በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁጣችሁን በመቆጣጠር ‘ምንጊዜም ክፉውን አሸንፉ’

ቁጣችሁን በመቆጣጠር ‘ምንጊዜም ክፉውን አሸንፉ’

 ቁጣችሁን በመቆጣጠር ‘ምንጊዜም ክፉውን አሸንፉ’

“የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ . . . ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም [አሸንፉ]።”—ሮም 12:19, 21

1, 2. ወደ አንድ ቦታ ይጓዙ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል?

ሠላሳ አራት የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውሰና ላይ ለመገኘት ጉዞ ላይ ነበሩ፤ በጉዟቸው መሃል ባጋጠማቸው ችግር የተነሳ በረራቸው ተስተጓጎለ። አውሮፕላኑ ነዳጅ ለመቅዳት ከከተማ ርቆ በሚገኝ አንድ የአውሮፕላን ማረፊያ ቆመ፤ ይህን ማድረግ አንድ ሰዓት ብቻ እንደሚፈጅ ቢታሰብም በቂ ምግብና ውኃ እንዲሁም የመጸዳጃ አገልግሎት በሌለበት በዚያ ቦታ ለ44 ሰዓታት ቆዩ። ብዙዎቹ ተሳፋሪዎች በሁኔታው ከመበሳጨታቸውም ሌላ በአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኞች ላይ ዛቻ መሰንዘር ጀመሩ። ወንድሞችና እህቶች ግን እስከ መጨረሻው ድረስ የመረጋጋት መንፈስ ይታይባቸው ነበር።

2 በመጨረሻም ወንድሞች የውሰናው ፕሮግራም ሳያልቅ መድረስ ቻሉ። ደክሟቸው የነበረ ቢሆንም ፕሮግራሙ ካበቃ በኋላም ከአካባቢው ወንድሞች ጋር ለመጫወት እዚያው ቆዩ። ወንድሞች በኋላ ላይ እንደተረዱት ችግር አጋጥሟቸው በነበረበት ወቅት ያሳዩትን ትዕግሥትና ራስን የመግዛት ባሕርይ ያስተዋሉ ሰዎች ነበሩ። በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች አንዱ ለአየር መንገዱ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እነዚያ 34 ክርስቲያኖች በዚያ በረራ ላይ ባይኖሩ ኖሮ በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ብጥብጥ ይነሳ ነበር።”

የምንኖረው ብስጩ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ነው

3, 4. (ሀ) ሰዎች ብስጩ መሆናቸው ምን አስከትሏል? እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ መታየት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) ቃየን ቁጣውን መቆጣጠር ይችል ነበር? አብራራ።

3 ይህ ክፉ ሥርዓት የሚያሳድረው ጫና ሰዎች ብስጩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (መክ. 7:7 የ1954 ትርጉም) ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጥላቻና ዓመፅ ይመራቸዋል። ሰዎች ብስጩ መሆናቸው በአንድ አገር ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲከፈት እንዲሁም በተለያዩ አገሮች መካከል ውጊያ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ ያለው ውጥረት በብዙ ቤቶች ውስጥ ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል። በሰዎች ላይ የሚታየው እንዲህ ዓይነቱ የቁጣና የዓመፅ መንፈስ ዛሬ የጀመረ ነገር አይደለም። የአዳምና የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ቃየን በታናሽ ወንድሙ በአቤል ላይ ያደረበት ቅናት በቁጣ ተነሳስቶ እንዲገድለው አድርጎታል። ይሖዋ፣ ቃየንን ቁጣውን እንዲቆጣጠር ከማስጠንቀቅም አልፎ ይህን ካደረገ እንደሚባርከው ቃል ገብቶለት ነበር፤ ቃየን ግን ይህን ክፉ ድርጊት ከመፈጸም አልተመለሰም።—ዘፍጥረት 4:6-8ን አንብብ።

4 ቃየን ከአዳም የወረሰው አለፍጽምና ቢኖርበትም ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ውስጥ የራሱን ምርጫ ማድረግ ይችል ነበር። ቁጣውን መቆጣጠር ይችል ነበር። ቃየን ለፈጸመው የዓመፅ ድርጊት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሆነው ለዚህ ነው። በተመሳሳይ እኛም ፍጹማን ስላልሆንን ቁጣችንን መቆጣጠርና በቁጣ ተነሳስተን እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በተጨማሪም የምንኖረው ‘በዓይነቱ ልዩ በሆነው በዚህ ዘመን’ ውስጥ በመሆኑ የሚገጥሙን ከበድ ያሉ ችግሮች ነገሩን ያባብሱታል። (2 ጢሞ. 3:1) ለምሳሌ ያህል፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ስሜታችንን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንዲሆንብን ሊያደርጉ ይችላሉ። ፖሊሶች እንዲሁም ቤተሰብን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ ድርጅቶች እንደሚገልጹት በዓለም ላይ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሰዎች ይበልጥ ቁጡ እንዲሆኑና በቤት ውስጥ የሚፈጸመው ዓመፅ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል።

5, 6. በዓለም ላይ የሚታዩት የትኞቹ ነገሮች ከቁጣ ጋር በተያያዘ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ?

5 ከዚህም በተጨማሪ በሕይወታችን ውስጥ የምናገኛቸው አብዛኞቹ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣” “ትዕቢተኞች” አልፎ ተርፎም “ጨካኞች” ናቸው። እንደነዚህ ያሉት መጥፎ ባሕርያት በቀላሉ ሊጋቡብን ወይም ሊያስቆጡን ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:2-5) እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በቀልን እንደ  ጥሩ ምግባር ዓመፅን ደግሞ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ትክክለኛና የተለመደ እርምጃ አድርገው ያሳያሉ። አብዛኞቹ ፊልሞች የሚደመደሙት ዋናው ገጸ ባሕርይ ክፉውን ሰው በጭካኔ ሲገድለው በማሳየት ነው፤ ታሪኩ የሚቀርብበት መንገድ ተመልካቾች ክፉው ሰው “የእጁን ሲያገኝ” ለመመልከት እንዲጓጉ ያደርጋቸዋል።

6 እንዲህ ያለው ፕሮፓጋንዳ “የዓለምን መንፈስ” እና ቁጡ የሆነውን ገዢውን ይኸውም የሰይጣንን ባሕርይ እንጂ የአምላክን መንገድ የሚያንጸባርቅ አይደለም። (1 ቆሮ. 2:12፤ ኤፌ. 2:2፤ ራእይ 12:12) ይህ መንፈስ፣ የሥጋችንን ምኞት እንድናረካ የሚያበረታታ ሲሆን ከመንፈስ ቅዱስና መንፈሱ ከሚያፈራው ፍሬ ጋር የሚቃረን ነው። መሠረታዊ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች አንዱ የሚያበሳጭ ነገር ሲገጥመን ብድር ከመመለስ እንድንቆጠብ ያበረታታል። (ማቴዎስ 5:39, 44, 45ን አንብብ።) ታዲያ የኢየሱስን ትምህርቶች ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ጥሩና መጥፎ ምሳሌዎች

7. ስምዖንና ሌዊ ቁጣቸውን አለመቆጣጠራቸው ምን አስከተለ?

7 መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን መቆጣጠርን በተመለከተ ብዙ ምክሮች የያዘ ከመሆኑም ሌላ ቁጣችንን መቆጣጠር ወይም አለመቆጣጠር የሚያስከትለውን ውጤት የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎች ይዟል። ስምዖንና ሌዊ የተባሉት የያዕቆብ ልጆች፣ እህታቸውን ዲናን የደፈረውን ሴኬምን በተበቀሉት ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። ወንድማማቾቹ እህታቸው ላይ በደረሰው ነገር “ዐዘኑ፤ ክፉኛም ተቈጡ።” (ዘፍ. 34:7) ከዚያም ሌሎቹ የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ወደ ሴኬም ከተማ በመሄድ ጥቃት ሰነዘሩ፤ እንዲሁም ከተማዋን ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ሁሉ ማርከው ተመለሱ። ይህን ሁሉ ያደረጉት ለዲና ስለተቆረቆሩ ብቻ ሳይሆን ክብራቸው እንደተነካና እንደተደፈሩ ስለተሰማቸው ነበር። ሴኬም እነሱንም ሆነ አባታቸውን ያዕቆብን እንዳዋረደ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና ያዕቆብ ስለፈጸሙት ድርጊት ምን ተሰማው?

8. መበቀልን በተመለከተ ከስምዖንና ከሌዊ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 ዲና በደረሰባት መጥፎ ነገር ያዕቆብ ከልቡ እንዳዘነ ጥርጥር የለውም፤ ያም ሆኖ ልጆቹ የወሰዱትን የበቀል እርምጃ አውግዞታል። ስምዖንና ሌዊ “ታዲያ፤ እኅታችንን እንደ ዝሙት አዳሪ ይድፈራት?” በማለት ድርጊታቸውን ለማስተባበል ሞክሩ። (ዘፍ. 34:31) ይሁንና ጉዳዩ በዚህ  ብቻ አላበቃም፤ ይሖዋም በድርጊታቸው አዝኖ ነበር። ስምዖንና ሌዊ በቁጣ ተነሳስተው በፈጸሙት የዓመፅ ድርጊት የተነሳ ዘሮቻቸው በእስራኤል ነገዶች መካከል እንደሚበተኑ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ትንቢት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 49:5-7ን አንብብ።) በእርግጥም፣ ስምዖንና ሌዊ ቁጣቸውን ባለመቆጣጠራቸው አምላክም ሆነ አባታቸው አዝነውባቸዋል።

9. ዳዊት በቁጣ ገንፍሎ እርምጃ ሊወስድ ተቃርቦ የነበረው መቼ ነው?

9 ንጉሥ ዳዊት ያደረገው ነገር ግን ፈጽሞ የተለየ ነበር። የበቀል እርምጃ መውሰድ የሚችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አግኝቶ የነበረ ቢሆንም እንዲህ ከማድረግ ተቆጥቧል። (1 ሳሙ. 24:3-7) በአንድ ወቅት ግን በቁጣ ገንፍሎ እርምጃ ሊወስድ ትንሽ ቀርቶት ነበር። የዳዊት ሰዎች፣ ናባል ለተባለ አንድ ባለጸጋ ሰው መንጋውንና እረኞቹን በመጠበቅ ውለታ የዋሉለት ቢሆንም ናባል የስድብ ናዳ አወረደባቸው። ዳዊት በተለይ አብረውት በነበሩት ሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር መድረሱ ስላበሳጨው ሳይሆን አይቀርም ናባልን ለመበቀል ተነሳ። ዳዊትና ሰዎቹ በናባልና በቤተሰቡ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሚገሰግሱበት ወቅት አንድ ወጣት፣ ብልህ ሴት ለሆነችው ለናባል ሚስት ለአቢግያ ስለ ሁኔታው ከነገራት በኋላ እርምጃ እንድትወስድ አሳሰባት። አቢግያም ጊዜ ሳታጠፋ በርካታ ስጦታዎችን ካዘጋጀች በኋላ ዳዊትን ለማግኘት ጉዞ ጀመረች። ዳዊትን ስታገኘውም ናባል ለፈጸመው አሳፋሪ ድርጊት በትሕትና ይቅርታ የጠየቀች ከመሆኑም በላይ ዳዊት ይሖዋን ስለሚፈራ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ለመነችው። በዚህ ጊዜ ዳዊት ወደ ልቡ በመመለስ አቢግያን ‘ደም እንዳላፈስ ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ የተባረክሽ ሁኚ’ አላት።—1 ሳሙ. 25:2-35

ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት

10. ክርስቲያኖች በቀልን በተመለከተ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

10 ከስምዖንና ከሌዊ እንዲሁም ከዳዊትና ከአቢግያ ሁኔታ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋ ልጓም ያልተበጀለት ቁጣንና ዓመፅን የሚቃወም ሲሆን ሰላም ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ግን ይባርካል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት ጽፏል። አክሎም “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ ስለተጻፈ ለአምላክ ቁጣ ዕድል ስጡ። ነገር ግን ‘ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።’ በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።”—ሮም 12:18-21 *

11. አንዲት እህት ቁጣዋን መቆጣጠር የተማረችው እንዴት ነው?

11 እኛም ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንዲት እህት አዲሷ አለቃዋ ምክንያታዊነትና ደግነት የጎደላት እንደሆነች በመግለጽ ቅሬታዋን ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነገረችው። እህት በአለቃዋ በጣም ስለተናደደች ሥራዋን ለመልቀቅ አስባ ነበር። ሽማግሌው ግን በችኮላ ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳትወስድ አጥብቆ አሳሰባት። አለቃዋ ተገቢ ያልሆነ ነገር ስታደርግባት እህት መቆጣቷ ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ የፈየደው ነገር እንደሌለ ሽማግሌው ማስተዋል ችሎ ነበር። (ቲቶ 3:1-3) ሽማግሌው፣ እህት ከጊዜ በኋላ ሌላ ሥራ ብትይዝም እንኳ ደግነት የጎደለው ነገር ሲደረግባት ምላሽ በምትሰጥበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ጠቆማት። ኢየሱስ ባስተማረን መሠረት ሌሎች እሷን ሊይዟት በምትፈልገው መንገድ አለቃዋን እንድትይዛት መከራት። (ሉቃስ 6:31ን አንብብ።) እህት ምክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማማች። ውጤቱ ምን ሆነ? ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአለቃዋ አመለካከት የተለወጠ ከመሆኑም በላይ እህትን ለሥራዋ አመሰገነቻት።

12. በተለይ በክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ሁኔታው በጣም ሊጎዳን የሚችለው ለምንድን ነው?

12 ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር እንዲህ ዓይነት ችግሮች መፈጠራቸው ብዙም አያስገርመን ይሆናል። በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ ስንኖር ብዙውን ጊዜ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉና ክፉዎች እንድንበሳጭ እንዳያደርጉን መጠንቀቅ እንዳለብን እናውቃለን። (መዝ. 37:1-11፤ መክ. 8:12, 13፤ 12:13, 14) ከአንድ መንፈሳዊ ወንድማችን ወይም እህታችን ጋር ባለን ግንኙነት ችግሮች ሲፈጠሩ ግን ስሜታችን በጣም ሊጎዳ ይችላል። አንዲት እህት “ወደ እውነት ስመጣ በጣም የከበደኝ ነገር የይሖዋ ሕዝቦች ፍጹማን እንዳልሆኑ መቀበል ነበር” በማለት ታስታውሳለች። ፍቅርና አሳቢነት ከጎደለው ዓለም ወጥተን ወደ ጉባኤ ስንመጣ ሁሉም ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ደግነት እንደሚያሳዩ  እንጠብቃለን። በዚህም የተነሳ አንድ የእምነት ባልንጀራችን በተለይ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያለው ክርስቲያን አሳቢነት የጎደለው ወይም ከክርስቲያኖች የማይጠበቅ ነገር ቢያደርግ በሁኔታው ልንጎዳ ወይም ልንበሳጭ እንችላለን። ‘በይሖዋ ሕዝቦች መካከል እንዴት እንዲህ ዓይነት ነገር ይደረጋል?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ በሐዋርያት ዘመን በመንፈስ በተቀቡ ክርስቲያኖች መካከልም እንኳ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። (ገላ. 2:11-14፤ 5:15፤ ያዕ. 3:14, 15) ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር ሲደርስብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13. አለመግባባቶችን መፍታት ያለብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከላይ የተጠቀሰችው እህት “ለጎዳኝ ለማንኛውም ሰው መጸለይን ተማርኩ” ብላለች። “እንዲህ ማድረጉ ምንጊዜም ይረዳል።” ቀደም ብለን እንዳነበብነው ኢየሱስ ስደት ለሚያደርሱብን ሰዎች እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴ. 5:44) ታዲያ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይበልጥ ልንጸልይ አይገባም? አንድ አባት ልጆቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱ እንደሚፈልግ ሁሉ ይሖዋም በምድር ላይ ያሉት አገልጋዮቹ ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ በደስታ ለዘላለም አብረን የምንኖርበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን፤ ይሖዋ ይህን እንድናደርግ ከወዲሁ እያስተማረን ነው። የእሱን ታላቅ ሥራ ተባብረን እንድንሠራ ይፈልጋል። እንግዲያው በመካከላችን የሚፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ወይም በደልን ‘ይቅር ብለን’ ለማለፍና አንድነታችንን ጠብቀን ለመኖር ጥረት እናድርግ። (ምሳሌ 19:11ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ ከወንድሞቻችን ከመራቅ ይልቅ ከአምላክ ሕዝቦች መካከል እንዳንወጣና በይሖዋ ‘ዘላለማዊ ክንዶች’ ውስጥ ከአደጋ ተጠብቀን እንድንኖር አንዳችን ሌላውን መርዳት ይኖርብናል።—ዘዳ. 33:27

ለሰው ሁሉ ገር መሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛል

14. ሰይጣን ክፍፍል ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት መዋጋት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ሰይጣንና አጋንንቱ ምሥራቹን እንዳናሰራጭ እንቅፋት ለመፍጠር ሲሉ ደስተኛ በሆኑ ቤተሰቦችና ጉባኤዎች ውስጥ ያለውን ሰላም ለማደፍረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ክፍፍል መኖሩ ጎጂ እንደሆነ ስለሚያውቁ አለመግባባት ለመፍጠር ይጥራሉ። (ማቴ. 12:25) ሰይጣንና አጋንንቱ የሚያሳድሩትን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቋቋም እንድንችል ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን  ምክር መከተላችን ጠቃሚ ነው፦ “የጌታ ባሪያ ግን ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር . . . ሊሆን ይገባዋል።” (2 ጢሞ. 2:24) ትግል የምንገጥመው “ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን . . . ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር” መሆኑን አንዘንጋ። በዚህ ውጊያ አሸናፊ ለመሆን “የሰላምን ምሥራች እንደ ጫማ” መጫማትን ጨምሮ መንፈሳዊውን የጦር ትጥቅ መልበስ ይኖርብናል።—ኤፌ. 6:12-18

15. ከጉባኤ ውጪ ያሉ ሰዎች ጥቃት ሲሰነዝሩብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 ሰላማዊ የሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች ከጉባኤው ውጪ ባሉ የአምላክ ጠላቶች ከባድ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል። ከእነዚህ የአምላክ ጠላቶች አንዳንዶቹ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አካላዊ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ሌሎች ደግሞ በችሎት ፊት ወይም በመገናኛ ብዙኃን ስማችንን ያጠፋሉ። ኢየሱስ ይህን እንዲጠብቁ ለተከታዮቹ ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 5:11, 12) ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ፈጽሞ “በክፉ ፋንታ ክፉ” መመለስ የለብንም።—ሮም 12:17፤ 1 ጴጥሮስ 3:16ን አንብብ።

16, 17. አንድ ጉባኤ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመው?

16 ዲያብሎስ ምንም ዓይነት ጥቃት ቢሰነዝርብን ‘ክፉውን በመልካም በማሸነፍ’ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንችላለን። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በፓስፊክ ደሴቶች የሚገኝ አንድ ጉባኤ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር አንድ አዳራሽ ተከራይቶ ነበር። ይህን የተገነዘቡት በአካባቢው ያሉ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በዓሉ በሚከበርበት ሰዓት ምዕመኖቻቸው ለአምልኮ በዚያ አዳራሽ እንዲሰበሰቡ ጥሪ አደረጉ። የፖሊስ አዛዡ ግን የቤተ ክርስቲያኑ ኃላፊዎች አዳራሹን በዚያ ሰዓት ለይሖዋ ምሥክሮች መልቀቅ እንዳለባቸው አሳሰባቸው። ያም ሆኖ ግን መታሰቢያው የሚከበርበት ሰዓት ሲደርስ አዳራሹ በቤተ ክርስቲያኑ አባላት ጢም ብሎ የሞላ ሲሆን የአምልኮ ፕሮግራማቸውን ማካሄድ ጀመሩ።

17 ፖሊሶች አዳራሹን በኃይል ለማስለቀቅ እየተዘጋጁ እያለ የቤተ ክርስቲያኑ ፕሬዚዳንት ወደ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጠጋ ብሎ “በዚህ ምሽት ለማካሄድ ያሰባችሁት ልዩ ፕሮግራም አለ እንዴ?” በማለት ጠየቀው። ወንድም ስለ መታሰቢያው በዓል ሲነግረው ሰውየው “ኧረ! እኔ እኮ አላወቅኩም” በማለት መለሰ። በዚህ ጊዜ አንድ ፖሊስ “ዛሬ ጠዋት ነግረናችሁ የለም እንዴ?” በማለት ጮኸበት። የቤተ ክርስቲያኑ ፕሬዚዳንት ወደ ሽማግሌው ዞር ብሎ የተንኮል አስተያየት እያየው “ታዲያ አሁን ምን ልታደርጉ ነው? አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቷል። በፖሊሶች ተጠቅማችሁ ልታስወጡን ነው?” አለው። የቤተ ክርስቲያኑ ፕሬዚዳንት ሆን ብሎ ነገሮችን በማጣመም አሳዳጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ለማስመሰል ፈልጎ ነበር! ወንድሞች ምን ያደርጉ ይሆን?

18. ወንድሞች የሚያበሳጭ ድርጊት ቢፈጸምባቸውም ምን አደረጉ? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

18 ወንድሞች፣ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ለግማሽ ሰዓት ያህል አምልኳቸውን እንዲያከናውኑና እነሱ ከዚያ በኋላ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር እንደሚችሉ ሐሳብ አቀረቡ። የቤተ ክርስቲያኑ ሥነ ሥርዓት ከተባለው ሰዓት ያለፈ ቢሆንም ሰዎቹ ከወጡ በኋላ ወንድሞች መታሰቢያውን አከበሩ። በቀጣዩ ቀን መንግሥት ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቋመ። ኮሚቴው ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው የቤተ ክርስቲያኑ ፕሬዚዳንት እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች እንዳልሆኑ ለሕዝቡ እንዲያሳውቅ ቤተ ክርስቲያኑን አስገደደ። ከዚህም በተጨማሪ ኮሚቴው የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ በትዕግሥት በመያዛቸው አመሰገናቸው። ወንድሞች “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ጥረት ማድረጋቸው ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

19. ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዳን ሌላው ቁልፍ ምንድን ነው?

19 ከሌሎች ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ጠብቀን ለመኖር የሚረዳን ሌላው ቁልፍ ደግሞ ንግግራችን ለዛ ያለው እንዲሆን ማድረግ ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ለዛ ያለው ንግግር ሲባል ምን ማለት እንደሆነና እንዲህ ያለ አነጋገር ማዳበርም ሆነ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ‘ፍም መከመር’ የሚለው አገላለጽ በጥንት ዘመን ከነበረው ያልተጣራ ብረትን የማቅለጥ ዘዴ የተወሰደ ነው። ብረቱን ከቆሻሻው ለመለየት ከላይም ከታችም ፍም ይደረግበታል። እኛም በተመሳሳይ ደግነት የጎደለው ድርጊት ለሚፈጽሙ ሰዎች ደግነት ማሳየታችን አመለካከታቸው እንዲለወጥና መልካም ባሕርያቸው ጎልቶ እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ብስጩ የሆኑት ለምንድን ነው?

• ቁጣን መቆጣጠር ወይም አለመቆጣጠር የሚያስከትለውን ውጤት የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

• አንድ ክርስቲያን ቢጎዳን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

• ከጉባኤ ውጪ ያሉ ሰዎች ጥቃት ሲሰነዝሩብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስምዖንና ሌዊ በቁጣ ገንፍለው እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ሲመለሱ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደግነት ማሳየት የሌሎች አመለካከት እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል