በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅቶ ስለመጠበቅ ከኢየሱስ ሐዋርያት ተማሩ

ነቅቶ ስለመጠበቅ ከኢየሱስ ሐዋርያት ተማሩ

“ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ።”​—ማቴ. 26:38

1-3. ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ነቅተው እንዳልጠበቁ የሚያሳየው ምንድን ነው? ከስህተታቸው ተምረው ነበር የምንለውስ ለምንድን ነው?

እስቲ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ስለተከናወነው ነገር ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ወደሚገኘውና ብዙ ጊዜ ወደሚያዘወትርበት የጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ መጥቷል። እዚህ ቦታ የመጣው ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ነው። ኢየሱስ የሚያስጨንቁ ሐሳቦች በአእምሮው ይመላለሱ ስለነበር ለመጸለይ እንዲችል ገለል ያለ ቦታ ማግኘት ፈልጓል።​—ማቴ. 26:36፤ ዮሐ. 18:1, 2

2 ከሐዋርያቱ መካከል ሦስቱ ይኸውም ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስን ተከትለው ወደ አትክልት ቦታው ዘልቀው ገብተዋል። ኢየሱስ “እዚህ ሁኑና ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” ካላቸው በኋላ ሊጸልይ ሄደ። ተመልሶ ሲመጣ ግን ወዳጆቹ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዷቸው አገኛቸው። አሁንም በድጋሚ “ነቅታችሁ ጠብቁ” ሲል ተማጸናቸው። ሆኖም ከዚያ በኋላ ሁለት ጊዜ ወደ እነሱ ሲመለስ አንቀላፍተው ነበር! ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በዚያው ምሽት ሁሉም ሐዋርያት በመንፈሳዊ ነቅተው መጠበቅ ሳይችሉ ቀሩ። እንዲያውም ኢየሱስን ጥለውት ሸሹ!​—ማቴ. 26:38, 41, 56

3 ሐዋርያቱ ነቅተው መጠበቅ ስለተሳናቸው በእጅጉ እንደተቆጩ የተረጋገጠ ነው። እነዚህ ታማኝ ሰዎች ከስህተታቸው ለመማር ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መመልከት እንደሚቻለው እነዚህ ደቀ መዛሙርት ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ግሩም አርዓያ ትተዋል። ሐዋርያቱ የተከተሉት የታማኝነት ጎዳና ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውም የእነርሱን አርዓያ እንዲከተሉ እንዳነሳሳቸው ጥርጥር የለውም። ዛሬ፣ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ነቅተን መጠበቅ ያስፈልገናል። (ማቴ. 24:42) እንግዲያው ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የምናገኛቸውን ሦስት ትምህርቶች እስቲ እንመልከት።

የት መስበክ እንዳለባቸው የሚሰጣቸውን መመሪያ ለመከተል ንቁ ነበሩ

4, 5. መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስንና የጉዞ ጓደኞቹን የመራቸው እንዴት ነው?

4 ከሐዋርያቱ የምናገኘው የመጀመሪያው ትምህርት የሚከተለው  ነው፦ የት መስበክ እንዳለባቸው የሚሰጣቸውን አመራር ለመከተል ንቁ ነበሩ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ያለ አንድ ዘገባ፣ ጳውሎስና የጉዞ ባልደረቦቹ ለየት ያለ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ እንዴት እንደመራቸው ይተርካል። (ሥራ 2:33) እስቲ ምን እንዳጋጠማቸው ለማወቅ አብረናቸው እንጓዝ።​—የሐዋርያት ሥራ 16:6-10ን አንብብ።

5 ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ በደቡባዊ ገላትያ ከምትገኘው የልስጥራ ከተማ ተነስተዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ወደ ምዕራብ የሚያቀና ሮማውያን የሠሩት አውራ ጎዳና ላይ ደረሱ፤ ይህ ጎዳና በእስያ አውራጃ ውስጥ ብዙ ሕዝብ ወደሚኖርበት ክልል ይወስዳል። እነዚህ ወንድሞች ስለ ክርስቶስ መስማት የሚገባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ባሉባቸው ከተሞች ውስጥ ለመስበክ ስላሰቡ ይህን መንገድ ተከትለው ለመሄድ ፈለጉ። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ እንዳይቀጥሉ የሚያግድ ነገር ገጠማቸው። ቁጥር 6 እንዲህ ይላል፦ “መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በእስያ አውራጃ እንዳይናገሩ ስለከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አድርገው አለፉ።” መንፈስ ቅዱስ ይህን እንዴት እንዳደረገ ባይገለጽም መንገደኞቹ በእስያ አውራጃ እንዳይሰብኩ ከለከላቸው። ኢየሱስ በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ጳውሎስንና ባልንጀሮቹን በተለየ አቅጣጫ ሊመራቸው እንደፈለገ ግልጽ ነበር።

6, 7. (ሀ) ጳውሎስና ሌሎቹ መንገደኞች ወደ ቢቲኒያ ሲቃረቡ ምን አጋጠማቸው? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ምን ዓይነት ውሳኔ አደረጉ? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ?

6 ታዲያ እነዚህ ለመስበክ የጓጉ መንገደኞች ወዴት ሄዱ? ቁጥር 7 “ወደ ሚስያ በወረዱ ጊዜ ወደ ቢቲኒያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ሆኖም የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም” በማለት ይነግረናል። ጳውሎስና ባልደረቦቹ በእስያ እንዳይሰብኩ በመከልከላቸው ወደ ሰሜን በማቅናት በቢቲኒያ ከተሞች ለመስበክ አሰቡ። ይሁን እንጂ ወደ ቢቲኒያ ሲቃረቡ ኢየሱስ አሁንም በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ አገዳቸው። በዚህ ጊዜ እነዚህ ወንድሞች ግራ ሳይገባቸው አልቀረም። ምን እንደሚሰብኩና እንዴት እንደሚሰብኩ ያውቃሉ፤ የት እንደሚሰብኩ ግን አያውቁም። ሁኔታውን በዚህ መልክ ልናስቀምጠው እንችላለን፦ ወደ እስያ የሚያስገባቸውን በር አንኳኩ፤ ሆኖም በሩ ሳይከፈትላቸው ቀረ። ወደ ቢቲኒያ የሚያስገባውን በር አንኳኩ፤ አሁንም በሩ አልተከፈተላቸውም። ታዲያ ማንኳኳታቸውን ያቆሙ ይሆን? በፍጹም፣ እነዚህ ቀናተኛ ሰባኪዎች ማንኳኳታቸውን አላቆሙም!

7 በዚህ ጊዜ እነዚህ ወንድሞች ያደረጉት ውሳኔ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ይመስላል። ቁጥር 8 “ስለዚህ በሚስያ አልፈው ወደ ጥሮአስ ወረዱ” በማለት የወሰዱትን እርምጃ ይነግረናል። ሰዎቹ ወደ ምዕራብ ዘወር በማለት በርካታ ከተሞችን እያለፉ 563 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ ወደ መቄዶንያ የሚወስደውን መርከብ ለመያዝ ይበልጥ አመቺ ወደሆነችው የጥሮአስ ወደብ ደረሱ። በዚያም ጳውሎስና ባልንጀሮቹ ለሦስተኛ ጊዜ በሩን አንኳኳ። በዚህ ጊዜ ግን በሩ ወለል ብሎ ተከፈተላቸው! ቁጥር 9 ቀጥሎ የሆነውን ሲተርክ “ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ ‘ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን’ ብሎ ሲለምነው አየ” ይላል። በመጨረሻ ጳውሎስ የት መስበክ እንዳለበት አወቀ። መንገደኞቹ ምንም ጊዜ ሳያባክኑ ወደ መቄዶንያ የሚወስዳቸው መርከብ ላይ ተሳፈሩ።

8, 9. ጳውሎስ ስላደረገው ጉዞ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

8 ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? የአምላክ መንፈስ ጣልቃ የገባው ጳውሎስ ወደ እስያ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ልብ በሉ። ኢየሱስም መመሪያ የሰጠው ጳውሎስ ወደ ቢቲኒያ ከተቃረበ በኋላ ነበር። በመጨረሻም፣ ኢየሱስ ጳውሎስን ወደ መቄዶንያ የመራው ጥሮአስ ከደረሰ በኋላ ነበር። ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል። (ቆላ. 1:18) ለምሳሌ፣ አቅኚ ለመሆን ወይም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውራችሁ ለማገልገል ታስቡ ይሆናል። ኢየሱስ በአምላክ መንፈስ አማካኝነት የሚመራችሁ ግን እዚህ ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያስችሏችሁን የተወሰኑ እርምጃዎች ከወሰዳችሁ በኋላ ሊሆን ይችላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ አሽከርካሪ መኪናውን ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ሊጠመዝዝ የሚችለው መኪናው እየተንቀሳቀሰ ከሆነ ብቻ ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ አገልግሎታችንን ልናሰፋ የምንችልበትን መንገድ የሚመራን ቢሆንም ይህን የሚያደርገው የምንንቀሳቀስ ይኸውም ግባችን ላይ ለመድረስ ከልብ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው።

9 ይሁንና ጥረታችሁ ወዲያውኑ ፍሬ ባያስገኝስ? የአምላክ መንፈስ እየመራችሁ እንዳልሆነ በማሰብ  ተስፋ ትቆርጣላችሁ? ጳውሎስም እንቅፋቶች ገጥመውት እንደነበረ አስታውሱ። ይሁን እንጂ የሚከፈት በር እስኪያገኝ ድረስ መፈለጉንና ማንኳኳቱን አላቆመም። እናንተም የተከፈተ “ትልቅ የሥራ በር” ለማግኘት ጥረት ማድረጋችሁን የምትቀጥሉ ከሆነ እንደ ጳውሎስ በረከት ልታገኙ ትችላላችሁ።​—1 ቆሮ. 16:9

በጸሎት ረገድ ንቁዎች ነበሩ

10. ነቅቶ ለመጠበቅ በጸሎት መትጋት የግድ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

10 አሁን ደግሞ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ወንድሞቻችን ንቁ ስለ መሆን ልናገኝ የምንችለውን ሁለተኛ ትምህርት እንመልከት፦ በጸሎት ረገድ ንቁዎች ነበሩ። (1 ጴጥ. 4:7) ነቅቶ ለመጠበቅ በጸሎት መትጋት የግድ አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ከመያዙ ቀደም ብሎ በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ በነበረበት ወቅት ለሦስቱ ሐዋርያት “ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ሳታሰልሱም ጸልዩ” ብሏቸው እንደነበር አስታውሱ።​—ማቴ. 26:41

11, 12. ሄሮድስ፣ በጴጥሮስም ሆነ በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ ምን ስደት አደረሰ?

11 በዚያ ወቅት ከነበሩት ሐዋርያት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ የሚያስገኘውን ውጤት ከጊዜ በኋላ በራሱ ሕይወት ለማየት ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 12:1-6ን አንብብ።) በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ ሄሮድስ በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ ሲል ክርስቲያኖችን ማሳደድ እንደጀመረ እንመለከታለን። ያዕቆብ፣ ከሐዋርያቱ አንዱ እንደሆነና ከኢየሱስም ጋር በጣም ይቀራረብ እንደነበረ ሄሮድስ ሳያውቅ አይቀርም። በመሆኑም ሄሮድስ “ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው።” (ቁጥር 2) በዚህም ምክንያት ጉባኤው ተወዳጅ የሆነ አንድ ሐዋርያ አጣ። ይህ ለወንድሞች እንዴት ያለ ትልቅ ፈተና ነበር!

12 ሄሮድስ ቀጥሎ ምን አደረገ? ቁጥር 3 “ይህ ድርጊቱ አይሁዳውያንን እንዳስደሰተ ባየ ጊዜ ጴጥሮስን ደግሞ በቁጥጥር ሥር አዋለው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። ይሁን እንጂ ጴጥሮስን ጨምሮ አንዳንድ ሐዋርያት ከእስር ቤት በተአምራዊ መንገድ የወጡባቸው ወቅቶች ነበሩ። (ሥራ 5:17-20) ሄሮድስ ይህን ሳያውቅ አልቀረም። ተንኮለኛ የሆነው ይህ የፖለቲካ ሰው ጴጥሮስ ሊያመልጥ የሚችልበት ክፍተት እንዲፈጠር አልፈለገም። በመሆኑም ጴጥሮስን “በአራት ፈረቃ፣ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህንም ያደረገው ከፋሲካ በኋላ ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው አስቦ ነው።” (ቁጥር 4) እስቲ አስቡት! ሄሮድስ፣ ጴጥሮስ እንዳያመልጥ ለማድረግ ሲል በ2 ጠባቂዎች መካከል በሰንሰለት እንዲታሠር ያደረገ ሲሆን እነዚህን ጨምሮ 16 ጠባቂዎች ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ እንዲጠብቁት አድርጎ ነበር። የሄሮድስ ዕቅድ ከፋሲካ በዓል በኋላ በጴጥሮስ ላይ የሞት ብይን በማስተላለፍ ሕዝቡን ማስደሰት ነበር። ታዲያ እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የእምነት ባልንጀሮቹ ምን ማድረግ ይችላሉ?

13, 14. (ሀ) ጴጥሮስ በታሰረበት ወቅት ጉባኤው ምን አደረገ? (ለ) የጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮች በጸሎት ረገድ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

13 ጉባኤው ምን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ ያውቅ ነበር። ቁጥር 5 እንዲህ ይላል፦ “ጴጥሮስ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፤ ሆኖም ጉባኤው ስለ እሱ ወደ አምላክ አጥብቆ ይጸልይ ነበር።” አዎ፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ስለዚህ ተወዳጅ ወንድማቸው አጥብቀው ልባዊ ጸሎት ያቀርቡ ነበር። የያዕቆብ መገደል ተስፋ እንዲቆርጡ ወይም ጸሎት ምንም ፋይዳ እንደሌለው እንዲሰማቸው አላደረጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡት ጸሎት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ተገንዝበው ነበር። አገልጋዮቹ የሚያቀርቧቸው ጸሎቶች ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙ ከሆነ መልስ ይሰጣል።​—ዕብ. 13:18, 19፤ ያዕ. 5:16

14 የጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮች ካደረጉት ነገር ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? ነቅቶ መጠበቅ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችንም ጭምር መጸለይን ያካትታል። (ኤፌ. 6:18) መከራ እየደረሰባቸው ስላሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሰማችሁት ነገር አለ? አንዳንዶቹ ስደት እየደረሰባቸው ወይም ከመንግሥት እገዳ ተጥሎባቸው አሊያም የተፈጥሮ አደጋ ደርሶባቸው ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ወንድሞች አስመልክታችሁ ለምን ከልብ የመነጨ ጸሎት አታቀርቡም? እምብዛም ጎልቶ የማይታይ መከራ ተቋቁመው የሚኖሩ ሌሎች ክርስቲያኖች እንዳሉም ታውቁ ይሆናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ከቤተሰብ ችግር፣ ከተስፋ መቁረጥ ወይም እምነትን ከሚፈታተን ሌላ ችግር ጋር እየታገሉ ይሆናል። ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነውን ይሖዋን ከማነጋገራችሁ በፊት፣ ስማቸውን ጠቅሳችሁ ልትጸልዩላቸው የምትችሏቸውን ግለሰቦች  ለማስታወስ ለምን ቆም ብላችሁ አታስቡም?​—መዝ. 65:2

15, 16. (ሀ) የይሖዋ መልአክ ጴጥሮስን ከእስር ነፃ ያወጣው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (ከታች ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ይሖዋ ጴጥሮስን ስላዳነበት መንገድ ማሰላሰላችን የሚያበረታታን እንዴት ነው?

15 እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ጴጥሮስ መለስ እንበል፣ እንዴት ሆኖ ይሆን? ጴጥሮስ እስር ቤት ባሳለፈው የመጨረሻ ሌሊት ላይ አስደናቂ የሆኑ ሁኔታዎች በተከታታይ ሲፈጸሙ ሊመለከት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 12:7-11ን አንብብ።) እስቲ የተከሰተውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር፦ ጴጥሮስ በሁለት ጠባቂዎች መካከል ሆኖ ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ በድንገት በታሰረበት ክፍል ውስጥ ደማቅ ብርሃን በራ። አንድ መልአክ ጴጥሮስ አጠገብ ቆመና በፍጥነት ቀሰቀሰው፤ በዚህ ወቅት ጠባቂዎቹ መልአኩን እንዳላዩት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ የታሰረበት ሰንሰለት አለምንም ችግር ከእጆቹ ላይ ወደቀ! ከዚያም መልአኩ ጴጥሮስን እየመራ ከታሰረበት ክፍል ካወጣው በኋላ ውጭ የቆሙትን ጠባቂዎች አልፈው ወደ ትልቁ የብረት መዝጊያ ደረሱ፤ በዚህ ጊዜ መዝጊያው “በራሱ ተከፈተ።” ልክ ከእስር ቤቱ እንደወጡ መልአኩ ተሰወረ። ጴጥሮስ ነፃ ሆነ!

16 ይሖዋ አገልጋዮቹን ለማዳን ኃይሉን የሚጠቀም መሆኑን ስናስብ እምነታችን አይጠናከርም? እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከችግር ነፃ ያወጣናል ብለን አንጠብቅም። ሆኖም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሕዝቦቹን ለመጠበቅ ኃይሉን እንደሚጠቀም ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን። (2 ዜና 16:9) የሚደርስብንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም የሚያስችለንን ያህል ኃይል በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ 2 ጴጥ. 2:9) በተጨማሪም በቅርቡ ይሖዋ፣ በልጁ አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከማይደፈረው እስር ቤት ይኸውም ከሞት ነፃ ያወጣቸዋል። (ዮሐ. 5:28, 29) ዛሬም የተለያዩ መከራዎች ሲደርሱብን ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ይህ ነው የማይባል ድፍረት እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል።

እንቅፋቶች ቢኖሩም የተሟላ ምሥክርነት መስጠት

17. ጳውሎስ፣ በቅንዓትና በጥድፊያ ስሜት በመስበክ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

17 ነቅቶ ስለ መጠበቅ ከሐዋርያት የምናገኘው ሦስተኛው ትምህርት ደግሞ የሚከተለው ነው፦ የተለያዩ እንቅፋቶች ቢያጋጥሟቸውም የተሟላ ምሥክርነት ከመስጠት ወደኋላ አላሉም። በቅንዓትና በጥድፊያ ስሜት መስበክ ነቅቶ ለመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ነው። ወደ ብዙ ቦታዎች በመጓዝና በርካታ ጉባኤዎችን በማቋቋም በቅንዓት አገልግሏል። የተለያዩ መከራዎች የደረሱበት ቢሆንም ቅንዓቱም ሆነ የጥድፊያ ስሜቱ ፈጽሞ አልቀዘቀዘም።​—2 ቆሮ. 11:23-29

18. ጳውሎስ በሮም በጥበቃ ሥር ሳለ ምሥክርነት መስጠቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

18 ጳውሎስ ያከናወናቸውን ነገሮች አስመልክቶ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ከምናገኘው ዘገባ የመጨረሻውን እንመልከት፤ ታሪኩ የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 28 ላይ ነው። ጳውሎስ፣ ኔሮ ፊት ለመቅረብ ሮም ደርሷል። በዚያም በጥበቃ ሥር እንዲሆን ተደረገ፤ ምናልባትም በዚህ ወቅት እሱን ከሚጠብቀው ወታደር ጋር በሰንሰለት ሳይቆራኝ አልቀረም። ይሁን እንጂ ማንኛውም ዓይነት ሰንሰለት ይህን ቀናተኛ ሐዋርያ ዝም ሊያሰኘው አልቻለም! ጳውሎስ ለመመሥከር  የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች መፈለጉን አላቆመም። (የሐዋርያት ሥራ 28:17, 23, 24ን አንብብ።) ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ምሥክርነት ለመስጠት የአይሁዳውያንን ታላላቅ ሰዎች አስጠራ። ከዚያም ለመገናኘት በወሰኑበት ቀን ሰፋ ያለ ምሥክርነት ሰጣቸው። ቁጥር 23 እንዲህ ይላል፦ “[አይሁዳውያኑ] በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ቀን ከወሰኑ በኋላ ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያ ስፍራው መጡ። እሱም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት በመስጠትና ስለ ኢየሱስ ከሙሴ ሕግና ከነቢያት እየጠቀሰ አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ጉዳዩን አብራራላቸው።”

19, 20. (ሀ) ጳውሎስ ምሥክርነት በመስጠት ረገድ ውጤታማ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ሁሉም ሰው ምሥራቹን ባለመቀበሉ ተስፋ ቆርጦ ነበር? አብራራ።

19 ጳውሎስ ምሥክርነት በመስጠት ረገድ ውጤታማ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ቁጥር 23 በርካታ ምክንያቶችን እንደሚጠቅስ ልብ በሉ። (1) ትኩረት ያደረገው በአምላክ መንግሥትና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር። (2) “አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ” የአድማጮቹን ልብ ለመንካት ይጥር ነበር። (3) ቅዱሳን መጻሕፍትን እየጠቀሰ ያወያያቸው ነበር። (4) “ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ” በመመሥከር የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አሳይቷል። ጳውሎስ ጥሩ ምሥክርነት ቢሰጥም መልእክቱን የተቀበሉት ሁሉም አድማጮቹ አልነበሩም። ቁጥር 24 “አንዳንዶቹ የተናገረውን ነገር ሲያምኑ ሌሎቹ ግን አላመኑም” ይላል። በዚህም የተነሳ በመካከላቸው የሐሳብ መለያየት ተፈጠረና ሰዎቹ ተበታተኑ።

20 ታዲያ ጳውሎስ ሁሉም ሰው ምሥራቹን ባለመቀበሉ ተስፋ ቆርጦ ነበር? በፍጹም! የሐዋርያት ሥራ 28:30, 31 እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ኖረ፤ ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ይቀበላቸው ነበር፤ ያለምንም እንቅፋት በታላቅ የመናገር ነፃነት ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።” በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚደመደመው በዚህ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው።

21. ጳውሎስ በቁም እስር ላይ ሳለ ካደረገው ነገር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

21 ከጳውሎስ ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን? በቁም እስር ላይ ሳለ ከቤት ወደ ቤት ሄዶ ሊመሠክር አይችልም ነበር። ያም ቢሆን አዎንታዊ የሆነ አመለካከት ስለነበረው ወደ እሱ ለሚመጡ ሁሉ ይመሠክር ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ በርካታ የአምላክ ሕዝቦች በእምነታቸው ምክንያት በግፍ ቢታሰሩም ደስታቸውን ሳያጡ መስበካቸውን ይቀጥላሉ። አንዳንድ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ቤት ውለዋል፤ አሊያም በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት እንክብካቤ በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል ለዶክተሮች፣ ሊጠይቋቸው ለሚመጡና ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ ይሰብካሉ። ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት የመስጠት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ናቸው!

22. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጥቅም እንድናገኝ ምን ዝግጅት ተደርጎልናል? (ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) የዚህን አሮጌ ሥርዓት መጨረሻ በምንጠባበቅበት በአሁኑ ጊዜ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

22 እስካሁን ለማየት እንደሞከርነው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ሐዋርያትና ሌሎች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ካሳለፉት ታሪክ ብዙ ልንማረው የምንችለው ነገር አለ። የዚህን አሮጌ ሥርዓት መጨረሻ በምንጠባበቅበት በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በቅንዓትና በድፍረት በመመሥከር ረገድ የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ሁላችንም ስለ አምላክ መንግሥት “የተሟላ ምሥክርነት” የመስጠት ታላቅ ሥራ ተሰጥቶናል፤ በዚህ ዘመን ከዚህ መብት ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ነገር የለም!​—ሥራ 28:23

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ከዚህ በኋላ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የማየው በተለየ መንገድ ነው”

አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ስለ አምላክ መንግሥት ‘የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’ የተባለውን መጽሐፍ (በአማርኛ አይገኝም) ካነበበ በኋላ እንዲህ በማለት የተሰማውን ገልጿል፦ “ከዚህ በኋላ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የማየው በተለየ መንገድ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን አንብቤዋለሁ፤ ይሁንና ያኔ፣ የቆሸሸ መነጽር አድርጎ በሻማ ብርሃን መጽሐፉን የማንበብ ያህል ነበር። አሁን ግን የመጽሐፉን አስደናቂነት በፀሐይ ብርሃን እንደማየው ሆኖ ይሰማኛል።”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ ትልቁን የብረት መዝጊያ አልፎ እንዲሄድ አንድ መልአክ ረድቶታል