በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መስበክ የምችለው እንዴት ነው?’

‘መስበክ የምችለው እንዴት ነው?’

 ‘መስበክ የምችለው እንዴት ነው?’

በዓለም ዙሪያ፣ ከባድ የጤና ችግር ቢኖርባቸውም በስብከቱ ሥራ በታማኝነት በመካፈል ረገድ ግሩም አርዓያ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች አሉ። የሊትዌኒያ ዋና ከተማ በሆነችው በቪልኒየስ የምትኖረውን ዳሊያን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ዳሊያ በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ እህታችን ናት። ዳሊያ ከተወለደችበት ጊዜ ጀምሮ ሴረብረል አፖፕሌክሲ በሚባል በሽታ ትሠቃያለች። ይህ የጤና እክል ሽባ እንድትሆን ያደረጋት ከመሆኑም በላይ የመናገር ችግር አስከትሎባታል። በዚህም የተነሳ የምትናገረውን መረዳት የሚችሉት የቤተሰቧ አባላት ብቻ ናቸው። ዳሊያ የምትኖረው ከእናቷ ከጋሊና ጋር ሲሆን እሷም የሚያስፈልጋትን እንክብካቤ ታደርግላታለች። ዳሊያ፣ ሕይወቷ በመከራና በጭንቀት የተሞላ ቢሆንም አዎንታዊ የሆነ አመለካከት አላት። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

ጋሊና እንደሚከተለው በማለት ትናገራለች፦ “በ1999 አፖሎኒጃ የተባለች አንዲት ዘመዳችን ልታየን መጣች። አፖሎኒጃ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነችና መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ እንደምታውቅ ተገነዘብን፤ በመሆኑም ዳሊያ ብዙ ጥያቄዎችን ትጠይቃት ጀመር። ብዙም ሳይቆይ ዳሊያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ዳሊያ የምትናገረውን ለማስረዳት እኔም አልፎ አልፎ በጥናቱ ላይ እገኝ ነበር። በዚህ ወቅት ዳሊያ የምትማረው ነገር ሁሉ በጣም እየጠቀማት እንደሆነ አስተዋልኩ። ብዙም ሳይቆይ እኔም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።”

ዳሊያ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በደንብ እየገባት ሲመጣ አንድ ጉዳይ ያሳስባት ጀመር። በመጨረሻም “እንደ እኔ ያለ ሽባ የሆነ ሰው መስበክ የሚችለው እንዴት ነው?” በማለት ሲያስጨንቃት የነበረውን ነገር ለአፖሎኒጃ አውጥታ ነገረቻት። (ማቴ. 28:19, 20) አፖሎኒጃም ረጋ ብላ “አይዞሽ፣ ይሖዋ ይረዳሻል” በማለት አበረታታቻት። በእርግጥም ይሖዋ ረድቷታል።

ታዲያ ዳሊያ የምትሰብከው እንዴት ነው? የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው። አንዳንድ እህቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የያዙ ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት ይረዷታል። በመጀመሪያ ዳሊያ መጻፍ የምትፈልገውን ነገር ለእህቶች ትገልጽላቸዋለች። እነሱም የእሷን ሐሳብ በማቀነባበር ደብዳቤ ይጽፉላታል። በተጨማሪም ዳሊያ በሞባይል ስልኳ የጽሑፍ መልእክት በመላክ ትመሠክራለች። የአየሩ ጠባይ ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜም በመንገድ ላይና በአካባቢው በሚገኙ መናፈሻዎች የምታገኛቸውን ሰዎች ማነጋገር እንድትችል የጉባኤው አባላት ይዘዋት ይወጣሉ።

ዳሊያ እና እናቷ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ኅዳር 2004 ሁለቱም ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠመቁ። መስከረም 2008 በቪልኒየስ ውስጥ በፖላንድ ቋንቋ የሚመራ አንድ ቡድን ተቋቋመ። ቡድኑ ተጨማሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያስፈልጉት ስለነበር ዳሊያ እና እናቷ ቡድኑን ለመርዳት ወደዚያ ተዛወሩ። ዳሊያ እንዲህ ትላለች፦ “አገልግሎት ሳልወጣ ወሩ ሊያልቅብኝ ነው ብዬ የምጨነቅባቸው ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ስጸልይ፣ አገልግሎት ይዞኝ ለመውጣት የሚቀጥረኝ ሰው ወዲያውኑ አገኛለሁ።” ታዲያ ይህች ውድ እህታችን ስላለችበት ሁኔታ ምን ይሰማታል? እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “በሽታው ሽባ ያደረገው ሰውነቴን ነው እንጂ አእምሮዬን አይደለም። ለሌሎች ስለ ይሖዋ መናገር በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ!”