በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዝግጁ ሁኑ!

ዝግጁ ሁኑ!

 ዝግጁ ሁኑ!

“እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።”​—ማቴ. 24:44

1, 2. (ሀ) አንድ ታይገር ከሰነዘረው ጥቃት ጋር ሊመሳሰል የሚችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት የተነገረው የትኛው ክንውን ነው? (ለ) ክርስቶስ የተቀረውን የሰይጣን ዓለም ሲያጠፋ እኛ ከጥፋቱ ለመትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

የእንስሳት ትርዒት በማሳየት የታወቀ አንድ ሰው ቤንጋል ታይገር የተባሉ የነብር ዝርያዎችን በማላመድና በማሠልጠን ለዓመታት ሕዝብን ያዝናና ነበር። “የአንድን እንስሳ አመኔታ ማትረፍ ስትችል በዓለም ላይ ከሁሉ የላቀ ስጦታ እንዳገኘህ ይሰማሃል” በማለት ተናግሯል። ይሁንና ጥቅምት 3, 2003 ይህ መተማመን በድንገት ጠፋ። ካሠለጠናቸው እንስሳት መካከል አንዱ የሆነውና 172 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ታይገር በውል ባልታወቀ ምክንያት በሰውየው ላይ ጉዳይ አደረሰበት። ታይገሩ እንዲህ ዓይነት ጥቃት ይሰነዝራል ተብሎ ፈጽሞ አልተጠበቀም፤ በመሆኑም አሠልጣኙ ዝግጁ አልነበረም።

2 መጽሐፍ ቅዱስ አንድ “አውሬ” ጥቃት እንደሚሰነዝርና ዝግጁ ልንሆን እንደሚገባ አስቀድሞ የተናገረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ራእይ 17:15-18ን አንብብ።) ይህ አውሬ የሚያጠቃው ማንን ነው? ነገሮች በድንገት ይለዋወጡና የዲያብሎስ ዓለም እርስ በርሱ ይከፋፈላል። ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው አውሬ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚያመለክት ሲሆን “አሥሩ ቀንዶች” ደግሞ የዓለምን የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ይወክላሉ። እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች በጋለሞታ በተመሰለችውና የዓለምን የሐሰት ሃይማኖት በምታመለክተው ታላቂቱ ባቢሎን ላይ በመነሳት ሙሉ በሙሉ ያጠፏታል። ይህ የሚከናወነው መቼ ነው? ቀኑንና ሰዓቱን አናውቅም። (ማቴ. 24:36) ሆኖም ይህ የሚሆነው ባልጠበቅነው ሰዓት እንደሆነ እንዲሁም የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን እናውቃለን። (ማቴ. 24:44፤ 1 ቆሮ. 7:29) እንግዲያው ይህ ጥቃት በሚሰነዘርበትና ክርስቶስ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ በሚመጣበት ወቅት መዳን እንድንችል በመንፈሳዊ ዝግጁ መሆናችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 21:28) ይህን ማድረግ እንድንችል ዝግጁ በመሆናቸው አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ሲፈጸሙ የዓይን ምሥክር መሆን ከቻሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ትምህርት እንውሰድ። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ታሪክ በቁም ነገር እንመለከተዋለን?

እንደ ኖኅ ዝግጁ ሁኑ

3. ኖኅ፣ አምላክን በታማኝነት ማገልገል ፈታኝ እንዲሆንበት ያደረገው ምን ነበር?

3 ኖኅ በኖረበት ዘመን በምድር ላይ የነበረው ሁኔታ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ እጅግ የሚያንገሸግሽ ቢሆንም እሱ አምላክ ቃል የገባው ነገር የሚፈጸምበትን ጊዜ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቅ ነበር። በአምላክ ላይ ያመፁት መላእክት ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር መምጣታቸውና ቆንጆ ከሆኑ ሴቶች ጋር መኖራቸው በኖኅ ላይ ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ አስከትሎ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር! ከተፈጥሮ ውጭ ከሆነው ጥምረት የተገኙትና ከሰው በላይ ብርቱ የሆኑት እነዚህ ልጆች “ኃያላን” የተባሉ ሲሆን እነሱም በሌሎች ላይ ግፍ ይፈጽሙ ነበር። (ዘፍ. 6:4 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ግዙፍ ፍጥረታት በሄዱበት ሁሉ ሁከት ስለሚፈጥሩ ምድር ምን ያህል በዓመፅ ተሞልታ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ትችላለህ! በዚህም የተነሳ ክፋት የነገሠ ሲሆን ሰዎች በአስተሳሰብና በባሕርይ እጅግ ያዘቀጡ ሆኑ። በዚህም ምክንያት የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ፣ አምላካዊ ፍርሃት የሌለውን ይህን ዓለም ለማጥፋት ወሰነ።​—ዘፍጥረት 6:3, 5, 11, 12ን አንብብ። *

4, 5. በዛሬው ጊዜ ያለው ሁኔታ በኖኅ ዘመን ከነበረው ጋር የሚመሳሰለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

4 ኢየሱስ በዘመናችን የሚኖረው ሁኔታ በኖኅ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ትንቢት ተናግሯል። (ማቴ. 24:37) ለምሳሌ፣ ክፉ መናፍስት በሰው ልጆች ላይ ዛሬም ተጽዕኖ ሲያሳድሩ እንመለከታለን። (ራእይ 12:7-9, 12) አጋንንት የሆኑት እነዚህ መላእክት በኖኅ ዘመን ሥጋ ለብሰው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሥጋ እንዳይለብሱ የታገዱ ቢሆንም ወጣት አዋቂ ሳይሉ ሁሉንም በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ ይፈልጋሉ። ወራዳ የፆታ ምኞት ያላቸው  እነዚህ ፍጥረታት ከበስተጀርባ ሆነው የሰዎችን አእምሮ በመበከል ክፉና ጸያፍ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸው ሲሆን ይህን በማድረግ እርካታ ያገኛሉ።​—ኤፌ. 6:11, 12

5 የአምላክ ቃል፣ ዲያብሎስን “ነፍሰ ገዳይ” በማለት የሚጠራው ሲሆን “ሞት የማስከተል ኃይል” እንዳለውም ይናገራል። (ዮሐ. 8:44፤ ዕብ. 2:14) በእርግጥ ይህ ሲባል የፈለገውን ሁሉ እንዲገድል አምላክ ይፈቅድለታል ማለት አይደለም። ይሁንና ይህ አረመኔ የሆነ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ሰዎች ተታልለው በራሳቸው ላይ ጉዳት የሚያመጣና ለሞት የሚዳርጋቸው ነገር እንዲፈጽሙ ያደርጋል። በሰዎች ልብና አእምሮ ውስጥ ጥላቻ በመዝራት ነፍስ ለማጥፋት እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚወለዱ 142 ልጆች መካከል አንዱ በሰው እጅ ሕይወቱ ያልፋል። እንደነዚህ ያሉ ዘግናኝ የዓመፅ ድርጊቶች እየተስፋፉ ሲሄዱ ይሖዋ ዝም ብሎ የሚመለከት ይመስልሃል? በኖኅ ዘመን እንዳደረገው በዛሬው ጊዜም እርምጃ የሚወስድ አይመስልህም?

6, 7. ኖኅና ቤተሰቡ እምነትና አምላካዊ ፍርሃት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

6 ከጊዜ በኋላ አምላክ በምድር ላይ የጥፋት ውኃ በማምጣት ሥጋ ለባሽን ሁሉ ለማጥፋት እንደወሰነ ለኖኅ ነገረው። (ዘፍ. 6:13, 17) ይሖዋ፣ የሣጥን ቅርጽ ያለው ግዙፍ የሆነ መርከብ እንዲሠራ ኖኅን አዘዘው። ኖኅና ቤተሰቡም በተነገራቸው መሠረት ሥራውን ተያያዙት። ለመሆኑ ይሖዋን እንዲታዘዙና የአምላክ የፍርድ ቀን ሲመጣ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ የረዳቸው ምን ነበር?

7 ኖኅና ቤተሰቡ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነትና አምላካዊ ፍርሃት ስለነበራቸው አምላክ እንዳዘዛቸው አድርገዋል። (ዘፍ. 6:22፤ ዕብ. 11:7) ኖኅ የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በዙሪያው የነበሩት ሰዎች በሚፈጽሙት መጥፎ ድርጊት ከመካፈል ተቆጥቧል። (ዘፍ. 6:9) ቤተሰቡ በአካባቢያቸው ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ የሚታየው የጭካኔና የዓመፀኝነት ባሕርይ እንዳይጋባባቸው መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ተገንዝቦ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከልክ በላይ ላለመጠመድ ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። አምላክ ለኖኅና ለቤተሰቡ የሰጣቸው ሥራ ነበር፤ በመሆኑም ቤተሰቡ በአጠቃላይ በሕይወታቸው ውስጥ ለዚህ ሥራ ሙሉ ትኩረት መስጠታቸው በጣም አስፈላጊ ነበር።​—ዘፍጥረት 6:14, 18ን አንብብ።

ኖኅና ቤተሰቡ ዝግጁ ነበሩ

8. የኖኅ ቤተሰብ አባላት ለአምላክ ያደሩ እንደነበሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትኩረት የሚያደርገው የቤተሰብ ራስ በሆነው በኖኅ ላይ ቢሆንም የኖኅ ሚስት እንዲሁም ወንዶች ልጆቻቸውና የልጆቹ ሚስቶችም ጭምር የይሖዋ አምላኪዎች ነበሩ። ነቢዩ ሕዝቅኤል የተናገረው ነገር ይህ እውነት መሆኑን ያረጋግጥልናል። ኖኅ በሕዝቅኤል ዘመን ቢኖር ኖሮ ልጆቹ በአባታቸው ጽድቅ እንደማይድኑ ነቢዩ ተናግሯል። ልጆቹ ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ነበሩ። በመሆኑም የኖኅ ልጆች አምላክንና መንገዶቹን እንደሚወዱ በግለሰብ ደረጃ አሳይተው መሆን አለበት። (ሕዝ. 14:19, 20) የኖኅ ቤተሰብ፣ እሱ የሚሰጣቸውን መመሪያ ይታዘዙ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ልክ እንደ እሱ ጠንካራ እምነት አዳብረዋል፤ ሌሎች የሚያሳድሩባቸው ተጽዕኖ አምላክ ከሰጣቸው ሥራ ወደኋላ እንዲሉ እንዲያደርጋቸው አልፈቀዱም።

9. በዘመናችን እንደ ኖኅ ዓይነት እምነት እንዳላቸው ያሳዩት እነማን ናቸው?

9 ዛሬም በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የኖኅን ምሳሌ ለመከተል ከልብ የሚጥሩ የቤተሰብ ራሶች እንዳሉ መመልከት ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እነዚህ ወንድሞች ቤተሰባቸው ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ትምህርት  እንዲያገኝ ማድረግ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። መንፈሳዊ ፍላጎታቸውንም ማሟላት ይኖርባቸዋል። የቤተሰብ ራሶች ይህን ሲያደርጉ በቅርቡ ይሖዋ ለሚወስደው እርምጃ ራሳቸውን ዝግጁ ያደርጋሉ።

10, 11. (ሀ) ኖኅና ቤተሰቡ መርከቧ ውስጥ ከገቡ በኋላ ምን ተሰምቷቸው መሆን አለበት? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይገባናል?

10 ኖኅ፣ ሚስቱ፣ ወንዶች ልጆቹና ሚስቶቻቸው መርከቡን ሠርተው ለመጨረስ 50 ዓመት ገደማ ፈጅቶባቸው ሊሆን ይችላል። መርከቡን በሚሠሩበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ በአእምሮህ መሳል ትችላለህ። በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ መርከቡ ይገቡና ይወጡ እንደነበር ግልጽ ነው። መርከቡ ውኃ እንዳያስገባ በቅጥራን ሲለቀልቁት፣ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሲያከማቹ እንዲሁም እንስሳቱን ሲያስገቡ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በመጨረሻም ሲጠበቅ የነበረው ቀን ደረሰ። ይህ ዕለት የዋለው በ2370 ዓ.ዓ. በሁለተኛው ወር በ17ኛው ቀን ሲሆን በዚያ ዕለት ኖኅና ቤተሰቡ ወደ መርከቡ ገቡ። ይሖዋ የመርከቡን በር ከዘጋው በኋላ ዝናብ መጣል ጀመረ። በዛሬ ጊዜ ኃይለኛ የተባለው ዝናብ እንኳ በዚያን ወቅት የጣለውን ዶፍ አይተካከለውም። ዝናቡ እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሰማዩ የተቀደደ ይመስል ነበር። (ዘፍ. 7:11, 16) ከመርከቡ ውጭ ያሉት ሰዎች ሲሞቱ መርከቡ ውስጥ ያሉት ግን በሕይወት ተረፉ። የኖኅ ቤተሰብ በዚያ ወቅት ምን ተሰምቷቸው ይሆን? አምላክን ከልባቸው እንደሚያመሰግኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ ‘አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር በማድረግ ዝግጁ መሆናችን በእርግጥም ጥሩ ውሳኔ ነበር!’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። (ዘፍ. 6:9) አንተም ከአርማጌዶን በሕይወት ተርፈህ ልክ እንደ እነሱ ልብህ በአድናቆት ሲሞላ በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃል?

11 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የሰይጣንን ሥርዓት ለማጥፋት የገባውን ቃል እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም። ‘አምላክ የገባውን ቃል አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽምና የተናገረው ነገር ሁሉ እሱ በቀጠረው ጊዜ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ከልቤ አምናለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። መልስህ አዎን ከሆነ በፍጥነት እየቀረበ ያለውን “የይሖዋን ቀን” በአእምሮህ አቅርበህ በመመልከት ዝግጁ ሁን።​—2 ጴጥ. 3:12

ሙሴ ምንጊዜም ንቁ ነበር

12. የሙሴን ትኩረት ሊሰርቁ ይችሉ የነበሩት የትኞቹ ነገሮች ናቸው?

12 እስቲ አሁን ደግሞ ሌላ ምሳሌ እንመልከት። ከሥጋዊ አመለካከት አንጻር ሙሴ በግብፅ ውስጥ በጣም ግሩም የሆኑ አጋጣሚዎች የነበሩት ይመስላል። የፈርዖን ሴት ልጅ ያሳደገችው መሆኑ ከፍተኛ ከበሬታን የማግኘት ብሎም ጥሩ ጥሩ ምግቦችን የመመገብ፣ ምርጥ ልብሶችን የመልበስ እንዲሁም ምቾትና ድሎት ባለው አካባቢ የመኖር አጋጣሚ አስገኝቶለት መሆን አለበት። ከፍተኛ ትምህርትም ተከታትሏል። (የሐዋርያት ሥራ 7:20-22ን አንብብ።) ምናልባትም ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሀብትና ንብረት መውረስ ይችል ነበር።

13. ሙሴ ምንጊዜም ትኩረቱ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነበር?

13 ወላጆቹ በልጅነቱ የሰጡት ሥልጠና የግብፃውያን የጣዖት አምልኮ ከንቱ መሆኑን እንዲገነዘብ ሳያደርገው አልቀረም። (ዘፀ. 32:8) የግብፃውያን ሥርዓተ ትምህርትና የቤተ መንግሥቱ ውበት ሙሴ እውነተኛውን አምልኮ እንዲተው አላማለሉትም። አምላክ ለአባቶቹ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ማሰላሰሉ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ዝግጁ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርበት አድርጎት መሆን  አለበት። ሙሴ፣ እስራኤላውያንን “የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ወደ እናንተ ልኮኛል” ብሏቸዋል።​—ዘፀአት 3:15-17ን አንብብ።

14. ሙሴ እምነትና ድፍረት የሚጠይቅ ምን ፈተና አጋጥሞት ነበር?

14 በድን የሆኑትን የግብፃውያን አማልክት ከሚወክሉት ጣዖታት በተቃራኒ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ለሙሴ እውን ነበር። ሙሴ “የማይታየውን እንደሚያየው” አድርጎ ይመላለስ ነበር። ሙሴ የአምላክ ሕዝቦች ነፃ እንደሚወጡ እምነት ቢኖረውም ይህ የሚሆንበትን ጊዜ አያውቅም ነበር። (ዕብ. 11:24, 25, 27) በደል የደረሰበትን እስራኤላዊ ባሪያ ለማገዝ እርምጃ መውሰዱ ዕብራውያን ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያል። (ዘፀ. 2:11, 12) ይሁንና ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ የሚያወጣበት ጊዜ ገና ስላልደረሰ ሙሴ ወደ ሩቅ አገር በመሄድ በስደት ለመኖር ተገደደ። በግብፃውያን ቤተ መንግሥት የለመደውን የቅንጦት ሕይወት ትቶ በምድረ በዳ መኖር አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ምንም ጥርጥር የለውም። እንደዚያም ሆኖ ሙሴ፣ ይሖዋ የሚሰጠውን እያንዳንዱን መመሪያ በንቃት በመከታተል ዝግጁ መሆኑን አሳይቷል። በመሆኑም በምድያም 40 ዓመት ከቆየ በኋላ ወንድሞቹን ከባርነት ነፃ ለማውጣት አምላክ ሊጠቀምበት ችሏል። ሙሴ አምላክ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል በታዛዥነት ወደ ግብፅ ተመለሰ። ሙሴ መለኮታዊ ተልእኮ የሚፈጽምበት ጊዜ ደርሶ ነበር፤ አሁን የአምላክን ሥራ እሱ ባዘዘው መንገድ ማከናወን ይችላል። (ዘፀ. 3:2, 7, 8, 10) “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት” የሆነው ሙሴ ወደ ግብፅ ከተመለሰ በኋላ በፈርዖን ፊት ለመቅረብ እምነትና ድፍረት ጠይቆበታል። (ዘኍ. 12:3) በፈርዖን ፊት የቀረበው አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጊዜ ነው፤ አምላክ የተለያዩ መቅሰፍቶችን ለማምጣት ባሰበ ቁጥር ሙሴ ወደ ፈርዖን ይገባ ነበር። የሚገርመው ነገር፣ ይህንን ያደረገው ሁኔታው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል ሳያውቅ ነበር።

15. ሙሴ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም በሰማይ ያለውን አባቱን ለማክበር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንዲፈልግ ያነሳሳው ምንድን ነው?

15 ሙሴ፣ ከ1513 ዓ.ዓ. እስከ 1473 ዓ.ዓ. ባሉት 40 ዓመታት ውስጥ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች አጋጥመውታል። ያም ሆኖ ይሖዋን ለማክበር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈልግ የነበረ ሲሆን እስራኤላውያንም እንዲሁ እንዲያደርጉ በሙሉ ልቡ ያበረታታቸው ነበር። (ዘዳ. 31:1-8) እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ከራሱ ስም ይበልጥ የይሖዋን ስም ይወድ እንዲሁም ሉዓላዊነቱን ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። (ዘፀ. 32:10-13፤ ዘኍ. 14:11-16) እኛም ተስፋ የሚያስቆርጡ ወይም እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ቢያጋጥሙንም አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ የላቀ ጥበብና ጽድቅ የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ በማመን የአምላክን አገዛዝ መደገፋችንን መቀጠል ይኖርብናል። (ኢሳ. 55:8-11፤ ኤር. 10:23) አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል?

ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ!

16, 17. ማርቆስ 13:35-37 ለአንተ ትልቅ ትርጉም ያለው ለምንድን ነው?

16 “የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፣ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማር. 13:33) ኢየሱስ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠው የዚህን ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ የሚጠቁመውን ምልክት በተናገረበት ወቅት ነው። ማርቆስ እንደዘገበው ኢየሱስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ይህን ትንቢት አስመልክቶ የተናገረውን ሐሳብ የደመደመው እንዲህ በማለት ነበር፦ “የቤቱ ባለቤት፣ በምሽት ይሁን በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ይሁን ንጋት ላይ፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ! ይሁንና ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።”​—ማር. 13:35-37

17 ኢየሱስ የሰጠው ማሳሰቢያ ትኩረት የሚስብ ነው። ሌሊት ላይ የሚኖሩትን አራት ክፍለ ጊዜያት ጠቅሷል። የመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አንስቶ ጎህ  እስኪቀድ ድረስ ያለውን ጊዜ ስለሚሸፍን ይህ ጊዜ ነቅቶ ለመጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። የጦር ስልት አዋቂዎች ይህ ጊዜ በጠላት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከሁሉ ይበልጥ አመቺ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ምክንያቱም የጠላት ሠራዊት ‘ተኝቶ’ እያለ ለመድረስ ያመቻል። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ ሁኔታ ዓለም ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት ባለበት በአሁኑ ወቅት እኛ ነቅተን መጠበቅ በጣም ሊያታግለን ይችላል። ታዲያ በትንቢት የተነገረውን የመጨረሻውን ጊዜ እንዲሁም መዳን የምናገኝበትን ጊዜ ‘ነቅተን መጠበቅ’ እና ‘በንቃት መከታተል’ እንዳለብን እንጠራጠራለን?

18. የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ምን በዋጋ የማይተመን መብት አለን?

18 በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው እንስሳትን የሚያሠለጥነው ሰው ታይገሩ ካደረሰበት ጉዳት በሕይወት መትረፍ ችሏል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት፣ የሐሰት ሃይማኖትም ሆነ የዚህ ክፉ ሥርዓት ቀሪ ክፍል ከሚመጣው ጥፋት እንደማያመልጡ በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል። (ራእይ 18:4-8) ወጣት አረጋዊ ሳይል የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ኖኅና ቤተሰቡ እንዳደረጉት ዝግጁ ሆነው ለመገኘት የቻሉትን ሁሉ ማድረጋቸው አንገብጋቢ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ለአምላክ ክብር በማይሰጠው በዚህ ዓለም ውስጥ የሐሰት አስተማሪዎች እንዲሁም የአምላክን መኖር የሚጠራጠሩና በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች በፈጣሪ ላይ ያፌዛሉ። ይህ ሁኔታ ተጽዕኖ አያሳድርብንም ብለን ማሰብ የለብንም። እንግዲያው ከላይ የተመለከትናቸውን ምሳሌዎች በቁም ነገር እናስብባቸው፤ ይሖዋ “የአማልክት አምላክ” እንዲሁም “ታላቅ አምላክ፣ ኀያልና የሚያስፈራ” መሆኑን ለማስረዳት ብሎም እሱን ለማክበር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በመፈለግ ንቁ ሆነን እንኑር!​—ዘዳ. 10:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በ⁠ዘፍጥረት 6:3 ላይ የተጠቀሰውን “120 ዓመት” የሚለውን አገላለጽ በተመለከተ የታኅሣሥ 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30⁠ን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• ኖኅ ለቤተሰቡ መንፈሳዊ ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት የነበረበት ለምንድን ነው?

• የምንኖርበት ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር በእጅጉ የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

• ሙሴ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢያጋጥሙትም ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ ያተኮረው ለምንድን ነው?

• ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ እንድትሆን የሚያነሳሱህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኖኅና ቤተሰቡ ምንጊዜም ትኩረታቸውን ይሖዋ በሰጣቸው ሥራ ላይ አድርገዋል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የሰጠው አስተማማኝ ተስፋ ሙሴ ምንጊዜም ንቁ ሆኖ እንዲኖር ረድቶታል