በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን በረከት ከልብ ፈልጉ

የይሖዋን በረከት ከልብ ፈልጉ

 የይሖዋን በረከት ከልብ ፈልጉ

“[አምላክ] ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ [ነው]።”—ዕብ. 11:6

1, 2. (ሀ) ብዙ ሰዎች የአምላክን በረከት ለማግኘት የሚሞክሩት እንዴት ነው? (ለ) እኛስ የይሖዋን በረከት ማግኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

“ተባረክ!” ትልልቅ ሰዎች መልካም ነገር ሲደረግላቸው እንዲህ ያለውን ምርቃት መጠቀማቸው የተለመደ ነው። በርካታ የሃይማኖት መሪዎች ሰዎችን፣ እንስሳትንና ግዑዝ የሆኑ ነገሮችን ሲባርኩ ይታያሉ። ብዙ ሰዎች በረከት እንደሚያገኙ በማሰብ ቅዱስ ወደሚባሉ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ይጓዛሉ። የፖለቲካ መሪዎችም አምላክ አገራቸውን እንዲባርክ ሲጠይቁ ይስተዋላሉ። ሰዎች በረከት ለማግኘት እንደነዚህ ያሉ ልመናዎችን ማቅረባቸው ተገቢ ይመስልሃል? ልመናቸው ምላሽ ያገኛል? ለመሆኑ የአምላክን በረከት የሚያገኙት እነማን ናቸው? ለምንስ?

2 ይሖዋ በመጨረሻው ዘመን፣ ጥላቻና ተቃውሞ እየደረሰባቸውም የመንግሥቱን ምሥራች እስከ ምድር ዳር ድረስ የሚሰብኩ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ንጹሕና ሰላማዊ ሰዎች እንደሚኖሩት አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 2:2-4፤ ማቴ. 24:14፤ ራእይ 7:9, 14) የዚህ ሕዝብ አባል መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት የተቀበልን ሁላችን የአምላክን በረከት ለማግኘት እንፈልጋለን፣ ደግሞም በረከቱን ማግኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ አለበለዚያ የምናደርጋቸው ነገሮች ሊሳኩልን አይችሉም። (መዝ. 127:1) ይሁንና የአምላክን በረከት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በረከት አይለያቸውም

3. እስራኤላውያን ታዛዥ ቢሆኑ ኖሮ ምን ያገኙ ነበር?

3 ምሳሌ 10:6, 7ን አንብብ። ይሖዋ፣ የእስራኤል ብሔር እሱን የሚታዘዝ ከሆነ ልዩ የሆነ ብልጽግና ብሎም ጥበቃ እንደሚያገኝ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተናግሮ ነበር። (ዘዳ. 28:1, 2) የአምላክ ሕዝቦች የይሖዋን በረከት እንደሚያገኙ ብቻ ሳይሆን በረከቱ ‘እንደማይለያቸውም’ ተነግሯቸው ነበር። በእርግጥም ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በረከቱን እንደሚያገኙ ጥርጥር አልነበረውም።

4. ከልብ መታዘዝ ሲባል ምን ይጨምራል?

 4 እስራኤላውያን ታዛዥ መሆን ያለባቸው በምን ዓይነት መንፈስ ነበር? ሕዝቡ “በደስታና በሐሤት” የማያገለግሉት ከሆነ ይሖዋ እንደሚያዝንባቸው የአምላክ ሕግ ይገልጻል። (ዘዳግም 28:45-47ን አንብብ።) ሕዝቡ ግድ ስለሆነበት ብቻ አንዳንድ መመሪያዎችን እንዲታዘዝ ይሖዋ አይፈልግም፤ እንስሳትና አጋንንትም እንኳ እንዲህ ያደርጋሉ። (ማር. 1:27፤ ያዕ. 3:3) አምላክን ከልብ መታዘዝ የፍቅር መግለጫ ነው። እንዲህ ዓይነት መንፈስ ያለው ሰው የሚታዘዘው በደስታ ነው፤ ይህም ደስታ የይሖዋ ትእዛዛት ከባዶች አለመሆናቸውን እንዲሁም “ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን” አምኖ ከመቀበል የሚመነጭ ነው።—ዕብ. 11:6፤ 1 ዮሐ. 5:3

5. አንድ ሰው ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት ማሳደሩ በ⁠ዘዳግም 15:7, 8 ላይ የሚገኘውን ሕግ እንዲታዘዝ የሚረዳው እንዴት ነው?

5 በ⁠ዘዳግም 15:7, 8 (አንብብ።) ላይ ከሚገኘው ሕግ ጋር በተያያዘ በአምላክ ላይ እምነት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ መታዘዝ እንዴት ሊገለጥ እንደሚችል እስቲ እንመልከት። ይህን ሕግ ደስተኛ ሳይሆኑ መፈጸም ለድሆች ጊዜያዊ እፎይታ ያስገኝ ይሆናል፤ ይሁንና በአምላክ ሕዝቦች መካከል ፍቅር እንዲሰፍንና ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል? ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን የመስጠት ችሎታ እንዳለው እንደሚያምኑ ያሳይ ነበር? ደግሞስ የእሱን የልግስና ባሕርይ የማንጸባረቅ አጋጣሚ በማግኘታቸው አመስጋኞች መሆናቸውን የሚጠቁም ይሆናል? በጭራሽ! አምላክ እውነተኛ ልግስና የሚያሳየውን ግለሰብ የልብ ዝንባሌ የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ እንዲህ ያለውን ሰው በሥራው ሁሉና እጁ ባረፈበት በማናቸውም ነገር እንደሚባርከው ቃል ገብቷል። (ዘዳ. 15:10) አንድ ሰው አምላክ በገባው በዚህ ቃል ላይ እምነት ማሳደሩ ለተግባር የሚያንቀሳቅሰው ሲሆን ይህም የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝለታል።—ምሳሌ 28:20

6. ዕብራውያን 11:6 ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል?

6 ይሖዋ ወሮታ ከፋይ መሆኑን ከማመን ባሻገር የአምላክን በረከት ለማግኘት የሚያስፈልግ ሌላም ባሕርይ እንዳለ ዕብራውያን 11:6 ይጠቁማል። ይሖዋ ወሮታ የሚከፍለው “ከልብ ለሚፈልጉት” መሆኑን ማስተዋል ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ላይ የተሠራበት ቃል መትጋትንና ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ያመለክታል። ይህ ጥቅስ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ትጋት የተሞላበት ጥረት ካደረግን በረከት እናገኛለን። የዚህ በረከት ምንጭ “ሊዋሽ የማይችለው” ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ነው። (ቲቶ 1:2) ይሖዋ የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ባለፉት ዘመናት አስመሥክሯል። የተናገራቸው ቃላት መሬት ጠብ አይሉም፤ ምንጊዜም ይፈጸማሉ። (ኢሳ. 55:11) በመሆኑም እምነታችን ጠንካራ ከሆነ አምላክ ወሮታችንን እንደሚከፍለን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን!

7. በአብርሃም “ዘር” አማካኝነት የአምላክን በረከት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

7 በእሱ በኩል በረከት እንደሚመጣ ተስፋ የተሰጠበት የአብርሃም “ዘር” ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ደግሞ የዚህ “ዘር” ሁለተኛ ክፍል ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች “ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ [የጠራቸውን] የእሱን ድንቅ ባሕርያት በስፋት [እንዲያስታውቁ]” ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። (ገላ. 3:7-9, 14, 16, 26-29፤ 1 ጴጥ. 2:9) ኢየሱስ ንብረቶቹን እንዲንከባከቡ የሾማቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆንን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል ብለን መጠበቅ አንችልም። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ባይረዳን ኖሮ በአምላክ ቃል ውስጥ የምናነበውን ነገር ሙሉ በሙሉ መረዳትም ሆነ እንዴት በሥራ ላይ እንደምናውለው ማወቅ አንችልም ነበር። (ማቴ. 24:45-47) ከቅዱሳን መጻሕፍት የምንማረውን ነገር ሥራ ላይ በማዋል የአምላክን በረከት ማግኘት እንችላለን።

በአምላክ ፈቃድ ላይ ትኩረት አድርጉ

8, 9. ያዕቆብ አምላክ ከገባው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ጥረት ያደረገው እንዴት ነው?

8 የአምላክን በረከት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ስለማድረግ ሲነሳ ያዕቆብን እናስታውስ ይሆናል። ያዕቆብ፣ አምላክ ለአብርሃም የገባው ቃል እንዴት እንደሚፈጸም ባያውቅም ይሖዋ የአያቱን የአብርሃምን ዘሮች እጅግ እንደሚያበዛቸውና ታላቅ ብሔር እንደሚያደርጋቸው ያምን ነበር። በመሆኑም በ1781 ዓ.ዓ. ያዕቆብ ሚስት ለማግኘት ወደ ካራን ተጓዘ። የያዕቆብ ዓላማ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለልጆቹ ጥሩ እናት የምትሆንና መንፈሳዊ አመለካከት ያላት ይሖዋን የምታመልክ ሴት ማግኘት ነበር።

 9 ታሪኩን እንደምናውቀው ያዕቆብ በካራን ዘመዱ የሆነችውን ራሔልን አገኘ። ራሔልን ስለወደዳት እሷን እንደ ሚስቱ አድርጎ ለመውሰድ ሲል ለአባቷ ለላባ ሰባት ዓመት ለመሥራት ተስማማ። ይህ ዘገባ እንዲሁ አስደሳች የፍቅር ታሪክ ብቻ አይደለም። ያዕቆብ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለአያቱ ለአብርሃም የገባውን ቃል እንዲሁም ይህን ቃሉን ለአባቱ ለይስሐቅ መድገሙን ያውቅ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍ. 18:18፤ 22:17, 18፤ 26:3-5, 24, 25) ይስሐቅ ደግሞ ለልጁ ለያዕቆብ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ይባርክህ፤ ብዙ ሕዝብ እስክትሆን ድረስ ልጆች አፍራ፤ ዘርህን ያብዛው። [አምላክ] ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ።” (ዘፍ. 28:3, 4) ያዕቆብ ተስማሚ ሚስት ለማግኘትና ቤተሰብ ለማፍራት ጥረት ማድረጉ ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንደነበረው ያሳያል።

10. ይሖዋ ያዕቆብን ለመባረክ የተነሳሳው ለምንድን ነው?

10 ያዕቆብ ቤተሰቡን ለመንከባከብ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ጥረት አላደረገም። እሱን ያሳስበው የነበረው ይሖዋ የገባው ቃል ነበር። የይሖዋ ፈቃድ በሚፈጸምበት መንገድ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። ያዕቆብ ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥመውም የአምላክን በረከት ለማግኘት ሲል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበረው፤ በዚህም የተነሳ ይሖዋ ባርኮታል።—ዘፍጥረት 32:24-29ን አንብብ።

11. አምላክ በቃሉ ውስጥ ከገለጠው ፈቃዱ ጋር በሚስማማ መልኩ ምን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል?

11 እኛም እንደ ያዕቆብ የይሖዋ ዓላማ ስለሚፈጸምበት መንገድ ሁሉንም ነገር አናውቅም። ያም ሆኖ የአምላክን ቃል በማጥናት ‘የይሖዋን ቀን’ በተመለከተ ምን መጠበቅ እንዳለብን ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን። (2 ጴጥ. 3:10, 17) ለምሳሌ፣ የይሖዋ ቀን መቼ እንደሚመጣ ባናውቅም ይህ ቀን መቅረቡን እንገነዘባለን። በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላ ምሥክርነት በመስጠት ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን ማዳን እንደምንችል የሚናገረውን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ እናምናለን።—1 ጢሞ. 4:16

12. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

12 መጨረሻው በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል እንገነዘባለን፤ ይሖዋ በዚህች ምድር ላይ ለሚኖር ለእያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ ምሥክርነት እስክንሰጥ መጠበቅ አያስፈልገውም። (ማቴ. 10:23) የስብከቱን  ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ማከናወን እንደምንችል ጥሩ መመሪያ እናገኛለን። ያለንን ማንኛውንም ነገር ተጠቅመን በዚህ ሥራ አቅማችን በፈቀደው መጠን በእምነት እንካፈላለን። በክልላችን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የምንሰብከውን መልእክት ይቀበሉ ይሆን? ይህን አስቀድሞ ማወቅ እንዴት ይቻላል? (መክብብ 11:5, 6ን አንብብ።) የእኛ ሥራ ይሖዋ እንደሚባርከን በመተማመን ምሥራቹን መስበክ ነው። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ይሖዋ የምናደርገውን ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደሚመለከትና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የሚያስፈልገንን ማንኛውንም ዝርዝር መመሪያ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝ. 32:8

የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጉ

13, 14. አምላክ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አገልጋዮቹ ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚችል የታየው እንዴት ነው?

13 የተሰጠንን አንድ ዓይነት ኃላፊነት ለመወጣት ወይም በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቁ እንዳልሆንን ቢሰማንስ? የእሱን አገልግሎት በምናከናውንበት ጊዜ ያለንን ችሎታ ማሻሻል እንድንችል ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ አለብን። (ሉቃስ 11:13ን አንብብ።) ሰዎች የኋላ ታሪካቸው ወይም ያካበቱት ልምድ ምንም ይሁን ምን፣ የአምላክ መንፈስ አንድን ሥራ ወይም የአገልግሎት መብት ለመወጣት ብቁ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ እረኛና ባሪያ የነበሩት እስራኤላውያን የጦርነት ልምድ ያልነበራቸው ቢሆንም ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ጠላቶቻቸውን ድል ማድረግ እንዲችሉ የአምላክ መንፈስ ረድቷቸዋል። (ዘፀ. 17:8-13) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ባስልኤልና ኤልያብ አምላክ ስለ ማደሪያው ድንኳን አሠራር የሰጣቸውን ንድፍ በመከተል ውብ የሆኑ ነገሮችን መሥራት እንዲችሉ ይኸው መንፈስ ረድቷቸዋል።—ዘፀ. 31:2-6፤ 35:30-35

14 ኃያል የሆነው ይህ መንፈስ፣ በዘመናችን የሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች የራሳቸውን ማተሚያ ለማቋቋም በተገደዱ ጊዜ ድርጅቱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ብቁ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። በወቅቱ የፋብሪካው የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም ሮበርት ማርቲን እስከ 1927 ድረስ የተከናወነውን ሁኔታ በአንድ ደብዳቤ ላይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ በተገቢው ጊዜ ላይ በሩን ከፈተ፤ ትልቁ የማተሚያ መሣሪያ በእጃችን ገባ፤ ማሽኑ ስለተሠራበት መንገድም ሆነ ስለ አጠቃቀሙ በማናውቀው ሰዎች እጅ ገባ። ሆኖም ጌታ፣ ባላቸው ችሎታ ሁሉ እሱን ለማገልገል ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ፈጣን አእምሮ እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላል። . . . በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይህን ማተሚያ ማንቀሳቀስ ቻልን፤ ማሽኑ እስከ አሁን ድረስ እየሠራ ሲሆን መጀመሪያ የሠሩት ሰዎች እንኳ ይሠራል ብለው የማይጠብቁትን ነገር እያከናወነ ነው።” ይሖዋ እንዲህ ያለውን ትጋት የተሞላበት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን አሁንም ድረስ መባረኩን ቀጥሏል።

15. ሮም 8:11 ፈተና የሚያጋጥማቸውን ሰዎች የሚያበረታታው እንዴት ነው?

15 የይሖዋ መንፈስ በተለያዩ መንገዶች ይሠራል። ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይህን መንፈስ ማግኘት የሚችሉ  ሲሆን የማይገፉ የሚመስሉ መሰናክሎችን ለመወጣት ይረዳቸዋል። የገጠመን ፈተና ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ቢሰማንስ? በ⁠ሮም 7:21, 25 እንዲሁም 8:11 ላይ ከሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ብርታት ማግኘት እንችላለን። “ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው የእሱ መንፈስ” ከሥጋ ምኞቶቻችን ጋር በምናደርገው ትግል ማሸነፍ እንድንችል ኃይል በመስጠት ይረዳናል። ይህ ጥቅስ የተጻፈው በመንፈስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይሠራል። ሁላችንም በክርስቶስ ላይ እምነት እንዳለን በማሳየት፣ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶቻችንን ለመግደል ጥረት በማድረግ እንዲሁም የአምላክ መንፈስ ከሚሰጠን መመሪያ ጋር ተስማምተን በመኖር ሕይወት ማግኘት እንችላለን።

16. የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ምንም ጥረት ሳናደርግ አምላክ መንፈሱን ይሰጠናል ብለን መጠበቅ እንችላለን? በፍጹም። አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠን ከመጸለይ በተጨማሪ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናት አለብን። (ምሳሌ 2:1-6) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ መንፈስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አለ። አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን “መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን” ለመስማት እንደምንፈልግ ያሳያል። (ራእይ 3:6) ከዚህም በላይ ትሑት በመሆን የምንማረውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ምሳሌ 1:23 (የ1954 ትርጉም) “ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፤ እነሆ፣ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ” የሚል ምክር ይሰጠናል። በእርግጥም አምላክ “እሱን እንደ ገዥያቸው አድርገው እየታዘዙት ላሉት” ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣቸዋል።—ሥራ 5:32

17. የአምላክን በረከት ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን የሚያስገኘው ውጤት ከምን ጋር ሊመሳሰል ይችላል?

17 የአምላክን በረከት ለማግኘት ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ይሖዋ ለሕዝቡ መልካም ነገሮችን አትረፍርፎ የሰጣቸው ጥረት በማድረጋቸው ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ ሁኔታ ምግብ ከመመገብ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውነታችን ከምንመገበው ምግብ ጥቅም የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ምግብ በመመገብ ከዚህ ሂደት ጋር መተባበር እንዳለብን ብቻ ነው። ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን የምንመገብ ከሆነ ደግሞ የምናገኘው ውጤት የዚያኑ ያህል የተሻለ ይሆናል። ይሁንና ምግቡን የሚሰጠን አምላክ ነው፤ ከምንመገበው ምግብ የምናገኛቸው ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ከሰውነታችን ጋር እንዲዋሐዱ እንዲሁም ከምግቡ ኃይልና እርካታ እንድናገኝ አድርጎ የፈጠረንም እሱ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስፈልገውን መሥፈርት ነግሮናል፤ እንዲሁም ከዚህ መሥፈርት ጋር ተስማምተን ለመኖር የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጣው ይሖዋ በመሆኑ ሊመሰገን የሚገባው እሱ ነው። እንደዚያም ሆኖ በረከት ለማግኘት ከፈለግን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መልኩ በመመላለስ ከእሱ ጋር መተባበር አለብን።—ሐጌ 2:18, 19

18. ምን ለማድረግ ቆርጠሃል? ለምንስ?

18 የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት ለመወጣት ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርግ። ከዚህም ባሻገር የምታደርጋቸው ነገሮች እንዲሳኩልህ ምንጊዜም የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። (ማር. 11:23, 24) እንዲህ ስታደርግ “የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል” በሚለው አባባል ላይ እምነት መጣል ትችላለህ። (ማቴ. 7:8) በመንፈስ የተቀቡት፣ በሰማይ “የሕይወት አክሊል” በማግኘት ይባረካሉ። (ያዕ. 1:12) በአብርሃም ዘር አማካኝነት ራሳቸውን ለመባረክ ልባዊ ጥረት የሚያደርጉ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ደግሞ ኢየሱስ “እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፣ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ሲላቸው ለመስማት ይጓጓሉ። (ዮሐ. 10:16፤ ማቴ. 25:34) አዎን፣ “[አምላክ] የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ . . . በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝ. 37:22, 29

ልታብራራ ትችላለህ?

• ከልብ መታዘዝ ሲባል ምን ይጨምራል?

• የአምላክን በረከት ለማግኘት ምን ያስፈልጋል?

• የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ምን እርዳታስ ሊያደርግልን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያዕቆብ የይሖዋን በረከት ለማግኘት ከአንድ መልአክ ጋር ታግሎ ነበር

አንተስ እንደ ያዕቆብ በረከት ለማግኘት ልባዊ ጥረት ታደርጋለህ?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንፈስ ባስልኤልና ኤልያብ የላቀ ጥበብ እንዲኖራቸው አድርጓል