በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር እረፍት አግኙ

መንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር እረፍት አግኙ

 መንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር እረፍት አግኙ

“ቀንበሬን ተሸከሙ፣ . . . ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።”—ማቴ. 11:29

1. አምላክ በሲና ተራራ ላይ ምን ዝግጅት አደረገ? እንዲህ ያደረገውስ ለምን ነበር?

በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤላውያን የተሰጣቸው የሕጉ ቃል ኪዳን ሳምንታዊውን የሰንበት ዝግጅትም ያካትት ነበር። ይሖዋ ቃል አቀባዩ በሆነው በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ብሔር እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠ፦ “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።” (ዘፀ. 23:12) አዎን፣ ይሖዋ በሕጉ ሥር ለነበሩት ሰዎች በማሰብ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት አንድ ‘የእረፍት’ ቀን እንዲኖር ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎ ነበር።

2. እስራኤላውያን ሰንበትን መጠበቃቸው ምን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል?

2 የሰንበት ዝግጅት የተደረገው ሕዝቡ በዚያ ቀን ዘና እንዲሉ ብቻ ነበር? አይደለም፤ ሰንበት እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ክፍል ነበር። እስራኤላውያን ሰንበትን መጠበቃቸው የቤተሰብ ራሶች “ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ” ቤተሰባቸውን ለማስተማር ጊዜ ይሰጣቸው ነበር። (ዘፍ. 18:19) ከዚህ በተጨማሪ ወዳጅ ዘመድ አንድ ላይ ተሰባስቦ ስለ ይሖዋ ሥራዎች በማሰብ አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ እንዲችል አጋጣሚ ይፈጥር ነበር። (ኢሳ. 58:13, 14) ከሁሉ በላይ ደግሞ የሰንበት ዝግጅት፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት አማካኝነት እውነተኛ እረፍት ለሚገኝበት ጊዜ ትንቢታዊ ጥላ ሆኖ አገልግሏል። (ሮም 8:21) ዛሬስ? የይሖዋን መንገዶች መጠበቅ የሚፈልጉ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን እረፍት ማግኘት የሚችሉት የትና እንዴት ነው?

ከእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ጊዜ በማሳለፍ እረፍት አግኙ

3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እርስ በርስ የሚደጋገፉት ምን በማድረግ ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን “የእውነት ዓምድና ድጋፍ” በማለት ገልጾታል። (1 ጢሞ. 3:15) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እርስ በርስ መበረታታታቸውና በፍቅር መተናነጻቸው ትልቅ ድጋፍ ሆኖላቸው ነበር። (ኤፌ. 4:11, 12, 16) ጳውሎስ በኤፌሶን በነበረበት ወቅት የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት ወደ እሱ በመምጣት አበረታተውት ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው በጳውሎስ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ልብ በል፦ “በእስጢፋናስና በፈርጡናጦስ እንዲሁም በአካይቆስ መኖር እጅግ ተደስቻለሁ፤ . . . እነሱ የእኔን . . . መንፈስ አድሰዋል” ብሏል። (1 ቆሮ. 16:17, 18) በተመሳሳይም ቲቶ በቆሮንቶስ ያሉትን ወንድሞች ለማገልገል ወደዚያ ሄዶ ከተመለሰ በኋላ ጳውሎስ “የቲቶ መንፈስ በእናንተ በሁላችሁ [ታድሷል]” በማለት ለጉባኤው ጽፎ ነበር። (2 ቆሮ. 7:13) ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምሥክሮች ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር የሚያንጽ ጊዜ በማሳለፍ እውነተኛ እረፍት ያገኛሉ።

4. የጉባኤ ስብሰባዎች የእረፍት ቦታ የሚሆኑልን እንዴት ነው?

4 የጉባኤ ስብሰባዎች ታላቅ ደስታ የሚገኝባቸው ቦታዎች እንደሆኑ በራስህ ሕይወት ሳትመለከት አትቀርም። ወደ እነዚህ ስብሰባዎች መሄዳችን አንዳችን በሌላው “እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” አጋጣሚ ይሰጠናል። (ሮም 1:12) ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ያለን ቅርበት፣ ከሰላምታ ያለፈ ትውውቅ በሌላቸውና አልፎ አልፎ ብቻ በሚገናኙ ሰዎች መካከል ከሚታየው ጥልቀት የሌለው ግንኙነት የተለየ ነው። ወንድሞቻችን ከልብ የምንወዳቸውና የምናከብራቸው እውነተኛ ወዳጆቻችን ናቸው። ከእነሱ ጋር ዘወትር አብረን መሰብሰባችን እጅግ ያስደስተናል እንዲሁም ያጽናናናል።—ፊል. 7

5. በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ አንዳችን ለሌላው የእረፍት ምንጭ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

5 እረፍት የምናገኝበት ሌላው መንገድ ደግሞ በየዓመቱ የምናደርጋቸው ትልልቅ ስብሰባዎች ናቸው። እነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች በአምላክ ቃል በመጽሐፍ  ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ የእውነት ውኃ የሚያቀርቡልን ከመሆኑም በላይ ለወንድሞቻችን ‘ልባችንን ወለል አድርገን ለመክፈት’ አጋጣሚ ይሰጡናል። (2 ቆሮ. 6:12, 13) ይሁን እንጂ ዓይናፋር ወይም ሌሎች ሰዎችን መቅረብ የሚከብደን ብንሆንስ? ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ለመተዋወቅ የሚያስችለን አንዱ መንገድ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ራሳችንን ለሥራ ማቅረብ ነው። አንዲት እህት በብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ በልዩ ልዩ ሥራ ስትካፈል ከቆየች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “በስብሰባው ላይ ከቤተሰቦቼና በጣት ከሚቆጠሩ ወዳጆቼ በስተቀር ብዙም የማውቀው ሰው አልነበረም። ሆኖም በጽዳት ሥራ ስካፈል ከበርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተዋወቅሁ! በጣም አስደሳች ጊዜ ነበር!”

6. ለእረፍት በምንወጣበት ጊዜ ፕሮግራሙ መንፈስን የሚያድስ እንዲሆን ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?

6 እስራኤላውያን በየዓመቱ በሦስት በዓላት ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። (ዘፀ. 34:23) አብዛኛውን ጊዜ ይህን ለማድረግ እርሻቸውንና ንግዳቸውን ትተው መሄድ እንዲሁም አቧራማ በሆነ መንገድ ላይ ለበርካታ ቀናት በእግር መጓዝ ነበረባቸው። ያም ሆኖ ወደ ቤተ መቅደሱ መሄዳቸው በዚያ ያሉት ሰዎች ‘ለይሖዋ ሲዘምሩ’ ለመመልከት አጋጣሚ ስለሚሰጣቸው “ታላቅ ደስታ” ያስገኝላቸው ነበር። (2 ዜና 30:21) በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችም ቤቴልን ማለትም በአቅራቢያቸው የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው በመጎብኘት ታላቅ ደስታ አግኝተዋል። እናንተስ በቤተሰብ ሆናችሁ እረፍት ለመውጣት በምታስቡበት ጊዜ ቤቴል መጎብኘትን በፕሮግራማችሁ ውስጥ ማካተት ትችላላችሁ?

7. (ሀ) ከቤተሰቦቻችንና ከወዳጆቻችን ጋር ሰብሰብ ብሎ መጫወት ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) እንዲህ ያሉ ወቅቶች የማይረሱና የሚያንጹ እንዲሆኑ ምን ማድረጉ የተሻለ ነው?

7 ከቤተሰቦቻችንና ከወዳጆቻችን ጋር ሰብሰብ ብሎ መጫወትም ሊያበረታታን ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም” በማለት ተናግሯል። (መክ. 2:24) ሰብሰብ ብሎ መጫወት ነፍሳችንን የሚያድስ ከመሆኑም ሌላ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ይበልጥ ለማወቅ ስለሚያስችለን በመካከላችን ያለውን ፍቅር ያጠናክርልናል። እንዲህ ያሉ ወቅቶች የማይረሱና የሚያንጹ እንዲሆኑ የተጋባዦቹ ቁጥር አነስ ያለ እንዲሆን ማድረግና  በተለይ አልኮል የሚቀርብ ከሆነ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረጉ በጣም የተሻለ ነው።

አገልግሎት እረፍት ያስገኛል

8, 9. (ሀ) የኢየሱስን መልእክት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ካወጧቸው ሕግጋት ጋር አነጻጽር። (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሰዎች ማካፈል እኛን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በአገልግሎቱ በቅንዓት ይካፈል የነበረ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱንም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። እንደሚከተለው በማለት መናገሩ ይህንን በግልጽ ያሳያል፦ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴ. 9:37, 38) ኢየሱስ ይሰብክ የነበረው መልእክት “ምሥራች” በመሆኑ በእውነትም እረፍት የሚሰጥ ነበር። (ማቴ. 4:23፤ 24:14) የኢየሱስ ትምህርት ፈሪሳውያን በርካታ ሕጎችን በማውጣት በሕዝቡ ላይ ከጫኑት ከባድ ሸክም ፈጽሞ የተለየ ነበር።—ማቴዎስ 23:4, 23, 24ን አንብብ።

9 የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች ስንናገር መንፈሳዊ እረፍት እንዲያገኙ እንረዳቸዋለን፤ እግረ መንገዳችንንም ውድ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይበልጥ እየተረዳንና እያደነቅን እንመጣለን። በእርግጥም መዝሙራዊው እንደሚከተለው ብሎ መናገሩ ትክክል ነው፦ “ሃሌ ሉያ። አምላካችንን በመዝሙር ማወደስ እንዴት መልካም ነው፤ እርሱን ማመስገን ደስ ያሰኛል፤ ይህ ተገቢም ነው።” (መዝ. 147:1) አንተስ በሰዎች ፊት ይሖዋን በማወደስ ደስታህ እንዲጨምር ማድረግ ትችላለህ?

10. በአገልግሎት ስኬታማ መሆናችን ሰዎች ምሥራቹን በመቀበላቸው ላይ የተመካ ነው? አብራራ።

10 እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ሰዎች ምሥራቹን ይቀበላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 18:1, 5-8ን አንብብ።) በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች ምሥራቹን ብዙም የማይቀበሉ ከሆነ አገልግሎትህን ማከናወንህ በሚያስገኘው መልካም ውጤት ላይ ለማተኮር ጥረት አድርግ። የይሖዋን ስም ለማወጅ ሁልጊዜ የምታደርገው ጥረት ከንቱ አለመሆኑን አስታውስ። (1 ቆሮ. 15:58) ከዚህም በላይ በአገልግሎት ስኬታማ መሆናችን የሚለካው ሰዎች ለምሥራቹ በሚሰጡት ምላሽ አይደለም። ይሖዋ፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 6:44

የቤተሰብ አምልኮ እረፍት ያስገኛል

11. ይሖዋ ለወላጆች ምን ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል? ይህንንስ ለመወጣት ምን ማድረግ ይችላሉ?

11 ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶቹ የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው። (ዘዳ. 11:18, 19) ወላጅ ከሆንክ አፍቃሪ ስለሆነው ሰማያዊ አባታችን ልጆችህን ለማስተማር ጊዜ መድበሃል? ይህን ትልቅ ኃላፊነት ለመወጣትና የቤተሰብህን ፍላጎት ለማሟላት እንድትችል ይሖዋ በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶች፣ በቪዲዮዎች እንዲሁም በድምፅ ብቻ በተቀረጹ ጽሑፎችና ድራማዎች አማካኝነት እረፍት ለማግኘት የሚረዳ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቧል።

12, 13. (ሀ) ቤተሰቦች ከቤተሰብ የአምልኮ ምሽት ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው እረፍት የሚገኝበት እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ከዚህም በተጨማሪ ታማኝና ልባም ባሪያ የቤተሰብ አምልኮ የሚደረግበት ምሽት እንዲኖር ዝግጅት አድርጓል። ይህ ዝግጅት ቤተሰቦች በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው የሚያጠኑበት ምሽት እንዲኖር ያስችላል። ብዙዎች ይህን ዝግጅት በቤተሰባቸው መካከል ያለው አንድነትና ፍቅር እንዲጨምር እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲጠናከር የሚረዳ ሆኖ አግኝተውታል። ይሁንና ወላጆች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው መንፈሳዊ እረፍት የሚያስገኝ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

13 የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራሙ አሰልቺና ድርቅ ያለ መሆን የለበትም። ደግሞም የምናመልከው ‘ደስተኛ የሆነውን አምላክ’ ሲሆን እሱም በአምልኳችን ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 1:11፤ ፊልጵ. 4:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት መንፈሳዊ ዕንቁዎች ላይ የምንወያይበት ተጨማሪ ምሽት ማግኘታችን በእርግጥም በረከት ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት ጊዜ ልጆቹ ትምህርቱን በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ የሚያደርጉ አቀራረቦችንና አዳዲስ ዘዴዎችን በመጠቀም ትምህርቱን በተለያዩ መንገዶች ማቅረብ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቤተሰብ ብራንደን የተባለው የአሥር ዓመት ልጃቸው “ይሖዋ፣ ሰይጣንን በእባብ የመሰለው ለምንድን ነው?” በሚል ርዕስ ምርምር አድርጎ እንዲያቀርብ አድርገው ነበር። ብራንደን እባብ ስለሚወድ ሰይጣን  በእባብ መመሰሉ ያበሳጨው ነበር። አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነቡበት ጊዜ በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በማከፋፈል ባለ ታሪኮቹን ወክለው እንዲያነቡት ያደርጋሉ፤ ወይም ደግሞ ታሪኩን በድራማ መልክ ይሠሩታል። የቤተሰብ አምልኮው በዚህ መልክ መደረጉ ፕሮግራሙ አስደሳች ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁም የሚሳተፉበት እንዲሆን ስለሚያስችል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ልባቸውን በሚነካ መንገድ ለማስተማር ያስችላል። *

ሸክም የሚሆኑባችሁን ነገሮች አስወግዱ

14, 15. (ሀ) በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ውጥረትና ስጋት እየጨመረ የመጣው እንዴት ነው? (ለ) ተጨማሪ ውጥረት የሚፈጥር ምን ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል?

14 በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ውጥረትና ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ሥራ አጥነትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ነክተዋል። ሥራ ያላቸው ሰዎችም እንኳ የሚያገኙት ደሞዝ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር የሚሸፍን ባለመሆኑ ገንዘባቸውን በቀዳዳ ኪስ ያስቀመጡት ያህል ሆኖባቸዋል። (ከሐጌ 1:4-6 ጋር አወዳድር።) ፖለቲከኞችና የአገር መሪዎች ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና ሌሎች የክፋት ድርጊቶችን ለማስወገድ የሚያደርጉት ጥረት ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል። ብዙ ሰዎች ያሉባቸው ድክመቶች በሚፈጥሩባቸው መጥፎ ስሜት ይሠቃያሉ።—መዝ. 38:4

15 እውነተኛ ክርስቲያኖችም ቢሆን የሰይጣን ሥርዓት ከሚያመጣቸው ችግሮችና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ነፃ አይደሉም። (1 ዮሐ. 5:19) አንዳንድ ጊዜ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ለመመላለስ ጥረት ሲያደርጉ የሚያጋጥማቸው ፈተና ተጨማሪ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል። ኢየሱስ “እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” ብሏል። (ዮሐ. 15:20) ይሁንና “ስደት ቢደርስብንም ያለ ረዳት ተጥለን አንቀርም።” (2 ቆሮ. 4:9) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

16. ደስተኛ ሆነን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል?

16 ኢየሱስ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” ብሏል። (ማቴ. 11:28) በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ሙሉ እምነት ስናሳድር በምሳሌያዊ ሁኔታ በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንሆናለን። እንዲህ ስናደርግ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነውን] ኃይል” እናገኛለን። (2 ቆሮ. 4:7) “ረዳት” የሆነው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እምነታችንን በእጅጉ የሚያጠናክርልን ሲሆን ይህም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎችና መከራዎች ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን ደስተኛ ሆነን ለመቀጠል እንድንችልም ይረዳናል።—ዮሐ. 14:26፤ ያዕ. 1:2-4

17, 18. (ሀ) የትኛው መንፈስ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል? (ለ) የግል ፍላጎታችንን በማርካት ላይ ትኩረት ማድረግ ምን ሊያስከትል ይችላል?

17 በዛሬው ጊዜ የምንኖር እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ የሚታየው ተድላን የማሳደድ አባዜ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይገባናል። (ኤፌሶን 2:2-5ን አንብብ።) እንዲህ ካላደረግን “የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” ወጥመድ ሊሆንብን ይችላል። (1 ዮሐ. 2:16) አሊያም ደግሞ የሥጋን ምኞት ማርካት እረፍት ያስገኛል የሚል የተሳሳተ እምነት ሊያድርብን ይችላል። (ሮም 8:6) ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ዕፅ በመውሰድ፣ የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ በመጠጣት፣ የብልግና ምስሎችን በመመልከት፣ አደገኛ በሆኑ ስፖርቶች በመካፈል ወይም መጥፎ እንደሆኑ ተደርገው በሚታዩ ሌሎች ተግባራት በመካፈል ደስታ ለማግኘት ይጥራሉ። ሰይጣን የሚጠቀምባቸው “መሠሪ ዘዴዎች” አንድን ሰው ለማሳሳት ማለትም ደስታ ያስገኛሉ ለሚባሉ ነገሮች ያለው አመለካከት እንዲዛባ ለማድረግ ታልመው የተዘጋጁ ናቸው።—ኤፌ. 6:11

 18 እውነት ነው፣ በልኩ እስከተደረገ ድረስ መብላት፣ መጠጣትና ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች መካፈል ምንም ስህተት የለውም። ይሁንና እነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዙ አንፈልግም። በተለይ ከምንኖርበት ጊዜ አንጻር ሚዛናችንን መጠበቃችንና ራሳችንን መግዛታችን በጣም አስፈላጊ ነው። የግል ፍላጎታችንን ለማርካት የምናደርገው ሩጫ ሸክም ሊሆንብንና “ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ [ያለንን] ትክክለኛ እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች” እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል።—2 ጴጥ. 1:8

19, 20. እውነተኛ እረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

19 ከይሖዋ መመሪያዎች ጋር ተስማምተን መኖር ስንጀምር ይህ ዓለም የሚሰጠው ማንኛውም ደስታ ጊዜያዊ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሙሴ ይህንን ተገንዝቦ ነበር፤ እኛም የእሱን አርዓያ እንከተል። (ዕብ. 11:25) ዘላቂ ብሎም ጥልቅ የሆነ ደስታና እርካታ ማግኘት የሚያስችለን እውነተኛ እረፍት የሚገኘው በሰማይ ያለውን የአባታችንን ፈቃድ በማድረግ ነው።—ማቴ. 5:6

20 መንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር እረፍት ማግኘታችንን እንቀጥል። እንዲህ በማድረግ “አምላካዊ ያልሆነ ምግባርንና ዓለማዊ ምኞቶችን [እንክዳለን]፤ . . . በዚህ ሁኔታ አስደሳች የሆነውን ተስፋና የታላቁን አምላክ እንዲሁም የአዳኛችንን የክርስቶስ ኢየሱስን ክብራማ መገለጥ እንጠባበቃለን።” (ቲቶ 2:12, 13) እንግዲያው ለኢየሱስ ሥልጣንና መመሪያ ራሳችንን በማስገዛት ምንጊዜም በእሱ ቀንበር ሥር ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በዚህ መንገድ እውነተኛ ደስታና እረፍት እናገኛለን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 የቤተሰብ ጥናት አስደሳችና ትምህርት ሰጪ እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የጥቅምት 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-31 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች እረፍት ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

• አገልግሎታችን ለእኛም ሆነ ለምንሰብክላቸው ሰዎች እረፍት የሚያስገኘው እንዴት ነው?

• የቤተሰብ ራሶች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው እረፍት የሚያስገኝ እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

• መንፈሳዊ ነገር ላይ እንዳናተኩር የትኞቹ ነገሮች ሸክም ሊሆኑብን ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የኢየሱስን ቀንበር ስንሸከም በብዙ መንገዶች እረፍት እናገኛለን