በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ግሩም የበላይ ተመልካችና ጥሩ ወዳጅ”

“ግሩም የበላይ ተመልካችና ጥሩ ወዳጅ”

 “ግሩም የበላይ ተመልካችና ጥሩ ወዳጅ”

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጆን (ጃክ) ባር ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4, 2010 ማለዳ ላይ በ97 ዓመቱ ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቅቋል። ብዙዎች ወንድም ባር “ግሩም የበላይ ተመልካችና ጥሩ ወዳጅ” እንደሆነ ይገልጹ ነበር።

ወንድም ጃክ ባር የተወለደው በአበርዲን፣ ስኮትላንድ ሲሆን ከሦስት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነው። አባቱና እናቱ ቅቡዓን ነበሩ። ወንድም ባር፣ በልጅነቱ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እንዳሳለፈ ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር፤ እንዲሁም የሚወዳቸው ወላጆቹ የተዉለትን ግሩም ምሳሌ በጣም ያደንቃል።

ወንድም ጃክ ባር በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረበት ጊዜ የማያውቃቸውን ሰዎች ማነጋገር በጣም ይከብደው ነበር። ሆኖም ይህን ችግር ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ሲሆን በ1927 አንድ እሁድ ቀን ከሰዓት በኋላ ከአባቱ ጋር ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ። በወቅቱ 14 ዓመቱ ነበር፤ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን አገልግሎቱን ሀ ብሎ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። ወንድም ባር ከዚያ ቀን አንስቶ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የምሥራቹ ቀናተኛ ሰባኪ ነበር።

ወንድም ጃክ ወጣት ሳለ እናቱ ሕይወቷን ሊያሳጣት የሚችል ከባድ አደጋ አጋጥሟት ነበር፤ ይህ ሁኔታ ስለ ሕይወት ዓላማ ቆም ብሎ እንዲያስብ ስላደረገው በ1929 ራሱን ለይሖዋ ወሰነ። ከዚያም መጀመሪያ ባገኘው አጋጣሚ በ1934 ተጠመቀ። በ1939 በለንደን፣ እንግሊዝ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነ። ለ71 ዓመታት ያከናወነውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

ጥቅምት 29, 1960 ወንድም ባር፣ ሚልድረድ ዊለት ከተባለች ለረጅም ዓመታት በቅንዓት ስታገለግል የቆየች አቅኚና ሚስዮናዊት ጋር ትዳር መሠረተ፤ ወንድም ባር ከእህት ሚልድረድ ጋር ያለውን ግንኙነት “ውድና ልዩ የሆነ ወዳጅነት” በማለት ጠርቶታል። እህት ሚልድረድ ጥቅምት 2004 ምድራዊ ሕይወቷን እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ ወንድም ባርና ባለቤቱ የሚዋደዱና ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ባልና ሚስት ሆነው ኖረዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በትዳር ሕይወታቸው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አብረው ያነብቡ ነበር።

ወንድም ጃክ ባርን የሚያውቁት ሰዎች የሚያስታውሱት አሳቢነት በሚንጸባረቅበት ምክሩ ነው፤ የሚሰጠው ምክር ምንጊዜም ሚዛናዊ፣ ደግነት የተሞላበትና በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ነበር። ወንድም ባር ትጉህ ሠራተኛ፣ አሳቢና አፍቃሪ የበላይ ተመልካች እንዲሁም ታማኝ ወዳጅ ነበር። የሚሰጣቸው ሐሳቦችና ንግግሮች እንዲሁም የሚያቀርበው ጸሎት ጠንካራ መንፈሳዊ አቋምና ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንደነበረው ያሳያሉ።

ውድ ወንድማችን ከእኛ መለየቱ ቢያሳዝነንም የማይሞት ሕይወት ስጦታ በማግኘቱ ደስ ይለናል፤ ወንድም ባር ይህን መብት በጉጉት ይጠባበቀው እንዲሁም ደጋግሞ ያነሳው ነበር። ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው መብት ነበር።​—1 ቆሮ. 15:53, 54 *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 የወንድም ጆን ባር የሕይወት ታሪክ በሐምሌ 1, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 26-31 ላይ ይገኛል።