በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ

እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ

“እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላ. 3:13

1, 2. ይቅር ባይ ለመሆን ፈቃደኛ መሆን አለመሆንህን በቁም ነገር ልታስብበት የሚገባው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለኃጢአት ያለውን አመለካከትና ኃጢአት ስንሠራ ምን እንደሚሰማው እንድንገነዘብ ያስችለናል። በተጨማሪም ይቅርታ ማድረግን አስመልክቶ በርካታ ትምህርቶችን ይዟል። ይሖዋ ዳዊትንና ምናሴን ይቅር እንዲላቸው ያነሳሳው ለፈጸሙት ኃጢአት የነበራቸው አመለካከት እንደሆነ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። መጸጸታቸው ማለትም በፈጸሙት ነገር ከልብ ማዘናቸው ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙ፣ መጥፎ ሥራቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉና እውነተኛ ንስሐ እንዲገቡ አስችሏቸዋል። በመሆኑም የይሖዋን ሞገስ እንደገና ማግኘት ችለዋል።

2 እስቲ አሁን ደግሞ ይቅር ባይነትን ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው። የምናሴ የግፍ ድርጊት ሰለባ ከሆኑት ንጹሐን ሰዎች መካከል አንዱ ዘመድህ ቢሆን ለምናሴ ምን ዓይነት አመለካከት ይኖርህ ነበር? ይቅርታ ታደርግለት ነበር? የምንኖረው ሕገወጥነት፣ ዓመፅና ራስ ወዳድነት በነገሠበት ዓለም ውስጥ ስለሆነ ይህን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው። ታዲያ አንድ ክርስቲያን የይቅር ባይነትን መንፈስ ማዳበር ያለበት ለምንድን ነው? ስሜት የሚጎዳ ወይም ፍትሐዊ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጸምብህ ስሜትህን ተቆጣጥረህ ጉዳዩን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ለመያዝና ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ለመሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?

ይቅር ባይ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

3-5. (ሀ) ኢየሱስ አድማጮቹ ይቅር የማለትን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ምን ምሳሌ ተናገረ? (ለ) ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 18:21-35 ላይ ያለውን ምሳሌ ሲናገር ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው?

3 የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሲበድሉን እነሱን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆናችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ከቤተሰባችን አባላት፣ ከጓደኞቻችን፣ ከሌሎች ሰዎችና ከይሖዋ ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ይዘን እንድንቀጥል ያስችለናል። ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ሰዎች ምንም ያህል ጊዜ ቢበድሉን ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን ክርስቲያናዊ ግዴታችን እንደሆነ  ይናገራሉ። ኢየሱስ፣ አምላክ እንዲህ እንድናደርግ መጠበቁ ምክንያታዊ እንደሆነ ለማስረዳት ሲል ዕዳ ስለነበረበት ባሪያ የሚያወሳ ምሳሌ ተናግሮ ነበር።

4 ባሪያው፣ አንድ የቀን ሠራተኛ 60,000,000 ቀናት ሠርቶ የሚያገኘውን ያህል ገንዘብ ከጌታው ተበድሮ ነበር፤ ያም ሆኖ ጌታው ዕዳውን ሰረዘለት። ከዚያም ባሪያው ወጥቶ ሲሄድ የ100 ቀን ደሞዝ የሚያህል ገንዘብ ብቻ የተበደረውን እንደ እሱ ያለ ባሪያ አገኘ። ባለ ዕዳውም እንዲታገሠው ለመነው፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕዳ የተሰረዘለት ባሪያ ግን ባልንጀራውን ወህኒ ቤት አሳሰረው። ይህ ሁኔታ የእነዚህን ባሪያዎች ጌታ በእጅጉ አስቆጣው። ጌታውም “እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም?” አለው። “ጌታውም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ያለበትን ዕዳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ [ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ያልሆነውን ባሪያ] ለወህኒ ቤት ጠባቂዎቹ አሳልፎ ሰጠው።”—ማቴ. 18:21-34

ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ሲናገር ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ሲናገር ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ኢየሱስ “እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል” ብሏል። (ማቴ. 18:35) ኢየሱስ ለማለት የፈለገው ግልጽ ነው። ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የሠራናቸው ኃጢአቶች የይሖዋን መሥፈርት ማሟላት እንደማንችል በግልጽ ያሳያሉ። ይሁንና ይሖዋ እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው፤ እንዲያውም በምሳሌያዊ አነጋገር አንድን ሰሌዳ ሙልጭ አድርጎ ያጸዳ ያህል ነው። በመሆኑም የይሖዋ ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የበደሉትን ሰዎች ይቅር የማለት ግዴታ አለበት። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል፤ እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው።—ማቴ. 6:14, 15

6. ይቅር ማለት ሁልጊዜ ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው?

6 ‘ይህ ሐሳብ ጥሩ ነው፤ ይሁንና ይህን ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሲያስቀይሙን ስሜታዊ እንሆናለን። አንድ ሰው ይናደድ፣ ክህደት እንደተፈጸመበት ይሰማው፣ ፍትሕ የማግኘት አልፎ ተርፎም የበቀል ስሜት ያድርበት ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች ያስቀየማቸውን  ሰው መቼም ቢሆን ይቅር ሊሉት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ሌሎችን ይቅር እንድትል እንደሚፈልግ ማስታወስ ይኖርብሃል፤ ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳህ ይችላል?

ስሜታችሁን አጢኑ

7, 8. ሌሎች በፈጸሙት ደግነት የጎደለው ድርጊት በምትናደድበት ወቅት ይቅር ባይ ለመሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?

7 ስንበደል ወይም በደል እንደተፈጸመብን ሲሰማን ስሜታዊ ሆነን መልስ መስጠት ይቀናናል። ንዴትን አስመልክቶ የተደረገ ጥናት፣ አንድ ወጣት በተናደደበት ጊዜ ያጋጠመውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት . . . በጣም ተናድጄ ስለነበር ፈጽሞ ወደ ቤት ተመልሼ እንደማልመጣ በመዛት ከቤት ወጣሁ። ወቅቱ በጋ ሲሆን ደስ በሚል መንገድ ላይ ብዙ ተጓዝኩ፤ አካባቢው ሰላም የሰፈነበትና የሚያምር መሆኑ ቀስ በቀስ እንድረጋጋና ውስጣዊ ሰላም እንዲሰማኝ አደረገኝ። ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ የጸጸት ስሜት ተሰምቶኝና ንዴቴ በርዶ ወደ ቤት ተመለስኩ።” ይህ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጊዜ ወስደህ ለመረጋጋት ጥረት ማድረግህና ነገሩን በእርጋታ ለማጤን መሞከርህ በኋላ የምትቆጭበትን ነገር ከማድረግ እንድትቆጠብ ሊረዳህ ይችላል።—መዝ. 4:4፤ ምሳሌ 14:29፤ ያዕ. 1:19, 20

8 ይሁንና ለመረጋጋት ጥረት አድርገህም ንዴትህ ባይበርድልህስ? እንድትናደድ ያደረገህ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክር። ተገቢ ባልሆነ ወይም አክብሮት በጎደለው መንገድ እንደተያዝክ ስለተሰማህ ነው? ወይስ ግለሰቡ ሆን ብሎ አንተን ለመጉዳት እንዳደረገው ስለተሰማህ? የፈጸመው ድርጊት በእርግጥ ያን ያህል ከባድ ነው? እንድትናደድ ያደረገህን ነገር ለይተህ ማወቅህ ከሁሉ የተሻለና ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንድትወስድ ያስችልሃል። (ምሳሌ 15:28ን፤ 17:27ን አንብብ።) ጉዳዩን በዚህ መንገድ ማጤንህ ይበልጥ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖርህና ይቅር ባይ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆን ቢችልም የአምላክ ቃል ‘የልብህን ሐሳብና ዓላማ’ እንዲመረምር መፍቀድ ይኖርብሃል፤ በተጨማሪም ቃሉ ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል እንድትችል ይረዳሃል።—ዕብ. 4:12

አንተን ለመጉዳት ሆን ተብሎ እንደተደረገ ይሰማሃል?

9, 10. (ሀ) በደል እንደተፈጸመብህ ሆኖ በሚሰማህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? (ለ) አዎንታዊ አመለካከት መያዝና ይቅር ባይ መሆን በሕይወትህ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል?

9 በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንድንናደድ የሚያደርጉ በርካታ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ለምሳሌ፣ መኪና እየነዳህ ሳለ በሌላ መኪና ከመገጨት ለጥቂት ተረፍክ እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ? አንዳንድ አሽከርካሪዎች በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ በሌላኛው አሽከርካሪ ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩ የሚገልጽ ዘገባ አንብበህ ታውቅ ይሆናል። አንተ ግን ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን እንዲህ ያለ ነገር ማድረግ እንደማትፈልግ ግልጽ ነው።

10 በዚህ ወቅት ነገሮችን ቆም ብሎ ማሰብ ምንኛ የተሻለ ነው! ትኩረትህ በሆነ ምክንያት በመከፋፈሉ የተነሳ ለተፈጠረው ሁኔታ አንተም በተወሰነ መጠን ተጠያቂ ልትሆን ትችላለህ። ወይም ደግሞ አደጋ ሊያደርስብህ የነበረው መኪና ችግር ይኖርበት ይሆናል። ከዚህ ሁኔታ ማየት እንደምንችለው አስተዋይነት፣ ነገሮችን ሰፋ አድርጎ መመልከትና ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ቁጣን፣ ብስጭትንና ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን ለመቀነስ ይረዳል። መክብብ 7:9 “የሞኞች ቍጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣ በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል” ይላል። ሁሉ ነገር አንተን ለማጥቃት ሆን ተብሎ እንደተደረገ አይሰማህ። ብዙውን ጊዜ፣ ሆን ተብሎ በአንተ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት እንደሆነ የምታስበው ነገር የተከሰተው በሌሎች አለፍጽምና ምክንያት ይሆናል፤ አሊያም እንዲህ የተሰማህ ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ባለመረዳትህ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው በድርጊት ወይም በንግግር እንደጎዳህ ሲሰማህ ሰፋ ያለ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርግ፤ እንዲሁም በፍቅር ተነሳስተህ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ሁን። እንዲህ ካደረግክ ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለህ።—1 ጴጥሮስ 4:8ን አንብብ።

‘ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ’

11. የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን ሰዎች ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?

11 በአገልግሎት ላይ ሳለህ አንድ ሰው ቢያመናጭቅህ ራስህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?  ኢየሱስ 70 ሰባኪዎችን ሲልክ በሚሄዱበት ቤት ሁሉ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ እንዲሉ ነግሯቸው ነበር። ኢየሱስ “ሰላም ወዳድ ሰው ከሌለ ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል። ሰላም ወዳድ ሰው ካለ ግን ሰላማችሁ ያርፍበታል” ብሏል። (ሉቃስ 10:1, 5, 6) በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሲሰጡን ደስ ይለናል፤ ምክንያቱም የምንነግራቸው መልእክት ጥቅም ያስገኝላቸዋል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የምናገኛቸው ሰዎች የሚሰጡት መልስ ሰላም የሚያደፈርስ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ኢየሱስ ለቤቱ ባለቤት የተመኘንለት ሰላም እኛው ጋር መቆየት እንዳለበት ተናግሯል። ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን በእያንዳንዱ ቤት የምናገኛቸውን ሰዎች አነጋግረን ስናበቃ ውስጣዊ ሰላም ሊኖረን ይገባል። ሰዎች በሚሰጡን ምላሽ የምንበሳጭ ከሆነ ሰላማችንን መጠበቅ አንችልም።

12. ጳውሎስ በ⁠ኤፌሶን 4:31, 32 ላይ በተናገረው መሠረት ምን ማድረግ አለብን?

12 በክርስቲያናዊ አገልግሎት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ ሰላምህን ለመጠበቅ ጥረት አድርግ። ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ሲባል መጥፎ ባሕርያቸውን ትክክል እንደሆነ አድርገህ ትቀበላለህ ወይም ያደረሱትን ጉዳት አቅልለህ ትመለከተዋለህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለ በደል ሲፈጸምብህ ቅሬታ እንዳያድርብህና ሰላምህን እንዳታጣ ጥረት ታደርጋለህ ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች አሉታዊ ሐሳቦችን ማውጠንጠናቸውና ሌሎች የፈጸሙባቸውን ደግነት የጎደለው ድርጊት ማብሰልሰላቸው ደስታቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል። አንተ ግን እነዚህ ነገሮች እንዲቆጣጠሩህ መፍቀድ አይኖርብህም። ቂም ይዘህ ደስተኛ ልትሆን እንደማትችል አስታውስ። በመሆኑም ይቅር ባይ ሁን!—ኤፌሶን 4:31, 32ን አንብብ።

ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ምላሽ ስጡ

13. (ሀ) አንድ ክርስቲያን በጠላቱ ራስ ላይ ‘ፍም የሚከምረው’ እንዴት ነው? (ለ) የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥመን ገርነት ማሳየታችን ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

13 አንዳንድ ጊዜ የበደለህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት እንዲገነዘብ ማድረግ ትችል ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “‘ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።’ በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።” (ሮም 12:20, 21) የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥምህ ጉዳዩን ረጋ ብለህ ለመፍታት ጥረት በማድረግ ልበ ደንዳና የሆነ ሰው እንኳ ልቡ እንዲለሰልስና መልካም ባሕርይው ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ትችላለህ። አስተዋይ በመሆን፣ የሰዎችን ችግር እንደራስ አድርጎ በመመልከት አልፎ ተርፎም ርኅራኄ በማሳየት የበደለህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቅ ልትረዳው ትችላለህ። ግለሰቡ የሚሰጠው ምላሽ ምንም ይሁን ምን ገርና ደግ መሆንህ ያሳየኸውን መልካም ምግባር ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል።—1 ጴጥ. 2:12፤ 3:16

14. አንድ ሰው የፈጸመብህ በደል ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ቂም መያዝ የማይኖርብህ ለምንድን ነው?

14 ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ቅርርብ መፍጠር ተገቢ የማይሆንባቸው ለየት ያሉ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት የጉባኤው አባላት የነበሩና ኃጢአት ሠርተው ንስሐ ባለመግባታቸው ከተወገዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት አይኖርብንም። ተወግዶ የነበረ አንድ ግለሰብ አንተን በግል ጎድቶህ ከነበረ ንስሐ ገብቶ ቢመለስም እንኳ እሱን ይቅር ለማለት በጣም ሊከብድህ ይችላል፤ ምክንያቱም የደረሰብህ የስሜት ቁስል ቶሎ አይሽርም። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ይቅር ማለት እንድትችል ወደ ይሖዋ አዘውትረህ መጸለይ ይኖርብህ ይሆናል። ደግሞስ በሌላ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ነገር እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ይሖዋ ግን ያውቃል። የሰዎችን ውስጣዊ ዝንባሌ ይመረምራል፤ እንዲሁም ኃጢአተኞችን በትዕግሥት ይይዛል። (መዝ. 7:9፤ ምሳሌ 17:3) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አድርጉ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ ስለተጻፈ ለአምላክ ቁጣ ዕድል ስጡ።” (ሮም 12:17-19) ታዲያ በሌላ ሰው ላይ  መፍረድህ ትክክል ሊሆን ይችላል? በፍጹም! (ማቴ. 7:1, 2) ይሁንና ይሖዋ በትክክል እንደሚፈርድ መተማመን ትችላለህ።

15. በደል በፈጸመብን ሰው ላይ ከልክ በላይ እንዳንቆጣ ምን ሊረዳን ይችላል?

15 አንድ ሰው እንደበደለህ ከተሰማህና ግለሰቡ ንስሐ ቢገባም ይቅር ለማለት የሚከብድህ ከሆነ እሱም ቢሆን ከከባድ ችግር ጋር እየታገለ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። በተጨማሪም የወረሰው አለፍጽምና ከሚያስከትልበት ችግር ነፃ አይደለም። (ሮም 3:23) ይሖዋ ፍጹማን ላልሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ይራራል። ስለሆነም ለበደለን ሰው መጸለያችን ተገቢ ነው። ደግሞም ስለ አንድ ሰው እየጸለይን በእሱ ላይ ቂም እንደማንይዝ ግልጽ ነው። ኢየሱስ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” ብሎ መናገሩ ደግነት የጎደለው ድርጊት በሚፈጽሙብን ሰዎች ላይ እንኳ ቂም መያዝ እንደሌለብን በግልጽ ያሳያል።—ማቴ. 5:44

16, 17. ክርስቲያን ሽማግሌዎች አንድ ኃጢአተኛ ወደ ጉባኤ እንዲመለስ ሲወስኑ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል? ለምንስ?

16 ክርስቲያን ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ከኃጢአት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የማየት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ወንድሞች ስለ ጉዳዩ የአምላክን ያህል የተሟላ ግንዛቤ አይኖራቸውም፤ ይሁንና በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ውሳኔያቸው በአምላክ ቃል ውስጥ ከሰፈረው መመሪያ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በሚያዩበት ወቅት ውሳኔ የሚያደርጉት የይሖዋን እርዳታ በጸሎት ከጠየቁ በኋላ ስለሆነ ውሳኔያቸው የይሖዋን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ይሆናል።—ማቴ. 18:18

ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው

17 በዚህ ረገድ ታማኝ መሆን ይኖርብናል። ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ንስሐ ገብተው ወደ ጉባኤ ሲመለሱ ይቅር ልትሏቸውና እንደምትወዷቸው ልትገልጹላቸው ትችላላችሁ? (2 ቆሮ. 2:5-8) በተለይ ግለሰቡ የሠራው ኃጢአት አንተን ወይም የምትወዳቸውን ሰዎች ጎድቶ ከሆነ ይቅርታ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በይሖዋና እሱ በጉባኤው አማካኝነት ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት መጣል የጥበብ አካሄድ ነው። እንዲህ ካደረግክ በነፃ ይቅር እንደምትል ታሳያለህ።—ምሳሌ 3:5, 6

18. በነፃ ይቅር ማለትህ ምን ጥቅሞች ያስገኝልሃል?

18 የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች ይቅር ባይ መሆን ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝበዋል። ይቅር ባይነት ቁጣንና ንዴትን እንድንተው ስለሚያስችለን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። ከዚህም ሌላ ከሌሎች ሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል። ከዚህ በተቃራኒ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆን ጤንነታችን እንዲቃወስ፣ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሻክር፣ ውጥረት እንዲያድርብንና ከሌሎች ጋር መግባባት ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋል። ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን የሚያስገኘው ከሁሉ የላቀው በረከት በሰማይ ካለው አባታችን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረጉ ነው።—ቆላስይስ 3:12-14ን አንብብ።