በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

 የአንባቢያን ጥያቄዎች

ይሖዋ ጣዖት አምልኮን የሚያወግዝ ሆኖ ሳለ አሮን የወርቅ ጥጃውን በመሥራቱ ያልቀጣው ለምንድን ነው?

በዘፀአት ምዕራፍ 32 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አሮን የወርቅ ጥጃውን ሲሠራ አምላክ ጣዖት አምልኮን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ ጥሷል። (ዘፀ. 20:3-5) በዚህም ምክንያት ይሖዋ “አሮንን ሊያጠፋው ክፉኛ ተቈጥቶ ነበር፤ በዚያን ጊዜ [ሙሴ] ለአሮንም [ጸለየ]።” (ዘዳ. 9:19, 20) ጻድቅ ሰው የነበረው ሙሴ ለአሮን ያቀረበው ምልጃ “ታላቅ ኃይል” ነበረው? (ያዕ. 5:16) አዎን፣ ይሖዋ የሙሴን ጸሎት ሰምቶ አሮንን ሳይቀጣው የቀረው ሙሴ ምልጃ በማቅረቡ እንዲሁም ቢያንስ በሌሎች ሁለት ምክንያቶች ሳይሆን አይቀርም።

አንዱ ምክንያት አሮን ካስመዘገበው የታማኝነት ታሪክ ጋር ግንኙነት እንዳለው ከሁኔታው መገንዘብ ይቻላል። ሙሴ በፈርዖን ፊት እንዲቀርብና እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ እንዲያወጣ በተላከ ጊዜ አሮን ከሙሴ ጋር በመሄድ እሱን ወክሎ እንዲናገር ይሖዋ ሾሞት ነበር። (ዘፀ. 4:10-16) እነዚህ ሁለት ሰዎች የፈርዖንን ልበ ደንዳናነት መጋፈጥ ቢጠይቅባቸውም በፊቱ በተደጋጋሚ ጊዜያት በታዛዥነት ቀርበዋል። አሮን በግብፅ ሳለ ይሖዋን በጽናት በማገልገል የታማኝነት ታሪክ አስመዝግቧል።—ዘፀ. 4:21

ሁለተኛውን ምክንያት ለማወቅ አሮን የወርቅ ጥጃውን እንዲሠራ ያነሳሳው ምን እንደሆነ እንመልከት። ሙሴ ለ40 ቀናት በሲና ተራራ ላይ ቆይቶ ነበር። “ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ እንደ ቆየ ባዩ ጊዜ” አሮንን ጣዖት እንዲሠራላቸው አግባቡት። ስለዚህ አሮን ጥያቄያቸውን በመቀበል አንድ የወርቅ ጥጃ ሠራላቸው። (ዘፀ. 32:1-6) ይሁን እንጂ አሮን ከዚያ በኋላ የወሰዳቸው እርምጃዎች እንደሚያሳዩት የጣዖት አምልኮውን አላመነበትም ነበር። በግልጽ ማየት እንደምንችለው ጣዖቱን የሠራው በተጽዕኗቸው በመሸነፉ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ በጣዖት አምላኪዎቹ ላይ እርምጃ በወሰደበት ወቅት አሮንን ጨምሮ ሁሉም የሌዊ ቤተሰቦች በድፍረት ከይሖዋ ጎን ቆመዋል። በጣዖት አምልኮው ግንባር ቀደም የሆኑት ሦስት ሺህ ጣዖት አምላኪዎች ግን በሰይፍ ተገድለዋል።—ዘፀ. 32:25-29

ከዚያ በኋላ ሙሴ ለሕዝቡ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል” በማለት ነገራቸው። (ዘፀ. 32:30) በመሆኑም ለተሠራው ጥፋት በመጠኑም ቢሆን ተጠያቂ የሚሆነው አሮን ብቻ አልነበረም። እሱም ሆነ ሕዝቡ ከይሖዋ ታላቅ ምሕረት ተጠቃሚዎች ነበሩ።

ከወርቁ ጥጃ ጋር በተያያዘ የተነሳው ችግር እልባት ካገኘ በኋላ ይሖዋ አሮን ሊቀ ካህናት ሆኖ እንዲሾም ትእዛዝ ሰጠ። አምላክ “አሮንን የተቀደሰውን ልብስ አልብሰው፤ ካህን ሆኖ ያገለግለኝ ዘንድ ቅባው፤ ቀድሰውም” ብሎ ለሙሴ ነገረው። (ዘፀ. 40:12, 13) በግልጽ ማየት እንደምንችለው አሮን ስህተት ቢሠራም ይሖዋ ይቅር ብሎታል። በእርግጥም አሮን እውነተኛውን አምልኮ ከልቡ የሚደግፍ ታማኝ ሰው እንጂ ጣዖትን የሚያመልክ ዓመፀኛ አልነበረም።