በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁ ከይሖዋ ድርጅት ጋር እንዲተዋወቁ እርዷቸው

ልጆቻችሁ ከይሖዋ ድርጅት ጋር እንዲተዋወቁ እርዷቸው

 ልጆቻችሁ ከይሖዋ ድርጅት ጋር እንዲተዋወቁ እርዷቸው

ልጆች የማወቅ ጉጉት አላቸው። እስራኤላውያን በግብፅ የመጀመሪያውን የፋሲካ በዓል ባከበሩበት ሌሊት ልጆቻቸው እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀው ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፦ ‘በጉ የታረደው ለምንድን ነው?’ ‘አባዬ ደሙን የበሩ ጉበን ላይ የሚቀባው ለምንድን ነው?’ ‘የት ልንሄድ ነው?’ ይሖዋም እንዲህ ዓይነቶቹን ጥያቄዎች በደስታ እንደሚቀበል ለእስራኤላውያን አባቶች ከሰጠው ትእዛዝ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይሖዋ ወደፊት ስለሚያከብሩት የፋሲካ በዓል ለሕዝቡ ሲናገር እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣ ‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” (ዘፀ. 12:24-27) እስራኤላውያን ልጆች “አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የመመሪያዎቹ፣ የሥርዐቶቹና የሕጎቹ ትርጕም ምንድነው?” ብለው ወላጆቻቸውን በሚጠይቋቸው ጊዜ ለጥያቄያቸው መልስ የመስጠትን አስፈላጊነት ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለወላጆች ገልጾላቸዋል።—ዘዳ. 6:20-25

 ከዚህ በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ ልጆች ስለ እውነተኛው አምልኮ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይኸውም ይሖዋን እንደ አምላካቸውና አዳኛቸው አድርገው እንዲወዱት የሚያነሳሳቸው መልስ እንዲያገኙ ይፈልጋል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ለልጆች የሚመኝላቸው ይህንኑ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ለአምላክና ለሕዝቡ ከልብ የመነጨ ፍቅር እንዲያዳብሩ መርዳት የሚችሉበት አንዱ መንገድ ከይሖዋ ድርጅት ጋር በማስተዋወቅና ከዝግጅቶቹ እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በማስረዳት ነው። እንግዲያው ልጆች ስለ አምላክ ድርጅት ይበልጥ እንዲያውቁ መርዳት የሚቻልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ጉባኤያችሁ

ልጆች ጉባኤያቸውን በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ወላጆች ልጆቻችሁን ወደ ሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛችኋቸው መሄድ ያስፈልጋችኋል። ይህን በማድረግ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን መመሪያ ትከተላላችሁ፦ “ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችን . . . ሰብስብ። . . . ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።”—ዘዳ. 31:12, 13

ልጆች ከጨቅላነታቸው ጀምረው ስለ ይሖዋ ቃል መማር ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በተመለከተ ሲናገር ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን ከጨቅላነቱ ጀምሮ እንዳወቀ’ ገልጾ ነበር። (2 ጢሞ. 3:15) ሕፃናትም እንኳ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ የሚቀርበውን ትምህርት መረዳትና ከመንግሥቱ መዝሙሮች ጋር መተዋወቅ ይጀምራሉ። በተጨማሪም በጉባኤ፣ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን መጠቀምና በጥንቃቄ መያዝን ይማራሉ። ከዚህም በላይ በስብሰባዎቻችን ላይ የክርስቶስን  እውነተኛ ተከታዮች ለይቶ የሚያሳውቀው እውነተኛ ፍቅር መኖሩን ያስተውላሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:34, 35) ልጆች በመንግሥት አዳራሹ በግልጽ የሚታየው ሞቅ ያለ ፍቅርና የተረጋጋ መንፈስ ሊማርካቸውና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን የሕይወታቸው ቋሚ ክፍል እንዲያደርጉት ሊረዳቸው ይችላል።

ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ቀደም ብላችሁ የመድረስና ስብሰባው ካለቀ በኋላ የተወሰነ ጊዜ የመቆየት ልማድ ካላችሁ ልጆቻችሁ ጓደኛ ለማፍራት አጋጣሚ ያገኛሉ። ከልጆች ጋር ብቻ እንዲሆኑ ከመተው ይልቅ በሁሉም የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ጋር ለምን አታስተዋውቋቸውም? ልጆቻችሁ ከትልልቆች ጋር መተዋወቃቸው እነዚህ ወንድሞች አስደሳች ተሞክሮና ጥበብ እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። ለይሁዳ ንጉሥ ለዖዝያን ‘እግዚአብሔርን መፍራት ያስተማረው’ በጥንት ዘመን የኖረው ዘካርያስ፣ በወጣቱ ንጉሥ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሁሉ በዛሬው ጊዜም ይሖዋን ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ ወንድሞች በወጣቶች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። (2 ዜና 26:1, 4, 5) በመንግሥት አዳራሹ ስትሆኑ ስለ ቤተ መጻሕፍቱ፣ ስለ ማስታወቂያ ሰሌዳውና ስለ ሌሎች ነገሮችም ለልጆቻችሁ ልታብራሩላቸው ትችላላችሁ።

ዓለም አቀፉ ድርጅት

ልጆች፣ ጉባኤያቸው ከ100,000 በላይ ጉባኤዎችን ያቀፈው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ክፍል እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። የዚህን ድርጅት ገጽታዎችና አሠራሩን እንዲሁም ልጆች ሥራውን በመደገፍ ረገድ ምን ድርሻ እንዳላቸው ግለጹላቸው። የወረዳ ስብሰባዎችን፣ የአውራጃ ስብሰባዎችንና የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጉብኝት በጉጉት የምትጠብቁበትን ምክንያት ግለጹላቸው።— “በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ልትወያዩባቸው የምትችሉ ርዕሰ ጉዳዮች” የሚለውን በገጽ 28 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከቱ።

አጋጣሚ ስታገኙ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ ሚስዮናውያንን፣ የቤቴል ቤተሰብ አባላትን እንዲሁም ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በቤታችሁ ምግብ ጋብዟቸው። እነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከልጆቻችሁ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ እንደሌላቸው አድርጋችሁ አታስቡ። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሁልጊዜም ልጆችን በደስታ ይቀበልና ከእነሱ ጋር ያወራ የነበረውን የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ይጥራሉ። (ማር. 10:13-16) ልጆቻችሁ እንደነዚህ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ተሞክሯቸውን ሲያወሩ ማዳመጣቸውና በቅዱስ አገልግሎት የሚያገኙትን ደስታ መመልከታቸው እነሱም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግባቸው እንዲያደርጉት ሊያነሳሳቸው ይችላል።

ልጆቻችሁ ከይሖዋ ድርጅት ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ ለመርዳት በቤተሰብ ደረጃ ሌላ ልታደርጉ የምትችሉት ነገር አለ? አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በቤተሰብ ለማጥናት ፕሮግራም አውጡ። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት የይሖዋ አገልጋዮች ያሳዩትን ለአምላክ የማደር ባሕርይ፣ ትሕትና እንዲሁም ታማኝነት ጎላ አድርጋችሁ ግለጹ። ይሖዋ እነዚህን አገልጋዮቹን የመንግሥቱን ምሥራች በምድር ዙሪያ ለማስፋፋት እንዴት እንደተጠቀመባቸው ለልጆቻችሁ ንገሯቸው። የይሖዋ ድርጅት ከጥንትም ሆነ ከዘመናችን የሚገኙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማስተላለፍ ባዘጋጃቸው ቪዲዮዎች ተጠቀሙ። ከቻላችሁ በአገራችሁ ያለውን (ምናልባትም ወደ ሌሎች አገሮች ሄዳችሁ) ቅርንጫፍ ቢሮና የቤቴል ቤት ጎብኙ። ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ጉብኝት ማድረጋቸው ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በታማኝና ልባም ባሪያ አመራር ሥር ሆኖ በመላው ዓለም ላሉት ወንድሞች መንፈሳዊ ምግብና አመራር ለመስጠት እንዴት እንደተደራጀ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።—ማቴ. 24:45-47፤ ሥራ 15:22-31

ከልጆቻችሁ አቅም ጋር በሚስማማ መንገድ ማስተማር

ልጆቻችሁን ስታስተምሩ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ያስተማረበትን መንገድ አስታውሱ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 16:12) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከአቅማቸው በላይ ብዙ  መረጃ አላዥጎደጎደባቸውም። ከዚህ ይልቅ ወሳኝ እውነቶች ወደ ልባቸው ጠልቀው መግባት እንዲችሉ ቀስ በቀስ አስተምሯቸዋል። በተመሳሳይ እናንተም ልጆቻችሁን በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር አታስተምሯቸው። ስለ ድርጅቱ ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በጥቂት በጥቂቱ ሆኖም አዘውትራችሁ ካስተማራችኋቸው ሳይሰለቻቸው በጉጉት እንዲያዳምጡና ስለ ክርስቲያናዊው ጉባኤ መማር አስደሳች እንዲሆንላቸው ልታደርጉ ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ ቀደም ሲል የተማሩትን ነገር በድጋሚ በማንሳት ሰፋ አድርጋችሁ ልታብራሩላቸው ትችላላችሁ።

የክርስቲያን ጉባኤ መንፈሳዊ ጥንካሬ የምናገኝበት አምባ ሲሆን ጉባኤው በሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች በቅንዓት የሚሳተፉ ወጣቶችም የሰይጣን ዓለም የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የተሻለ ብቃት ይኖራቸዋል። (ሮም 12:2) ልጆቻችሁ ከይሖዋ ድርጅት ጋር እንዲተዋወቁ መርዳት ከፍተኛ ደስታ እንደሚያስገኝላችሁ እንተማመናለን! በምታደርጉት ጥረት ላይ የይሖዋ በረከት ታክሎበት ልጆቻችሁ ከድርጅቱና ከምናገለግለው አፍቃሪ አምላክ ጋር ተቀራርበውና ታማኝነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ እንመኛለን!

[ገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ልትወያዩባቸው የምትችሉ ርዕሰ ጉዳዮች

የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ምሽት ልትወያዩባቸው የምትችሉ ከይሖዋ ድርጅት ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦

የጉባኤያችሁን ታሪክ አንስታችሁ ተወያዩ። የተቋቋመው መቼና እንዴት ነበር? ጉባኤው ይሰበሰብባቸው የነበሩ ቦታዎች የትኞቹ ናቸው? እንዲህ ዓይነት ውይይት ስታደርጉ የልጆቻችሁን ጥያቄዎች ለመመለስ በጉባኤው ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ወንድሞችን ቤታችሁ ለምን አትጋብዙም?

የጉባኤና የትልልቅ ስብሰባዎችን ዓላማ እንዲሁም ልጆቹ ከእነዚህ ስብሰባዎች ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ግለጹላቸው።

በይሖዋ ድርጅት የተቋቋሙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን ዓላማ አብራሩላቸው። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች የተመረቁ ክርስቲያኖች ያፈሯቸውን መልካም ፍሬዎች የሚያሳዩ ተሞክሮዎች ንገሯቸው።

ልጆቻችሁ አዘውታሪ የምሥራቹ አስፋፊዎች መሆናቸው ያለውን ጥቅም እንዲገነዘቡ እርዷቸው። በይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ ለሚወጣው ዓለም አቀፋዊ ሪፖርት ምን ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ግለጹላቸው።

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ወጣቶች ሊካፈሉባቸው ስለሚችሉ የተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ተወያዩ። የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ በተሰኘው መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ላይ ጥሩ ማብራሪያ ቀርቧል።

ልጆቻችሁ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን የተወሰኑ አሠራሮች መከተል አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እንዲያስተውሉ እርዷቸው። ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮችም እንኳ ሳይቀር የይሖዋን ድርጅት አመራር ትተው የራሳቸውን አካሄድ መከተል የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ግለጹላቸው። የሽማግሌዎችን አመራር በመከተል በጉባኤ ውስጥ ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ንገሯቸው።

[ሥዕል]

ልጆቻችሁ ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ካገለገሉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረታቸው ይጠቅማቸዋል

[ገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንቷ እስራኤል እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችም ልጆቻቸው ስለ ይሖዋ ድርጅት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ