በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ ኤርምያስ በንቃት ተጠባበቁ

እንደ ኤርምያስ በንቃት ተጠባበቁ

 እንደ ኤርምያስ በንቃት ተጠባበቁ

“እኔ [ይሖዋ] ቃሌን ለመፈጸም በንቃት እየተጠባበቅኩ ነው።”​—ኤር. 1:12 NW

1, 2. ይሖዋ ‘በንቃት የሚጠባበቅ’ መሆኑ ከአልሞንድ ዛፍ ጋር ተያይዞ የተገለጸው ለምንድን ነው?

በሊባኖስና በእስራኤል ኮረብታዎች ላይ ቀድመው ከሚያብቡት ዛፎች መካከል አንዱ የአልሞንድ ዛፍ ነው። ሮዝ ወይም ነጭ ቀለም ያላቸውና ውብ የሆኑት የዚህ ዛፍ አበቦች ቀደም ብለው ማለትም በጥር ወር መገባደጃ ወይም በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ሊያብቡ ይችላሉ። የዛፉ የዕብራይስጥ ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “ንቁ የሆነው” የሚል ፍቺ አለው።

2 ይሖዋ ኤርምያስን ነቢይ አድርጎ በሾመው ጊዜ አንድን አስፈላጊ እውነታ ለማስረዳት የአልሞንድ ዛፍ ያለውን ይህን ልዩ ባሕርይ ምሳሌ አድርጎ መጠቀሙ ተገቢ ነው። ኤርምያስ አገልግሎቱን ሲጀምር የዚህን ዛፍ ቁጥቋጦ በራእይ እንዲያይ ተደርጎ ነበር። ይህ ምን ትርጉም ነበረው? ይሖዋ “እኔ ቃሌን ለመፈጸም በንቃት እየተጠባበቅኩ ነው” በማለት ሁኔታውን ግልጽ አድርጎታል። (ኤር. 1:11, 12 NW) የአልሞንድ ዛፍ ቀደም ብሎ ‘እንደሚነቃ’ ሁሉ ይሖዋም ሕዝቡ ታዛዥ አለመሆናቸው ምን እንደሚያስከትልባቸው እንዲያስጠነቅቁ በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ማለዳ’ በመንቃት ነቢያቱን ይልክ ነበር። (ኤር. 7:25 የ1954 ትርጉም) ይሖዋ በትንቢት የተናገረው ቃሉ እስኪፈጸም ድረስ አያርፍም ወይም ‘በንቃት ይጠባበቃል።’ ልክ በተወሰነው ጊዜ ላይ ማለትም በ607 ዓ.ዓ. የይሖዋ ፍርድ ከሃዲ በሆነችው የይሁዳ ብሔር ላይ መጣ።

3. ከይሖዋ ጋር በተያያዘ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

3 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም በንቃት የሚጠባበቅ ከመሆኑም ሌላ ሁኔታዎችን በትኩረት ይከታተላል። የተናገረው ቃል ፍጻሜ ማግኘቱን በንቃት ይከታተላል እንጂ ፈጽሞ ችላ አይለውም። ይሖዋ ነገሮችን  በትኩረት የሚከታተል መሆኑ አንተን የሚነካህ እንዴት ነው? በዚህ በያዝነው ዓመት ማለትም በ2011 ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸም “በንቃት” እንደሚጠባበቅ ሙሉ እምነት አለህ? ይሖዋ የሰጣቸው እርግጠኛ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ ካለን ከመንፈሳዊ ድብታ ለመንቃት ጊዜው አሁን ነው። (ሮም 13:11) ኤርምያስ የይሖዋ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም ንቁ ነበር። ኤርምያስ አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም እንዴት በንቃት እንደተጠባበቀና እንዲህ ያደረገው ለምን እንደሆነ መመርመራችን ይሖዋ በሰጠን ሥራ እንዴት መጽናት እንደምንችል ለማወቅ ይረዳናል።

አጣዳፊ መልእክት

4. ኤርምያስ መልእክቱን ሲያውጅ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል? መልእክቱ አጣዳፊ የነበረውስ ለምንድን ነው?

4 ኤርምያስ ጠባቂ ሆኖ የማገልገል ተልእኮ ሲሰጠው ዕድሜው ወደ 25 ዓመት ሳይጠጋ አይቀርም። (ኤር. 1:1, 2) ይሁንና በዕድሜ ለገፉትና ትልቅ ሥልጣን ላላቸው የሕዝቡ ሽማግሌዎች መልእክቱን ለመናገር ጨርሶ ብቃት የሌለው አንድ ፍሬ ልጅ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። (ኤር. 1:6) ኤርምያስ በተለይ ለካህናቱ፣ ለሐሰተኛ ነቢያቱና ለገዥዎቹ እንዲሁም ‘ብዙሃኑ በሚከተለው መንገድ’ ለሚመላለሱትና ‘በክህደት ሥራቸው ለጸኑት’ ሕዝብ ከባድ ውግዘት የተሞላበት ብሎም አስፈሪ የሆነ የፍርድ መልእክት ማወጅ ነበረበት። (ኤር. 6:13፤ 8:5, 6 NW) ወደ አራት መቶ ለሚጠጉ ዓመታት የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል የነበረው ንጉሥ ሰለሞን ያሠራው ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ሊጠፋ ነው። ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ባድማ ይሆናሉ፤ ነዋሪዎቹም በግዞት ይወሰዳሉ። ኤርምያስ እንዲያውጅ የተላከው መልእክት አጣዳፊ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም!

5, 6. (ሀ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የኤርምያስን ክፍል እየተጠቀመበት ያለው እንዴት ነው? (ለ) ጥናታችን የሚያተኩረው በምን ላይ ነው?

5 በዘመናችንም ይሖዋ በዚህ ዓለም ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ሰዎችን ለማስጠንቀቅ እንደ ጠባቂ ሆነው የሚያገለግሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በፍቅር ተነሳስቶ ሰጥቶናል። የኤርምያስ ክፍል የሆኑት እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ሰዎች ለምንኖርበት ጊዜ ትኩረት እንዲሰጡ ለዘመናት ሲያስጠነቅቁ ኖረዋል። (ኤር. 6:17) የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ይሖዋ እንደማይዘገይ መጽሐፍ ቅዱስ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የይሖዋ ቀን እሱ ካሰበው ጊዜ ምንም ዝንፍ ሳይል በድንገት ከተፍ ይላል።​—ሶፎ. 3:8፤ ማር. 13:33፤ 2 ጴጥ. 3:9, 10

6 ይሖዋ በንቃት እንደሚጠባበቅና ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ዓለም ልክ በቀጠረው ጊዜ እንደሚያመጣ እናስታውስ። የኤርምያስ ክፍል የሆኑት ክርስቲያኖችም ሆነ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አጋሮቻቸው ይህን ማወቃቸው መልእክታቸው ከምንጊዜውም ይበልጥ አጣዳፊ መሆኑን በመገንዘብ ንቁ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይገባል። ታዲያ ይህ አንተን የሚነካህ እንዴት ነው? ኢየሱስ ሁላችንም ከአምላክ መንግሥት ጎን መቆማችን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል። ኤርምያስ ተልእኮውን በንቃት እንዲያከናውን የረዱትንና እኛም እንዲህ እንድናደርግ የሚረዱንን ሦስት ባሕርያት እስቲ እንመርምር።

ለሰዎች ያለው ፍቅር

7. ኤርምያስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙትም መስበኩን እንዲቀጥል ፍቅር እንዴት እንደረዳው አብራራ።

7 ኤርምያስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙትም መስበኩን እንዲቀጥል ያነሳሳው ምን ነበር? ለሰዎች ያለው ፍቅር ነበር። ኤርምያስ በሕዝቡ ላይ ለሚደርሰው አብዛኛው ችግር መንስኤው ሐሰተኛ እረኞች መሆናቸውን ያውቅ ነበር። (ኤር. 23:1, 2) ይህን ማወቁ ሥራውን በፍቅርና በርኅራኄ እንዲያከናውን ረድቶታል። የአገሩ ሰዎች የአምላክን ቃል ሰምተው በሕይወት እንዲኖሩ ይፈልግ ነበር። የሕዝቡ ሁኔታ በጣም ስላስጨነቀው በእነሱ ላይ የሚመጣውን መከራ በማሰብ አልቅሷል። (ኤርምያስ 8:21⁠ን እና 9:1ን አንብብ።) የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ፣ ኤርምያስ የይሖዋን ስምና ሕዝቡን በጥልቅ እንደሚወድና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት በግልጽ ያሳያል። (ሰቆ. 4:6, 9) በዛሬው ጊዜ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ስትመለከት አጽናኝ የሆነውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች ለመንገር አትገፋፋም?​—ማቴ. 9:36

8. ኤርምያስ መከራ ቢደርስበትም እንዳልተማረረ የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 ኤርምያስ፣ ሊረዳቸው ይጥር የነበሩት ሰዎች ፍዳውን ቢያሳዩትም አጸፋውን አልመለሰም ወይም በሁኔታው አልተማረረም። ኤርምያስ፣ ምግባረ ብልሹ ለነበረው ለንጉሥ ሴዴቅያስ እንኳ ደግና ታጋሽ ነበር! ሴዴቅያስ፣ ኤርምያስን እንዲገደል አሳልፎ ከሰጠውም በኋላ ነቢዩ ይሖዋን  እንዲሰማ ንጉሡን ተማጽኖታል። (ኤር. 38:4, 5, 19, 20) እኛስ ለሰዎች እንደ ኤርምያስ ያለ ጠንካራ ፍቅር አለን?

አምላክ የሰጠው ድፍረት

9. ኤርምያስ ድፍረት ያገኘው ከይሖዋ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

9 ይሖዋ መጀመሪያ ባናገረው ወቅት ኤርምያስ ኃላፊነቱን ላለመቀበል ሰበብ አስባብ ደርድሮ ነበር። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው በኋላ ላይ ያሳየው ድፍረትና ቆራጥነት በተፈጥሮው ያገኘው ነገር አልነበረም። ኤርምያስ በነቢይነት ባገለገለበት ወቅት አስደናቂ ጥንካሬ ሊኖረው የቻለው በአምላክ ሙሉ በሙሉ ይታመን ስለነበር ነው። በእውነትም ይሖዋ “እንደ ኀያል ተዋጊ” ከነቢዩ ጋር ስለነበር ኤርምያስን ደግፎታል፤ እንዲሁም ተልእኮውን እንዲወጣ ብርታት ሰጥቶታል። (ኤር. 20:11) ኤርምያስ ያለ ፍርሃት በድፍረት በመናገር በጣም ይታወቅ ስለነበር ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን ያዩት አንዳንዶች ኤርምያስ ተመልሶ እንደመጣ አስበው ነበር!​—ማቴ. 16:13, 14

10. ቅቡዓን ቀሪዎች “በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ” ተሹመዋል የምንለው ለምንድን ነው?

10 “የሕዝቦች ሁሉ ንጉሥ” የሆነው ይሖዋ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ የፍርድ መልእክት እንዲናገር ኤርምያስን ልኮት ነበር። (ኤር. 10:6, 7) ቅቡዓን ቀሪዎች “በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ” የተሾሙት በምን መንገድ ነው? (ኤር. 1:10) በጥንት ጊዜ እንደነበረው ነቢይ በዛሬው ጊዜ የሚገኘው የኤርምያስ ክፍልም ከጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ተልእኮ ተቀብሏል። በመሆኑም የተቀቡት የአምላክ አገልጋዮች በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት አሕዛብና መንግሥታት አዋጅ እንዲናገሩ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። የኤርምያስ ክፍል፣ ከሉዓላዊው አምላክ ባገኘው ሥልጣንና በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ በሚገኘው ግልጽ የሆነ መልእክት በመጠቀም ዛሬ ያሉት አሕዛብና መንግሥታት አምላክ በወሰነው ጊዜና እሱ በመረጠው መንገድ ተነቅለው እንደሚጣሉ ብሎም እንደሚጠፉ እያወጀ ነው። (ኤር. 18:7-10፤ ራእይ 11:18) የኤርምያስ ክፍል በምድር ዙሪያ የይሖዋን የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ከመፈጸም ወደኋላ ላለማለት ቆርጧል።

11. አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ያለማሰለስ መስበካችንን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል?

11 ተቃውሞ ሲያጋጥመን፣ ሰዎች ግዴለሽ ሲሆኑ ወይም ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲደርሱብን አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (2 ቆሮ. 1:8) ይሁንና እንደ ኤርምያስ ወደፊት መግፋታችንን እንቀጥል። ተስፋ አንቁረጥ! ሁላችንም የአምላክን እርዳታ በምንፈልግበት ጊዜ ወደ እሱ ምልጃ ማቅረባችንን፣ በእሱ መታመናችንንና ‘ድፍረት ማግኘታችንን’ እንቀጥል። (1 ተሰ. 2:2) እውነተኛ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አምላክ የሰጠንን ኃላፊነቶች ለመፈጸም ምንጊዜም ንቁዎች መሆን ይኖርብናል። ከሃዲ የሆነችው ኢየሩሳሌም ጥላ የሆነችላት ሕዝበ ክርስትና እንደምትጠፋ ያለማሰለስ ለመስበክ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። የኤርምያስ ክፍል “የተወደደውን የእግዚአብሔርን ዓመት” ብቻ ሳይሆን “የአምላካችንንም የበቀል ቀን” ያውጃል።​—ኢሳ. 61:1, 2፤ 2 ቆሮ. 6:2

ከልብ የመነጨ ደስታ

12. ኤርምያስ ደስታውን ጠብቆ ይመላለስ እንደነበር ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ደስተኛ ለመሆን የረዳው ቁልፍ ምን ነበር?

12 ኤርምያስ በተሰጠው ሥራ ይደሰት ነበር። ለይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ቃልህ በተገኘ ጊዜ በላሁት፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነልኝ።” (ኤር. 15:16) ኤርምያስ እውነተኛውን አምላክ ወክሎ ቃሉን መስበክን እንደ ትልቅ መብት ይመለከተው ነበር። ነቢዩ ሕዝቡ በሚሰነዝርበት ፌዝ ላይ ትኩረት ሲያደርግ ደስታውን ያጣ እንደነበር ልብ ሊባል ይገባል። መልእክቱ ምን ያህል ማራኪና አስፈላጊ እንደሆነ ሲያስብ ግን ደስታውን መልሶ ያገኝ ነበር።​—ኤር. 20:8, 9

13. ደስታችንን ለመጠበቅ ጥልቀት ያላቸውን መንፈሳዊ እውነቶች መመገብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ዛሬም በስብከቱ ሥራ ላይ ደስተኛ ሆነን መቀጠል እንድንችል “ጠንካራ ምግብ” ይኸውም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ እውነቶች መመገብ ይኖርብናል። (ዕብ. 5:14) ጥልቀት ያለው ጥናት እምነታችንን ያጠናክራል። (ቆላ. 2:6, 7) የምናደርጋቸው ነገሮች የይሖዋን ልብ ምን ያህል እንደሚያስደስቱት ወይም እንደሚያሳዝኑት እንድንገነዘብ ያደርገናል። መጽሐፍ ቅዱስን  ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ ለማግኘት የምንቸገር ከሆነ ፕሮግራማችንን መለስ ብለን መመርመር አለብን። ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ቃሉን በየዕለቱ ማጥናታችንና ማሰላሰላችን ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ልክ እንደ ኤርምያስ “ሐሤትና የልብ ደስታ” እንድናገኝ ያስችለናል።

14, 15. (ሀ) ኤርምያስ እስከ መጨረሻው ድረስ ተልእኮውን በታማኝነት መወጣቱ ምን ፍሬ አስገኝቶለታል? (ለ) በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የትኛውን ሐቅ ይገነዘባሉ?

14 ኤርምያስ የይሖዋን የማስጠንቀቂያና የፍርድ መልእክት ያለማሰለስ አውጇል፤ ያም ሆኖ ‘እንዲያንጽና እንዲተክል’ የተሰጠውን ተልእኮም አልዘነጋም። (ኤር. 1:10) የማነጽና የመትከል ሥራው ፍሬ አፍርቷል። በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ስትጠፋ አንዳንድ አይሁዳውያንና እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች በሕይወት ተርፈዋል። ሬካባውያን፣ አቤሜሌክና ባሮክ ከጥፋቱ እንደተረፉ እናውቃለን። (ኤር. 35:19፤ 39:15-18፤ 43:5-7) ታማኝ የነበሩትና አምላክን የሚፈሩት እነዚህ የኤርምያስ ወዳጆች በዛሬው ጊዜ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውንና የኤርምያስ ክፍል አጋር የሆኑትን ክርስቲያኖች ያመለክታሉ። የኤርምያስ ክፍል አባላት ይህን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በመንፈሳዊ መገንባት ታላቅ ደስታ አምጥቶላቸዋል። (ራእይ 7:9) በተመሳሳይም የቅቡዓን አጋሮች የሆኑት እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ መርዳት ጥልቅ እርካታ ያስገኝላቸዋል።

 15 የአምላክ ሕዝቦች፣ ምሥራቹን መስበክ መልእክቱን ለሚሰሙ ሰዎች ሕዝባዊ አገልግሎት የማቅረብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ክፍል እንደሆነ ይገነዘባሉ። ሰዎች ሰሙንም አልሰሙን በስብከቱ ሥራችን አማካኝነት ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችን ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል።​—መዝ. 71:23፤ ሮም 1:9ን አንብብ።

ተልእኳችሁን ለመወጣት ‘በንቃት ተጠባበቁ’!

16, 17. ራእይ 17:10 እና ዕንባቆም 2:3 የምንኖርበት ጊዜ አጣዳፊ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

16 በራእይ 17:10 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ትንቢት፣ የምንኖርበት ጊዜ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ያጎላል። ሰባተኛው ንጉሥ ይኸውም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ወደ ሕልውና መጥቷል። ሰባተኛውን የዓለም ኃያል መንግሥት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል” ይላል። ዛሬ ይህ “አጭር ጊዜ” ሊጠናቀቅ እየተቃረበ መሆን አለበት። ነቢዩ ዕንባቆም የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በተመለከተ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃል፤ . . . የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በእርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም።”​—ዕን. 2:3

17 ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አኗኗሬ የጊዜያችንን አጣዳፊነት በእርግጥ እንደተገነዘብኩ ያሳያል? ሕይወቴን የምመራበት መንገድ መጨረሻው በቅርቡ ይመጣል ብዬ እንደምጠብቅ ይጠቁማል? ወይስ የማደርጋቸው ውሳኔዎችና ቅድሚያ የምሰጣቸው ነገሮች መጨረሻው በቅርቡ ይመጣል ብዬ እንደማልጠብቅ ይባስ ብሎም መጨረሻው መምጣቱን እንደምጠራጠር ያሳያሉ?’

18, 19. ጊዜው ቅንዓታችን የሚቀዘቅዝበት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

18 ጠባቂው ክፍል የሚያከናውነው ሥራ ገና አልተጠናቀቀም። (ኤርምያስ 1:17-19ን አንብብ።) ቅቡዓን ቀሪዎች እንደ “ብረት ምሰሶ” እና እንደ “ተመሸገ ከተማ” ፈጽሞ የማይነቃነቁ መሆናቸውን ማወቅ ምንኛ የሚያስደስት ነው! እነዚህ ክርስቲያኖች የተሰጣቸው ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአምላክ ቃል እንዲያጠናክራቸው በመፍቀድ ‘ወገባቸውን በእውነት ታጥቀዋል።’ (ኤፌ. 6:14) እጅግ ብዙ ሕዝብም የኤርምያስ ክፍል መለኮታዊ ተልእኮውን እንዲወጣ በቅንዓት በመደገፍ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት ያሳያሉ።

19 ጊዜው ከመንግሥቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ቅንዓታችን የሚቀዘቅዝበት ሳይሆን ኤርምያስ 12:5 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ያለውን ትርጉም የምናስተውልበት ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) ሁላችንም ጽናት የሚጠይቁ መከራዎች ያጋጥሙናል። እነዚህ የእምነት ፈተናዎች አብረናቸው ከምንሮጥ “እግረኞች” ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ይሁንና ‘ታላቁ መከራ’ እየቀረበ ሲመጣ የሚደርሱብን መከራዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱ መጠበቅ እንችላለን። (ማቴ. 24:21) ወደፊት ከሚገጥሙን ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ጋር የምናደርገው ትግል “ከፈረሰኞች ጋር” እንደ መወዳደር ሊቆጠር ይችላል። አንድ ሰው በግልቢያ ላይ ካሉ ፈረሶች እኩል በጽናት ለመሮጥ ከፍተኛ ኃይል ይጠይቅበታል። እንግዲያው በአሁኑ ጊዜ የሚደርሱብንን መከራዎች በጽናት መቋቋማችን አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን የወደፊቱን ጊዜ በጽናት ለመወጣት ሊያዘጋጀን ይችላል።

20. ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

20 ሁላችንም የኤርምያስን ምሳሌ በመከተል የስብከቱን ተልእኳችንን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም እንችላለን! እንደ ፍቅር፣ ድፍረትና ደስታ ያሉት ባሕርያት ኤርምያስ ለ67 ዓመታት አገልግሎቱን በታማኝነት እንዲያከናውን ረድተውታል። ውብ የሆኑት የአልሞንድ አበባዎች ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸም ‘በንቃት እንደሚጠባበቅ’ ያስታውሱናል። እንግዲያው እኛም ንቁዎች ለመሆን የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን። ኤርምያስ ‘በንቃት ተጠባብቋል’፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።

ታስታውሳለህ?

• ኤርምያስ፣ ተልእኮውን “በንቃት” እንዲያከናውን ፍቅር የረዳው እንዴት ነው?

• ደፋሮች እንድንሆን የአምላክ እርዳታ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

• ኤርምያስ ደስታውን ጠብቆ እንዲመላለስ የረዳው ምንድን ነው?

• ‘በንቃት መጠባበቅ’ የምትፈልገው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 31 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ተቃውሞ ቢያጋጥማችሁም መስበካችሁን ትቀጥላላችሁ?