በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለዘላለም የአካል ጉዳተኛ ሆኜ አልቀርም!”

“ለዘላለም የአካል ጉዳተኛ ሆኜ አልቀርም!”

 “ለዘላለም የአካል ጉዳተኛ ሆኜ አልቀርም!”

ሣራ ቫን ደር ሞንድ እንደተናገረችው

ብዙውን ጊዜ ሰዎች “ሣራ፣ ፈገግታሽ በጣም ያምራል። ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን የቻልሽው እንዴት ነው?” ይሉኛል። እኔም ደስተኛ የሆንኩት ለየት ያለ ተስፋ ስላለኝ እንደሆነ እነግራቸዋለሁ። ይህን ተስፋ በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጌ መግለጽ እችላለሁ፦ “ለዘላለም የአካል ጉዳተኛ ሆኜ አልቀርም!”

የተወለድኩት በ1974 በፓሪስ፣ ፈረንሳይ ነው። በምወለድበት ወቅት ችግር አጋጥሞኝ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሴሬብራል ፖልዚ የተባለ የአንጎል ችግር እንዳለብኝ ታወቀ። እጅና እግሬን እንደልብ ማንቀሳቀስ የማልችል ከመሆኑም በላይ የምናገረው ነገር ለሌሎች አይገባም። በተጨማሪም የሚጥል በሽታ የያዘኝ ሲሆን በቀላሉ ኢንፌክሽን ያጠቃኝ ጀመር።

ሁለት ዓመት ሲሆነኝ ወላጆቼ አውስትራሊያ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ሜልቦርን ከተማ ተዘዋውረው መኖር ጀመሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ አባቴ እኔና እናቴን ጥሎን ሄደ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከአምላክ ጋር እንደተቀራረብኩ ሆኖ የተሰማኝ ያን ወቅት ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናቴ ሁልጊዜ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ትወስደኝ ነበር፤ በዚያም አምላክ እንደሚወደኝና እንደሚያስብልኝ ተማርኩ። አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመንም በስብሰባዎች ላይ ያገኘሁት እውቀት እናቴ ከምትሰጠኝ ፍቅርና ማበረታቻ ጋር ተዳምሮ የደኅንነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።

እናቴ ወደ ይሖዋ እንዴት መጸለይ እንዳለብኝም አስተምራኛለች። እንዲያውም ከማውራት ይልቅ መጸለይ ይበልጥ ቀላል ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በምጸልይበት ወቅት ቃላቱን ከአንደበቴ ማውጣት አያስፈልገኝም፤ መናገር የምፈልገውን ነገር ልክ በጆሮዬ በግልጽ እንደምሰማው ያህል በአእምሮዬ ውስጥ በደንብ አቀናብረዋለሁ። የምናገረው ነገር ለሌሎች የሚገባ ባይሆንም ይሖዋ የምጸልየው በልቤም ይሁን በተንተባተበ አንደበት ሐሳቤን አንድም ሳይቀር የሚረዳ መሆኑን ማወቄ ያጽናናኛል።​—መዝ. 65:2

አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ መኖር

አምስት ዓመት ሲሞላኝ አንጎሌ ላይ ያለው ችግር እየተባባሰ ስለሄደ መራመድ እንድችል የግድ ክራንች እግሮቼ ላይ መገጠም ነበረበት። በትክክል መራመድ ስለማልችል ስሄድ ወደ ግራና ወደ ቀኝ የምወዛወዝ እመስል ነበር። አሥራ አንድ ዓመት ሲሆነኝ ሙሉ በሙሉ መራመድ አቃተኝ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በኤሌትሪክ በሚሠራ መሸከሚያ መሣሪያ በመታገዝ ካልሆነ በስተቀር ወደ አልጋዬ መውጣትም ሆነ ከአልጋዬ ወርጄ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ መቀመጥ ተሳነኝ፤ ተሽከርካሪ ወንበሬ በሞተር የሚሠራ በመሆኑ አቅጣጫ መቀያየሪያውን በቀላሉ በእጄ በማንቀሳቀስ ወደ ፈለግሁት አቅጣጫ መሄድ እችላለሁ።

ያለብኝ የአካል ጉዳት አንዳንድ ጊዜ በሐዘን እንድዋጥ እንደሚያደርገኝ አልክድም። በዚህ ወቅት ግን የቤተሰባችንን የተለመደ አባባል አስታውሳለሁ፦ “ማድረግ ስለማትችለው ነገር አትጨነቅ። ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርግ።” እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዜ ፈረስ እንደ መጋለብ፣ ጀልባ እንደ መንዳት፣ ታንኳ እንደ መቅዘፍ፣ ለሽርሽር ወጣ ብሎ በድንኳን እንደማደር ሌላው ቀርቶ በተከለሉ ቦታዎች መኪና እንደመንዳት በመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች እንድካፈል አስችሎኛል! ሥዕል በመሳል፣ ልብስ በመስፋት፣ የአልጋ ልብስ በመሥራት፣ ጥልፍ በመጥለፍና የሸክላ ዕቃዎችን በመሥራትም የሥነ ጥበብ ተሰጥኦዬን ለመጠቀም እሞክራለሁ።

አንዳንድ ሰዎች፣ ከባድ የአካል ጉዳት ስላለብኝ ብቻ እንደ ማንኛውም ሰው አምላክን ከማምለክ ጋር በተያያዘ የራሴን  ውሳኔ ማድረግ እንደማልችል ይሰማቸዋል። የ18 ዓመት ወጣት እያለሁ አንዲት አስተማሪዬ ከእናቴ ሃይማኖት “እንድገላገል” ከቤት መውጣት እንደሚኖርብኝ መከረችኝ። እንዲያውም ማረፊያ ቦታ በማፈላለግ እንደምትተባበረኝ ነገረችኝ። እኔ ግን እምነቴን በፍጹም እንደማልተውና ራሴን ችዬ ለመውጣት ዝግጁ እስክሆን ድረስ ከቤት እንደማልወጣ ነገርኳት።

ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ከቤት ወጥቼ በአንዲት ትንሽ አፓርታማ ውስጥ መኖር ጀመርኩ። አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም በአንድ በኩል የሚያስፈልገኝን እርዳታ የማገኝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የራሴ ነፃነት አለኝ።

ፈጽሞ ያልተጠበቀ ጥያቄ

ባለፉት ዓመታት እምነቴን የሚፈታተኑ ሌሎች ነገሮች አጋጥመውኛል። አንድ ቀን፣ አብሮኝ የሚማርና እንደኔው የአካል ጉዳተኛ የሆነ ተማሪ የጋብቻ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ክው ብዬ ቀረሁ። መጀመሪያ ላይ ደስ ብሎኝ ነበር። ምክንያቱም እንደ አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች ሁሉ እኔም የሕይወቴ አጋር የሚሆን ሰው የማግኘት ጉጉት አለኝ። ይሁንና ሁለታችንም ተመሳሳይ ችግር ያለብን መሆኑ የተሳካ ትዳር ለመመሥረት ዋስትና ሊሆን እንደማይችል አሰብኩ። በዚያ ላይ እምነታችን አንድ አይደለም። እንዲሁም የምናምንባቸው ነገሮች፣ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም ሆኑ ግቦቻችን ፈጽሞ የተለያዩ ነበሩ። ታዲያ ከዚህ ሰው ጋር እንዴት ትዳር መመሥረት እችላለሁ? ከዚህም በላይ አምላክ ከእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ብቻ እንድናገባ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። (1 ቆሮ. 7:39) በመሆኑም ያቀረበልኝን የጋብቻ ጥያቄ እንደማልቀበል በደግነት ነገርኩት።

ዛሬም ቢሆን ያደረግኩት ውሳኔ ትክክል እንደሆነ ይሰማኛል። አምላክ እንደሚያመጣው ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ደስተኛ ሕይወት እንደምመራ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። (መዝ. 145:16፤ 2 ጴጥ. 3:13) እስከዚያ ድረስ ግን ለይሖዋ ያለኝን ታማኝነት እስከመጨረሻው ይዤ ለመቀጠልና ያለሁበትን ሁኔታ ተቀብዬ ለመኖር ቆርጫለሁ።

ከተሽከርካሪ ወንበሬ ዘልዬ የምነሳበትንና እንደ ልቤ የምቦርቅበትን ቀን እናፍቃለሁ። ያን ጊዜ በደስታ እንዲህ እላለሁ፦ “የአካል ጉዳተኛ ነበርኩ። አሁን ግን ፍጹም ጤነኛ ነኝ፤ ያውም ለዘላለም!”