በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ያዘኑትን አጽናኑ’

‘ያዘኑትን አጽናኑ’

 ‘ያዘኑትን አጽናኑ’

‘ይሖዋ ቀብቶኛል። ያዘኑትን እንዳጽናና ልኮኛል።’​—ኢሳ. 61:1, 2 የ1980 ትርጉም

1. ኢየሱስ ላዘኑ ሰዎች ምን አድርጎላቸዋል? ለምንስ?

ኢየሱስ ክርስቶስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐ. 4:34) ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ሲወጣ የአባቱን ግሩም ባሕርያት አንጸባርቋል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ይሖዋ ለሰዎች ያሳየው ታላቅ ፍቅር ይገኝበታል። (1 ዮሐ. 4:7-10) ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” እንደሆነ ሲናገር ይህ ፍቅር የተገለጸበትን አንዱን መንገድ ጠቁሟል። (2 ቆሮ. 1:3) ኢየሱስ፣ ኢሳይያስ የተናገረውን ትንቢት በፈጸመበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አሳይቷል። (ኢሳይያስ 61:1, 2ን አንብብ።) በናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ የኢሳይያስን ትንቢት ካነበበ በኋላ ጥቅሱ በእሱ ላይ እንደተፈጸመ ተናግሯል። (ሉቃስ 4:16-21) ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ በፍቅር ተነሳስቶ የሚያለቅሱትን ወይም ያዘኑትን በማጽናናት እንዲበረታቱና የአእምሮ ሰላም እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

2, 3. የክርስቶስ ተከታዮች ሌሎችን በማጽናናት ረገድ የእሱን አርዓያ መከተል የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

2 የኢየሱስ ተከታዮች በሙሉ ያዘኑ ሰዎችን በማጽናናት የእሱን አርዓያ መከተል ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁንና እርስ በርስ መተናነጻችሁን ቀጥሉ” ብሏል። (1 ተሰ. 5:11) በተለይም በአሁኑ ጊዜ የሰው ዘር የሚኖረው “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን”  ውስጥ በመሆኑ ሌሎችን ማጽናናት ያስፈልገናል። (2 ጢሞ. 3:1) በመላው ዓለም የሚኖሩ በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች፣ በሌሎች ንግግርና ድርጊት የተነሳ ለሐዘን የሚዳረጉ ከመሆኑም ሌላ ስሜታቸው ይደቆሳል።

3 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚናገረው በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” ናቸው። “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ [በመሄዳቸው]” ከላይ የተገለጹት ዓይነት ዝንባሌዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ከፍተዋል።​—2 ጢሞ. 3:2-4, 13

4. በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ይታያሉ?

4 የአምላክ ቃል “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” በማለት በግልጽ ስለሚናገር ከላይ የተገለጹት ዓይነት ሁኔታዎች መስፋፋታቸው ሊያስገርመን አይገባም። (1 ዮሐ. 5:19) “መላው ዓለም” የሚለው አገላለጽ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የንግድ ተቋማትን እንዲሁም ፕሮፖጋንዳ የሚተላለፍባቸውን የመገናኛ ዘዴዎች ይጨምራል። በእርግጥም ሰይጣን ዲያብሎስ “የዚህ ዓለም ገዥ” እንዲሁም “የዚህ ሥርዓት አምላክ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (ዮሐ. 14:30፤ 2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን ሊጠፋ የቀረው ጥቂት ጊዜ መሆኑን በማወቁ በእጅጉ ስለተቆጣ በዓለም ዙሪያ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። (ራእይ 12:12) ይሖዋ፣ ሰይጣንንም ሆነ የእሱን ክፉ ሥርዓት የሚታገሥበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚያበቃ እንዲሁም ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት አስመልክቶ ያስነሳው ጥያቄ እልባት እንደሚያገኝ ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!​—ዘፍ. ምዕ. 3፤ ኢዮብ ምዕ. 2

ምሥራቹ በመላው ምድር እየተሰበከ ነው

5. ስለ ስብከቱ ሥራ የተነገረው ትንቢት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?

5 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ ዘመን ኢየሱስ የተናገረው የሚከተለው ትንቢት እየተፈጸመ ነው፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14) ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመላው ምድር በስፋት እየተሰበከ ነው። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ107,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የታቀፉ ከ7,500,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት እየሰበኩ ነው፤ የኢየሱስም ስብከትና ትምህርት በዋነኝነት ያተኮረው በዚህ መንግሥት ላይ ነበር። (ማቴ. 4:17) የሚያዝኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ባለው በዚህ የስብከት ሥራ አማካኝነት ታላቅ ማጽናኛ እያገኙ ነው። በቅርቡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ በአጠቃላይ 570,601 ግለሰቦች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል!

6. በስብከቱ ሥራችን ላይ ስለሚታየው እድገት ምን ይሰማሃል?

 6 በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች እየተረጎሙና እያሰራጩ እንደሆነ ማወቃችን የስብከቱ ሥራ ምን ያህል በስፋት እንደሚከናወን ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ሥራ ፈጽሞ ታይቶ አይታወቅም! የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል መኖር መቻሉ በራሱ እንዲሁም የሚያከናውነው ሥራና የሚያደርገው እድገት በእርግጥም በጣም አስደናቂ ነው። ይህ ድርጅት ኃያል ከሆነው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመሪያና ድጋፍ ባያገኝ ኖሮ ሰይጣን በሚቆጣጠረው በዚህ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ተግባር ማከናወን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ምሥራቹ በመላው ዓለም እየተሰበከ በመሆኑ ከቅዱሳን መጻሕፍት ማጽናኛ ማግኘት የቻሉት የእምነት ባልንጀሮቻችን ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ያዘኑ ሰዎችም ጭምር ናቸው።

የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማጽናናት

7. (ሀ) ይሖዋ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን በሙሉ አሁን እንዲያስወግድ መጠበቅ የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ስደትና መከራን በጽናት መቋቋም እንደምንችል እንዴት እናውቃለን?

7 ክፋትና መከራ በበዛበት በዚህ ዓለም ውስጥ የሚያስጨንቁን ሁኔታዎች መከሰታቸው የማይቀር ነው። አምላክ ይህን ሥርዓት እስኪያጠፋው ድረስ ደስታ የሚያሳጡንንና ለሐዘን የሚዳርጉንን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳቸዋል ብለን አንጠብቅም። ያ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ፣ አስቀድሞ እንደተነገረው ለይሖዋ ያለንን ታማኝነትና ሉዓላዊነቱን የምንደግፍ መሆናችንን የሚፈትን ስደት ያጋጥመናል። (2 ጢሞ. 3:12) ይሁን እንጂ በሰማይ ያለው አባታችን ስለሚደግፈንና ስለሚያጽናናን በጥንቷ ተሰሎንቄ እንደነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚደርስብንን ስደትም ሆነ መከራ በጽናትና በእምነት መቋቋም እንችላለን።​—2 ተሰሎንቄ 1:3-5ን አንብብ።

8. ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚያጽናና የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?

8 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ማጽናኛ እንደሚሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኤልያስ ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው በዛተችበት ወቅት ፍርሃት ስላደረበት የሸሸ ሲሆን እንዲያውም ሞትን ተመኝቶ ነበር። ይሖዋ ግን ኤልያስን እንዲህ በማድረጉ ከመገሠጽ ይልቅ ያጽናናው ከመሆኑም ሌላ የነቢይነት ተልእኮውን ለመፈጸም የሚያስችለው ድፍረት ሰጥቶታል። (1 ነገ. 19:1-21) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የተከናወነው ሁኔታም ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚያጽናና ያሳያል። ለአብነት ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ሁሉ ያለው ጉባኤ ሰላም አገኘ፤ በእምነትም እየጠነከረ ሄደ” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም “መላው ጉባኤ ይሖዋን በመፍራትና መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ ጋር በመስማማት ይኖር ስለነበር በቁጥር እየበዛ ሄደ” ይላል። (ሥራ 9:31) እኛም “መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ” መጠቀም የምንችል በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

9. ስለ ኢየሱስ መማራችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?

9 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመማርና አርዓያውን በመከተል ማጽናኛ ማግኘት ችለናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ምክንያቱም ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው።” (ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ ሰዎችን በፍቅርና በደግነት የሚይዝበትን መንገድ መማራችንና እሱ የተወውን ግሩም ምሳሌ መከተላችን በራሱ፣ የሚያጋጥመንን ጫና ለመቋቋም ከፍተኛ እርዳታ ያደርግልናል።

10, 11. በጉባኤ ውስጥ ወንድሞችን ማጽናናት የሚችሉት እነማን ናቸው?

10 የእምነት ባልንጀሮቻችንም ሊያጽናኑን ይችላሉ። የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚያስጨንቅ ሁኔታ ያጋጠማቸውን የሚረዱበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእናንተ መካከል [በመንፈሳዊ] የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም . . . ይጸልዩለት።” ይህ ምን ውጤት ያስገኛል? “በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባልለታል።” (ያዕ. 5:14, 15) ሌሎች የጉባኤ አባላትም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ማጽናናት ይችላሉ።

11 ብዙውን ጊዜ ሴቶች ስለሚያጋጥሟቸው የተለያዩ  ችግሮች ከሌሎች ሴቶች ጋር መወያየት ይቀላቸዋል። በተለይ ደግሞ በዕድሜ የገፉና ተሞክሮ ያካበቱ እህቶች ለወጣት እህቶች ግሩም ምክር ሊሰጧቸው ይችላሉ። በዕድሜ የገፉት እነዚህ የጎለመሱ ክርስቲያን ሴቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟቸው ያውቅ ይሆናል። እነዚህ ሴቶች፣ ወጣት እህቶችን በአዘኔታና በርኅራኄ ስለሚያዳምጧቸው ከፍተኛ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይችላሉ። (ቲቶ 2:3-5ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች በመካከላችን ያሉትን “የተጨነቁትን ነፍሳት [ማጽናናት]” ይችላሉ፤ እንዲህ ማድረግም ይኖርባቸዋል። (1 ተሰ. 5:14, 15) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ “በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል እሱ በመከራችን ሁሉ [እንደሚያጽናናን]” ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።​—2 ቆሮ. 1:4

12. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 መጽናኛ ለማግኘት ልንወስደው የሚገባው አንዱ ወሳኝ እርምጃ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲሆን በዚያ የሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ያበረታታናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሁዳና ሲላስ “ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው እንዲሁም አጠናከሯቸው” ይላል። (ሥራ 15:32) ስብሰባዎች ከመጀመራቸው በፊትና ካበቁ በኋላ የጉባኤው አባላት የሚያንጹ ጭውውቶችን ያደርጋሉ። በመሆኑም አንዳንድ አስጨናቂ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን እንኳ ራሳችንን ማግለል የለብንም፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን ያለንበት ሁኔታ እንዲሻሻል አይረዳንም። (ምሳሌ 18:1) ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።”​—ዕብ. 10:24, 25

ከአምላክ ቃል ማጽናኛ ማግኘት

13, 14. ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያጽናኑን እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

13 የተጠመቅን ክርስቲያኖችም ሆንን ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ መማር የጀመርን ሰዎች፣ በጽሑፍ ከሰፈረው የአምላክ ቃል ታላቅ ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” (ሮም 15:4) ቅዱሳን መጻሕፍት ሊያጽናኑን እንዲሁም “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ስለ አምላክ ዓላማዎች እውነቱን ማወቅና ስለ ወደፊቱ ጊዜ እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ማግኘት በእጅጉ እንደሚያጽናናን ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው የአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ሊያጽናኑን እንዲሁም በብዙ መንገዶች ሊረዱን ስለሚችሉ በሚገባ እንጠቀምባቸው።

14 በቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅሞ ሌሎችን በማስተማርና  በማጽናናት ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት ወቅት “ቅዱሳን መጻሕፍትን ግልጽልጽ አድርጎ” አስረድቷቸው ነበር። ባነጋገራቸው ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ልባቸው በጥልቅ ተነክቷል። (ሉቃስ 24:32) ሐዋርያው ጳውሎስም የኢየሱስን ግሩም ምሳሌ በመከተል “ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ” ከሰዎች ጋር ይወያይ ነበር። በቤርያ ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች “በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።” (ሥራ 17:2, 10, 11) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችን እንዲሁም ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን መመርመራችን ምንኛ የተገባ ነው! እንዲህ በማድረግ በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ማጽናኛና ተስፋ ማግኘት እንችላለን።

ሌሎችን ማጽናናት የምንችልባቸው ተጨማሪ መንገዶች

15, 16. የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳትና ለማጽናናት ልናደርጋቸው ከምንችላቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

15 የእምነት ባልንጀሮቻችንን በተለያዩ መንገዶች በመርዳት ልናጽናናቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በዕድሜ ለገፉ ወይም ለታመሙ የእምነት ባልንጀሮቻችን ገበያ ወጥተን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ልንሸምትላቸው እንችል ይሆናል። ለሌሎች ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ከልብ እንደምናስብላቸው ልናሳያቸው እንችላለን። (ፊልጵ. 2:4) ከዚህም ሌላ እንደ ፍቅር፣ ድፍረትና እምነት ያሉ ግሩም ባሕርያትን ስለሚያንጸባርቁ ወይም ብልሃተኛ ስለሆኑ እንደምናደንቃቸው በመግለጽ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ልናጽናናቸው እንችላለን።

16 በዕድሜ የገፉትን ሄደን በመጠየቅ እንዲሁም ያሳለፉትን ተሞክሮና ይሖዋን በማገልገላቸው ያገኟቸውን በረከቶች ሲያጫውቱን በጥሞና በማዳመጥ ልናጽናናቸው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን እኛንም ሊያበረታታንና ሊያጽናናን ይችላል። ልንጠይቃቸው ስንሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን ልናነብላቸው እንችላለን። በዚያ ሳምንት በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የሚወሰደውን ርዕስ ወይም በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የሚሸፈነውን ጽሑፍ ልናነብላቸው እንችል ይሆናል። ቅዱስ ጽሑፋዊ ይዘት ያሏቸውን ፊልሞች አብረናቸው ልናይ እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ በጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን ልናነብላቸው ወይም ልንነግራቸው እንችል ይሆናል።

17, 18. ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በመሆናችን እንደሚያጽናናን ብሎም እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

17 አንድ የይሖዋ አገልጋይ ማጽናኛ እንደሚያስፈልገው ካስተዋልን በግላችን በምናቀርበው ጸሎት ልናስበው እንችላለን። (ሮም 15:30፤ ቆላ. 4:12) በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እየተቋቋምን ሌሎችን ለማጽናናት ጥረት በምናደርግበት ጊዜ እንደ መዝሙራዊው በይሖዋ ላይ ልንተማመን እንችላለን፤ መዝሙራዊው “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” ብሏል። (መዝ. 55:22) በእርግጥም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በመሆናችን ምንጊዜም ያጽናናናል እንዲሁም ይደግፈናል።

18 አምላክ በጥንት ዘመን የነበሩ አምላኪዎቹን “የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ” ብሏቸው ነበር። (ኢሳ. 51:12) ይሖዋ በንግግራችንም ይሁን መልካም ሥራዎችን በመሥራት ያዘኑትን ለማጽናናት የምናደርገውን ጥረት የሚባርክልን ከመሆኑም ሌላ እኛንም ያጽናናናል። ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ በምድር ላይ መኖር ጳውሎስ በመንፈስ ለተቀቡ የእምነት ባልንጀሮቹ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ሁላችንንም ያጽናናናል፦ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም የወደደንና በጸጋ አማካኝነት ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ የሰጠን አባታችን የሆነው አምላክ ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም በመልካም ሥራና ቃል ሁሉ ያጽኗችሁ።”​—2 ተሰ. 2:16, 17

ታስታውሳለህ?

• ያዘኑትን የማጽናናት ሥራችን ምን ያህል በስፋት እየተከናወነ ነው?

• ሌሎችን ለማጽናናት ልናደርጋቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚያጽናና የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያዘኑትን በማጽናናቱ ሥራ ትካፈላለህ?

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ሌሎችን ማጽናናት ይችላሉ