በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታችን ነው!

ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታችን ነው!

 ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታችን ነው!

“ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ።”—መዝ. 73:28 NW

1. ጳውሎስ በ⁠1 ቆሮንቶስ 7:31 ላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር በተዘዋዋሪ መንገድ ስለ ምን ነገር እየጠቀሰ ሊሆን ይችላል?

ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 7:31) ጳውሎስ ይህን ሲናገር፣ ዓለምን ትእይንቱ እስኪለወጥ ድረስ ጥሩ ወይም መጥፎ ገጸ ባሕርያትን ተላብሰው ድራማ የሚጫወቱ ተዋንያን ከሚተውኑበት መድረክ ጋር ማመሳሰሉ ሳይሆን አይቀርም።

2, 3. (ሀ) በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳውን ግድድር ከምን ጋር ልናመሳስለው እንችላለን? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜ በጣም ወሳኝ የሆነ አንድ ድራማ እየተከናወነ ሲሆን ይህ ድራማ አንተንም ይጨምራል! ድራማው በተለይ ከይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ድራማ በአንድ አገር ሊከሰት ከሚችል ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በአንድ በኩል ሕጋዊነት ባለው መንገድ የተቋቋመ የአገሪቱን ሥርዓት የሚያስከብር መንግሥት አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ማጭበርበርን፣ ዓመፅንና ነፍስ ግድያን መርሕ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ወንጀለኛ ድርጅት አለ። ሕገ ወጥ የሆነው ይህ ድርጅት የመንግሥትን ሉዓላዊነት የሚገዳደር ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱ ዜጋ ለመንግሥቱ ያለው ታማኝነት ፈተና ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል።

3 በጽንፈ ዓለም ደረጃም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል። በአንድ በኩል ሕጋዊነት ያለው ‘የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ’ አገዛዝ አለ። (መዝ. 71:5 NW) በሌላ በኩል ግን የሰው ዘር “ክፉው” በሚመራው ወንጀለኛ ድርጅት ምክንያት ስጋት ተጋርጦበታል። (1 ዮሐ. 5:19) ይህ ድርጅት ሕጋዊነት ያለውን የአምላክን አገዛዝ እየተገዳደረ ከመሆኑም በላይ በዚህ ሉዓላዊ አገዛዝ ሥር የሚገኘውን የእያንዳንዱን ሰው ታማኝነት እየተፈታተነ ነው። ታዲያ ይህ ሁኔታ ሊከሰት የቻለው እንዴት ነው? አምላክ እንዲህ ያለውን ሁኔታ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይህን ሁኔታ በተመለከተ በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን?

የድራማው ገጽታዎች

4. በጽንፈ ዓለም መድረክ ላይ እየተካሄደ ያለው ድራማ እርስ በርስ ተያያዥነት ባላቸው በየትኞቹ ሁለት ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠነ ነው?

4 በጽንፈ ዓለም መድረክ ላይ እየተካሄደ ያለው ይህ ድራማ እርስ በርስ ተያያዥነት ባላቸው ሁለት ጉዳዮች ይኸውም በይሖዋ ሉዓላዊነትና በሰው ልጆች ንጹሕ አቋም ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይሖዋ ሉዓላዊው ጌታ’ ተብሎ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠርቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይታመን የነበረ አንድ መዝሙራዊ “ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 73:28 NW) “ሉዓላዊነት” ሲባል በኃይል ወይም በአገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆን ማለት ነው። ሉዓላዊ የሆነው አካል ፍጹም ተወዳዳሪ የሌለው ሥልጣን አለው። በእርግጥም  ይሖዋን ከሁሉ የላቀ አምላክ አድርገን እንድንመለከተው የሚያደርጉን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን።—ዳን. 7:22

5. የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ ያለብን ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የምድርና የመላው ጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ነው። (ራእይ 4:11ን አንብብ።) በተጨማሪም ይሖዋ በጽንፈ ዓለሙ አገዛዝ ውስጥ ሕግን የመተርጎም፣ የማርቀቅና የማስፈጸም ሥልጣንን አጣምሮ የያዘ ዳኛችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን ነው። (ኢሳ. 33:22) ወደ ሕልውና የመጣነውም ሆነ በሕይወት መቆየታችን የተመካው በአምላክ ስለሆነ እሱን ሉዓላዊ ጌታችን አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ይሖዋ ‘ዙፋኑን በሰማይ እንዳጸናና መንግሥቱም ሁሉን እንደሚገዛ’ ዘወትር የምናስታውስ ከሆነ ያለውን የላቀ ቦታ ለመደገፍ እንነሳሳለን።—መዝ. 103:19፤ ሥራ 4:24

6. ንጹሕ አቋም ሲባል ምን ማለት ነው?

6 የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ ይኖርብናል። “ንጹሕ አቋም” የሚለው አገላለጽ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅን ወይም በሙሉ ልብ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ያመለክታል። ንጹሕ አቋሙን የሚጠብቅ ሰው ነቀፋ የሌለበት ከመሆኑም ሌላ ቅን ነው። በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ እንዲህ ዓይነት ሰው ነበር።—ኢዮብ 1:1

ድራማው የጀመረው እንዴት ነው?

7, 8. ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት የተገዳደረው እንዴት ነው?

7 ከ6,000 ዓመታት በፊት አንድ መንፈሳዊ ፍጡር የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት ተገዳደረ። ይህ ዓመፀኛ እንዲህ ያለውን ነገር እንዲናገርና እንዲያደርግ ያነሳሳው ለመመለክ ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ነው። የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋንን የአምላክን ሉዓላዊነት በታማኝነት እንዳይደግፉ ያደረጋቸው ከመሆኑም ባሻገር ይሖዋ እንደ ዋሸ አድርጎ በመናገር ስሙን አጉድፏል። (ዘፍጥረት 3:1-5ን አንብብ።) ዓመፀኛ የሆነው ይህ ፍጡር ቀንደኛ ጠላት፣ ሰይጣን (ተቃዋሚ)፣ ዲያብሎስ (ስም አጥፊ)፣ እባብ (አሳሳች) እና ዘንዶ (አጥፊ) ሆነ።—ራእይ 12:9

8 ሰይጣን ራሱን ተቀናቃኝ ገዥ አድርጎ አቀረበ። ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ያለ ግድድር ሲያጋጥመው ምን ያደርግ ይሆን? ሦስቱን ተቃዋሚዎች ማለትም ሰይጣንን፣ አዳምንና ሔዋንን ወዲያውኑ ያጠፋቸው ይሆን? እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም፤ እንዲህ ያለው እርምጃ ተወስዶ ቢሆን ኖሮ የላቀ ኃይል ያለው ማን እንደሆነ ማረጋገጫ ይሆን ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ ይህን እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ሕጉን መተላለፍ የሚያስከትለውን ቅጣት በተመለከተ እውነቱን እንደተናገረ የሚያሳይ ማስረጃ ይሆን ነበር። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ያለውን እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው?

9. ሰይጣን ምን ጥያቄዎች አስነስቷል?

9 ሰይጣን ውሸት ተናግሮ አዳምና ሔዋን ለአምላክ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ባደረገበት ወቅት ይሖዋ ከሰው ልጆች ታዛዥነት የመጠበቅ መብት የለውም የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ አስነስቷል። ከዚህም በላይ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አምላክን እንዳይታዘዙ በማድረግ፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ ታማኝነታቸውን የሚጠብቁ ስለመሆናቸው ጥያቄ አስነስቷል። የይሖዋን ሉዓላዊነት በታማኝነት ከደገፈው ከኢዮብ ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው ሰይጣን ሰዎችን ሁሉ ለአምላክ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚችል የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል።—ኢዮብ 2:1-5

10. ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ማራዘሙ ምን አጋጣሚ እንዲከፈት አድርጓል?

10 ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በማራዘም ሰይጣን ላቀረበው ክስ ማስረጃ እንዲያቀርብ ጊዜ ሰጥቶታል። በተጨማሪም አምላክ የሰው ልጆች ለሉዓላዊነቱ ያላቸውን ታማኝነት እንዲያሳዩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ታዲያ ባለፉት ዘመናት ምን ነገሮች ተከናውነዋል? ሰይጣን ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ወንጀለኛ ድርጅት አቋቁሟል። ይሖዋ ወደፊት ይህን ድርጅትም ሆነ ዲያብሎስን በማጥፋት የመግዛት መብት እንዳለው በማያዳግም ሁኔታ መልስ ይሰጣል። ይሖዋ የመጨረሻው ውጤት ጥሩ እንደሚሆን በጣም እርግጠኛ ስለነበር ይህን በተመለከተ ትንቢት የተናገረው በኤደን ገነት ዓመፅ በተነሳበት ጊዜ ነበር።—ዘፍ. 3:15

11. ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ምን አድርገዋል?

11 በርካታ ሰዎች እምነት እንዳላቸው በተግባር ያሳዩ ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ ሉዓላዊነትና ከስሙ መቀደስ ጋር በተያያዘ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ሩት፣ ዳዊት፣ ኢየሱስና የጥንቶቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይገኙበታል፤ በዛሬው ጊዜም ንጹሕ  አቋማቸውን የሚጠብቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። የአምላክን ሉዓላዊነት የሚደግፉት እነዚህ ሰዎች፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን በማጋለጥ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ፤ እንዲሁም ዲያብሎስ ሰዎች ሁሉ ለአምላክ ጀርባቸውን እንዲሰጡ እንደሚያደርግ በጉራ በመናገር በይሖዋ ስም ላይ የከመረውን ነቀፋ በማንጻት ረገድ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—ምሳሌ 27:11

የድራማው መጨረሻ የታወቀ ነው

12. ይሖዋ ክፋትን ለዘላለም እንደማይታገሥ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

12 ይሖዋ በቅርቡ ሉዓላዊነቱን እንደሚያረጋግጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ክፋትን ለዘላለም አይታገሥም፤ በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ እንደሆነ እናውቃለን። ይሖዋ በኖኅ ዘመን በክፉዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። ሰዶምና ገሞራን እንዲሁም ፈርዖንንና ሠራዊቱን አጥፍቷል። ሲሣራና ሠራዊቱ እንዲሁም የአሦር ንጉሥ ሰናክሬምና ሠራዊቱ ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ ሊቋቋሙት አልቻሉም። (ዘፍ. 7:1, 23፤ 19:24, 25፤ ዘፀ. 14:30, 31፤ መሳ. 4:15, 16፤ 2 ነገ. 19:35, 36) በመሆኑም ይሖዋ አምላክ ስሙን የሚንቁትንና ምሥክሮቹን የሚጨቁኑትን ለዘላለም እንደማይታገሥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የኢየሱስን መገኘትና የዚህን ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቶች እያየን ነው።—ማቴ. 24:3

13. ከይሖዋ ጠላቶች ጋር እንዳንጠፋ ምን ማድረግ እንችላለን?

13 ከአምላክ ጠላቶች ጋር እንዳንጠፋ የይሖዋን ሉዓላዊነት በታማኝነት እንደምንደግፍ ማስመሥከር ይኖርብናል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ወንጀለኛ ከሆነው ከሰይጣን አገዛዝ ምንጊዜም ተለይተን በመኖርና የእሱ ግብረ አበሮች በሚሰነዝሩት ዛቻ ባለመሸበር ነው። (ኢሳ. 52:11፤ ዮሐ. 17:16፤ ሥራ 5:29) በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ሉዓላዊነት መደገፍ የምንችለውም ሆነ ይሖዋ ስሙን ከነቀፋ አንጽቶ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን ሲያረጋግጥ መዳን የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።

14. በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ የትኞቹ ነገሮች ተገልጸዋል?

14 ስለ ሰው ዘርም ሆነ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት የሚናገሩ ሐሳቦችን በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት እንችላለን። የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት ምዕራፎች ስለ ፍጥረትና የሰው ልጅ ኃጢአት ውስጥ ስለመውደቁ የሚናገሩ ሲሆን የመጨረሻዎቹ ሦስት ምዕራፎች ደግሞ ሰዎች ኃጢአት ካመጣባቸው ጣጣ እንደሚገላገሉ ይናገራሉ። በእነዚህ መካከል የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ደግሞ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለሰው ልጆች፣ ለምድርና ለጽንፈ ዓለም ያለውን ዓላማ ከፍጻሜ ለማድረስ ምን እርምጃዎችን እንደሚወስድ ዝርዝር መረጃ ይዘዋል። የዘፍጥረት መጽሐፍ ሰይጣንም ሆነ ክፋት እንዴት ወደ ዓለም መድረክ ብቅ እንዳሉ ይናገራል፤ የራእይ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፎች ደግሞ ክፋት እንዴት እንደሚወገድ፣ ዲያብሎስ እንዴት እንደሚጠፋና የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድር ላይም እንዴት እንደሚሆን ይገልጻሉ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአትና የሞት መንስኤ ምን እንደሆነ ይናገራል፤ አልፎ ተርፎም እነዚህ ነገሮች ከምድር ገጽ ተወግደው ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ማለቂያ የሌለው ደስታና የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

15. ሉዓላዊነትን በተመለከተ ሲካሄድ የቆየው ድራማ ሲጠናቀቅ በግለሰብ ደረጃ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?

 15 በቅርቡ የዚህ ዓለም ትእይንት ሙሉ በሙሉ ይለወጣል። ሉዓላዊነትን በተመለከተ ለዘመናት ሲካሄድ የቆየው ድራማ መጋረጃ ይዘጋል። ሰይጣን ከመድረኩ እንዲወገድ ከተደረገ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደመሰስ ሲሆን በዚያን ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል። ከዚህ ለመጠቀምና በአምላክ ቃል ውስጥ በትንቢት የተነገሩ ሌሎች በረከቶችን ለማግኘት በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ ይኖርብናል። መሃል ሰፋሪ መሆን አንችልም። “ይሖዋ ከጎኔ ነው” ማለት እንድንችል ምንጊዜም ከእሱ ጎን መቆም ይኖርብናል።—መዝ. 118:6, 7 NW

ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን!

16. የሰው ልጆች ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ ከተናገረው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍም ሆነ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን። ሐዋርያው እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም። ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” (1 ቆሮ. 10:13) ጳውሎስ እየገለጸ ያለው ስለ ምን ዓይነት ፈተና ነው? አምላክስ መውጫ መንገዱን የሚያዘጋጅልን እንዴት ነው?

17-19. (ሀ) እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ በየትኛው ፈተና ተሸንፈዋል? (ለ) ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ ከአቅማችን በላይ አይሆንብንም የምንለው ለምንድን ነው?

17 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ካሳለፉት ተሞክሮ መረዳት እንደምንችለው “ፈተናው” የሚመጣው የአምላክን ሕግ ለመጣስ እንድንነሳሳ ከሚያደርጉን ሁኔታዎች ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:6-10ን አንብብ።) እስራኤላውያን ፈተናን መቋቋም ይችሉ ነበር፤ ይሁንና ይሖዋ ድርጭቶችን በተአምር በመስጠት ለወር የሚሆናቸውን ምግብ ባቀረበላቸው ጊዜ “ጎጂ የሆኑ ነገሮችን” ተመኝተው ነበር። ሕዝቡ ለተወሰነ ጊዜ ሥጋ ባይበሉም እንኳ አምላክ የሚመገቡት በቂ መና ይሰጣቸው ነበር። ያም ሆኖ ሕዝቡ ድርጭቶቹን በሚሰበስቡበት ጊዜ ያለ ልክ በመስገብገብ ለፈተና ተሸንፈዋል።—ዘኍ. 11:19, 20, 31-35

18 ከዚያ ቀደም ብሎ ሙሴ ሕጉን ለመቀበል ወደ ሲና ተራራ በወጣ ጊዜ እስራኤላውያን በዝሙት፣ በጣዖት አምልኮና ሥጋዊ ተድላን በማሳደድ ተጠመዱ። በዓይን የሚታየው መሪያቸው ከአጠገባቸው ዞር ሲል ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ራሳቸውን ለፈተና አጋለጡ። (ዘፀ. 32:1, 6) ተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ በደረሱበት ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በሞዓባውያን ሴቶች ተታለው ከእነሱ ጋር የፆታ ብልግና ፈጸሙ። በመሆኑም በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት በሞት ተቀሰፉ። (ዘኍ. 25:1, 9) ከዚህም በላይ እስራኤላውያን አጉረምራሚዎች በመሆን ፈተና ላይ የወደቁባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ለምሳሌ በአንድ ወቅት በሙሴ ላይ አልፎ ተርፎም በአምላክ ላይ አማርረው ነበር! (ዘኍ. 21:5) ሌላው ቀርቶ ዓመፀኛ የነበሩት ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን እንዲሁም ግብረ አበሮቻቸው እንዲጠፉ ከተደረገ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በእነዚህ ዓመፀኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ በማሰብ አጉረምርመው ነበር። በዚህም ምክንያት አምላክ መቅሰፍት ስለሰደደባቸው 14,700 የሚሆኑ እስራኤላውያን አልቀዋል።—ዘኍ. 16:41, 49

19 ከተጠቀሱት ፈተናዎች መካከል አንዱም ቢሆን እስራኤላውያን ሊቋቋሙት የማይችሉት ዓይነት አልነበረም። እስራኤላውያን ፈተና ላይ የወደቁት እምነት በማጣታቸው፣ ይሖዋንና እሱ ያደረገላቸውን እንክብካቤ በመርሳታቸውና መንገዱ ትክክል መሆኑን በመጠራጠራቸው ምክንያት ነበር። ከእስራኤላውያን ታሪክ መመልከት እንደምንችለው የሚያጋጥሙን ፈተናዎች በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለዩ አይደሉም። እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም አስፈላጊውን ጥረት ካደረግንና አምላክ እንደሚደግፈን ከተማመንን ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን። ‘አምላክ ታማኝ ስለሆነ እንዲሁም ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን’ ስለማይፈቅድ ንጹሕ  አቋማችንን መጠበቅ ከባድ እንደማይሆንብን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ፈቃዱን መፈጸም ከአቅማችን በላይ እንድንፈተን በመፍቀድ ፈጽሞ አይጥለንም።—መዝ. 94:14

20, 21. ፈተና ሲደርስብን አምላክ “መውጫ መንገዱን” የሚያዘጋጅልን እንዴት ነው?

20 ይሖዋ ፈተናውን እንድንቋቋም የሚያስችለንን ብርታት በመስጠት “መውጫ መንገዱን” ያዘጋጅልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ስደት የሚያደርሱብን ሰዎች እምነታችንን እንድንክድ ለማድረግ ሲሉ አካላዊ ጥቃት ይሰነዝሩብን ይሆናል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲያጋጥመን ተጨማሪ ድብደባና ሥቃይ ምናልባትም ከሞት ለማምለጥ ስንል አቋማችንን ለማላላት ልንፈተን እንችላለን። ይሁን እንጂ በ⁠1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ ከሚገኘውና ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ መሪነት ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው እንድንፈተን የሚያደርገን ሁኔታ የሚቆየው ለጊዜው ነው። ይሖዋ ለእሱ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ከአቅም በላይ እስኪሆንብን ድረስ እንድንፈተን አይፈቅድም። አምላክ እምነታችንን ሊያጠነክርልን እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ የሚረዳንን መንፈሳዊ ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል።

21 ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይደግፈናል። ይህ መንፈስ ፈተናውን ለመቋቋም የሚረዱንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ማስታወስ እንድንችልም ይረዳናል። (ዮሐ. 14:26) በዚህም ምክንያት ተታለን የተሳሳተ አካሄድ አንከተልም። ለምሳሌ ያህል፣ እርስ በርስ ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ይኸውም የይሖዋ ሉዓላዊነትና የሰው ልጆች ንጹሕ አቋም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ እንገነዘባለን። ብዙዎች ይህን መገንዘባቸው እንዲሁም የአምላክን እገዛ ማግኘታቸው እስከ ሞት ድረስ ታማኝ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ሆኖም መውጫ መንገድ የሆነላቸው ሞት አይደለም፤ በፈተናው ሳይሸነፉ እስከ መጨረሻው ድረስ በጽናት መቋቋም የቻሉት ይሖዋ ስለረዳቸው ነው። ይሖዋ እኛንም ይረዳናል። እንዲያውም እኛን ለመርዳት “መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩትን የሕዝብ አገልጋዮች” የሆኑ ታማኝ መላእክቱን ይጠቀማል። (ዕብ. 1:14) የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንደሚያሳየው የአምላክን ሉዓላዊነት ለዘላለም የመደገፍ አስደሳች መብት የሚኖራቸው ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋን ሉዓላዊ ጌታችን አድርገን በመቀበል እሱን የሙጥኝ ብለን ከኖርን ከእነዚህ ሰዎች መካከል የመቆጠር መብት እናገኛለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋን ሉዓላዊ ገዥያችን አድርገን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?

• ንጹሕ አቋምን መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

• ይሖዋ በቅርቡ ሉዓላዊነቱን እንደሚያረጋግጥ እንዴት እናውቃለን?

አንደኛ ቆሮንቶስ 10:13 ንጹሕ አቋምን መጠበቅ እንደሚቻል የሚጠቁመው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰይጣን ለይሖዋ ታማኝ እንዳይሆኑ አዳምና ሔዋንን ገፋፍቷቸዋል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን