በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል

አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል

 አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል

“የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት [ይነግሣል]።”—ሮም 5:21

1, 2. አንዳንዶች ትልቅ ቦታ እንዳለው አድርገው የሚመለከቱት ስጦታ የትኛው ነው? ከዚህ የሚበልጠው ስጦታ ምንድን ነው?

“ሮማውያን . . . ለቀጣዩ ትውልድ ትተውት ካለፉት ቅርስ ሁሉ የላቀው ሕጋቸውና ሕይወት በሕግ መመራት አለበት የሚለው መርሓቸው ነው።” (የሜልቦርን፣ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዴቪድ ዊሊያምስ) ይህ አባባል የቱንም ያህል ትክክል ቢሆን ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ትልቅ ውርስ ወይም ስጦታ አለ። ይህ ስጦታ የሰው ልጆች በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ጻድቃን ሆነው እንዲቆጠሩ እንዲሁም የመዳንና የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዲኖራቸው አምላክ ያደረገው ዝግጅት ነው።

2 አምላክ ይህንን ስጦታ ያዘጋጀበት መንገድ ከፍትሑና ከሕጉ ጋር የተያያዘ ነበር ማለት ይቻላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ምዕራፍ 5 ላይ ይህን ዝግጅት አብራርቶታል፤ ሆኖም ሁኔታውን የገለጸው እንዲሁ ከሕግ አንጻር ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ምዕራፉን የጀመረው የሚከተለውን የሚያበረታታ ሐሳብ በመናገር ነው፦ “በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ተብለን ስለተጠራን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን እንኑር።” በእርግጥም የአምላክን ስጦታ የተቀበሉ ሰዎች በምላሹ እሱን ለመውደድ ይነሳሳሉ። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ጳውሎስ ነበር። “የአምላክ ፍቅር፣ በተሰጠን መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ውስጥ ፈስሷል” በማለት ጽፏል።—ሮም 5:1, 5

3. የትኞቹ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተገቢ ነው?

3 ይሁንና ፍቅር የተንጸባረቀበት ይህ ስጦታ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ ይህን ስጦታ ፍትሐዊ በሆነና ሁሉንም ሰው በሚጠቅም መንገድ መስጠት የቻለው እንዴት  ነው? ሰዎች ይህን ስጦታ ለማግኘት ብቁ እንዲሆኑ ምን ማድረግ አለባቸው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የተሰጡትን አጥጋቢ መልሶችና እነዚህ መልሶች የአምላክን ፍቅር ጎላ አድርገው የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የአምላክ ፍቅርና ኃጢአት

4, 5. (ሀ) ይሖዋ ታላቅ ፍቅሩን የገለጸው በምን መንገድ ነው? (ለ) ሮም 5:12⁠ን ለመረዳት የትኛውን ታሪክ ማወቅ ያስፈልገናል?

4 ይሖዋ የሰውን ዘር ለመርዳት ሲል አንድያ ልጁን በመላክ ታላቅ ፍቅሩን አሳይቷል። ጳውሎስ፣ “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ለእኛ እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” በማለት ሁኔታውን ገልጾታል። (ሮም 5:8) “ገና ኃጢአተኞች ሳለን” የሚለውን ነጥብ ልብ በል። ኃጢአተኞች የሆንነው እንዴት እንደሆነ ሁሉም ሰው ማወቅ ያስፈልገዋል።

5 ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ማብራራት የጀመረው የሚከተለውን ነጥብ በመናገር ነው፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) አምላክ የሰውን ሕይወት አጀማመር አስመልክቶ ያስጻፈው ዘገባ ስላለ ጳውሎስ የጠቀሰውን ነጥብ መረዳት እንችላለን። በመጀመሪያ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን የተባሉ ሁለት ሰዎችን ፈጥሮ ነበር። ፈጣሪ ፍጹም ነው፤ ወላጆቻችን የሆኑት የመጀመሪያዎቹ ሰዎችም ፍጹማን ነበሩ። አምላክ፣ እነዚህን ሰዎች አንድ ነገር ብቻ የከለከላቸው ሲሆን ይህንን ሕግ አለመታዘዝም የሞት ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው ነግሯቸው ነበር። (ዘፍ. 2:17) ይሁንና አዳምና ሔዋን፣ ምክንያታዊ የሆነውን የአምላክን ሕግ ሆን ብለው በመጣስ ክፋት ፈጸሙ፤ በዚህ መንገድ አምላክን እንደ ሕግ ሰጪያቸውና ሉዓላዊ ገዥያቸው አድርገው ለመቀበል አሻፈረን አሉ።—ዘዳ. 32:4, 5

6. (ሀ) የአዳም ዘሮች የሚሞቱት ለምንድን ነው? የሙሴ ሕግ መሰጠቱ ይህንን ሁኔታ ለውጦታል? (ለ) የወረስነው ኃጢአት የሚያስከትለውን መዘዝ ለመረዳት የትኛውን በሽታ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል?

6 አዳም ልጆች የወለደው ኃጢአተኛ ከሆነ በኋላ በመሆኑ ኃጢአትንና ኃጢአት የሚያስከትላቸውን መዘዞች ለልጆቹ በሙሉ አስተላልፏል። እርግጥ ነው፣ ዘሮቹ አዳም እንዳደረገው መለኮታዊውን ሕግ ስላልጣሱ እሱ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ፈጽማችኋል ተብለው አልተከሰሱም፤ ደግሞም በወቅቱ ምንም ዓይነት ሕግ አልተሰጠም ነበር። (ዘፍ. 2:17) ያም ሆኖ የአዳም ዘሮች ኃጢአትን ወርሰዋል። በመሆኑም አምላክ ለእስራኤላውያን ሕግ እስከሰጠበት ጊዜ ድረስ ኃጢአትና ሞት ነግሦ ቆይቷል፤ ሕጉም ሕዝቡ ኃጢአተኞች መሆናቸውን በግልጽ አሳይቷል። (ሮም 5:13, 14ን አንብብ።) ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት በዘር ከሚተላለፉት እንደ ሜድትራንያን አኒሚያ ወይም ሂሞፊሊያ ካሉት በሽታዎች ጋር ማመሳሰል ይቻላል። የሩሲያ ዛር የነበረው የዳግማዊ ኒኮላስ እና የአሊግዛንድረ ልጅ የሆነው አሌክሰስ፣ ሂሞፊሊያ የተባለውን ደም እንዳይረጋ የሚያደርግ እክል ከወላጆቹ እንደወረሰ አንብበህ ይሆናል። እውነት ነው፣ እንደዚህ ባለው ቤተሰብ ውስጥም እንኳ አንዳንድ ልጆች ይህን እክል የሚያስተላልፈው ጂን ቢኖራቸውም የሕመም ምልክት አይታይባቸው ይሆናል። ከኃጢአት ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። አዳም ለዘሮቹ ያወረሳቸው ኃጢአት ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ የሚቻልበት መንገድ የለም። ሁሉም የዚህ ችግር ሰለባ ናቸው። በመሆኑም ሁሉም መሞታቸው አይቀርም። እንዲሁም በዘር ከሚተላለፉ አንዳንድ በሽታዎች በተቃራኒ የአዳም ልጆች በሙሉ ኃጢአትን ይወርሳሉ። ታዲያ ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ነፃ መውጣት የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን?

አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያደረገው ዝግጅት

7, 8. ሁለት ፍጹማን ሰዎች የተከተሉት አካሄድ የተለያየ ውጤት ያስገኘው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ፣ የሰው ልጆች ከወረሱት ኃጢአት ነፃ መውጣት የሚችሉበትን ዝግጅት አድርጓል። ጳውሎስ ይህ ሊሆን የቻለው ከጊዜ በኋላ በመጣ ሌላ ፍጹም ሰው አማካኝነት እንደሆነ ገልጿል፤ ይህ ሰው ሁለተኛው አዳም ነው ሊባል ይችላል። (1 ቆሮ. 15:45) ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ፍጹም ሰዎች የተከተሉት አካሄድ በጣም የተለያየ ውጤት አስከትሏል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?—ሮም 5:15, 16ን አንብብ።

8 ጳውሎስ “ስጦታው ያስገኘው ነገር በደሉ ካስከተለው ነገር የተለየ ነው” በማለት ጽፏል። አዳም በደለኛ ስለነበር በእሱ ላይ የሞት ፍርድ መበየኑ ተገቢ ነበር፤ በመሆኑም አዳም ሞቷል። ይሁንና የሚሞተው እሱ ብቻ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋል” ይላል። በአዳም ላይ ሞት እንዲበየን ያደረገው የአምላክ ፍትሕ እኛን ጨምሮ ፍጽምና በጎደላቸው ዘሮቹ ሁሉ ላይ ተመሳሳይ ፍርድ እንዲበየን የግድ ይላል። ያም ሆኖ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ከዚህ የተለየ ውጤት ማስገኘት እንደሚችል ማወቃችን የሚያጽናና ነው። ኢየሱስ የሚያስገኘው ውጤት ምንድን ነው? ጳውሎስ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን  ተብለው በመጠራት ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል” በማለት መልሱን ሰጥቶናል።—ሮም 5:18

9. በ⁠ሮም 5:16, 18 ላይ የሚገኘው “ጻድቃን ተብለው እንዲጠሩ” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው?

9 “ጻድቃን ተብለው እንዲጠሩ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ይህን አገላለጽ በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ተለዋጭ ዘይቤን በመጠቀም ሁኔታው ከሕግ አንጻር ተገልጿል ማለት ይቻላል። አንድ ሰው በአምላክ ፊት ያለው ሁኔታ እንደተለወጠ የሚጠቁም ሐሳብ ነው፤ ይሁን እንጂ ግለሰቡ ውስጣዊ ለውጥ ይኖረዋል ማለት አይደለም። . . . ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር አምላክን እንደ ዳኛ አድርጎ ይገልጸዋል፤ ይህ ዳኛ፣ ጻድቅ ባለመሆኑ ምክንያት ተከስሶ በምሳሌያዊ አነጋገር በእሱ ችሎት ፊት ለቀረበው ሰው ፈርዶለታል። አምላክ፣ ተከሳሹ ነፃ እንደሆነ የሚገልጽ ብያኔ አስተላልፏል።”

10. ኢየሱስ የሰው ልጆች ጻድቃን ተብለው መጠራት እንዲችሉ መሠረት የሚሆን ምን ነገር አድርጓል?

10 ጻድቅ የሆነው “የምድር ሁሉ ዳኛ” ጻድቅ ያልሆነን ሰው ነፃ ለማውጣት መሠረት የሚሆነው ምንድን ነው? (ዘፍ. 18:25) አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ይህን ለማድረግ የሚያስችለውን መሠረት ጥሏል። ኢየሱስ ፈተናዎች ያጋጠሙት፣ የተፌዘበትና ከፍተኛ እንግልት የደረሰበት ቢሆንም የአባቱን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታማኝ ሆኗል። (ዕብ. 2:10) ኢየሱስ፣ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የአዳምን ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ወይም ለመዋጀት የሚያስችል ቤዛ አቅርቧል።—ማቴ. 20:28፤ ሮም 5:6-8

11. ቤዛው ተመጣጣኝ የሆነው በምን መንገድ ነው?

11 ጳውሎስ፣ የኢየሱስን መሥዋዕት በሌላ ጥቅስ ላይ “ተመጣጣኝ ቤዛ” በማለት ጠርቶታል። (1 ጢሞ. 2:6) ቤዛው ተመጣጣኝ የሆነው በምን መንገድ ነው? አዳም በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዘሮቹ በሙሉ ኃጢአትንና ሞትን አውርሷቸዋል። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ፍጹም ልጆች ሊኖሩት ይችል ነበር። * በመሆኑም የኢየሱስ ሕይወትና በአብራኩ የነበሩት ፍጹማን ልጆች ሕይወት አንድ ላይ ተዳምሮ አዳምና ፍጹማን ያልሆኑት ዘሮቹ ያጡትን ነገር ለማስገኘት የሚያስችል ተመጣጣኝ ቤዛ ይሆናል የሚል አመለካከት ነበረን። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ አብራክ የነበሩ ልጆች የቤዛው ክፍል እንደሆኑ አይገልጽም። ሮም 5:15-19 እንደሚገልጸው የሰው ዘሮችን ነፃ የሚያወጣው ‘የአንድ ሰው’ ሞት ብቻ ነው። አዎን፣ ከአዳም ጋር ተመጣጣኝ የሚሆነው የኢየሱስ ፍጹም ሕይወት ነው። ትኩረት መደረግ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ ነው። ኢየሱስ ባከናወነው “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊት” ይኸውም እስከ ሞት ድረስ የታዛዥነት ጎዳና በመከተሉና ታማኝ በመሆኑ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ነፃ ስጦታንና ሕይወትን ማግኘት ችለዋል። (2 ቆሮ. 5:14, 15፤ 1 ጴጥ. 3:18) ይሁንና ቤዛው ከኃጢአት ነፃ የሚያወጣው እንዴት ነው?

በቤዛው አማካኝነት ነፃ መውጣት

12, 13. ጻድቃን ተብለው የተጠሩት ሰዎች የአምላክ ምሕረትና ፍቅር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ አምላክ፣ ልጁ ያቀረበውን ቤዛዊ መሥዋዕት ተቀብሎታል። (ዕብ. 9:24፤ 10:10, 12) ያም ሆኖ ግን  የኢየሱስን ታማኝ ሐዋርያት ጨምሮ በምድር ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ፍጹማን አልሆኑም። መጥፎ ድርጊቶችን ላለመፈጸም ቢጥሩም የሚሳካላቸው ሁልጊዜ አልነበረም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ከአዳም የወረሱት ኃጢአት ስለነበረባቸው ነው። (ሮም 7:18-20) ሆኖም አምላክ ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ይችላል፤ ደግሞም እንዲህ አድርጓል። ይሖዋ፣ ኢየሱስ ያቀረበውን “ተመጣጣኝ ቤዛ” የተቀበለ ሲሆን ሰብዓዊ አገልጋዮቹ ከዚህ ቤዛዊ ዝግጅት እንዲጠቀሙ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል።

13 እርግጥ ነው፣ ሐዋርያትና ሌሎች ሰዎች አንዳንድ መልካም ሥራዎችን ስላከናወኑ አምላክ እነሱን ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ አለበት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ በታላቅ ፍቅሩና ምሕረቱ ተነሳስቶ ከቤዛው ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህን ያደረገው ሐዋርያትና ሌሎች ሰዎች ከአዳም የወረሱትን ኃጢአት ይቅር በማለት ከተበየነባቸው ፍርድ ነፃ ሊያወጣቸው ስለመረጠ ነው። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ሁኔታውን በግልጽ አስቀምጦታል፦ “በእርግጥም እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት በዚህ ጸጋ ነው፤ ይህም እናንተ በራሳችሁ ያገኛችሁት ሳይሆን የአምላክ ስጦታ ነው።”—ኤፌ. 2:8

14, 15. አምላክ ጻድቃን ብሎ የጠራቸው ሰዎች ምን ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል? ያም ሆኖ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

14 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንድ ሰው የወረሰውን ኃጢአትም ሆነ በሕይወቱ ውስጥ የፈጸማቸውን ስህተቶች ይቅር ማለቱ ምን ያህል ታላቅ ስጦታ እንደሆነ እስቲ አስበው! ሰዎች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት የፈጸሟቸውን ኃጢአቶች ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፤ ሆኖም አምላክ በቤዛው መሠረት ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር ማለት ይችላል። ጳውሎስ “የብዙዎችን በደል ተከትሎ የመጣው ስጦታ . . . ብዙዎች ጻድቃን ተብለው እንዲጠሩ አስችሏል” ሲል ጽፏል። (ሮም 5:16) ፍቅር የተንጸባረቀበትን ይህን ስጦታ (ይኸውም ጻድቃን ተብለው መጠራትን) የተቀበሉት ሐዋርያትና ሌሎች ሰዎች እውነተኛውን አምላክ በእምነት ማምለካቸውን መቀጠል አለባቸው። ይህን ማድረጋቸው ወደፊት ምን ሽልማት ያስገኝላቸዋል? “የአምላክን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ነፃ ስጦታ [የሚቀበሉት] በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሕይወት አግኝተው ነገሥታት ሆነው [ይገዛሉ]።” በእርግጥም የጽድቅ ስጦታ የሚያስገኘው ውጤት የተለየ ነው። ይህ ስጦታ ሕይወት ያስገኛል።—ሮም 5:17፤ ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ።

15 ጻድቃን ተብለው በመጠራት ይህን ስጦታ የተቀበሉት ሰዎች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ይሆናሉ። ከክርስቶስ ጋር የሚወርሱት እነዚህ ሰዎች፣ ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የመሄድና መንፈሳዊ ልጆች የመሆን እንዲሁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር “ነገሥታት ሆነው [የመግዛት]” ተስፋ አላቸው።—ሮም 8:15-17, 23ን አንብብ።

አምላክ ለሌሎች ያሳየው ፍቅር

16. ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች በአሁኑ ጊዜ እንኳ ምን ዓይነት ስጦታ ማግኘት ይችላሉ?

16 እምነት ያላቸውና በታማኝነት አምላክን የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ‘ነገሥታት ሆነው የመግዛት’ ተስፋ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች፣ ከክርስትና በፊት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች የነበራቸው ዓይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ አላቸው። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች አሁንም እንኳ ፍቅር የተንጸባረቀበትን ይህን የአምላክ ስጦታ ሊያገኙና እንደ ጻድቃን ተቆጥረው በምድር ላይ ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል? ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች ከጻፈው የሚያጽናና ሐሳብ አንጻር መልሱ አዎን የሚል ነው!

17, 18. (ሀ) አብርሃም እምነት በማሳየቱ አምላክ እንዴት ተመልክቶታል? (ለ) ይሖዋ፣ አብርሃምን እንደ ጻድቅ ሊቆጥረው የቻለው እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ፣ ዋነኛ ምሳሌ ሊሆነን የሚችለውን አብርሃምን ጠቅሷል፤ አብርሃም፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሕግ ከመስጠቱና ክርስቶስ ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት የሚቻልበትን አጋጣሚ ከመክፈቱ ከረጅም ጊዜ በፊት የኖረ የእምነት ሰው ነበር። (ዕብ. 10:19, 20) እሱን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አብርሃም ወይም ዘሩ የዓለም ወራሽ እንደሚሆን ተስፋ ያገኘው በሕግ አማካኝነት ሳይሆን በእምነት በሚገኘው ጽድቅ ነው።” (ሮም 4:13፤ ያዕ. 2:23, 24) በመሆኑም አምላክ ታማኙን አብርሃምን ጻድቅ እንደሆነ አድርጎ ቆጥሮታል።—ሮም 4:20-22ን አንብብ።

18 ይህ ሲባል ግን አብርሃም ይሖዋን ባገለገለባቸው በርካታ ዓመታት ሁሉ ኃጢአት አልሠራም ማለት አይደለም። ጻድቅ የተባለው ከዚህ አንጻር አይደለም። (ሮም 3:10, 23) ይሁንና ወደር የሌለው ጥበብ ምንጭ የሆነው ይሖዋ፣ አብርሃም ያሳየውን ልዩ እምነትና በዚህም የተነሳ ያከናወናቸውን ሥራዎች ከግምት አስገብቷል። በተለይ ደግሞ አብርሃም በእሱ የዘር ሐረግ በሚመጣው ተስፋ የተሰጠበት  “ዘር” ላይ እምነት ነበረው። ይህ ዘር መሲሑ ወይም ክርስቶስ ነበር። (ዘፍ. 15:6፤ 22:15-18) መለኮታዊው ዳኛ ‘ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለውን ቤዛ’ መሠረት በማድረግ ቀደም ባሉት ዘመናት የተፈጸሙ ኃጢአቶችን ይቅር ማለት ችሏል። በመሆኑም አብርሃምና ሌሎች በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ የእምነት ሰዎች ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ አላቸው።—ሮም 3:24, 25ን አንብብ፤ መዝ. 32:1, 2

በአሁኑ ጊዜ ጻድቅ ሆኖ መቆጠር

19. አምላክ፣ አብርሃምን እንደ ጻድቅ የቆጠረው መሆኑ በዛሬ ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎችን የሚያጽናና ነው የምንለው ለምንድን ነው?

19 አፍቃሪ የሆነው አምላክ፣ አብርሃምን እንደ ጻድቅ የቆጠረው መሆኑ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚያጽናና ነው። ይሖዋ፣ አብርሃምን እንደ ጻድቅ ቆጥሮታል ሲባል በመንፈስ እንደቀባቸውና ‘ከክርስቶስ ጋር እንደሚወርሱት’ ክርስቲያኖች ጻድቅ ተብሎ እንዲጠራ አድርጎታል ማለት አይደለም። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ የተጠሩ’ ሲሆን አምላክ እንደ ‘ልጆቹ’ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። (ሮም 1:7፤ 8:14, 17, 33) ከዚህ በተቃራኒ አብርሃም “የይሖዋ ወዳጅ” ተብሏል፤ ይህን መብት ያገኘው ቤዛዊው መሥዋዕት ከመቅረቡ በፊት ነበር። (ያዕ. 2:23፤ ኢሳ. 41:8) እንደገና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ስላላቸው እውነተኛ ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል?

20. አምላክ በዛሬው ጊዜ እንደ አብርሃም ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥራቸውን ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል?

20 እነዚህ ክርስቲያኖች “ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት” በሰማይ የመኖር ተስፋ የሚያስገኘውን “የጽድቅን ነፃ ስጦታ” አልተቀበሉም። (ሮም 3:24፤ 5:15, 17) ያም ቢሆን በአምላክና በዝግጅቶቹ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሲሆን እምነታቸውንም በመልካም ሥራዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ “ስለ አምላክ መንግሥት [መስበክና] . . . ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ [ማስተማር]” ነው። (ሥራ 28:31) በዚህም ምክንያት ይሖዋ፣ አብርሃምን ጻድቅ አድርጎ እንደቆጠረው ሁሉ እነዚህንም ክርስቲያኖች እንደ ጻድቅ ሊቆጥራቸው ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚያገኙት ስጦታ ማለትም የአምላክ ወዳጅ መሆን፣ ቅቡዓን ከሚቀበሉት “ነፃ ስጦታ” የተለየ ነው። ቢሆንም ለዚህ ስጦታ በጣም አመስጋኞች ናቸው።

21. ከይሖዋ ፍቅርና ፍትሕ ምን ጥቅም አግኝተናል?

21 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰብዓዊ ገዥዎች በርካታ ነገሮችን ለማከናወን ቃል የሚገቡ ቢሆንም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ማግኘት የቻልከው ግን ከእነሱ አይደለም። ይህ ተስፋ በአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ጥበብ የተንጸባረቀበት ዓላማ ላይ የተመካ ነው። ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ደረጃ በደረጃ እርምጃዎችን ወስዷል። እነዚህ እርምጃዎችም ከትክክለኛ ፍትሕ ጋር የሚስማሙ ናቸው። ከዚህም በላይ የአምላክን ታላቅ ፍቅር ያንጸባርቃሉ። ጳውሎስ “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ለእኛ እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” ማለቱ ምንኛ የተገባ ነው!—ሮም 5:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ለምሳሌ ያህል፣ በኢየሱስ አብራክ የነበሩ ልጆች የቤዛው ክፍል እንደሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ ገጽ 736 አንቀጽ 4 እና 5 ላይ ወጥቶ ነበር። በተጨማሪም የመጋቢት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4 አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• አዳም ለዘሮቹ ምን አውርሷቸዋል? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?

• “ተመጣጣኝ ቤዛ” የቀረበው እንዴት ነው? ተመጣጣኝ የሆነውስ በምን መንገድ ነው?

• ጻድቅ ተብሎ የመጠራት ስጦታ አንተ ምን ተስፋ እንዲኖርህ አድርጓል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ኃጢአት ሠርቷል፤ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ግን “ተመጣጣኝ ቤዛ” አቅርቧል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሱስ አማካኝነት ጻድቃን ተብለን መጠራታችን እንዴት ያለ ታላቅ የምሥራች ነው!