በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ መንፈሳዊ ውርሻችን ነው

ይህ መንፈሳዊ ውርሻችን ነው

“የይሖዋ አገልጋዮች ውርስ ይህ ነው።”ኢሳ. 54:17 ባይንግተን

1. አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ምን አድርጓል?

‘ሕያውና ጸንቶ የሚኖር አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ሕይወት ሰጪ የሆነው መልእክቱ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። ‘የይሖዋ ቃል ለዘላለም ጸንቶ ስለሚኖር’ ይህ መልእክት መቼም ቢሆን ሊጠፋ እንደማይችል ጥርጥር የለውም። (1 ጴጥ. 1:23-25) አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ እንዲህ ያለውን አስፈላጊ መረጃ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጠብቆ ስላቆየልን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

2. አምላክ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ውስጥ ምን ነገር ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል?

2 አምላክ፣ ለራሱ ያወጣው መጠሪያ በቃሉ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ ሕዝቦቹ በስሙ እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል። “ያህዌ” ወይም ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ስለ ‘ሰማያትና ምድር’ መፈጠር በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። (ዘፍ. 2:4) አሥርቱን ትእዛዛት በያዘው የድንጋይ ጽላት ላይም የአምላክ ስም በተአምራዊ መንገድ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተቀርጿል። ለምሳሌ ያህል የመጀመሪያው ትእዛዝ ላይ “እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ” (NW) የሚል ሐሳብ ይገኛል። (ዘፀ. 20:1-17) ሰይጣን፣ የአምላክን ቃል በማጥፋት የይሖዋ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግ የሚችለውን ያህል ቢጥርም ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ጥረቱን አክሽፎበታል፤ በመሆኑም የአምላክ ስም ጸንቶ ይኖራል።—ሥራ 4:24

3. የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት የተሳሳተ ትምህርት ቢስፋፋም አምላክ ምን ነገር ተጠብቆ እንዲቆይልን አድርጓል?

3 ይሖዋ፣ እውነትም በቃሉ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይልን አድርጓል። በመላው ዓለም የሚገኙ የሐሰት ሃይማኖቶች፣ ሰዎች በተሳሳተ ትምህርት ተተብትበው እንዲያዙ ቢያደርጉም አምላክ መንፈሳዊ ብርሃን እንድናገኝና እውነቱን እንድናውቅ ስላስቻለን ምንኛ አመስጋኞችን ነን! (መዝሙር 43:3, 4ን አንብብ።) አብዛኛው የሰው ዘር በጨለማ እየዳከረ ቢሆንም እኛ ግን አምላክ በፈነጠቀልን መንፈሳዊ ብርሃን መመላለስ በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን።—1 ዮሐ. 1:6, 7

ከፍ አድርገን ልንመለከተው የሚገባ ውርስ አለን

4, 5. ከ1931 ወዲህ ምን ልዩ መብት አግኝተናል?

4 ክርስቲያኖች በመሆናችን ያገኘነው ውርስ ወይም ቅርስ እጅግ ውድ ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ቅርስ ለሚለው ቃል “የአንድን ሃገር ጥንታዊ ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቅ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈና የሚተላለፍ ቋሚ መረጃ” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። መንፈሳዊ  ውርሻችን፣ ስለ አምላክ ቃል የቀሰምነውን ትክክለኛ እውቀት እንዲሁም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት በተመለከተ ያገኘነውን ግልጽ ግንዛቤ ያካትታል። ይህ ውርሻ ሌላም ልዩ መብት አስገኝቶልናል።

በ1931 ባደረግነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ስም መጠራት በመጀመራችን በጣም ተደስተናል

5 ይህ ልዩ መብት የመንፈሳዊ ውርሻችን ወይም ቅርሳችን ክፍል የሆነው በ1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ነው። በስብሰባው ፕሮግራም ላይ “JW” የሚሉት የእንግሊዝኛ ፊደላት ታትመው ነበር። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ፊደላት ምን እንደሚያመለክቱ የተለያዩ ግምቶች ተሰንዝረው ነበር፤ ከእነዚህ መካከል ጀስት ዌይት፣ ጀስት ዋች እና ጀሆቫስ ዊትነስስ የሚሉት ይገኙበታል።” ከዚያ ቀደም የምንታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚለው መጠሪያ ቢሆንም ከእሁድ ሐምሌ 26 ቀን 1931 ጀምሮ “የይሖዋ ምሥክሮች” ተብለን እንደምንጠራ የሚገልጽ የአቋም መግለጫ ወጣ። ተሰብሳቢዎቹ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም በማግኘታቸው በደስታ ፈነደቁ። (ኢሳይያስ 43:12ን አንብብ።) አንድ ወንድም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “በስብሰባው አዳራሽ ከዳር እስከ ዳር ያስተጋባው ጭብጨባ ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም” በማለት ተናግሯል። በዓለም ላይ በዚህ ስም ለመጠራት የፈለገ አንድም ቡድን የለም፤ እኛ ግን ከስምንት አሥርተ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ በዚህ ስም እንድንጠራ አምላክ ፈቅዶልናል። በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችን እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው!

6. መንፈሳዊው ውርሻችን የትኛውን ትክክለኛ እውቀት ያካትታል?

6 በጥንት ዘመናት ስለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ያገኘነው ትክክለኛና ጠቃሚ መረጃም በመንፈሳዊ ውርሻችን ውስጥ ይካተታል። አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። እነዚህ የእምነት አባቶችና ቤተሰቦቻቸው ይሖዋን ማስደሰት ስለሚችሉበት መንገድ እርስ በርስ ተወያይተው መሆን አለበት። ከዚህ አንጻር፣ ጻድቅ የነበረው ዮሴፍ “በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት” ላለመሥራት ሲል የፆታ ብልግና ከመፈጸም መራቁ የሚያስገርም አይሆንም! (ዘፍ. 39:7-9) በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ክርስቲያናዊ ወጎች የተላለፉት ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖች በአኗኗራቸውም ሆነ በቃላቸው በሚሰጡት ትምህርት አማካኝነት ነበር። ከእነዚህ ወጎች መካከል ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታ ራትን አስመልክቶ ለክርስቲያን ጉባኤዎች ያስተላለፈው መመሪያ ይገኝበታል። (1 ቆሮ. 11:2, 23) በዛሬው ጊዜ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጹ ዝርዝር መመሪያዎችን በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ውስጥ ማግኘት እንችላለን። (ዮሐንስ 4:23, 24ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተዘጋጀው ለመላው የሰው ዘር የእውነትን ብርሃን እንዲፈነጥቅ ነው፤ እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ግን ከሌሎች በተለየ መልኩ ለአምላክ ቃል እጅግ የላቀ ቦታ እንሰጠዋለን።

7. መንፈሳዊ ውርሻችን ይሖዋ የገባልንን የትኛውን የሚያበረታታ ቃል ይጨምራል?

7 መንፈሳዊ ውርሻችን፣ ይሖዋ ‘ከእኛ ጋር’ እንደሆነ የሚያሳዩ በቅርብ ጊዜ የወጡ ዘገባዎችንም ያካትታል። (መዝ. 118:7) እነዚህን ዘገባዎች ማንበባችን ስደት በሚደርስብን ጊዜም እንኳ እንዳንሸበር ይረዳናል። “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት [“ውርስ፣” ባይንግተን] ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው” በማለት ይሖዋ የገባልን የሚያበረታታ ቃልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው መንፈሳዊ  ውርሻችን ክፍል ነው። (ኢሳ. 54:17) የትኛውም የሰይጣን መሣሪያ ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም።

8. በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

8 ሰይጣን የአምላክን ቃል ለማጥፋት፣ የይሖዋ ስም እንዲረሳ ለማድረግ እንዲሁም እውነትን ለማዳፈን ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ይሁን እንጂ ሰይጣን ከይሖዋ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር እንደማይችል ጥያቄ የለውም፤ ያደረጋቸውን ጥረቶች በሙሉ ይሖዋ አክሽፎበታል። በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ አምላክ (1) ቃሉ እና (2) ስሙ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው እንዲሁም (3) ዛሬ ያገኘነው እውነት ምንጭ የሆነው ብሎም ይህ እውነት ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ይሖዋ ቃሉ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል

9-11. መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የተደረጉት የተለያዩ ጥረቶች እንዳልተሳኩ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

9 ይሖዋ፣ ቃሉን ለማጥፋት የተደረጉ ጥረቶችን በማክሸፍ ቃሉ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። ኤንቺክሎፔዲያ ካቶሊካ (የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ) እንዲህ ይላል፦ “አልበጀንሳውያንን እና ዎልደንሳውያንን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ሲባል በ1229 የቱሉዝ ጉባኤ ተራው ሕዝብ [በቋንቋው የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን] እንዳይጠቀም አገደ። . . . በ1234 በቀዳማዊ ጄምስ መሪነት በታራጎና፣ ስፔን በተደረገው ጉባኤ ላይም ተመሳሳይ እገዳ ተጣለ። . . . በ1559 ደግሞ [የሮም ቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት] ይህን እገዳ የሚደግፍ አቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ወሰዱ፤ ይህም የሆነው [ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት] ፖል አራተኛ፣ በ1559 ባዘጋጀው አደገኛ ተብለው የተፈረጁ መጻሕፍት ዝርዝር ላይ ሕዝቡ በቋንቋው የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን ያለ ቅዱስ ቢሮው ፈቃድ ማተምም ሆነ ይዞ መገኘት እንደማይችል በመግለጹ ነው።”

10 መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም አልተሳኩም። በ1382 ገደማ ጆን ዊክሊፍና የሥራ ባልደረቦቹ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እንግሊዝኛ ተረጎሙ። ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ዊልያም ቲንደል ሲሆን ይህ ሰው በ1536 ተገድሏል። ቲንደል በእንጨት ላይ ታስሮ በነበረበት ወቅት “ጌታ ሆይ፣ የእንግሊዝን ንጉሥ ዓይን እንድትከፍት እለምንሃለሁ” ብሎ እንደጮኸ ይነገራል። ከዚያም አሳዳጆቹ አንቀው ከገደሉት በኋላ አቃጠሉት።

11 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከመጥፋት ሊተርፍ ችሏል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1535 ማይልዝ ከቨርዴል የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጀ። ከቨርዴል “አዲስ ኪዳንን” እና ከዘፍጥረት እስከ ዜና መዋዕል ያለውን “የብሉይ ኪዳን” ክፍል ለማዘጋጀት የተጠቀመው የቲንደልን ትርጉም ነው። ሌሎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደግሞ በላቲን ከተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስና ማርቲን ሉተር ካዘጋጀው የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጉሟል። በዛሬው ጊዜ ያለው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ግልጽና ቀላል አቀራረብ ያለው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሳያዛባ በትክክል የሚያስተላልፍ እንዲሁም ለአገልግሎታችን ጠቃሚ መሆኑ ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል። አጋንንትም ሆነ ሰዎች የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት የይሖዋን ቃል ማጥፋት ባለመቻሉ ደስተኞች ነን።

ይሖዋ ስሙ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል

እንደ ቲንደል ያሉ ሰዎች ለአምላክ ቃል ሲሉ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል

12. አዲስ ዓለም ትርጉም መለኮታዊው ስም እንዳይጠፋ በማድረግ ረገድ ምን ሚና ተጫውቷል?

12 ይሖዋ አምላክ፣ ስሙ ከቃሉ ውስጥ እንዳይጠፋ አድርጓል። አዲስ ዓለም ትርጉም በዚህ ረገድ ትልቅ  ሚና ተጫውቷል። የዚህ ትርጉም አዘጋጆች በመግቢያው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የዚህ የትርጉም ሥራ ዋነኛ ዓላማ መለኮታዊው ስም በእንግሊዝኛው ጽሑፍ ውስጥ በትክክለኛ ቦታው ላይ ተመልሶ እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። ይህንም ለማድረግ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ‘ጀሆቫ’ የሚለውን የእንግሊዝኛ አጠራር በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 6,973 ጊዜ፣ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ 237 ጊዜ አስገብተናል።” የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በ116 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን ከ178,545,862 በሚበልጡ ቅጂዎች ታትሟል።

13. የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ የአምላክን ስም ያውቁ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

13 የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ የአምላክን ስም ያውቁ ነበር። አዳምና ሔዋን የአምላክን ስም ያውቁ የነበረ ሲሆን ሔዋን በዚህ ስም እንደተጠቀመች የሚያሳይ ዘገባ አለ። ከጥፋት ውኃ በኋላ ካም የአባቱን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነገር በፈጸመ ጊዜ ኖኅ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “የሴም አምላክ ያህዌ ይባረክ፤ [የካም ልጅ የሆነው] ከነዓንም የሴም ባሪያ ይሁን።” (ዘፍ. 4:1፤ 9:26) አምላክ ራሱም “እኔ . . . [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ . . . አልሰጥም” ብሏል። በተጨማሪም “እኔ . . . [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔ በቀር አምላክ የለም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳ. 42:8፤ 45:5) ይሖዋ ስሙ ተጠብቆ እንዲቆይና በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች እንዲታወቅ አድርጓል። ይሖዋ በሚለው ስም መጠቀምና የእሱ ምሥክሮች መሆን መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በእርግጥም “በአምላካችን ስም አርማችንን ከፍ እናደርጋለን” ብለን በደስታ መናገር እንችላለን።—መዝ. 20:5

14. የአምላክ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ምን ላይ ተጠቅሶ ይገኛል?

14 የአምላክ ስም የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ አይደለም። ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ 21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው በዚባን (ዲቦን) የተገኘውን የሞዓባውያን ጽላት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በጽላቱ ላይ የእስራኤል ንጉሥ ዖምሪ የተጠቀሰ ሲሆን የሞዓብ ንጉሥ ሞሳ በእስራኤል ላይ ስለማመፁም የሚገልጽ ዘገባ አለ። (1 ነገ. 16:28፤ 2 ነገ. 1:1፤ 3:4, 5) የሞዓባውያኑ ጽላት በተለይ ትኩረታችንን የሚስበው የይሖዋ ስም የሚጻፍባቸውን አራቱን የዕብራይስጥ ፊደላት የያዘ በመሆኑ ነው። የለኪሶ ደብዳቤ ተብሎ በሚጠራው በእስራኤል በተገኘ የሸክላ ስብርባሪ ላይም የይሖዋ ስም የሚጻፍባቸው አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሰዋል።

15. ሴፕቱጀንት ምንድን ነው? ይህ ትርጉም የተዘጋጀውስ ለምንድን ነው?

15 ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችም መለኮታዊው ስም ተጠብቆ እንዲቆይ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እስራኤላውያን ከ607 ዓ.ዓ. እስከ 537 ዓ.ዓ. በባቢሎን በግዞት ከቆዩ በኋላ ነፃ ሲወጡ በርካታ አይሁዳውያን ወደ ይሁዳና እስራኤል ምድር አልተመለሱም። በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በአሌክሳንድሪያ፣ ግብፅ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር፤ እነዚህ አይሁዳውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብ እንዲችሉ ቅዱሳን መጻሕፍት በወቅቱ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ወደነበረው ወደ ግሪክኛ መተርጎም ያስፈልጋቸው ነበር። ወደ ግሪክኛ የተተረጎመውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተጠናቀቀው የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ሴፕቱጀንት ወይም የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ተብሎ ይጠራል። በዚህ ትርጉም አንዳንድ ቅጂዎች ላይ ይሖዋ የሚለው ስም በዕብራይስጥ አጻጻፍ ይገኛል።

16. ለመጀመሪያ ጊዜ በ1640 በታተመው መጽሐፍ ላይ የአምላክ ስም እንደሚገኝ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

16 መለኮታዊው ስም፣ ቤይ ሳልም ቡክ በተባለው በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር በነበሩ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የታተመ የመጀመሪያው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ላይም ይገኛል። በ1640 በታተመው በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ እትም ላይ የመዝሙር መጽሐፍ ከዕብራይስጥ በዘመኑ ወደሚነገረው እንግሊዝኛ ተተርጉሟል። ይህ መጽሐፍ እንደ መዝሙር 1:1, 2 ባሉት ጥቅሶች ላይ የአምላክን ስም ይዟል፤ ጥቅሱ በክፉዎች ምክር ስለማይሄድ “ብሩክ ሰው” የሚናገር ሲሆን እንዲህ ያለው ሰው “በየሆቫ ሕግ እጅግ ደስ ይለዋል” ተብሎለታል። ስለ አምላክ ስም ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።

ይሖዋ መንፈሳዊው እውነት ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል

17, 18. (ሀ) “እውነት” ምንድን ነው? (ለ) ‘የምሥራቹ እውነት’ የትኞቹን ነገሮች ያካትታል?

17 “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን በደስታ እናገለግለዋለን። (መዝ. 31:5) ኮሊንስ ኮቢልድ ኢንግሊሽ  ዲክሽነሪ እውነት ለሚለው ቃል “ስለ አንድ ነገር የሚገልጽ በፈጠራ ወይም በምናብ በታሰበ ነገር ላይ ያልተመሠረተ ትክክለኛ መረጃ” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። ብዙውን ጊዜ “እውነት” ተብሎ የሚተረጎመው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዕብራይስጥ ሐቅ የሆነ፣ የሚታመን፣ እምነት የሚጣልበት ወይም በማስረጃ የተደገፈ ነገርን ያመለክታል። “እውነት” ተብሎ የሚተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሐቅ ከሆነው ወይም ትክክል እና ተገቢ ከሆነው ጋር የሚስማማ ነገርን ያመለክታል።

18 ይሖዋ መንፈሳዊው እውነት ተጠብቆ እንዲቆይልን እንዲሁም ስለዚህ እውነት ያለን እውቀት በየጊዜው እየጨመረ እንዲሄድ አድርጓል። (2 ዮሐ. 1, 2) “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን” በመሆኑ ስለ እውነት ያለን ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ ይሄዳል። (ምሳሌ 4:18) ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ ከተናገረው “ቃልህ እውነት ነው” ከሚለው ሐሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደምንስማማ ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 17:17) በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ‘የምሥራቹን እውነት’ ይዟል፤ ይህ እውነት የክርስትና ትምህርቶችን በሙሉ ያቀፈ ነው። (ገላ. 2:14) ከእነዚህም መካከል ስለ ይሖዋ ስም፣ ስለ ሉዓላዊነቱ፣ ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ ስለ ትንሣኤ እንዲሁም ስለ መንግሥቱ የሚገልጹት ትምህርቶች ይገኙበታል። ሰይጣን ይህ እውነት እንዲዳፈን ለማድረግ ቢጥርም አምላክ እውነት ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ይሖዋ በእውነት ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን አክሽፏል

19, 20. ናምሩድ ማን ነበር? በእሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች ምን ለማድረግ ሞክረው ነበር?

19 ከጥፋት ውኃ በኋላ “እንደ ናምሩድ ያለ ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” የሚል አባባል ነበር። (ዘፍ. 10:9 NW) ናምሩድ፣ ይሖዋ አምላክን ይቃወም ስለነበረ የሰይጣን አምላኪ ነበር ማለት ይቻላል፤ በመሆኑም ናምሩድ፣ ኢየሱስ “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ። እሱ . . . በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” ብሎ ከተናገራቸው ተቃዋሚዎች ጋር ሊመደብ ይችላል።—ዮሐ. 8:44

20 የናምሩድ ግዛት ባቢሎንን እንዲሁም በጤግሮስና በኤፍራጥስ ወንዞች መካከል የሚገኙ ሌሎች ከተሞችን ያጠቃልላል። (ዘፍ. 10:10) በ2269 ዓ.ዓ. ገደማ የባቢሎን ከተማና ግንብ ሲሠራ የግንባታ ሥራውን ይመራ የነበረው ናምሩድ ሳይሆን አይቀርም። የይሖዋ ዓላማ፣ የሰው ልጆች በምድር ላይ በተለያዩ ቦታዎች እንዲኖሩ ነበር፤ ከተማዋን የሚገነቡት ሰዎች ግን “ለስማችን መጠሪያ እንዲሆንና በምድር ላይ እንዳንበተን፣ ኑ፤ ከተማና ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንሥራ” በማለት የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ሐሳብ አቀረቡ። ይሁንና አምላክ “የመላውን ዓለም ቋንቋ ስለ ደበላለቀ” እነዚህ ሰዎች በምድር ሁሉ ተበታተኑ፤ በመሆኑም ዕቅዳቸው ከሸፈ። (ዘፍ. 11:1-4, 8, 9) በዚያ ወቅት ሰይጣን፣ ሰዎች ሁሉ እሱን የሚያመልኩበት አንድ ሃይማኖት የማቋቋም እቅድ ከነበረው ዓላማው አልተሳካም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ የተቋረጠበት ጊዜ የለም፤ እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የእሱ አምላኪዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።

21, 22. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖቶች፣ እውነተኛውን አምልኮ ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት መቼም ቢሆን ተሳክቶላቸው የማያውቀው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

21 የሐሰት ሃይማኖቶች፣ እውነተኛውን አምልኮ ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው አያውቅም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ታላቁ አስተማሪያችን ቃሉ ተጠብቆ እንዲቆይና ስሙ ለሰው ዘር እንዲታወቅ ስላደረገ እንዲሁም የማይነጥፍ መንፈሳዊ እውነት ምንጭ ስለሆነ ነው። (ኢሳ. 30:20, 21) አምላክን ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ማምለክ ደስታ ያስገኝልናል፤ ሆኖም ይህን ለማድረግ በመንፈሳዊ ንቁ መሆን፣ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንና የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተል ይኖርብናል።

22 በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ አንዳንድ የሐሰት ትምህርቶች አመጣጥ እንመረምራለን። እነዚህ ትምህርቶች ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር ሲታዩ የተሳሳቱ መሆናቸውን እንመለከታለን። ከዚህም በላይ እውነት ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ ረገድ ወደር የለሽ ችሎታ እንዳለው ያሳየው ይሖዋ እንደ ውድ አድርገን የምንመለከታቸውን የመንፈሳዊ ውርሻችን ክፍል የሆኑ እውነተኛ ትምህርቶች እንድናውቅ በማድረግ የባረከን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።