ሰዓት አክባሪ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
ሰዓት አክባሪ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
ቀጠሮ ማክበር ወይም በሰዓቱ መገኘት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ልንወጣቸው ከሚገቡን እንቅፋቶች መካከል የምንሄድበት ቦታ ርቀት፣ የትራፊክ መጨናነቅና የተጣበበ ፕሮግራም ይገኙበታል። ያም ቢሆን በሰዓቱ መገኘት አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሥራ ቦታ ሰዓት የሚያከብር ሰው አብዛኛውን ጊዜ ታማኝና ትጉህ ሠራተኛ ተደርጎ ይቆጠራል። በሌላ በኩል ግን የሚያረፍድ ሰው ሌሎች የሚያከናውኑትን ሥራ እንዲሁም የሥራውን ጥራትና የሚሰጠውን አገልግሎት ሊያስተጓጉል ይችላል። አንድ ተማሪ አርፋጅ መሆኑ አንዳንድ ትምህርቶች እንዲያመልጡትና በትምህርቱ ተገቢውን እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት እንዲሆንበት ያደርጋል። አንድ ሰው ለጥርስ ወይም ለሌላ ሕክምና ቀጠሮ ኖሮት በሰዓቱ ባይደርስ ተገቢውን ሕክምና እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል።
ያም ሆኖ በአንዳንድ ቦታዎች ቀጠሮ ማክበር ያን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አይታይም። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች የምንኖር ከሆነ ማርፈድ በቀላሉ ልማድ ሊሆንብን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ካለብን ቀጠሮ የማክበር ፍላጎት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው። በሰዓቱ መገኘት ያለውን ጥቅም መረዳታችን ቀጠሮ አክባሪ እንድንሆን እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። ቀጠሮ የምናከብርባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ቀጠሮ እንዳናከብር የሚያደርጉንን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ሰዓት አክባሪዎች መሆናችን ምን ጥቅሞች ሊያስገኝልን ይችላል?
ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ የሚያከብር አምላክ ነው
ቀጠሮ እንድናከብር የሚያደርገን ከሁሉ የላቀው ምክንያት የምናመልከውን አምላክ መምሰል ስለምንፈልግ ኤፌ. 5:1) ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ በማክበር ረገድ በጣም ግሩም ምሳሌ ነው። ዘግይቶ አያውቅም። ዓላማውን ለማስፈጸም የወሰነውን ጊዜ በጥብቅ ይከተላል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ክፉውን ዓለም በውኃ ለማጥፋት ሲወስን ለኖኅ “በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ” ብሎት ነበር። የጥፋቱ ጊዜ ሲቃረብ ይሖዋ ኖኅን መርከቡ ውስጥ እንዲገባ ከነገረው በኋላ እንዲህ በማለት አሳሰበው፦ “ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ።” ከዚያም በወሰነው ጊዜ ማለትም ‘ከሰባት ቀን በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ መጣ።’ (ዘፍ. 6:14፤ 7:4, 10) ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ውስጥ በተባሉት ጊዜ ባይገቡ ኖሮ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማሰብ ትችላለህ። እነሱም ልክ እንደሚያመልኩት አምላክ የተቀጠረውን ጊዜ ማክበር ነበረባቸው።
ነው። (የውኃው ጥፋት ከመጣ ከ450 ዓመታት በኋላ ይሖዋ ለአብርሃም ልጅ እንደሚወልድና በልጁ በኩል ተስፋ የተደረገበት ዘር እንደሚመጣ ነገረው። (ዘፍ. 17:15-17) አምላክ፣ ይስሐቅ “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ” እንደሚወለድ ተናገረ። ታዲያ እንደተባለው ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት” በማለት ይነግረናል።—ዘፍ. 17:21፤ 21:2
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የቀጠረውን ጊዜ እንደሚያከብር የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን ይዟል። (ኤር. 25:11-13፤ ዳን. 4:20-25፤ 9:25) መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት የሚመጣውን የይሖዋን የፍርድ ቀን ነቅተን እንድንጠብቅ ይነግረናል። የይሖዋ ቀን ከሰው አስተሳሰብ አንጻር ‘የዘገየ’ ቢመስልም እንኳ ‘ከቶ አይዘገይም።’—ዕን. 2:3
በአምልኮ ፕሮግራሞች ረገድ ሰዓት ማክበር አስፈላጊ ነው
ሁሉም እስራኤላውያን ወንዶች ‘የይሖዋ በዓላት’ በሚከበሩባቸው ቦታዎች መገኘት ብቻ ሳይሆን ሰዓት ማክበር ነበረባቸው። (ዘሌ. 23:2, 4) በተጨማሪም አምላክ አንዳንድ መሥዋዕቶች መቼ መቅረብ እንዳለባቸው ቁርጥ ያለ ጊዜ ወስኖ ነበር። (ዘፀ. 29:38, 39፤ ዘሌ. 23:37, 38) ታዲያ ይህ ሁኔታ አምላክ አገልጋዮቹ በአምልኮ ረገድ ሰዓት አክባሪ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ አያሳይም?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለቆሮንቶስ ሰዎች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዴት መመራት እንዳለባቸው ሲነግራቸው “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 14:40) በመሆኑም ለአምልኮ ተብለው የሚደረጉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በሰዓቱ ይጀመሩ ነበር። ይሖዋ ጊዜን ስለማክበር ያለው አስተሳሰብ ዛሬም አልተለወጠም። (ሚል. 3:6) ታዲያ በእነዚህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ ለመገኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
በሰዓቱ በመገኘት ረገድ የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት
አንዳንዶች አስቀድሞ እቅድ ማውጣት በጣም እንደሚረዳ አስተውለዋል። (ምሳሌ 21:5) ለምሳሌ በተወሰነ ሰዓት አንድ ቦታ መድረስ ቢኖርብን ለመንገድ የሚበቃንን ሰዓት ብቻ አስልተን ጉዞ መጀመራችን ጥበብ ይሆናል? “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ቢያጋጥሙን እንኳ እንዳናረፍድ ለጉዞ ከሚያስፈልገን ሌላ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ተረፍ አድርገን መመደባችን ብልህነት አይሆንም? (መክ. 9:11 NW) ቀጠሮ አክባሪ የሆነ ሆሴ * የተባለ ወጣት “አንድ ሰው የሚፈልግበት ቦታ በሰዓቱ እንዲደርስ የሚረዳው አንደኛው ነገር ጉዞው ምን ያህል እንደሚፈጅ በትክክል የሚያውቅ መሆኑ ነው” በማለት ተናግሯል።
አንዳንዶች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በጥሩ ሰዓት ለመድረስ ሲሉ ከሥራ ቦታቸው አስቀድመው መውጣት የሚችሉባቸውን ዝግጅቶች ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል። በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ዓይነት ዝግጅት አድርጎ ነበር፤ ይህ ወንድም በፈረቃ ሥራው ምክንያት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ 45 ደቂቃ አርፍዶ እንደሚደርስ ተገነዘበ። በዚህም ምክንያት ስብሰባዎች በሚደረጉባቸው ቀናት የሚተካው ሰው ከሰዓቱ ቀደም ብሎ እንዲመጣና ቶሎ እንዲለቀው ሁኔታዎችን አመቻቸ። ወንድም ደግሞ ለሥራ ባልደረባው ሰባት ተጨማሪ ሰዓት ሊሠራለት ተስማማ።
ትንንሽ ልጆች ካሉን በስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ መገኘት ይበልጥ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹን ለስብሰባ የማዘጋጀቱ ኃላፊነት የሚወድቀው በእናት ላይ ቢሆንም ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ሊረዷት ይችላሉ፤ ደግሞም ሊረዷት ይገባል። በሜክሲኮ የምትኖረው ኤስፐራንዛ የተባለች አንዲት እናት ስምንት ልጆቿን የምታሳድገው ብቻዋን ነው። ልጆቹ አሁን ከ5 እስከ 23 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። ኤስፐራንዛ ቤተሰቦቿ በስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ መገኘት የቻሉት እንዴት እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ትልልቆቹ ሴቶች ልጆቼ ትንንሾቹን ያዘጋጇቸዋል። ይህ ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራዬን እንድጨርስና ራሴን አዘገጃጅቼ በወሰንነው ሰዓት ከቤት እንድንወጣ አስችሎናል።” ይህ ቤተሰብ ከቤት የሚወጣበትን ሰዓት የወሰነ ሲሆን እያንዳንዱ የቤተሰብ አባልም በሰዓቱ ለመውጣት ይተባበራል።
በአምልኮ ፕሮግራሞች ላይ በሰዓቱ መገኘት ያለው ጥቅም
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ መገኘታችን በሚያስገኝልን ጥቅም ላይ ማሰላሰላችን በሰዓቱ ለመገኘት ያለንን ፍላጎት የሚያጠናክርልን ከመሆኑም በላይ በዚህ ረገድ ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ያነሳሳናል። በስብሰባዎች ላይ በጥሩ ሰዓት የመገኘት ልማድ ያዳበረች ሳንድራ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በጊዜ መድረስ የሚያስደስተኝ ወንድሞችንና እህቶችን ሰላም ለማለት፣ ከእነሱ ጋር ለመጨዋወት እንዲሁም የበለጠ እንዳውቃቸው አጋጣሚ ስለሚከፍትልኝ ነው።” በመንግሥት አዳራሽ ቀደም ብለን ከደረስን በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች ዕብ. 10:24, 25
ስላሳዩት ጽናትና በታማኝነት ስላከናወኑት አገልግሎት በመስማት ጥቅም ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ ቀደም ብለን መገኘታችንና የሚያንጽ ጭውውት ማድረጋችን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች እንዲነቃቁ’ ስለሚያስችል ዘወትር ይህን ማድረጋችን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።—በእያንዳንዱ ክርስቲያናዊ ስብሰባ መክፈቻ ላይ የሚቀርበው ጸሎትና መዝሙር የአምልኳችን ዓበይት ክፍል ናቸው። (መዝ. 149:1) መዝሙሮቻችን ይሖዋን ያወድሳሉ፣ ልናዳብራቸው የሚገቡ ባሕርያትን እንድናስታውስ ያደርጉናል እንዲሁም በአገልግሎት ላይ በደስታ እንድንካፈል ያበረታቱናል። ስለ መክፈቻ ጸሎትስ ምን ማለት ይቻላል? በጥንት ጊዜ ይሖዋ ቤተ መቅደሱን ‘የጸሎት ቤቴ’ በማለት ጠርቶታል። (ኢሳ. 56:7) በዛሬው ጊዜ በስብሰባዎቻችን ላይ ጸሎት ለማቅረብ እንሰበሰባለን። የመክፈቻው ጸሎት የሚቀርበው የይሖዋን መመሪያና መንፈስ ቅዱስ ለመጠየቅ ብቻ ሳይሆን አእምሯችንና ልባችን የሚቀርበውን ትምህርት እንዲቀበል ለማዘጋጀት ጭምር ነው። በመሆኑም በስብሰባዎቻችን ላይ በሚቀርበው የመክፈቻ ጸሎትና መዝሙር ላይ በሰዓቱ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።
የ23 ዓመቷ ሄለን በስብሰባዎች ላይ ቀደም ብላ የምትገኝበትን ምክንያት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የመክፈቻውን መዝሙርና ጸሎት ጨምሮ በስብሰባው ላይ የሚቀርበውን ትምህርት ሁሉ ስላዘጋጀ ቀደም ብዬ መገኘቴ ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር የማሳይበት መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል።” እኛስ ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረን አይገባም? አዎን፣ ሊኖረን ይገባል። በመሆኑም በሁሉም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን በተለይም ከእውነተኛው አምላክ አምልኮ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ የሰዓት አክባሪነት ልማድ ለማዳበር ልባዊ ጥረት እናድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 ስሞቹ ተቀይረዋል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስቀድማችሁ በደንብ ተዘጋጁ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሟችሁ እንደሚችሉ በማሰብ የተወሰኑ ደቂቃዎችን መድቡ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብሰባዎች ላይ ቀደም ብሎ መድረስ የሚያስገኘውን በረከት እጨዱ