በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

 ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

“ለሰዎች እንድንሰብክና የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ አዘዘን።”—ሥራ 10:42 NW

1. ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ቤት ንግግር ባቀረበበት ወቅት ጎላ አድርጎ እንደገለጸው ለሐዋርያት ምን ተልእኮ ተሰጥቷቸው ነበር?

ጣሊያናዊው የመቶ አለቃ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን አሰባስቦ የጴጥሮስን መምጣት እየጠበቀ ነበር፤ በዚያ ወቅት የተፈጸመው ነገር አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ የጎላ ለውጥ አምጥቷል። ፈሪሃ አምላክ የነበረው ይህ ጣሊያናዊ ቆርኔሌዎስ ይባላል። ጴጥሮስ፣ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ‘ለሰዎች እንዲሰብኩና የተሟላ ምሥክርነት እንዲሰጡ’ እንደታዘዙ ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ነገራቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ ወቅት የሰጠው ምሥክርነት ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ያልተገረዙ አሕዛብ የአምላክን መንፈስ ተቀበሉ፣ ተጠመቁ፤ እንዲሁም ወደፊት ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ነገሥታት የመሆን አጋጣሚ ተከፈተላቸው። ጴጥሮስ የተሟላ ምሥክርነት መስጠቱ እንዴት ያለ ግሩም ውጤት አስገኝቷል!—ሥራ 10:22, 34-48

2. ምሥራቹን የመመሥከሩ ተልእኮ የተሰጠው ለ12ቱ ሐዋርያው ብቻ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

2 ይህ የሆነው በ36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ክርስቲያኖችን ክፉኛ ያሳድድ የነበረ አንድ ሰው፣ ከላይ የተገለጸው ሁኔታ ከመፈጸሙ ከሁለት ዓመት በፊት ሕይወቱን የሚለውጥ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። የጠርሴሱ ሳውል ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ ኢየሱስ ተገለጠለትና “ወደ ከተማይቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል” አለው። ሳውል “በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት” እንደሚመሠክር ኢየሱስ ለደቀ መዝሙሩ ሐናንያ አረጋገጠለት። (የሐዋርያት ሥራ 9:3-6, 13-20ን አንብብ።) ሐናንያ፣ ሳውልን ሲያገኘው እንዲህ አለው፦ “የአባቶቻችን አምላክ . . . መርጦሃል፤ . . . በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆነዋለህና።” (ሥራ 22:12-16) በኋላ ላይ ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው ሳውል ምሥክር እንዲሆን የተሰጠውን ተልእኮ ምን ያህል በቁም ነገር ተመልክቶት ነበር?

ምሥራቹን በሚገባ መሥክሯል!

3. (ሀ) በየትኛው ዘገባ ላይ እናተኩራለን? (ለ) በኤፌሶን የነበሩት ሽማግሌዎች ለጳውሎስ መልእክት ምን ምላሽ ሰጡ? ምን ጥሩ ምሳሌስ ትተውልናል?

3 ጳውሎስ ከዚያ በኋላ ያከናወናቸውን ነገሮች በሙሉ በዝርዝር ማጥናት በጣም አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፤ አሁን ግን በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘውና ጳውሎስ በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ በሰጠው ንግግር ላይ ትኩረት እናድርግ። ሐዋርያው ይህንን ንግግር ያቀረበው ሦስተኛውን የሚስዮናዊነት ጉዞውን ወደማጠናቀቁ በተቃረበበት ጊዜ ነበር። በኤጂያን ባሕር ላይ ወደምትገኘው ወደ ሚሊጢን ወደብ ሲደርስ በኤፌሶን የነበሩትን የጉባኤ ሽማግሌዎች አስጠራ። ኤፌሶን የምትገኘው 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ቢሆንም መንገዱ ጠመዝማዛ በመሆኑ ጉዞው የበለጠ ጊዜ ይወስድ ነበር። በኤፌሶን የሚገኙት የጉባኤ ሽማግሌዎች የጳውሎስ መልእክት ሲደርሳቸው ምንኛ ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ። (ከምሳሌ 10:28 የ1980 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ያም  ቢሆን ወደ ሚሊጢን ለመጓዝ አንዳንድ ዝግጅቶች ማድረግ ነበረባቸው። አንዳንዶቹ አሠሪያቸውን ፈቃድ መጠየቅ ወይም ሱቆቻቸውን መዝጋት አስፈልጓቸው ይሆን? በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖችም በዓመት አንድ ጊዜ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከሚቀርቡት ፕሮግራሞች የትኛውም እንዳያመልጣቸው ሲሉ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ።

4. ጳውሎስ በኤፌሶን በቆየባቸው ጥቂት ዓመታት ምን የማድረግ ልማድ ነበረው?

4 በኤፌሶን የነበሩት የጉባኤ ሽማግሌዎች ሚሊጢን እስኪደርሱ ድረስ በነበሩት ሦስት ወይም አራት ቀናት ጳውሎስ ምን ሲሠራ የቆየ ይመስልሃል? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? (ከሐዋርያት ሥራ 17:16, 17 ጋር አወዳድር።) ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት የጉባኤ ሽማግሌዎች የተናገረው ሐሳብ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ያስችለናል። ከዚያ ቀደም በኤፌሶን በነበረበት ጊዜ ያከናወነውን ነገር ጨምሮ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ለዓመታት ይከተለው የነበረውን ልማድ ነግሯቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:18-21ን በNW አንብብ።) ጳውሎስ እንዲህ ሲል በልበ ሙሉነት ተናግሯል፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ . . . በሚገባ መሥክሬላቸዋለሁ።” በእርግጥም ጳውሎስ ኢየሱስ የሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። ታዲያ በኤፌሶን ይህን ተልእኮውን የተወጣው እንዴት ነበር? አንደኛው መንገድ በርካታ አይሁዳውያንን ሊያገኝ ወደሚችልባቸው ቦታዎች ሄዶ በመመሥከር ነበር። ጳውሎስ ከ52-55 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ በኤፌሶን በነበረበት ወቅት በምኩራብ ውስጥ ‘እየተነጋገረ ያሳምናቸው’ እንደነበረ ሉቃስ ዘግቧል። አይሁዶች “ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች” ሳይሆኑ በቀሩበት ጊዜ ጳውሎስ በከተማው ውስጥ በሌላ ቦታ መስበኩን ቀጥሏል። በዚህ መንገድ በዚያ ትልቅ ከተማ ውስጥ ለሚገኙት አይሁዶችና ግሪኮች መሥክሯል።—ሥራ 19:1, 8, 9

5, 6. ጳውሎስ ከቤት ወደ ቤት የሰበከው አማኝ ላልሆኑ ሰዎች እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

5 ወደ ክርስትና ከመጡት ሰዎች አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ የጉባኤ ሽማግሌዎች መሆን የቻሉ ሲሆን ጳውሎስ በሚሊጢን ያነጋገረው እነሱን ነበር። ሐዋርያው እንደሚከተለው በማለት ለስብከት የተጠቀመበትን ዘዴ አስታውሷቸዋል፦ “በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም።” በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎች፣ ጳውሎስ እዚህ ላይ የገለጸው አማኝ ለሆኑ ሰዎች እረኝነት ስለማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ‘በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር ማስተማር’ የሚለው አገላለጽ በዋነኝነት የሚያመለክተው አማኝ ላልሆኑ ሰዎች መመሥከርን ነው። ጳውሎስ ቀጥሎ ከተናገረው ሐሳብ ይህንን በግልጽ መረዳት ይቻላል፤ “በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ፣ ለአይሁድም ለግሪክ ሰዎችም” እንደመሠከረ ገልጿል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ የመሠከረው ንስሐ መግባትና በኢየሱስ ማመን ለሚያስፈልጋቸው አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ነው።—ሥራ 20:20, 21

6 ስለ ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሰፊ መግለጫ የሰጡ አንድ ምሑር የሐዋርያት ሥራ 20:20⁠ን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “ጳውሎስ በኤፌሶን ባሳለፋቸው ሦስት ዓመታት እያንዳንዱን ቤት አንኳኩቷል ወይም ቢያንስ ለሁሉም ሰው መሥክሯል። (ቁጥር 26) ከቤት ወደ ቤትም ሆነ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለመመሥከር መሠረት የሚሆነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ይህ ነው።” እኚህ ምሑር  እንደገለጹት ጳውሎስ ቃል በቃል እያንዳንዱን ቤት አንኳኩቶ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩት ሽማግሌዎች፣ ምሥራቹን የሰበከበትን መንገድና ስብከቱ ያስገኘውን ውጤት እንዲያስታውሱ ፈልጎ ነበር። ሉቃስ “በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ” በማለት ዘግቧል። (ሥራ 19:10) ይሁን እንጂ በእስያ የሚኖሩ “ሰዎች ሁሉ” ምሥራቹን ሊሰሙ የቻሉት እንዴት ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ ስለምንሰጠው ምሥክርነት ምን ይጠቁመናል?

7. ጳውሎስ በቀጥታ ከመሠከረላቸው ሰዎች በተጨማሪ ሌሎችም መልእክቱን ሰምተው ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

7 ጳውሎስ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎችና ከቤት ወደ ቤት በመስበኩ ብዙ ሰዎች መልእክቱን መስማት ችለዋል። መልእክቱን የሰሙት ሰዎች ሁሉ በኤፌሶን የቆዩ ይመስልሃል? ወይስ አንዳንዶች ለመነገድ፣ ከዘመዶቻቸው ጋር ለመሆን ወይም በትልቅ ከተማ ውስጥ ያለውን ግርግር የበዛበት ሕይወት ትተው ጸጥታ በሰፈነበት አካባቢ ለመኖር ሲሉ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ይሆን? እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ኤፌሶንን ለቅቀው ሊሆን ይችላል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ከላይ ከተጠቀሱት ጋር በሚመሳሰሉ ምክንያቶች የተነሳ ወደ ሌሎች ቦታዎች ይሄዳሉ፤ ምናልባት አንተም እንደዚህ አድርገህ ይሆናል። በጥንት ዘመን ሰዎች ለማኅበራዊ ጉዳዮች ወይም ለንግድ ሲሉ ወደ ኤፌሶን ይመጡ ነበር። እነዚህ ሰዎች በኤፌሶን ቆይታቸው ከጳውሎስ ጋር ተገናኝተው አሊያም ሲመሠክር ሰምተው ሊሆን ይችላል። ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ምን ያደርጉ ይሆን? እውነትን የተቀበሉት ሰዎች ምሥራቹን መመሥከራቸው አይቀርም። ሌሎች ደግሞ አማኞች ባይሆኑም እንኳ በኤፌሶን በነበሩበት ወቅት ስለሰሙት ነገር ይናገሩ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ዘመዶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው ወይም ደንበኞቻቸው እውነትን የሰሙ ሲሆን አንዳንዶቹም ተቀብለውት ይሆናል። (ከማርቆስ 5:14 ጋር አወዳድር።) ይህ ሁኔታ አንተም ምሥራቹን በሚገባ መመሥከርህ ስለሚያስገኘው ውጤት ምን ይጠቁማል?

8. በመላው የእስያ አውራጃ የሚኖሩ ሰዎች እውነትን የሰሙት እንዴት ሊሆን ይችላል?

8 ጳውሎስ ቀደም ሲል በኤፌሶን ስላከናወነው አገልግሎት ሲጽፍ ‘ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶለት እንደነበር’ ገልጿል። (1 ቆሮ. 16:8, 9) ጳውሎስ የተከፈተለት በር ምን ነበር? በሩ የተከፈተለትስ እንዴት ነበር? ሐዋርያው በኤፌሶን መስበኩን በመቀጠሉ ምሥራቹ ሊሰራጭ ችሏል። ከኤፌሶን ራቅ ብለው የሚገኙትን ቈላስይስ፣ ሎዶቅያና ሂራጶሊስ የተባሉትን ሦስት ከተሞች እንመልከት። ጳውሎስ ወደ እነዚህ ከተሞች ጨርሶ ባይሄድም በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ምሥራቹ ደርሷቸዋል። ክርስቲያኑ ኤጳፍራ የተገኘው ከእነዚህ አካባቢዎች ነው። (ቈላ. 2:1፤ 4:12, 13) ኤጳፍራ፣ ወደ ክርስትና የመጣው ጳውሎስ በኤፌሶን ሲመሠክር ሰምቶ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ አይናገርም። ይሁንና ኤጳፍራ በሚኖርበት አካባቢ እውነትን የሰበከው ጳውሎስን ወክሎ ሳይሆን አይቀርም። (ቈላ. 1:7) የክርስትና መልእክት እንደ ፊላደልፊያ፣ ሰርዴስና ትያጥሮን ወዳሉት ከተሞች  የደረሰውም ጳውሎስ በኤፌሶን ይመሰክር በነበረባቸው ዓመታት ሊሆን ይችላል።

9. (ሀ) ጳውሎስ ምን የማድረግ ልባዊ ፍላጎት ነበረው? (ለ) የ2009 የዓመት ጥቅስ ምን የሚል ነው?

9 በዚህም የተነሳ በኤፌሶን የነበሩት የጉባኤ ሽማግሌዎች ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ሐሳብ ለመቀበል የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበራቸው፦ “ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም የአምላክን ጸጋ ምሥራች በሚገባ ለመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ለነፍሴ ምንም አልሳሳም።” የ2009 የዓመት ጥቅስ ‘ምሥራቹን በሚገባ መሥክሩ’ የሚል ሲሆን ለተግባር የሚያነሳሳው ይህ መልእክት የተወሰደው ጳውሎስ ከተናገረው ሐሳብ ላይ ነው።—ሥራ 20:24 NW

በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን በሚገባ መመሥከር

10. የተሟላ ምሥክርነት የመስጠቱ ተልእኮ እኛንም እንደሚጨምር እንዴት እናውቃለን?

10 ምሥራቹን ‘ለሰዎች እንዲሰብኩና የተሟላ ምሥክርነት እንዲሰጡ’ የታዘዙት ሐዋርያት ብቻ አይደሉም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በገሊላ ለተሰበሰቡት 500 የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” ኢየሱስ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት የተናገረው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ከላይ ያለው ትእዛዝ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችን በሙሉ ይመለከታል።—ማቴ. 28:19, 20

11. የይሖዋ ምሥክሮች የትኛውን ጠቃሚ ሥራ በመሥራት ተለይተው ይታወቃሉ?

11 ቀናተኛ ክርስቲያኖች ‘ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር’ ጥረት በማድረግ ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ መታዘዛቸውን ቀጥለዋል። ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት ሽማግሌዎች እንደገለጸው እንዲህ ለማድረግ የሚያስችላቸው ዋነኛ መንገድ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ነው። ዴቪድ ስቴዋርት ጁኒየር የተባሉ ሰው ውጤታማ የሆነ የሚስዮናዊነት ሥራን በተመለከተ በ2007 ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ግለሰቦች እምነታቸውን ለሌሎች እንዴት ማካፈል እንደሚችሉ የሚያስተምሩበት መንገድ፣ [ከመድረክ ሆኖ] ግልጽ ያልሆነና በተግባር ያልተደገፈ ትምህርት ከመስጠት ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነ ታይቷል። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን ለሌሎች ማካፈል በጣም የሚወዱት ሥራ ነው።” ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? ዴቪድ ስቴዋርት ጁኒየር እንዲህ ብለዋል፦ “በ1999 በሁለት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ዋና ከተሞች ውስጥ ባደረግሁት ጥናት ከተካፈሉት ሰዎች መካከል . . . ‘የሞርሞን’ ሚስዮናውያን አነጋግረዋቸው እንደሚያውቁ የገለጹት ከ2 እስከ 4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዳነጋገሯቸው የገለጹም አሉ።”

12. (ሀ) በክልላችን ውስጥ “በተደጋጋሚ ጊዜያት” ከቤት ወደ ቤት የምንሄደው ለምንድን ነው? (ለ) ለመልእክታችን የነበረውን አመለካከት ስለለወጠ ሰው የሚገልጽ የምታውቀው ተሞክሮ ካለ ተናገር።

12 አንተ ባለህበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟቸው ይሆናል። በዚህ ረገድ አንተም ያደረግከው አስተዋጽኦ ሊኖር ይችላል። ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ሰዎችን “በግለሰብ ደረጃ” ስታነጋግር ወንዶች፣ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶች ያጋጥሙሃል። አንዳንዶች “በተደጋጋሚ ጊዜያት” ምሥራቹን ቢሰሙም መልእክቱን አልተቀበሉ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ሐሳብ ስታካፍላቸው ለአፍታ ያህል ቆም ብለው ሰምተውህ ሊሆን ይችላል። ለአንዳንድ ሰዎች ጥሩ ምሥክርነት መስጠት የቻልክ ሲሆን እነሱም መልእክቱን ተቀብለው ይሆናል። ‘ምሥራቹን በሚገባ ስንመሠክር’ እነዚህ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። “በተደጋጋሚ ጊዜያት” ምሥራቹን ቢሰሙም እምብዛም ፍላጎት ያልነበራቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ እንደተለወጡ የሚያሳዩ በርካታ ተሞክሮዎች እንዳሉ ሳታውቅ አትቀርም። በራሳቸው ወይም በሚወዱት ሰው ላይ የደረሰ አንድ ነገር አመለካከታቸው እንዲለወጥና እውነትን እንዲቀበሉ አድርጓቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆነዋል። እንግዲያው ብዙዎች መልእክቱን ባይቀበሉህም ተስፋ አትቁረጥ። ሁሉም ሰው እውነትን ይቀበላል ብለን አንጠብቅም። አምላክ ግን በትጋትና በቅንዓት ምሥራቹን በሚገባ መመሥከራችንን እንድንቀጥል ይጠብቅብናል።

 እኛ የማናውቀው ውጤት

13. ምሥራቹን መመሥከራችን እኛ የማናውቀው ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው እንዴት ነው?

13 ጳውሎስ ባከናወነው አገልግሎት ክርስቲያኖች የሆኑት እሱ በቀጥታ የረዳቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ እኛ ከምናከናውነው አገልግሎት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አዘውትረን በመካፈል በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለመመሥከር ጥረት እናደርጋለን። ለጎረቤቶቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ለሚማሩ እንዲሁም ለዘመዶቻችን ምሥራቹን እንናገራለን። ይህ ሥራችን የሚያስገኘውን ውጤት በሙሉ ማወቅ እንችላለን? አንዳንድ ጊዜ ወዲያውኑ ጥሩ ውጤት እናገኝ ይሆናል። በሌላ ጊዜ ደግሞ የእውነት ዘር በአፈር በተመሰለው የግለሰቦች ልብ ውስጥ እድገት ሳያደርግ ለተወሰነ ጊዜ ይቆይ ይሆናል፤ ከጊዜ በኋላ ግን ዘሩ ሥር ሰድዶ ሊያድግ ይችላል። ይህ ባይሆን እንኳ ያነጋገርናቸው ሰዎች፣ የነገርናቸውን መልእክትና እምነታችንን እንዲሁም የምናደርጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ለሌሎች ማውራታቸው አይቀርም። እነዚህ ሰዎች ሳያውቁት የእውነት ዘር ለማደግ በሚያስችለው ጥሩ አፈር ላይ እንዲወድቅ ያደርጉ ይሆናል።

14, 15. አንድ ወንድም የሰጠው ምሥክርነት ምን ውጤት አስገኝቷል?

14 በፍሎሪዳ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩትን ራያንንና ባለቤቱን ማንዲን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ራያን አብሮት ለሚሠራ ሰው መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሠከረለት። የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነው ይህ ሰው የራያን አለባበስና አነጋገር ያስደንቀው ነበር። ራያን ስለ ትንሣኤና ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ከዚህ ሰው ጋር ይወያይ ነበር። በጥር ወር ላይ ይህ ሰው፣ ባለቤቱን ጆዲን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የምታውቀው ነገር እንዳለ ጠየቃት። ባለቤቱ፣ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረች ሲሆን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የምታውቀው ነገር ቢኖር “ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበካቸውን” ብቻ እንደሆነ ነገረችው። ከዚያ በኋላ ጆዲ በኢንተርኔት “ጀሆቫስ ዊትነስስ (የይሖዋ ምሥክሮች)” በሚል ርዕስ ምርምር ማድረግ የጀመረች ሲሆን ይህም ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ድረ ገጽ (www.watchtower.org) መራት። ጆዲ ለተወሰኑ ወራት ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ትኩረቷን የሳቡትን አንዳንድ ርዕሶች ከዚህ ድረ ገጽ ላይ አነበበች።

15 በነርስነት ሞያ ላይ የተሰማሩት ጆዲና ማንዲ ከጊዜ በኋላ ተዋወቁ። ማንዲ፣ ጆዲ ያነሳቻቸውን ጥያቄዎች በደስታ መለሰችላት። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ጆዲ እንደተናገረችው “ከአዳም እስከ አርማጌዶን” ባሉት ርዕሶች ላይ ተወያዩ። ጆዲ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። ብዙም ሳይቆይ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። በጥቅምት ወር ጆዲ ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች፤ በየካቲት ወር ደግሞ ተጠመቀች። ጆዲ “እውነትን በማወቄ ሕይወቴ በጣም የሚያስደስትና የሚያረካ ሆኗል” ስትል ጽፋለች።

16. በፍሎሪዳ የሚኖረው ወንድም ያገኘው ተሞክሮ ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ስለምናደርገው ጥረት ምን ይጠቁመናል?

16 ራያን ለአንድ ሰው መመሥከሩ ሌላ ሰው ወደ እውነት እንዲመጣ ሊያደርግ እንደሚችል ፈጽሞ አላሰበም ነበር። በእርግጥ ራያን “በሚገባ ለመመሥከር” ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉ ያስገኘውን ውጤት ማወቅ ችሏል። በሌላ በኩል ግን ከቤት ወደ ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥራቹን መስበክህ አንተ ሳታውቀው ሌሎች መልእክቱን የሚሰሙበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ጳውሎስ ያከናወነው የስብከት ሥራ “በእስያ አውራጃ” ያስገኘውን ውጤት በሙሉ እንዳላወቀ ሁሉ አንተም ምሥራቹን በሚገባ መመሥከርህ የሚያስገኘውን ጥሩ ውጤት በሙሉ ላታውቅ ትችላለህ። (የሐዋርያት ሥራ 23:11ንና 28:23⁠ን አንብብ።) ሆኖም እንዲህ ማድረግህን መቀጠልህ ምንኛ አስፈላጊ ነው!

17. በ2009 ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

17 ከቤት ወደ ቤትና በሌሎች መንገዶች እንድንመሠክር የተሰጠንን ተልእኮ በ2009 ሁላችንም በቁም ነገር እንመልከተው። እንዲህ ካደረግን እኛም እንደ ጳውሎስ እንደሚከተለው ብለን መናገር እንችላለን፦ “ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም የአምላክን ጸጋ ምሥራች በሚገባ ለመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ለነፍሴ ምንም አልሳሳም።”

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስ እንዲሁም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ምሥራቹን በሚገባ የሰበኩት እንዴት ነበር?

• የስብከት ሥራችን እኛ ከምናውቀው የበለጠ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

• የ2009 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህስ ተስማሚ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ2009 የዓመት ጥቅስ ‘ምሥራቹን በሚገባ መሥክሩ’ የሚል ነው።—የሐዋርያት ሥራ 20:24 NW

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኤፌሶን የነበሩት የጉባኤ ሽማግሌዎች ጳውሎስ ከቤት ወደ ቤት የመመሥከር ልማድ እንደነበረው ያውቁ ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥራቹን በሚገባ መመሥከርህ መልእክቱን በስፋት በማዳረስ ረገድ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል?