በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማስተካከያዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይክሳል

ማስተካከያዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይክሳል

 ማስተካከያዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይክሳል

ጄምስ ቶምፕሰን እንደተናገሩት

የተወለድኩት በ1928 በደቡብ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። በወቅቱ በዚያ አካባቢ ጥቁሮችንና ነጮችን የሚለያይ ሕግ ነበር። አንድ ሰው ይህን ሕግ ቢጥስ ዘብጥያ ሊወርድ አሊያም የከፋ ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል።

በወቅቱ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ነጭ የይሖዋ ምሥክሮችና ጥቁር የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤያቸው፣ ወረዳቸውም ሆነ አውራጃቸው የግድ የተለያየ መሆን ነበረበት። በ1937 አባቴ፣ በቴነሲ ግዛት በምትገኘው በቻተኑገ ከተማ ባለ አንድ ጉባኤ ውስጥ የቡድን አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ሆኖ ተሾመ። ወንድም ሄነሪ ኒኮልስ ደግሞ የነጮች ጉባኤ የቡድን አገልጋይ ነበር።

አስደሳች የሆኑ የልጅነት ትዝታዎች አሉኝ። ለምሳሌ፣ ማታ ማታ በጓሮ በኩል ባለው በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ አባቴና ወንድም ኒኮልስ የሚነጋገሩትን አዳምጥ እንደነበር ትዝ ይለኛል። በዚያን ጊዜ የሚነጋገሩት ነገር ሙሉ በሙሉ ባይገባኝም ካሉት ሁኔታዎች አንጻር የስብከቱን ሥራ በተሻለ መንገድ ማከናወን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ሲወያዩ ከአባቴ ጎን ሆኜ ማዳመጥ ያስደስተኝ ነበር።

ከዚህ ቀደም ብሎ ማለትም በ1930 አንድ አሳዛኝ ነገር በቤተሰባችን ላይ ደረሰ። እናቴ የሞተችው በዚህ ጊዜ ሲሆን በወቅቱ ገና 20 ዓመቷ ነበር። በመሆኑም አባቴ እኔንና እህቴ ዶሪስን ለብቻው መንከባከብ ነበረበት። እናታችን ስትሞት ዶሪስ አራት ዓመቷ ሲሆን እኔ ደግሞ ገና ሁለት ዓመቴ ነበር። አባቴ ከተጠመቀ ብዙ የቆየ ባይሆንም ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረገ ነበር።

ምሳሌነታቸው በሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል

በ1933 አባቴ፣ ሊሊ ማኢ ግዌንዶላይን ቶማስ ከምትባል አንዲት ጥሩ እህት ጋር ተዋወቀ። ብዙም ሳይቆይ ተጋብተው አብረው መኖር ጀመሩ። ሁለቱም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ረገድ ለእኔና ለዶሪስ ጥሩ ምሳሌ ሆነውናል።

በ1938፣ ሽማግሌዎች የሚሾሙት ጉባኤ ውስጥ በሚደረግ ምርጫ መሆኑ ቀርቶ ሹመታቸው የሚመጣው ብሩክሊን ኒው ዮርክ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ እንዲደግፉ ጉባኤዎች ተጠየቁ። በቻተኑገ የሚገኙ  አንዳንድ ወንድሞች ይህን ለውጥ መቀበል ከብዷቸው ነበር፤ አባቴ ግን ድርጅቱ ያደረገውን ማስተካከያ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል በግልጽ አሳወቀ። አባቴ ታማኝ በመሆን ረገድ የተወውን ምሳሌም ሆነ እናቴ ከእሱ ጋር ለመተባበር ያደረገችውን ልባዊ ጥረት መመልከቴ እስከ አሁን ድረስ ጠቅሞኛል።

ጥምቀትና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት

በ1940 የተወሰኑ የጉባኤያችን አባላት በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አውቶብስ ተከራይተው ወደ ዲትሮይት፣ ሚሺገን ተጉዘው ነበር። ከእኛ ጋር በአንድ አውቶብስ ከተጓዙት መካከል አንዳንዶቹ በዚያ ስብሰባ ላይ ተጠመቁ። በስብከቱ ሥራ መካፈል የጀመርኩት ከአምስት ዓመቴ አንስቶ ስለነበረና በአገልግሎትም ቀናተኛ ስለነበርኩ አንዳንዶች ለምን እንዳልተጠመቅኩ ግራ ገባቸው።

ወንድሞች ለምን እንዳልተጠመቅኩ ሲጠይቁኝ “ስለ ጥምቀት ሙሉ በሙሉ አልገባኝም” በማለት መለስኩላቸው። የሰጠሁት መልስ ድንገት አባቴ ጆሮ ጥልቅ አለ፤ እናም በመልሴ በጣም ተገረመ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ጥምቀት ምን ትርጉም እንዳለውና ለምን አስፈላጊ እንደሆነ እኔን ለማስረዳት ይበልጥ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ከአራት ወር በኋላ ማለትም ጥቅምት 1, 1940 በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ዕለት ከቻተኑገ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ኩሬ ውስጥ ተጠመቅሁ።

ከ14 ዓመቴ ጀምሮ ክረምት ክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ አቅኚ ሆኜ አገለግል ነበር። በቴነሲ ውስጥ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞችና አጎራባች በሆነው የጆርጂያ ግዛት ውስጥ እሰብክ ነበር። በዚያን ጊዜ፣ በሌሊት ተነስቼ ለጉዞ የሚሆነኝን ምሳ ካዘጋጀው በኋላ 12:00 ሰዓት ላይ ባቡር ወይም አውቶብስ ተሳፍሬ ወደማገለግልበት ክልል እሄዳለሁ። ወደ ቤቴ የምመለሰው ደግሞ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት አካባቢ ነበር። የያዝኩት ምግብ በአብዛኛው ገና ምሳ ሰዓት ሳይደርስ ያልቅብኝ ነበር። ገንዘብ ቢኖረኝም ጥቁር ስለሆንኩ በአካባቢው ወዳለ ሱቅ ገብቼ ተጨማሪ ምግብ መግዛት አልችልም ነበር። በአንድ ወቅት አይስክሬም ለመግዛት ወደ ሱቅ ገባሁ፤ ይሁንና የፈለኩትን ሳልገዛ ከሱቁ አስወጡኝ። ያም ሆኖ አንዲት ነጭ ሴት በደግነት አይስክሬሙን ገዝታ አመጣችልኝ።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ በደቡብ አካባቢ ለሰብዓዊ መብት የሚደረጉ ትግሎች በጣም ተፋፍመው ነበር። ናሽናል አሶሲዬሽን ፎር ዚ አድቫንስመንት ኦቭ ከለርድ ፒፕል (በአጽሕሮተ ቃል ኤን ኤ ኤ ሲ ፒ ይባላል) እንደተባለው ያሉ አንዳንድ ድርጅቶች ተማሪዎች የለውጥ አራማጅ እንዲሆኑ ይቀሰቅሱ ነበር። እኛም አባል እንድንሆን ይገፋፉን ነበር። እኔ የምማርበትን ጨምሮ በርካታ የጥቁር ትምህርት ቤቶች፣ ሁሉንም ተማሪ አባል ለማድረግ ቆርጠው ተነስተው ነበር። እኔም እንደነሱ አባባል “ዘራችንን እንድደግፍ” ጫና ይደረግብኝ ነበር። ሆኖም አምላክ እንደማያዳላና አንዱን ዘር ከሌላው እንደማያስበልጥ በመግለጽ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ እነግራቸዋለሁ። በመሆኑም እንዲህ ያሉ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ያስወግዳል ብዬ ተስፋ የማደርገው በአምላክ ላይ ነው።​—ዮሐ. 17:14፤ ሥራ 10:34, 35

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ ብዙም ሳይቆይ ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ ሄጄ ለመኖር ጉዞ ጀመርኩ። ይሁንና እግረ መንገዴን፣ ቀደም ሲል በአውራጃ ስብሰባ ላይ የተዋወቅኳቸው ጓደኞቼን ለማየት ፔንስልቬንያ ግዛት ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ፊላደልፊያ ከተማ ጎራ አልኩ። የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች በአንድነት በሚያደርጉት የጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁት በዚያ ከተማ ነበር። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ይህን ጉባኤ በሚጎበኝበት ወቅት ለብቻዬ ነጠል አድርጎ ወስዶኝ በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ ክፍል እንዳቀርብ የተመደብኩ መሆኔን ነገረኝ። በዚህም የተነሳ ሐሳቤን ቀይሬ እዚያው ለመቆየት ወሰንኩ።

በፊላደልፊያ ካፈራኋቸው ጓደኞቼ አንዷ ጀራልዲን ዋይት (ጄሪ) ናት። ጄሪ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላት ከመሆኑም በላይ ከቤት ወደ ቤት በምታገለግልበት ወቅት ሰዎችን ስታነጋግር በጣም ጎበዝ ናት። ከሁሉ በላይ ያስደሰተኝ እሷም እንደ እኔ አቅኚ የመሆን ፍላጎት እንዳላት ማወቄ ነው። በመሆኑም ሚያዝያ 23, 1949 ተጋባን።

ወደ ጊልያድ ተጠራን

ገና ከጅምሩ አንስቶ ሁለታችንም ጊልያድ ትምህርት ቤት የመግባትና በውጪ አገር ሚስዮናዊ ሆኖ የማገልገል ግብ ነበረን። ጊልያድ ገብቶ ለመሠልጠን የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላት ስለምንፈልግ ሁኔታዎቻችንን ለማስተካከል ፈቃደኞች  ነበረብን። ብዙም ሳይቆይ ኒው ጀርሲ ውስጥ ወዳለችው ወደ ላውንሳይድ እንድንዛወር ተጠየቅን፤ ከዚያም ፔንስልቬንያ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ቼስተር፣ በመጨረሻም ኒው ጀርሲ ውስጥ ወዳለችው ወደ አትላንቲክ ሲቲ ሄድን። በአትላንቲክ ሲቲ እያለን ከተጋባን ሁለት ዓመት ስለሆነን ጊልያድ ለመግባት አመለከትን። ይሁንና ለጊዜው ወደ ጊልያድ ሳንጠራ ቀረን። ምክንያቱ ምን ይሆን?

በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በርካታ ወጣቶች በውትድርና እንዲያገለግሉና በኮሪያ በሚደረገው ጦርነት እንዲካፈሉ ይመለመሉ ነበር። በፊላደልፊያ ያለው ምልመላውን የሚያካሂደው ቦርድ በገለልተኛነት አቋማችን ምክንያት ለይሖዋ ምሥክሮች ጭፍን ጥላቻ ያለው ይመስላል። በመጨረሻም አንድ ዳኛ፣ የፌዴራል ምርመራ ቢሮው (ኤፍ ቢ አይ) ጀርባዬን ሲያጠና እንደነበረና ገለልተኛ አቋም ያለኝ መሆኑን እንዳረጋገጠ ነገሩኝ። በመሆኑም ጥር 11, 1952 የፕሬዚዳንቱ ይግባኝ ሰሚ ቦርድ እኔን እንደ ሃማኖታዊ አገልጋይ በመቁጠር ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ አደረገኝ።

በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ እኔና ጄሪ መስከረም ላይ በሚጀምረው 20ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ግብዣ ቀረበልን። ትምህርታችንን በምንከታተልበት ወቅት፣ ከተመረቅን በኋላ ወደ ሌላ አገር እንመደባለን ብለን ጠብቀን ነበር። በወቅቱ፣ ከ13ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀችው እህቴ ዶሪስ በብራዚል ተመድባ እያገለገለች ነበር። ይሁን እንጂ በወረዳ ሥራ እንድናገለግልና የጥቁሮችን ጉባኤዎች እንድንጎበኝ ወደ ደቡባዊው የአላባማ ግዛት ስንመደብ በጣም ተገረምን! የጠበቅነው በውጭ አገር እናገለግላለን ብለን ስለነበር ምድባችንን ስናውቅ ትንሽ ቅር ብሎን ነበር።

መጀመሪያ የጎበኘነው በሃንስቪሌ የሚገኝን አንድ ጉባኤ ሲሆን በዚህ ወቅት ያረፍነው አንዲት እህት ቤት ነበር። ጓዛችንን እያወረድን እያለ የተቀበለችን እህት “ልጆቹ መጥተዋል” ብላ በስልክ ስትናገር ሰማናት። እርግጥ ገና 24 ዓመታችን ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ስንታይ 24 ዓመት የሆነን አንመስልም ነበር። በዚያ ወረዳ ውስጥ ባገለገልንባቸው ጊዜያት ሁሉ የምንታወቀው “ልጆቹ” በሚለው ቅጽል ስም ነበር።

በደቡብ አካባቢ ያለው የአሜሪካ ክልል ብዙውን ጊዜ ባይብል ቤልት በመባል ይጠራ ነበር፤ ይህ መጠሪያ የተሰጠው በዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት ስለነበራቸው ነው። በመሆኑም አገልግሎት ወጥተን ሰዎችን ስናነጋግር የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች እናነሳ ነበር፦

(1) ስለ ዓለም ሁኔታ በአጭሩ እንጠቅስላቸዋለን።

(2) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መፍትሔ እንነግራቸዋለን።

(3) ከእኛ ስለሚጠበቀው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ እንገልጽላቸዋለን።

ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዳቸውን ተስማሚ ጽሑፍ እንሰጣቸዋለን። ይህ አቀራረብ ጥሩ ውጤት ስላስገኘልን በ1953 ኒው ዮርክ ውስጥ በተደረገው የአዲሱ ዓለም ማኅበረሰብ ስብሰባ ላይ ከዚህ ጋር የተያያዘ ክፍል እንዳቀርብ ተመድቤ ነበር። በክፍሉ ላይ እነዚህን ሦስት ነጥቦች የያዘ አቀራረብ በሠርቶ ማሳያ ቀርቦ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ማለትም በ1953 ክረምት ላይ፣ በደቡብ አካባቢ ያሉትን የጥቁሮች ወረዳዎች በአውራጃ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። ክልላችን ከቨርጂኒያ አንስቶ እስከ ፍሎሪዳ፣ በምዕራብ በኩል ደግሞ እስከ አላባማና ቴነሲ ድረስ ያሉትን ግዛቶች በሙሉ ይጨምር ነበር። በወቅቱ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የተለያዩ አስቸጋሪ ነገሮች ስለሚያጋጥሟቸው ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኛውን ጊዜ የምናርፈው ክፍሎቹ ውስጥ የውኃ መስመር በሌላቸው ቤቶች ውስጥ ነበር፤ በመሆኑም ገላችንን የምንታጠበው ኩሽናው ውስጥ  ከምድጃው በስተጀርባ በሳፋ ነበር። ደስ የሚለው ቤቱ ውስጥ ካሉት ቦታዎች ሁሉ ሞቅ የሚለው ይህ ክፍል ነው!

ከዘር መድልዎ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙን ችግሮች

በደቡብ አካባቢ በምናገለግልበት ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን ለማከናወን የተለያዩ ዘዴዎችን መፍጠር ነበረብን። ለምሳሌ፣ ጥቁሮች በልብስ ንጽሕና መስጫ ቤቶች ገብተው የራሳቸውን ልብስ እንዲያጥቡ አይፈቀድላቸውም ነበር። ስለዚህ ጄሪ ወደዚህ ቦታ በምትሄድበት ጊዜ፣ የመጣችው “የሚስስ ቶምፕሰንን” ልብስ ለማጠብ እንደሆነ ትናገራለች። እንዲህ ስትል አብዛኞቹ ሰዎች የቤት ሠራተኛ እንደሆነችና ሚስስ ቶምፕሰን ደግሞ የእሷ አሠሪ እንደሆነች አድርገው ያስባሉ። እኔም የራሴን ዘዴ የምጠቀምበት ጊዜ ነበር። የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን የተባለውን ፊልም ያሳዩ ነበር፤ በመሆኑም ፊልሙን ለማሳየት ስፈልግ ትላልቅ ስክሪኖች ወደሚያከራይ መደብር ስልክ በመደወል “ሚስተር ቶምፕሰን” አንድ ስክሪን እንዲቀመጥላቸው እንደሚፈልጉ እናገራለሁ። ከዚያም ወደ መደብሩ ሄጄ አመጣዋለሁ። ምንጊዜም ሰዎችን በትሕትና ለመያዝ ስለምንጥር በአብዛኛው በአገልግሎት ላይ ምንም ችግር አያጋጥመንም ነበር።

በዚያን ጊዜ በደቡብ አሜሪካ ክፍል ሌላም ዓይነት ጥላቻ ተስፋፍቶ ነበር፤ በደቡብ ያሉ ሰዎች የሰሜን አካባቢ ሰዎችን አይወዱም ነበር። በአንድ ወቅት በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተወካይ የሆነው ጄምስ ቶምፕሰን በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር እንደሚያደርግ የሚገልጽ ዘገባ አውጥቶ ነበር። ይህን ያነበቡ አንዳንድ ሰዎች የኒው ዮርክ ሰው መስያቸው ነበር። በዚህም ምክንያት የትምህርት ቤቱን አዳራሽ ለስብሰባው ለመጠቀም ያደረግነው ውል ተሰረዘ። በዚህ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤቱ ቦርድ በመሄድ የተማርኩት በቻተኑገ መሆኑን አስረዳሁ። ከዚያም አዳራሹን ለወረዳ ስብሰባችን እንድንጠቀምበት ተፈቀደልን።

በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ የዘር መድልዎ የፈጠረው ውጥረት እየተባባሰ ስለሄደ አንዳንድ ጊዜ የዓመፅ ድርጊቶች ይፈጸሙ ነበር። በ1954 በተካሄዱት በርካታ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አንድም ጥቁር ተናጋሪ ባለመኖሩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅር ተሰኝተው ነበር። ጥቁር ወንድሞቻችን ነገሮችን በትዕግሥት እንዲጠባበቁ እናበረታታቸው ነበር። በሚቀጥለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ንግግር እንዳቀርብ ተመደብኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል በሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ንግግር የሚያቀርቡ ጥቁር ወንድሞች ቁጥር እየጨመረ መጣ።

በደቡብ አካባቢ በዘር ምክንያት የሚነሱት ዓመፆች ቀስ በቀስ እየቀነሱ መጡ። እንዲሁም ቀስ በቀስ ነጭና ጥቁር ወንድሞች በአንድ ጉባኤ ውስጥ አብረው መሰብሰብ ጀመሩ። በመሆኑም አስፋፊዎችን እንደ አዲስ ወደ ተለያዩ ጉባኤዎች መመደብን ጨምሮ የጉባኤ ክልሎችን ማስተካከልና የበላይ ተመልካቾች ኃላፊነት ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓል። ከጥቁርም ሆነ ከነጭ ወንድሞች መካከል ይህን አዲስ ዝግጅት ያልወደዱት ነበሩ። ይሁንና አብዛኞቹ ወንድሞች አድልዎ ባለማሳየት የሰማዩ አባታችንን ምሳሌ ተከትለዋል። ደግሞም ብዙዎቹ የቀለም ልዩነት ሳይገድባቸው ከተለያዩ ወንድሞች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ነበራቸው። ይህ ሁኔታ በእኛም ቤት ታይቷል፤ ልጅ ሳለሁ ማለትም በ1930ዎቹና 1940ዎቹ ቤተሰባችን ሌላ ዘር ካላቸው ወንድሞች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ችሎ ነበር።

አዲስ የአገልግሎት ምድብ

ጥር 1969 እኔና ጄሪ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ወደምትገኘው ጋያና ወደ ተባለች አገር እንድንሄድ ግብዣ ሲቀርብልን በጣም ደስ አለን። በመጀመሪያ ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ የሄድን ሲሆን በዚያም በጋያና ያለውን የስብከት ሥራ በበላይነት ለመከታተል የሚያስችል ሥልጠና ተሰጠኝ። ከዚያም ሐምሌ 1969 ጋያና ገባን። ለ16 ዓመታት በወረዳ ሥራ ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ ስናገለግል የቆየን እንደመሆኑ መጠን አንድ ቦታ ተቀምጦ ለመሥራት ትልቅ ማስተካከያ ማድረግ ጠይቆብን ነበር። ጄሪ እንደ አንድ ሚስዮናዊ አብዛኛውን ጊዜዋን በአገልግሎት የምታሳልፍ ሲሆን እኔ ደግሞ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እሠራ ነበር።

 በዚያ እያለሁ የግቢውን ሣር ከማጨድና ለ28 ጉባኤዎች ጽሑፎችን ከመላክ አንስቶ ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ጋር ደብዳቤ እስከ መጻጻፍ ድረስ ያሉ ማንኛውንም ሥራዎች አከናውን ነበር። በየቀኑ ከ14 እስከ 15 ሰዓታት እሠራ ነበር። እርግጥ ሥራው ለሁለታችንም ከባድ ነበር፤ ያም ቢሆን በተሰጠን ምድብ ደስተኞች ነበርን። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጋያና ስንመጣ የነበረው የአስፋፊዎች ቁጥር 950 ነበር፤ አሁን ግን በዚያች አገር ከ2,500 የሚበልጡ አስፋፊዎች ይገኛሉ።

በጋያና ያለው ተስማሚ አየር ብሎም በዚያ የሚገኙ የተለያዩ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ለደስታችን ምክንያት ቢሆኑም እውነተኛ እርካታ የሚሰጠን ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥማት ያላቸው ትሑት ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት መማራቸው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ጄሪ በየሳምንቱ 20 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ትመራ የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናናቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ እድገት አድርገው ተጠምቀዋል። ሌሎቹ ደግሞ ከጊዜ በኋላ አቅኚዎች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሌላው ቀርቶ ጊልያድ ገብተው በመሠልጠን እንደ እኛ ሚስዮናውያን ሆነዋል።

ጤና ማጣትና ሌሎች ችግሮች

በ1983 በዩናይትድ ስቴትስ ይኖሩ የነበሩት ወላጆቼ የእኛ እርዳታ አስፈለጋቸው። እኔና ጄሪ ከዶሪስ ጋር ተገናኝተን ስለ ቤተሰባችን ጉዳይ ተነጋገርን። በብራዚል ለ35 ዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገለችው ዶሪስ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሳ ወላጆቻችንን ለመንከባከብ ወሰነች። ዶሪስ ‘እነሱን ለመንከባከብ አንድ ሰው በቂ ሆኖ ሳለ ለምን ሁለት ሚስዮናዊያን አገልግሎታቸውን ያቋርጣሉ?’ የሚል ሐሳብ ስላቀረበችልን በእሷ መሄድ ተስማማን። ወላጆቻችን ከሞቱ በኋላ ዶሪስ እዚያው ቻተኑገ በመቆየት ልዩ አቅኚ ሆና ማገልገል ቀጠለች።

በ1995 የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለብኝ ስለታወቀ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ ነበረብኝ። ከዚያም በኖርዝ ካሮላይን በምትገኘው በጎልድስቦሮ መኖር ጀመርን። ምክንያቱም ይህ አካባቢ የእኔ ቤተሰቦች በሚኖሩበት በቴነሲ እና የጄሪ ቤተሰቦች በሚኖሩበት በፔንስልቬንያ መካከል የሚገኝ ቦታ ነው። በአሁኑ ወቅት በሽታው በሰውነቴ ውስጥ እንዳይሰራጭ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን አሁን በጎልድስቦሮ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ብቻ እየሠራን በልዩ አቅኚነት እናገለግላለን።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ከ65 የሚበልጡ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብዬ ስመለከት ይሖዋን ከልብ ለማመስገን እገፋፋለሁ፤ ምክንያቱም እኔና ጄሪ እሱን ለማገልገል ስንል ማስተካከያዎችን በማድረጋችን ባርኮናል። ዳዊት ይሖዋን አስመልክቶ “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ [ትሆናለህ]” በማለት የተናገረው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው!​—2 ሳሙ. 22:26

[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አባቴና ወንድም ኒኮልስ ግሩም ምሳሌ ትተውልኛል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እኔና ጄሪ በ1952 ወደ ጊልያድ ልንሄድ ስንል የተነሳነው

[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጊልያድ ከሠለጠንን በኋላ የወረዳ ሥራ እንድንሠራ በደቡብ አካባቢ ተመደብን

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው በ1966 ላይ ነጭና ጥቁር ወንድሞች በአንድነት ያደረጉት የአውራጃ ስብሰባ ሊካሄድ ሲል የተነሱት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጋያና በሚስዮናዊነት ያሳለፍነው ጊዜ አስደሳች ነበር