” ባበቁበትና መሲሐዊው መንግሥት በተቋቋመበት ጊዜ ይኸውም በ1914 ነው። እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ወደ ምሳሌያዊው ሸለቆ መሸሽ የጀመሩትስ መቼ ነው?

ወደ ሸለቆው መሸሽ ተጀመረ!

11, 12. (ሀ) ወደ ምሳሌያዊው ሸለቆ መሸሽ የተጀመረው መቼ ነው? (ለ) ይሖዋ በኃያል ክንዱ ሕዝቡን እንደሚያድን የሚያረጋግጥልን ምንድን ነው?

11 ኢየሱስ “በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸው ነበር። (ማቴ. 24:9) ከ1914 ወዲህ ይኸውም በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ደግሞ ይህ ጥላቻ ይበልጥ እየከረረ መጥቷል። ቅቡዓን ቀሪዎች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጠላቶቻቸው ከፍተኛ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም ጨርሶ አልጠፉም። የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶችን ከምትወክለው ከታላቂቱ ባቢሎን መዳፍ በ1919 ነፃ ወጥተዋል። (ራእይ 11:11, 12) * የአምላክ  ሕዝቦች በይሖዋ ተራሮች መካከል ወዳለው ሸለቆ መሸሽ የጀመሩት በዚህ ወቅት ነው።

12 ከ1919 አንስቶ በምድር ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች በሸለቆው ውስጥ መለኮታዊ ጥበቃ እያገኙ ነው። ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በዓለም ዙሪያ በርካታ አገሮች የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት የስብከት እንቅስቃሴና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸው ላይ እገዳ ጥለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አሁንም በእገዳ ሥር ናቸው። ይሁንና ብሔራት የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ እውነተኛውን አምልኮ ከምድር ገጽ ማጥፋት አይችሉም! ይሖዋ በኃያል ክንዱ ሕዝቡን ያድናል።—ዘዳ. 11:2

13. የይሖዋን ጥበቃ ከምናገኝበት ሸለቆ ሳንወጣ መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረጋችን በዛሬው ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ከይሖዋ ጋር ተጣብቀን ከቀጠልንና በእውነት ውስጥ ጸንተን ከቆምን ይሖዋ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃ ያደርጉልናል፤ አምላክ ማንኛውም አካል ወይም ምንም ነገር ‘ከእጁ እንዲነጥቀን’ አይፈቅድም። (ዮሐ. 10:28, 29) ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን ተቀብለን እሱን ለመታዘዝ እንዲሁም ለመሲሐዊው መንግሥት በታማኝነት ለመገዛት ጥረት ስናደርግ የሚያስፈልገንን ማንኛውም እርዳታ ለመስጠት አምላክ ፈቃደኛ ነው። እየቀረበ ባለው ታላቁ መከራ ወቅት የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች በዚህ ሸለቆ ውስጥ መሆናቸው ይበልጥ አስፈላጊ ስለሚሆን በአሁኑ ጊዜ ከሸለቆው ሳንወጣ መኖራችን የግድ ነው።

‘የጦርነት ጊዜ’ ቀርቧል

14, 15. አምላክ ከጠላቶቹ ጋር በሚዋጋበት ‘የጦርነት ጊዜ’ ከሸለቆው ውጭ ያሉ ሰዎች ዕጣ ምን ይሆናል?

14 የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ እየተቃረበ ሲመጣ ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት እየተጧጧፈ ይሄዳል። ከዚያም አምላክ ጠላቶቹን የሚዋጋበት ‘የጦርነት ጊዜ’ ይመጣል። ሰይጣን በዚህ ወቅት የሚሰነዝረው ጥቃት የመጨረሻው ይሆናል። በዚያ ጊዜ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ አምላክ ከዚያ ቀደም በነበሩ ‘የጦርነት ጊዜያት’ ሁሉ ካደረገው በላቀ መልኩ ኃያል ተዋጊ መሆኑን ያሳያል።—ዘካ. 14:3

15 በአምላክ የጦርነት ቀን ጥበቃ ከሚገኝበት “ታላቅ ሸለቆ” ውጭ የሆኑ ሰዎች ዕጣ ምን ይሆናል? የይሖዋን ሞገስ ስለማያገኙ “ብርሃን” አይኖራቸውም። መጪው የጦርነት ቀን “ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ” ይኸውም ብሔራት ያከማቹትን የጦር ኃይል መንካቱ አይቀርም። እነዚህ መሣሪያዎች ‘በውርጭ’ የደረቁ ያህል ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። ከዚህም ሌላ ይሖዋ በብሔራት ላይ ቸነፈርና “መቅሠፍት” ይልክባቸዋል። መቅሠፍቱ ምሳሌያዊ ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም፤ ያም ሆነ ይህ አስፈሪ ዛቻቸው ፀጥ እንዲል ማድረጉ አይቀርም። በዚያ ቀን ‘ዓይኖቻቸውም ሆነ ምላሶቻቸው ይበሰብሳሉ’፤ ይህም የአምላክ ጠላቶች ዓይናቸው ተሸፍኖ የሚዋጉ ያህል እንደሚሆኑ እንዲሁም በአምላክ ላይ በንቀት የሚናገሩበት አፋቸው እንደሚዘጋ የሚያመለክት ነው። (ዘካ. 14:6, 7, 12, 15) ከዚህ ጥፋት የሚያመልጥ አንድም የምድር ክፍል የለም። በዚህ ጦርነት ወቅት ከሰይጣን ጎን የሚሰለፉት ኃይሎች ብዙ ናቸው። (ራእይ 19:19-21) “በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ።”—ኤር. 25:32, 33

16. እየቀረበ ካለው የአምላክ የጦርነት ቀን ጋር በተያያዘ በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው? ምንስ ማድረግ ይኖርብናል?

16 ጦርነት፣ የኋላ ኋላ ድል በሚያደርገው ወገን ላይም እንኳ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። የምግብ እጥረት ሊኖር ይችላል። ንብረት ይወድም ይሆናል። የሰዎች የኑሮ ደረጃ ማሽቆልቆሉ አይቀርም። እንዲሁም የግለሰቦች ነፃነት ይገደብ ይሆናል። እኛም እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን ምን እናደርጋለን? በፍርሃት እንርድ ይሆን? ጫናው ሲበረታብን እምነታችንን እንክዳለን? በተስፋ መቁረጥ ተውጠን እንቆዝማለን? በታላቁ መከራ ወቅት፣ በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን መቀጠላችንና የእሱን ጥበቃ ከምናገኝበት ሸለቆ አለመውጣታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ዕንባቆም 3:17, 18ን አንብብ።

 “የሕይወት ውሃ . . . ይፈልቃል”

17, 18. (ሀ) “የሕይወት ውሃ” ምንድን ነው? (ለ) ‘የምሥራቁ ባሕር’ እና ‘የምዕራቡ ባሕር’ ምን ያመለክታሉ? (ሐ) ከወደፊቱ ጊዜ ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

17 ከመሲሐዊው መንግሥት ዙፋን የሚወጣው “የሕይወት ውሃ” ከአርማጌዶን በኋላም ያለማቋረጥ ይፈሳል። ይህ “የሕይወት ውሃ” ይሖዋ ሕይወት ለመስጠት ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። ‘የምሥራቁ ባሕር’ የሙት ባሕርን፣ ‘የምዕራቡ ባሕር’ ደግሞ የሜድትራንያን ባሕርን ያመለክታሉ። ሁለቱም ባሕሮች እዚህ ላይ የተሠራባቸው ሰዎችን ለማመልከት ነው። የሙት ባሕር፣ በመቃብር ውስጥ የሚገኙትን ሙታን ያመለክታል። ሕያዋን ፍጥረታት የሚርመሰመሱበት የሜድትራንያን ባሕር ደግሞ ከአርማጌዶን የሚተርፉትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማመልከቱ የተገባ ነው። (ዘካርያስ 14:8, 9ን አንብብ፤ ራእይ 7:9-15) ሁለቱም ወገኖች ከዚህ የሕይወት ውሃ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ፤ እነዚህ ሰዎች ከምሳሌያዊው “የሕይወት ውሃ” ወይም “የሕይወት ውኃ ወንዝ” በመጠጣት በአዳም ምክንያት ከመጣባቸው የሞት እርግማን ይላቀቃሉ።—ራእይ 22:1, 2

ጥበቃ ከምናገኝበት ከይሖዋ ሸለቆ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

18 ይሖዋ ጥበቃ ስለሚያደርግልን ይህ ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት ተርፈን አምላክ ወደሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም መግባት እንችላለን። ብሔራት በሙሉ ቢጠሉንም የአምላክ መንግሥት ታማኝ ተገዢዎች ሆነን ለመቀጠልና ጥበቃ ከምናገኝበት የይሖዋ ሸለቆ መቼም ቢሆን ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

^ စာပိုဒ်၊ 11 ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 169-170 ተመልከት