በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ መንፈስ የተመሩ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ አገልጋዮች

በአምላክ መንፈስ የተመሩ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ አገልጋዮች

 በአምላክ መንፈስ የተመሩ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ አገልጋዮች

“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ መንፈሱም ልኮኛል።”​—ኢሳ. 48:16 NW

1, 2. ጠንካራ እምነት ለማዳበር ምን ያስፈልጋል? በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ መመርመራችንስ ምን ማበረታቻ ይሰጠናል?

“እምነት ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር” እንዳልሆነ ከአቤል ዘመን ጀምሮ ከነበረው ታሪክ ማረጋገጥ ይቻላል። (2 ተሰ. 3:2) ለመሆኑ አንድ ሰው እምነት ሊኖረው የሚገባው ለምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ለማዳበርስ ምን ሊረዳው ይችላል? በአብዛኛው፣ እምነት የሚገኘው የአምላክን ቃል ከመስማት ነው። (ሮም 10:17) እምነት ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው። (ገላ. 5:22, 23) በመሆኑም ጠንካራ እምነት ለማዳበር የአምላክ መንፈስ ያስፈልገናል።

2 በእምነታቸው የሚጠቀሱ ወንዶችና ሴቶች ይህ ባሕርይ ሊኖራቸው የቻለው በተፈጥሮ ስላገኙት ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ምሳሌ የሚሆኑ የአምላክ አገልጋዮች “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ያላቸው ሰዎች ነበሩ። (ያዕ. 5:17) እነዚህ ሰዎች ጥርጣሬ የሚያድርባቸው፣ ፍርሃት የሚሰማቸውና ድክመቶች ያሉባቸው ነበሩ፤ ይሁንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት እንዲችሉ በአምላክ መንፈስ “ብርቱዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል።” (ዕብ. 11:34) የይሖዋ መንፈስ በጥንቶቹ ታማኝ አገልጋዮች ላይ እንዴት እንደሠራ መመልከታችን በእምነታችን ላይ ጥቃት በሚሰነዘርበት በዛሬው ጊዜ እምነታችንን ጠብቀን ለመመላለስ የሚያስችል ማበረታቻ ይሰጠናል።

የአምላክ መንፈስ ለሙሴ ኃይል ሰጥቶታል

3-5. (ሀ) ሙሴ ኃላፊነቱን የተወጣው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሆነ በምን እናውቃለን? (ለ) ይሖዋ መንፈሱን የሚሰጥበትን መንገድ አስመልክቶ ከሙሴ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

3 በ1513 ዓ.ዓ. ላይ በሕይወት ከነበሩት ሰዎች መካከል የሙሴን ያህል “እጅግ ትሑት” የሆነ ሰው አልነበረም። (ዘኍ. 12:3) ይህ ገር የሆነ የአምላክ አገልጋይ ከእስራኤል ብሔር ጋር በተያያዘ በርካታ ኃላፊነቶች ተሰጥተውት ነበር። የአምላክ መንፈስ ሙሴ ትንቢት እንዲናገር፣ ሕዝቡን እንዲዳኝና እንዲመራ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጽፍ እንዲሁም ተአምራትን እንዲሠራ አስችሎታል። (ኢሳይያስ 63:11-14ን አንብብ።) ያም ሆኖ ሙሴ፣ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት በጣም እንደከበደው በአንድ ወቅት በምሬት ተናግሯል። (ዘኍ. 11:14, 15) በመሆኑም ይሖዋ “በሙሴ ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ” ለ70 ሰዎች በመስጠት ሸክሙን እንዲያግዙት አድርጓል። (ዘኍ. 11:16, 17) እንደ እውነቱ ከሆነ የሙሴ ኃላፊነት ምንም ያህል ከባድ ቢመስልም ሙሴም ሆነ እሱን እንዲረዱት የተሾሙት 70 ሰዎች ሥራውን የሚያከናውኑት ብቻቸውን አልነበረም።

4 ሙሴ ለሥራው የሚመጥን ያህል መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶት ነበር። ሆኖም እሱ ላይ ከነበረው መንፈስ ተወስዶ ለሌሎች ከተሰጠ በኋላም ሥራውን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ያህል መንፈስ ነበረው። ሙሴ የነበረው መንፈስ ከሚያስፈልገው በታች አልነበረም፤ ሰባዎቹ ሽማግሌዎችም ከሚያስፈልጋቸው በላይ መንፈስ አልተሰጣቸውም። ይሖዋ ሁኔታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚያስፈልገንን ያህል መንፈስ ይሰጠናል። “አምላክ መንፈሱን ቆጥቦ አይሰጥም”፤ ከዚህ ይልቅ የሚሰጠው ‘በሙላት’ ነው።​—ዮሐ. 1:16፤ 3:34

5 መከራ እየደረሰብህ ነው? ያሉብህ ኃላፊነቶች ከመብዛታቸው የተነሳ ጊዜ እያሳጡህ እንደሆነ ይሰማሃል? በአንድ በኩል ከኑሮ ውድነት ወይም ካለብህ የጤና ችግር ጋር እየታገልክ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰብህን መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ደፋ ቀና እያልክ ነው? በጉባኤ ውስጥ ያሉብህን ከባድ ኃላፊነቶች ለመወጣት ጥረት እያደረግህ ነው? ያለህበት ሁኔታ ምን ይሁን ምን አምላክ ሁኔታውን ለመወጣት የሚያስችል ኃይል በመንፈሱ አማካኝነት ሊሰጥህ እንደሚችል እርግጠኛ ሁን።​—ሮም 15:13

መንፈስ ቅዱስ ባስልኤልን ብቁ እንዲሆን አድርጎታል

6-8. (ሀ) የአምላክ መንፈስ ባስልኤልና ኤልያብ ምን እንዲያከናውኑ አስችሏቸዋል? (ለ) ባስልኤልና ኤልያብ በአምላክ መንፈስ ይመሩ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው? (ሐ) በተለይ የባስልኤል ተሞክሮ የሚያበረታታ የሆነው እንዴት ነው?

6 በሙሴ ዘመን ይኖር የነበረው ባስልኤል በሕይወቱ ያጋጠመው  ነገር የአምላክ መንፈስ ስለሚሠራበት መንገድ ተጨማሪ ግንዛቤ ይሰጠናል። (ዘፀአት 35:30-35ን አንብብ።) ባስልኤል ለማደሪያው ድንኳን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲሠራ ተሹሞ ነበር። ለመሆኑ ይህን ከባድ ኃላፊነት ከመቀበሉ በፊት እንዲህ ዓይነት ሥራ ለማከናወን የሚያስችል የእጅ ጥበብ ሙያ ነበረው? ይኖረው ይሆናል፤ ይሁንና ከዚህ በፊት የተሰማራበት የሥራ መስክ ለግብፃውያን ጡብ ከመሥራት የዘለለ እንደማይሆን መገመት ይቻላል። (ዘፀ. 1:13, 14) ታዲያ ባስልኤል ይህን ውስብስብ ሥራ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ‘ጥበብ፣ ችሎታና እውቀት እንዲሁም ማናቸውም ዓይነት ሙያ’ እንዲኖረው መንፈሱን ሞላበት፤ ይህንንም ያደረገው “የጥበብ ሥራ እንዲሠራ” እንዲሁም “ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።” ባስልኤል በተፈጥሮው ምንም ዓይነት ተሰጥኦ ይኑረው መንፈስ ቅዱስ ይህን ችሎታውን ይበልጥ አሳድጎለታል። የኤልያብ ሁኔታም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ባስልኤልና ኤልያብ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ብቻ ሳይወሰኑ ሌሎችንም ማስተማራቸው በሙያው በደንብ የተካኑ እንዲሆኑ መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸው እንደነበር ይጠቁማል። አዎን፣ አምላክ የማስተማር ችሎታ ሰጥቷቸው ነበር።

7 ባስልኤልና ኤልያብ በአምላክ መንፈስ ይመሩ እንደነበር የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ የሥራቸው ውጤት በጣም ጠንካራ መሆኑ ነው። የሠሯቸው ነገሮች 500 ለሚያህሉ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። (2 ዜና 1:2-6) ዘመናዊ የሆኑ ድርጅቶች በምርታቸው ላይ ስማቸውን ወይም የንግድ ምልክታቸውን እንደሚያኖሩት ባስልኤልና ኤልያብ ይህን የማድረግ ፍላጎት አልነበራቸውም። በሠሩት ሥራ እንዲወደስ ያደረጉት ይሖዋን ነው።​—ዘፀ. 36:1, 2

8 በዛሬው ጊዜ አንዳንዶቻችን በግንባታና በኅትመት ሥራዎች እንደ መካፈል፣ የአውራጃ ስብሰባዎችን እንደ ማደራጀት፣ በአደጋ የተጎዱትን ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደ ማስተባበር ብሎም ደምን አስመልክቶ ያለንን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም ለማስረዳት ከሐኪሞችና ከሌሎች የሆስፒታል ሠራተኞች ጋር እንደ መነጋገር ያሉ ልዩ ችሎታ የሚጠይቁ ኃላፊነቶችን መወጣት ይኖርብን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ሥራዎች የሚከናወኑት ሙያው ባላቸው ሰዎች ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን ሥራው የሚሠራው ምንም ዓይነት ልምድ በሌላቸው ፈቃደኛ ግለሰቦች ነው። እነዚህ ሰዎች በሥራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የአምላክ መንፈስ እገዛ ያደርግላቸዋል። ሌሎች ከአንተ የተሻለ ብቃት እንዳላቸው ተሰምቶህ በይሖዋ አገልግሎት አንድ ዓይነት ኃላፊነት ከመቀበል ወደኋላ ያልክበት ጊዜ አለ? ይሖዋ፣ ያለህን እውቀትና ችሎታ በመንፈሱ አማካኝነት በማሳደግ እሱ የሚሰጥህን ማንኛውንም ኃላፊነት መወጣት እንድትችል የሚረዳህ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብሃል።

የአምላክ መንፈስ ኢያሱ ስኬታማ እንዲሆን ረድቶታል

9. እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጠማቸው? የትኛው ጥያቄ መልስ ያስፈልገዋል?

9 ሙሴና ባስልኤል በኖሩበት ዘመን በአምላክ መንፈስ ይመራ የነበረ ሌላም ሰው ነበር። እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ አማሌቃውያን ያልታሰበ ጥቃት ሰነዘሩባቸው። በመሆኑም እነዚህ የአምላክ ሕዝቦች ጥቃቱን መከላከል ነበረባቸው። እስራኤላውያን ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የውጊያ ልምድ ባይኖራቸውም ነፃ ከወጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦርነት መግጠም ግድ ሆነባቸው። (ዘፀ. 13:17፤ 17:8) ሆኖም ይህን ውጊያ የሚመራ አንድ ሰው ያስፈልግ ነበር። ታዲያ ለዚህ ኃላፊነት ብቁ የሚሆነው ማን ነው?

10. እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት ጠላቶቻቸውን ድል ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው?

10 የጦር መሪ እንዲሆን የተመረጠው ኢያሱ ነበር። ይሁንና ‘ለዚህ ሥራ እንድትመረጥ የሥራ ልምድህን አቅርብ’ ተብሎ ቢጠየቅ ኖሮ ምን ይጠቅስ ነበር? ምናልባትም የጉልበት ሥራ የሚሠራ ባሪያ የነበረ መሆኑን ወይም ጭቃ የማቡካት አሊያም መና የመሰብሰብ ልምድ ያለው መሆኑን ከመጥቀስ ያለፈ ነገር ሊናገር አይችልም። እርግጥ ነው፣ የኢያሱ አያት ኤሊሳማ የኤፍሬም ነገድ አለቃ ከመሆኑም ሌላ በሦስት በሦስት ነገዶች ከተከፋፈሉት ምድቦች በአንዱ ውስጥ ያሉትን 108,100 ሰዎችን ሳይመራ አልቀረም። (ዘኍ. 2:18, 24፤ 1 ዜና 7:26, 27) ያም ሆኖ ይሖዋ ጠላትን ድል የሚያደርገውን ጦር እንዲመራ በሙሴ በኩል የመረጠው ኤሊሳማን ወይም ልጁን ነዌን ሳይሆን ኢያሱን ነበር። ጦርነቱ በተካሄደበት ዕለት ውጊያው ረጅም ሰዓት ወሰደ። ኢያሱ አምላክን ሙሉ በሙሉ በመታዘዙና የመንፈሱን አመራር ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆኑ እስራኤላውያን ድል መቀዳጀት ችለዋል።​—ዘፀ. 17:9-13

11. ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ረገድ እንደ ኢያሱ ስኬታማ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

11 ‘በጥበብ መንፈስ የተሞላው’ ኢያሱ ከጊዜ በኋላ ሙሴን ተክቶ ማገልገል ጀመረ። (ዘዳ. 34:9) መንፈስ  ቅዱስ፣ ኢያሱ ልክ እንደ ሙሴ ትንቢት የመናገር ወይም ተአምራት የመፈጸም ችሎታ እንዲኖረው አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ የከነዓናውያንን ምድር ለመያዝ የተደረጉትን ወታደራዊ ዘመቻዎች በተሳካ ሁኔታ ለመምራት አስችሎታል። ዛሬም ቢሆን ከቅዱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ልምድ እንደሌለን ወይም ብቃት እንደሚጎድለን ይሰማን ይሆናል። እኛም እንደ ኢያሱ መለኮታዊውን መመሪያ በጥብቅ ለመከተል ጥረት የምናደርግ ከሆነ ስኬት እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም።​—ኢሳ. 48:16

የይሖዋ “መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ”

12-14. (ሀ) የጌዴዎን 300 ወታደሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የምድያማውያን ሠራዊት ማሸነፍ መቻላቸው ምን ያሳያል? (ለ) ይሖዋ ከእሱ ጋር መሆኑን ለጌዴዎን ያረጋገጠለት እንዴት ነው? (ሐ) በዛሬው ጊዜስ መለኮታዊ ማረጋገጫ የሚሰጠን እንዴት ነው?

12 ኢያሱ ከሞተ በኋላም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ኃይል በመስጠት ማበርታቱን ቀጥሏል። የመሳፍንት መጽሐፍ “ደካማ የነበሩ” ሰዎች “ብርቱዎች” እንደተደረጉ በሚተርኩ ዘገባዎች የተሞላ ነው። (ዕብ. 11:34) አምላክ መንፈስ ቅዱሱን በጌዴዎን ላይ በማውረድ ስለ ሕዝቡ እንዲዋጋ ገፋፍቶታል። (መሳ. 6:34) ይሁንና ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት የመጣው የምድያማውያን ጦር ከጌዴዎን ሠራዊት ጋር ሲነጻጸር 4 ለ1 ነበር። የሚገርመው፣ እጅግ ጥቂት የነበረው የእስራኤላውያን ሠራዊት በይሖዋ ዓይን ሲታይ በጣም ብዙ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ፣ ልዩነቱ 450 ለ1 እስኪሆን ድረስ ጌዴዎን የእስራኤልን ሠራዊት ቁጥር እንዲቀንስ ሁለት ጊዜ ነገረው። (መሳ. 7:2-8፤ 8:10) እስራኤላውያን በዚህ ሁኔታ ጠላታቸውን የማሸነፍ አጋጣሚያቸው እጅግ የመነመነ ቢመስልም ይሖዋ እንዲህ እንዲሆን ፈልጎ ነበር። ታዲያ እስራኤላውያን አስገራሚ ድል ቢቀዳጁ ድሉ የተገኘው በሰዎች ጥረት ወይም ጥበብ ነው ብሎ ለመናገር ማን ሊደፍር ይችላል?

13 ጌዴዎንና ወታደሮቹ ለውጊያው ተዘጋጅተዋል። እፍኝ የማይሞላው የጌዴዎን ጭፍራ አባል ብትሆንና አብረውህ ከነበሩት መካከል ፈሪ የሆኑትና ንቃት የጎደላቸው ሰዎች እንዲቀነሱ መደረጉን ብታውቅ የደኅንነት ስሜት ይሰማህ ነበር? ወይስ ምን ሊከሰት እንደሚችል በማሰብ በፍርሃት ትርድ ነበር? ጌዴዎንስ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል? ይህን መገመት አያስፈልገንም። ምክንያቱም ጌዴዎን የታዘዘውን ማድረጉ በይሖዋ እንደታመነ ያሳያል። (መሳፍንት 7:9-14ን አንብብ።) ጌዴዎን፣ አምላክ ከእሱ ጋር እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ምልክት እንዲያሳየው በመጠየቁ ይሖዋ አልወቀሰውም። (መሳ. 6:36-40) ከዚህ ይልቅ እምነቱን አጠናከረለት።

14 የይሖዋ የማዳን ኃይል ገደብ የለውም። ይሖዋ ደካማ ወይም አቅመ ቢስ በሚመስሉ ሰዎች ተጠቅሞ ሕዝቡን ከማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ማዳን ይችላል። የሚጠሉን ሰዎች ቁጥር ከእኛ ጋር ሲነጻጸር በጣም ብዙ እንደሆነና አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባን የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ልክ እንደ ጌዴዎን ይሖዋ፣ ከእኛ ጋር መሆኑን የሚያረጋግጥ ምልክት እንዲሰጠን ባንጠብቅም በቃሉና በመንፈሱ በሚመራው ጉባኤ አማካኝነት አስፈላጊውን መመሪያና ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ሮም 8:31, 32) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የሰጠን ተስፋዎች እምነታችንን ያጠናክሩልናል እንዲሁም ይሖዋ አስተማማኝ ረዳታችን መሆኑን እንድናምን ያደርጉናል።

የይሖዋ “መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ”

15, 16. የዮፍታሔ ልጅ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ልታዳብር የቻለችው እንዴት ነው? ወላጆችስ ከዚህ ምን ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ?

15 በአምላክ መንፈስ በመመራት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሌላ ሰው እንመልከት። እስራኤላውያን ከአሞናውያን ጋር ጦርነት ለመግጠም በተዘጋጁበት ጊዜ የይሖዋ “መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ።” ዮፍታሔ ድል አግኝቶ ይሖዋን ለማስከበር ከመጓጓቱ የተነሳ አንድ ስእለት ተሳለ፤ ሆኖም ስእለቱ ትልቅ መሥዋዕት የሚያስከፍል ሆነበት። ዮፍታሔ፣ አምላክ አሞናውያንን በእጁ አሳልፎ ቢሰጠው ወደ ቤቱ ሲመለስ በመጀመሪያ ሊቀበለው የሚወጣውን ሰው ለይሖዋ እንደሚሰጥ ቃል ገባ። ዮፍታሔ አሞናውያንን ድል አድርጎ ሲመለስ ሴት ልጁ ልትቀበለው እየሮጠች ወደ እሱ መጣች። (መሳ. 11:29-31, 34) ዮፍታሔ፣ ይህ ሁኔታ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር ነበር ሊባል ይችላል? ያለችው አንድ ልጅ ከመሆኗ አንጻር እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመው እንደሚችል ሳይጠብቅ አልቀረም። ዮፍታሔ ልጁን ሴሎ በሚገኘው የይሖዋ መቅደስ ሕይወቷን ሙሉ እንድታገለግል በመስጠት ስእለቱን ፈጸመ። ልጁም ብትሆን ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ስለነበረች አባቷ የገባው ስእለት መፈጸም እንዳለበት ታምን ነበር። (መሳፍንት 11:36ን አንብብ።) የይሖዋ መንፈስ ለሁለቱም የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል።

16 የዮፍታሔ ልጅ እንዲህ የመሰለ የራስን ጥቅም የመሠዋት  መንፈስ ልታዳብር የቻለችው እንዴት ነው? አባቷ የነበረውን ቅንዓትና ለአምላክ የማደር ባሕርይ መመልከቷ ጠንካራ እምነት እንድትገነባ ረድቷት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ አኗኗራችሁን በደንብ እንደሚያስተውሉ መዘንጋት የለባችሁም። የምታደርጉት ውሳኔ፣ የምትናገሩትን ነገር ታምኑበት እንደሆነና እንዳልሆነ ያሳያል። ልባዊ ጸሎት ስታቀርቡ፣ ውጤታማ በሆነ መንገድ ስታስተምሩና ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል ምን ማለት እንደሆነ በሚያሳይ መንገድ ለመኖር ጥረት ስታደርጉ ልጆቻችሁ ይመለከታሉ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንድነት ተዳምረው ልጆቻችሁ በይሖዋ አገልግሎት ራሳቸውን የማስጠመድ ጠንካራ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረጋቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ ለደስታችሁ ምክንያት ይሆናል።

የይሖዋ “መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት”

17. ሳምሶን በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ምን አድርጓል?

17 እስቲ አሁን ደግሞ በአምላክ መንፈስ የተመራ ሌላ ሰው እንመልከት። እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን እጅ ሲወድቁ ሳምሶን ሕዝቡን እንዲያድን የይሖዋ ‘መንፈስ አነቃቃው።’ (መሳ. 13:24, 25) ሳምሶን የተለየ ጥንካሬ የሚጠይቁ አስገራሚ ነገሮችን እንዲያከናውን ይሖዋ ኃይል ሰጥቶት ነበር። ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን ሳምሶንን በመያዝ ለፍልስጥኤማውያን አሳልፈው በሰጡት ጊዜ የይሖዋ “መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ።” (መሳ. 15:14) በወሰደው የተሳሳተ እርምጃ ሳቢያ የቀድሞ ኃይሉን ባጣበት ወቅትም እንኳ ሳምሶን “በእምነት” ብርቱ እንዲሆን ተደርጓል። (ዕብ. 11:32-34፤ መሳ. 16:18-21, 28-30) የይሖዋ መንፈስ በሳምሶን ላይ ባልተለመደ መንገድ የሠራው በወቅቱ ለየት ያሉ ሁኔታዎች ስለነበሩ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዚህ መልክ የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ ይሠራል ብለን ባንጠብቅም ታሪካዊ ዘገባው ትልቅ የብርታት ምንጭ ይሆነናል። እንዴት?

18, 19. (ሀ) ሳምሶን በሕይወቱ ያጋጠመው ነገር ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ታማኝ ሰዎች ታሪክ በመመርመርህ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

18 እኛም ብንሆን ልክ እንደ ሳምሶን በመንፈስ ቅዱስ መታመን ይኖርብናል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠውን ሥራ ስናከናውን ማለትም “ለሰዎች እንድንሰብክና የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ” የተጣለብንን ኃላፊነት ስንወጣ በመንፈስ ቅዱስ እንደምንታመን እናሳያለን። (ሥራ 10:42) እርግጥ ነው፣ የተሰጠን ሥራ ችሎታ የሚጠይቅ ነው፤ ሆኖም ይህ ችሎታ በተፈጥሮ የሚገኝ አይደለም። በመሆኑም የተሰጡንን ልዩ ልዩ ኃላፊነቶች እንድንወጣ  ይሖዋ መንፈሱን ተጠቅሞ የሚረዳን በመሆኑ እጅግ አመስጋኞች ነን! በዚህም ምክንያት ተልእኳችንን ስንወጣ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ መንፈሱም ልኮኛል” ብለን መናገር እንችላለን። (ኢሳ. 48:16 NW ) አዎን፣ የላከን የአምላክ መንፈስ ነው! ይሖዋ ለሙሴ፣ ለባስልኤልና ለኢያሱ እንዳደረገው ሁሉ ችሎታችንን እንደሚያሳድግልን በመተማመን እሱ የሰጠንን ሥራ በሙሉ ልብ እናከናውናለን። እንዲሁም ለጌዴዎን፣ ለዮፍታሔና ለሳምሶን ኃይል እንደሰጣቸው ሁሉ ለእኛም እንደሚሰጠን በመተማመን “የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል” እንጠቀማለን። (ኤፌ. 6:17, 18) ችግሮችን ለመወጣት በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ሳምሶን አካላዊ ጥንካሬ እንደነበረው ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ ብርቱ መሆን እንችላለን።

19 ይሖዋ፣ ለእውነተኛው አምልኮ ሲሉ ድፍረት የተሞላበት አቋም የሚወስዱትን እንደሚባርክ ምንም ጥርጥር የለውም። የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አመራር የምንከተል ከሆነ እምነታችን ይጠናከራል። በመሆኑም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተመዘገቡትን አስደናቂ ታሪኮች መመርመራችንም ጥቅም ያስገኝልናል። እነዚህ ዘገባዎች የይሖዋ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማለትም ከ33 ዓ.ም. በፊትና በኋላ በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ እንዴት ይሠራ እንደነበር እንድንገነዘብ ያስችሉናል። እነዚህን ዘገባዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

የአምላክ መንፈስ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሰዎች ላይ እንዴት እንደሠራ ማወቅህ የሚያበረታታህ እንዴት ነው?

• በሙሴ

• በባስልኤል

• በኢያሱ

• በጌዴዎን

• በዮፍታሔ

• በሳምሶን

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ መንፈስ ለሳምሶን አካላዊ ጥንካሬ እንደሰጠው ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ ብርቱዎች እንድንሆን ያደርገናል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ የምታሳዩት ቅንዓት በልጆቻችሁ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል