በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ

ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ

“የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ።”—ኢያሱ 24:15

1-3. (ሀ) ትክክለኛ ምርጫ በማድረግ ረገድ ኢያሱ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ሲያጋጥሙን ምን ነገር ማሰብ ይኖርብናል?

በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ምርጫዎች ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ። አንድ ሰው ምርጫ የሚያደርገው አማራጮች ሲኖሩት ነው፤ እንዲህ ያለው ሰው ሕይወቱን የሚመራበትን አቅጣጫ ለመወሰን በተወሰነ መጠን ነፃነት አለው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በጉዞ ላይ ያለ አንድ ሰው መንታ መንገድ ላይ ደረሰ እንበል። ይህ ሰው የትኛውን መንገድ ይመርጣል? ግለሰቡ መድረሻውን የሚያውቅ ከሆነ አንደኛው መንገድ ወደሚፈልገው ቦታ እንደሚያደርሰው ሌላኛው ጎዳና ደግሞ ካሰበው ቦታ እንደሚያርቀው የታወቀ ነው።

2 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የመሰለ ሁኔታ ስላጋጠማቸው በርካታ ሰዎች የሚናገር ታሪክ ይዟል። ለምሳሌ ቃየን ቁጣው እንዲቆጣጠረው የመፍቀድ አሊያም ቁጣውን የመቆጣጠር ምርጫ ነበረው። (ዘፍ. 4:6, 7) በሌላ በኩል ኢያሱ ከእውነተኛው አምላክና ከሐሰት አማልክት አንዱን መምረጥ ነበረበት። (ኢያሱ 24:15) የኢያሱ ግብ ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ መኖር ነበር፤ በመሆኑም ወደዚያ አቅጣጫ የሚመራውን መንገድ መርጧል። ቃየን ግን እንዲህ ያለ ግብ ስላልነበረው ከይሖዋ የሚያርቀውን የሕይወት ጎዳና ተከትሏል።

3 አንዳንድ ጊዜ እኛም በሕይወት ጎዳና ላይ ስንጓዝ መንታ መንገድ ያጋጥመናል። በዚህ ጊዜ መድረሻችንን ማለትም ግባችንን ማሰብ ይኖርብናል፤ ግባችን፣ በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋን ማስከበርና ምንም ነገር ከእሱ እንዲያርቀን አለመፍቀድ ነው። (ዕብራውያን 3:12ን አንብብ።) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ከይሖዋ ሊያርቁን ከሚችሉ ነገሮች መካከል ሰባቱን እንመረምራለን።

ሥራ

4. ሰብዓዊ ሥራ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ክርስቲያኖች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የማስተዳደር ግዴታ አለባቸው። አንድ ሰው ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን  ነገር ማቅረብ የማይፈልግ ከሆነ እምነት ከሌለው ሰው የከፋ ወይም ይሖዋን የካደ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። (2 ተሰ. 3:10፤ 1 ጢሞ. 5:8) ሰብዓዊ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምንሰጣቸው ነገሮች አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ይሁንና ጥንቃቄ ካላደረግን ሥራችን ከይሖዋ ሊያርቀን ይችላል። እንዴት?

5. ሥራ ስንመርጥ የትኞቹን ጉዳዮች ማጤናችን አስፈላጊ ነው?

5 ሥራ እየፈለግህ ነው እንበል። የምትኖረው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት አገር ውስጥ ከሆነ መጀመሪያ የምታገኘውን ማንኛውንም ሥራ ዓይንህን ሳታሽ ለመቀበል ትፈተናለህ? የሥራው ዓይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ቢሆንስ? የሥራው ጸባይ ብዙ ሰዓት እንድትሠራ ወይም እንድትጓዝ የሚጠይቅ በመሆኑ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችህን የሚያስተጓጉልብህ ወይም ከቤተሰብህ የሚያርቅህ ቢሆንስ? ሥራ አጥቶ ከመቀመጥ ይሻላል በሚል የማይሆን ሥራ ትይዛለህ? የተሳሳተ ጎዳና መከተል ከይሖዋ እንደሚያርቅህ አትዘንጋ። (ዕብ. 2:1) ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ሥራ ለመቀየር እያሰብክ ከሆነ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

6, 7. (ሀ) አንድ ሰው ከሰብዓዊ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ግቦች ሊኖሩት ይችላሉ? (ለ) ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ የሚያስችልህ የትኛው ግብ ነው? ለምንስ?

6 ቀደም ሲል እንደተገለጸው መድረሻህን በአእምሮህ መያዝህ ጠቃሚ ነው። ‘ይህ ሥራ እንዲያደርሰኝ የምፈልገው የት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሰብዓዊ ሥራን የምትመለከተው ግብህ ላይ ለመድረስ ይኸውም ራስህንና ቤተሰብህን እያስተዳደርክ ይሖዋን ለማገልገል እንደሚያስችል ነገር አድርገህ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን ይባርከዋል። (ማቴ. 6:33) ሥራህን ብታጣ ወይም ድንገተኛ የገንዘብ ችግር ቢያጋጥምህ ይሖዋ ዝም ብሎ እንደማይመለከትህ አስታውስ። (ኢሳ. 59:1) ይሖዋ ለእሱ “ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” ያውቃል።—2 ጴጥ. 2:9

7 በሌላ በኩል ደግሞ የምትፈልገው በቁሳዊ መበልጸግ ብቻ ከሆነስ? ሊሳካልህ ይችላል። ያም ሆኖ እንዲህ ያለው “ስኬት” ልትመልሰው የማትችል ዋጋ እንደሚያስከፍልህ አትዘንጋ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) ለሀብትና ለሥራ ከልክ ያለፈ ቦታ መስጠት አንተን ከይሖዋ ከማራቅ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።

8, 9. ወላጆች ለሰብዓዊ ሥራ ከሚኖራቸው አመለካከት ጋር በተያያዘ ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? አብራራ።

8 ወላጅ ከሆንክ የአንተ ምሳሌነት በልጆችህ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስብ። ልጆችህ የሚያስተውሉት ምንድን ነው? ከፍተኛ ቦታ የምትሰጠው ለሥራህ እንደሆነ ነው ወይስ ከይሖዋ ጋር ላለህ ዝምድና? ለዝና፣ ለክብር ወይም ለሀብት ትልቅ ቦታ የምትሰጥ ከሆነ እነሱም እንዲህ ያለውን የጥፋት ጎዳና ሊከተሉ ይችላሉ። እንደ ወላጅ መጠን ለአንተ የሚሰጡት አክብሮት ይቀንስ ይሆን? አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እኔ እስከማስታውሰው ድረስ አባቴ በሥራ በጣም የተወጠረ ሰው ነበር። መጀመሪያ ላይ እንዲህ ጠንክሮ የሚሠራው ለቤተሰቡ የተሻለ ነገር ለማቅረብና እኛን በእንክብካቤ ለማሳደግ ስለሚፈልግ ይመስለኝ ነበር። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነገሮች ግልጽ ሆኑ። ይሠራል፣ ይሠራል፤ እንዲህ የሚያደርገው ግን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሳይሆን የቅንጦት ዕቃዎችን ለመግዛት ነው። በዚህ ምክንያት ቤተሰባችን የሚታወቀው ሌሎችን በመንፈሳዊ በማበረታታት ሳይሆን በሀብት ነው። እኔ ግን ሀብቱ ቀርቶብኝ በመንፈሳዊ ቢረዳን ይሻለኝ ነበር።”

9 ወላጆች፣ ለሥራችሁ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ራሳችሁን ከይሖዋ እንዳታርቁ ተጠንቀቁ። ትልቁ ሀብት ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ መሆኑን ከልባችሁ እንደምታምኑ ለልጆቻችሁ በአኗኗራችሁ አሳዩአቸው።—ማቴ. 5:3

10. አንድ ወጣት የሥራ መስክ በሚመርጥበት ጊዜ ምን ነገር ማሰብ ይኖርበታል?

10 የሥራ መስክ በመምረጥ ላይ ያለህ ወጣት ከሆንክ ትክክለኛውን ጎዳና መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? ይህ የተመካው ቀደም ሲል  እንደተወያየነው ሕይወትህን መጠቀም በምትፈልግበት መንገድ ላይ ነው። ሥልጠና ለመውሰድ ወይም ለመቀጠር ያሰብከው የሥራ መስክ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይበልጥ ለማስቀደም ይረዳሃል ወይስ ከይሖዋ ያርቅሃል? (2 ጢሞ. 4:10) ግብህ ደስታቸው በኪሳቸው ላይ የተመካ ሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ ነው? ወይስ ምርጫህ “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም” በማለት በትምክህት የጻፈውን የዳዊትን ስሜት እንደምትጋራ ያሳያል? (መዝ. 37:25) አንደኛው መንገድ ከይሖዋ እንደሚያርቅህ ሌላኛው ደግሞ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንደሚያስገኝልህ አትዘንጋ። (ምሳሌ 10:22ን እና ሚልክያስ 3:10ን አንብብ።) ታዲያ የትኛውን መንገድ ትመርጣለህ? *

መዝናኛ

11. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መዝናኛ ምን ይናገራል? ይሁንና ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

11 መጽሐፍ ቅዱስ መዝናናትን አያወግዝም፤ እንዲሁም ጊዜን እንደማባከን አድርጎ አይመለከተውም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” በማለት ጽፎለታል። (1 ጢሞ. 4:8) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለሳቅና ለጭፈራ ጊዜ እንዳለው’ ይናገራል፤ በተጨማሪም መጠነኛ እረፍት ማድረግን ያበረታታል። (መክ. 3:4፤ 4:6) ይሁንና ጠንቃቃ ካልሆንን መዝናኛ ከይሖዋ ሊያርቀን ይችላል። እንዴት? ብዙ ጊዜ አደጋው የሚከሰተው ከሁለት አቅጣጫ ነው፤ አንደኛው የመዝናኛው ዓይነት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በመዝናናት የሚጠፋው ጊዜ ነው።

ተገቢ ዓይነት መዝናኛ በተገቢው መጠን መንፈስን ያድሳል

12. በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?

12 እስቲ በመጀመሪያ፣ ስለምንመርጠው የመዝናኛ ዓይነት እንመልከት። ጤናማና ጥሩ የሆነ መዝናኛ እንዳለ ግልጽ ነው። ይሁንና አብዛኛው መዝናኛ ዓመፅን፣ መናፍስታዊ ድርጊትንና የፆታ ብልግናን ጨምሮ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቅ እንደሆነ አይካድም። በመሆኑም የምንመርጠውን መዝናኛ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል። መዝናኛው በአንተ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል? የዓመፀኝነት፣ የፉክክር ወይም የብሔራዊ ስሜት እንዲኖርህ የሚያበረታታ ነው? (ምሳሌ 3:31) ገንዘብህን እንድታባክን ያደርግሃል? ሌሎችንስ ያሰናክላል? (ሮም 14:21) የምትመርጠው የመዝናኛ ዓይነት ከማን ጋር እንድትውል ያደርግሃል? (ምሳሌ 13:20) መጥፎ ነገር የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርብህ ያደርጋል?—ያዕ. 1:14, 15

13, 14. ለመዝናናት ከምታውለው ጊዜ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?

 13 በመዝናኛ የምታሳልፈው ጊዜም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ‘ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ጊዜ እስካጣ ድረስ በመዝናናት ብዙ ጊዜ አጠፋለሁ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። በመዝናኛ የምታጠፋው ጊዜ ከልክ ያለፈ ከሆነ የእረፍት ጊዜህ የምታስበውን ያህል መንፈስህን አያድስልህም። እንዲያውም በእረፍት ጊዜያቸው ይበልጥ የሚደሰቱት ለመዝናኛ ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” በማስቀደማቸው፣ ሲዝናኑ የሕሊና ወቀሳ አይሰማቸውም።ፊልጵስዩስ 1:10, 11ን አንብብ።

14 በመዝናናት ረጅም ጊዜ ማሳለፍ አስደሳች ቢመስልም ይህን መንገድ መከተል አንድን ሰው ከይሖዋ ሊያርቀው ይችላል። ኪም የተባለች የ20 ዓመት ወጣት ይህን ሁኔታ ከራሷ ሕይወት ተምራለች። ይህች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንድም ግብዣ አያመልጠኝም ነበር። ሁልጊዜ ዓርብ፣ ቅዳሜና እሁድ አንድ ትልቅ ግብዣ አይጠፋም ነበር። አሁን ግን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ማስተዋል ችያለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ አቅኚ እንደመሆኔ መጠን ለአገልግሎት ጠዋት 12 ሰዓት ላይ እነሳለሁ፤ በመሆኑም እስከ ሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት ድረስ ግብዣ ላይ መቆየት አልችልም። ሁሉም ማኅበራዊ ግብዣዎች መጥፎ እንዳልሆኑ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ትልቅ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ልክ እንደ ሌሎቹ ነገሮች ለግብዣዎችም ተገቢውን ቦታ መስጠት ይኖርብናል።”

15. ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈስን የሚያድስ መዝናኛ እንዲመርጡ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ወላጆች የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት የማሟላት ግዴታ አለባቸው። ይህ ደግሞ መዝናኛን ይጨምራል። ወላጅ ከሆንክ ሁሉም የመዝናኛ ዓይነቶች መጥፎ እንደሆኑ በመፈረጅ ቤተሰብህ ደስታ የራቀው ሕይወት እንዲመራ አታድርግ። በሌላ በኩል ደግሞ የመዝናኛ ምርጫችሁ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንዳይሆን ጥንቃቄ አድርግ። (1 ቆሮ. 5:6) አስቀድመህ በጉዳዩ ላይ በሚገባ ካሰብክበት ለቤተሰብህ የሚሆን መንፈስን የሚያድስ መዝናኛ ማግኘት ትችላለህ። * እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አንተንም ሆንክ ልጆችህ የመረጣችሁት ጎዳና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርቡ የሚያስችላችሁ ይሆናል።

ቤተሰብ

16, 17. በርካታ ወላጆች ምን ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል? ይሖዋ ሥቃያቸውን እንደሚረዳ እንዴት እናውቃለን?

16 በወላጅና በልጅ መካከል ያለው ዝምድና በጣም ጠንካራ በመሆኑ ይሖዋ ራሱ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ይህን ዝምድና እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (ኢሳ. 49:15) በመሆኑም አንድ የቤተሰባችን አባል ይሖዋን ሲተው በጥልቅ ማዘናችን የሚጠበቅ ነገር ነው። አንዲት እህት ልጇ ስትወገድ የተሰማትን ስሜት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “ቅስሜ ተሰብሮ ነበር። ‘ይሖዋን የተወችው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ያስጨንቀኝ ነበር። የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ራሴን እወቅስ ነበር።”

17 ይሖዋ ሥቃያችሁን ይረዳል። የምድራዊው ቤተሰብ የመጀመሪያ አባላትም ሆኑ ከጥፋት ውኃው በፊት የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ባመፁ ጊዜ ‘ልቡ እጅግ አዝኖ’ ነበር። (ዘፍ. 6:5, 6) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው የማያውቁ ሰዎች ሁኔታው ምን ያህል ሥቃይ እንደሚያስከትል መረዳት ሊከብዳቸው ይችላል። ያም ቢሆን የተወገደው የቤተሰብ አባል የተከተለው ተገቢ ያልሆነ ጎዳና እናንተን ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ መፍቀድ ጥበብ አይደለም። ታዲያ አንድ የቤተሰብ አባል ይሖዋን ሲተው የሚፈጠረውን ከባድ ሐዘን መቋቋም የምትችሉት እንዴት ነው?

18. ወላጆች፣ ልጃቸው ይሖዋን ሲተው ራሳቸውን መውቀስ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?

18 ለተፈጠረው ነገር ራሳችሁን አትውቀሱ። ይሖዋ በሰዎች ፊት ምርጫ አስቀምጧል፤ ራሱን ወስኖ የተጠመቀ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል  “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” መሸከም ይኖርበታል። (ገላ. 6:5) ይሖዋ፣ ኃጢአት የሠራው ሰው በወሰደው ምርጫ የሚጠይቀው እሱን እንጂ እናንተን አይደለም። (ሕዝ. 18:20) በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን መውቀስ አይኖርባችሁም። ይሖዋ ተግሣጽ ለመስጠት ያደረገውን ዝግጅት አክብሩ። ጉባኤውን ለመጠበቅ የተሾሙትን እረኞች መደገፍ እንጂ ከዲያብሎስ ጎን መቆም አይገባችሁም።—1 ጴጥ. 5:8, 9

ይሖዋን የተወው የቤተሰባችሁ አባል እንደሚመለስ ተስፋ ማድረጋችሁ ስህተት አይደለም

19, 20. (ሀ) ልጆቻቸው የተወገዱ ወላጆች ሐዘናቸውን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይችላሉ? (ለ) ልጆቻቸው የተወገዱባቸው ወላጆች ምን ነገር ተስፋ ማድረጋቸው ስህተት አይደለም?

19 በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ ላይ የምትቆጡ ከሆነ ከእሱ እየራቃችሁ ትሄዳላችሁ። ይሖዋን የተወው የቤተሰባችሁ አባል፣ እንዲያስተውል ማድረግ ያለባችሁ የቤተሰብ ዝምድናን ጨምሮ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ይሖዋን ለማስቀደም ያላችሁን ቁርጠኝነት ነው። በመሆኑም ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የራሳችሁን መንፈሳዊነት አጠናክሩ። ታማኝ ከሆኑ ወንድሞችና እህቶች ራሳችሁን አታግልሉ። (ምሳሌ 18:1) በጸሎት አማካኝነት ስሜታችሁን ለይሖዋ ንገሩት። (መዝ. 62:7, 8) በስልክ፣ በኢ-ሜይል ወይም በሌላ መንገድ ከተወገደው የቤተሰብ አባል ጋር ለመገናኘት ሰበብ አስባብ አትፈላልጉ። (1 ቆሮ. 5:11) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመዱ። (1 ቆሮ. 15:58) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው እህት እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ወደ ይሖዋ ስትመለስ እሷን በደንብ መርዳት እንድችል ራሴን በይሖዋ አገልግሎት ማስጠመድና መንፈሳዊነቴን መገንባት እንዳለብኝ ይሰማኛል።”

20 መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ተስፋ ያደርጋል” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4, 7) በመሆኑም ይሖዋን የተወው የቤተሰባችሁ አባል እንደሚመለስ ተስፋ ማድረጋችሁ ስህተት አይደለም። በየዓመቱ በርካታ ሰዎች ንስሐ ገብተው ወደ ይሖዋ ድርጅት ይመለሳሉ። ይሖዋ ንስሐ ስለገቡ አይናደድም። ከዚህ ይልቅ “ይቅር” ለማለት ዝግጁ ነው።—መዝ. 86:5

ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ አድርጉ

21, 22. ነፃ ምርጫህን ከምትጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

21 ይሖዋ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ነፃ ምርጫ ሰጥቷቸዋል። (ዘዳግም 30:19, 20ን አንብብ።) ይሁንና ይህ መብት ከባድ ኃላፊነት ያስከትላል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ራሱን እንደሚከተለው በማለት መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘የትኛውን መንገድ እየተከተልኩ ነው? ሥራ፣ መዝናኛ ወይም ቤተሰብ ከይሖዋ እንዲያርቀኝ እየፈቀድኩ ነው?’

22 ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር መቼም ቢሆን አይቀንስም። ከይሖዋ ልንርቅ የምንችለው እኛ ራሳችን የተሳሳተ ጎዳና ለመከተል ከመረጥን ብቻ ነው። (ሮም 8:38, 39) ይህ ደግሞ እንዲደርስብን አንፈልግም። እንግዲያው ምንም ነገር ከይሖዋ እንዳያርቀን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ቁርጥ ውሳኔያችንን ልናሳይ የምንችልባቸውን ሌሎች አራት አቅጣጫዎች ያብራራል።

^ စာပိုဒ်၊ 10 የሥራ መስክ ስለመምረጥ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 38 ተመልከት።

^ စာပိုဒ်၊ 15 በዚህ ረገድ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የኅዳር 2011 ንቁ! መጽሔትን ከገጽ 17-19 ተመልከት።