በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጤናን በመንከባከብ ረገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት ይኑራችሁ

ጤናን በመንከባከብ ረገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት ይኑራችሁ

 ጤናን በመንከባከብ ረገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት ይኑራችሁ

“አንተም ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህን . . . በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።”—ማር. 12:30

1. አምላክ ለሰው ዘር የነበረው የመጀመሪያው ዓላማ ምን ነበር?

ይሖዋ አምላክ ሰብዓዊ ፍጡሮቹ እንዲታመሙና እንዲሞቱ ዓላማው አልነበረም። አዳምንና ሔዋንን በዔድን የአትክልት ቦታ ማለትም በደስታ ገነት ውስጥ ያስቀመጣቸው ለ70 ወይም ለ80 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ‘እንዲያለሟትና እየተንከባከቡ እንዲጠብቋት’ ነበር። (ዘፍ. 2:8, 15፤ መዝ. 90:10) እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ቢዘልቁና ለሉዓላዊነቱ በፍቅር ቢገዙ ኖሮ ጤና ማጣትንም ሆነ እርጅና የሚያስከትለውን ጉስቁልና እንዲሁም ሞትን ባላዩ ነበር።

2, 3. (ሀ) በመክብብ መጽሐፍ ላይ እርጅና እንዴት ተደርጎ ተገልጿል? (ለ) ለአዳማዊው ሞት ተጠያቂ የሚሆነው ማን ነው? ከአዳማዊው ሞት ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚወገዱትስ እንዴት ነው?

2 መክብብ ምዕራፍ 12 ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ከእርጅና ጋር ተያይዞ ስለሚመጣው “የጭንቀት ጊዜ” ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። (መክብብ 12:1-7ን አንብብ።) ሽበት ‘ከለውዝ ዛፍ’ አበባ ጋር ተመሳስሏል። እግሮች፣ እየጎበጡና እየተብረከረኩ ከመጡ ‘ብርቱ’ ሰዎች ጋር ተመሳስለዋል። የዓይን መዳከም፣ ብርሃን እናያለን ብለው ወደ መስኮት ሲመጡ ከጨለማ ሌላ ምንም ነገር ባላገኙ ወይዛዝርት መመሰሉ ትክክለኛ መግለጫ ነው። የረገፉ ጥርሶች ‘ጥቂት በመሆናቸው ምክንያት መፍጨት ባቆሙ’ ሴቶች ተመስለዋል።

3 የሚብረከረኩ እግሮች፣ የደከሙ ዓይኖችና ጥርስ አልባ የሆኑ ድዶች አምላክ ለሰው ዘር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ክፍል አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ ከአዳም የወረስነው ሞት ‘ከዲያብሎስ ሥራዎች’ አንዱ ሲሆን የአምላክ ልጅ በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ያስወግደዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው” ሲል ጽፏል።—1 ዮሐ. 3:8

በተወሰነ ደረጃ መጨነቅ ያለ ነው

4. የይሖዋ አገልጋዮች በተወሰነ ደረጃ ስለ ጤንነታቸው መጨነቃቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ሆኖም የትኛውን ሐቅ ይገነዘባሉ?

4 በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች ሁሉ ላይ የሚደርሰው ከጤና ማጣትና ከእርጅና ጋር ተያይዞ በሚመጣው ችግር ይሠቃያሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ስለ ጤንነታችን በተወሰነ ደረጃ መጨነቃችን የሚጠበቅ ነገር ከመሆኑም በላይ ጠቃሚም ነው። ምክንያቱም ይሖዋን ‘በፍጹም ኀይላችን’ ማገልገል እንፈልጋለን። (ማር. 12:30) ይሁንና መጠነኛ ጤንነት እንዲኖረን ለማድረግ መጣራችን ተገቢ ቢሆንም እውነታውን መቀበል እንዲሁም የእርጅናን ሂደት ለማዘግየት ወይም ፈጽሞ በበሽታ ላለመያዝ ማድረግ የምንችለው ነገር በጣም ውስን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።

5. ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የነበረባቸውን በሽታ ከተቋቋሙበት መንገድ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

5 ብዙ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከጤና ማጣት ጋር መታገል ግድ ሆኖባቸዋል። አፍሮዲጡ ከእነዚህ አንዱ ነበር። (ፊልጵ. 2:25-27) የሐዋርያው ጳውሎስ ታማኝ ባልደረባ የሆነው ጢሞቴዎስ በየጊዜው የሚነሳበት የሆድ ሕመም ስለነበረበት ጳውሎስ “ጥቂት የወይን ጠጅ” እንዲጠጣ መክሮታል። (1 ጢሞ. 5:23) ጳውሎስ ራሱም  ቢሆን ‘የሥጋ መውጊያውን’ ችሎ ለመኖር ተገድዶ ነበር፤ ይህም በወቅቱ ፈውስ ያልተገኘለት የዓይን ሕመም ወይም ሌላ ዓይነት በሽታ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 12:7፤ ገላ. 4:15፤ 6:11) ጳውሎስ ‘የሥጋ መውጊያውን’ በተመለከተ ይሖዋን ተማጽኖ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:8-10ን አንብብ።) አምላክ ጳውሎስን ‘ከሥጋ መውጊያው’ በተአምር አላዳነውም። ከዚህ ይልቅ በሽታውን መቋቋም የሚችልበት ብርታት ሰጥቶታል። በመሆኑም ጳውሎስ ከነበረበት ድካም የተነሳ የይሖዋ ኃይል በግልጽ ሊታይ ችሏል። ታዲያ ይህ ሁኔታ ለእኛ የያዘው ትምህርት ይኖራል?

ስለ ጤና ጉዳይ ከልክ በላይ አትጨነቁ

6, 7. ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ ከመጨነቅ መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?

6 እንደሚታወቀው የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና ተቋማት የሚሰጡትን እርዳታም ሆነ የተለያዩ የሕክምና ዓይነቶችን ይቀበላሉ። ንቁ! መጽሔታችን ጤና ነክ የሆኑ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዞ ይወጣል። አንድን የሕክምና ዓይነት ለይተን በመጥቀስ የተሻለ ነው የሚል አስተያየት ባንሰጥም የሕክምና ባለሙያዎች የሚያደርጉልንን እርዳታም ሆነ የሚያሳዩንን የትብብር መንፈስ እናደንቃለን። እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ጤንነት የሚገኘው ገና ወደፊት እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ የጤንነታችን ጉዳይ ከልክ በላይ አእምሯችንን እንዲቆጣጠረው ወይም ነጋ ጠባ እንዲያስጨንቀን ከመፍቀድ መቆጠባችን ጥበብ መሆኑን እናውቃለን። ሕይወት የአሁኑ ብቻ እንደሆነ ከሚያስቡትና በዚህም ምክንያት ከሕመማቸው ለመዳን ማንኛውንም ዓይነት ሕክምና ከመሞከር ወደኋላ ከማይሉት እንዲሁም “ያለ ተስፋ” ከሚኖሩት የዓለም ሰዎች የተለየ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። (ኤፌ. 2:2, 12) ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ከጸናን “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም ቃል በገባልን አዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ እርግጠኛ ስለሆንን የአሁኑን ሕይወታችንን ለማዳን ስንል የይሖዋን ሞገስ የሚያሳጣ አንዳች ነገር ላለማድረግ ቆርጠናል።—1 ጢሞ. 6:12, 19፤ 2 ጴጥ. 3:13

7 ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ ከማሰብ የምንርቅበት ሌላም ምክንያት አለን። ስለ ጤንነታችን ከሚገባው በላይ መጨነቃችን ራስ ወዳዶች እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አደጋ በሚመለከት የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ሲያስጠነቅቅ “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” ብሏል። (ፊልጵ. 2:4) ለራሳችን ጤንነት አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረጋችን ተገቢ ቢሆንም ለወንድሞቻችንና ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ያለን ልባዊ አሳቢነት ለአካላዊ ጤንነታችን ከልክ በላይ ከመጨነቅ እንድንቆጠብ ያስችለናል።—ማቴ. 24:14

8. ስለ ጤንነታችን ከሚገባው በላይ መጨነቅ ወደ ምን ሊመራን ይችላል?

8 አንድ ክርስቲያን ካልተጠነቀቀ ለጤንነቱ የሚሰጠው ትኩረት በሕይወቱ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ሊይዝና ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ችላ ሊል ይችላል። በተጨማሪም ከሚገባው በላይ ስለ ጤንነት መጨነቅ አንዳንድ የአመጋገብ ሥርዓቶች፣ የሕክምና ዓይነቶች ወይም እንደ ቫይታሚን ያሉ ምግብ ነክ መድኃኒቶች ያላቸውን ጠቀሜታ በተመለከተ የግል አስተያየታችንን ሌሎች እንዲቀበሉ ለማስገደድ ሊገፋፋን ይችላል። በዚህ ረገድ ጳውሎስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ በማወቅ እስከ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንከን የማይገኝባችሁ [ሁኑ]” ሲል በሰጠው ምክር ውስጥ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ልብ በሉ።—ፊልጵ. 1:10 NW

ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

9. ቸል ልንላቸው ከማይገቡ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ምንድን ነው? ለምንስ?

9 ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለይተን ለማወቅ ጥረት የምናደርግ ከሆነ መንፈሳዊ ፈውስ በሚያስገኘው ሥራ በንቃት እንሳተፋለን። ይህ ሥራ የሚከናወነው የአምላክን ቃል በመስበክና በማስተማር ነው። ይህ አስደሳች ሥራ ለእኛም ሆነ ለምናስተምራቸው ሰዎች ጥቅም ያስገኛል። (ምሳሌ 17:22፤ 1 ጢሞ. 4:15, 16) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች አልፎ አልፎ ከባድ የጤና እክል ስላለባቸው መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚገልጹ ርዕሶችን ይዘው ይወጣሉ። አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ርዕሶች ላይ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው ክርስቲያኖች፣ ሌሎች ሰዎች ይሖዋንና እሱ የሰጣቸውን አስደናቂ ተስፋዎች እንዲያውቁ ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸው የራሳቸውን ችግር ተቋቁመው እንዲኖሩ ወይም ለጊዜውም ቢሆን ችግራቸውን እንዲረሱ እንዴት እንደረዳቸው የሚገልጹ ሐሳቦች ይወጣሉ። *

10. የምንመርጠው የሕክምና ዓይነት በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ የሆነው ለምንድን ነው?

 10 እያንዳንዱ በዕድሜ የጎለመሰ ክርስቲያን አንድ ዓይነት የጤና እክል ሲያጋጥመው ይሻለኛል የሚለውን የሕክምና ዓይነት በመምረጥ ረገድ ‘የራሱን ሸክም መሸከም’ ይኖርበታል። (ገላ. 6:5) ይሁን እንጂ የምንመርጠው የሕክምና ዓይነት ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይነካዋል። ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለን አክብሮት ‘ከደም እንድንርቅ’ እንደሚያደርገን ሁሉ ለአምላክ ቃል የምንሰጠው ከፍ ያለ ግምትም መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትልብን ወይም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ከሚችል የሕክምና ዓይነት እንድንርቅ ይገፋፋናል። (ሥራ 15:20) አንዳንድ ምርመራዎችና ሕክምናዎች የሚከናወኑበት መንገድ ከምትሐታዊ ድርጊት ጋር ይመሳሰላል። ይሖዋ ወደ “ምትሐታዊ ኃይል” ወይም ወደ መናፍስታዊ ድርጊቶች ዞር ያሉ ከሃዲ እስራኤላውያንን አውግዟል። “ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤ ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ፤ የወር መባቻ በዓላችሁን፣ ሰንበቶቻችሁን፣ ጉባኤያችሁንና በክፋት [“በምትሐታዊ ኃይል፣” NW] የተሞላውን ስብሰባችሁን መታገሥ አልቻልሁም” ብሎ ነበር። (ኢሳ. 1:13) በምንታመምበት ጊዜ ጸሎታችን እንዲታገድ የሚያደርግ ወይም ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና አደጋ ላይ የሚጥል አንዳች ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ እንዳለብን የታወቀ ነው።—ሰቆ. 3:44

ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ’ አስፈላጊ ነው

11, 12. የሕክምና ዓይነት በምንመርጥበት ጊዜ ‘ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 በምንታመምበት ጊዜ ይሖዋ በተአምር ይፈውሰናል ብለን መጠበቅ ባንችልም እንኳ የሕክምና ዓይነት በምንመርጥበት ጊዜ ጥበብ እንዲሰጠን መጸለይ እንችላለን። በዚህ ረገድ ምርጫ ስናደርግ በቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችና በጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መመራት ይኖርብናል። ያጋጠመን የጤና እክል አሳሳቢ በሚሆንበት ጊዜ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” በሚለው የምሳሌ 15:22 ጥቅስ መሠረት የሚቻል ከሆነ ከአንድ በላይ የሕክምና ባለሙያዎችን ማማከራችን ጥበብ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር” እንዲኖሩ አሳስቧቸዋል።—ቲቶ 2:12 NW

12 ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ዘመን የኖረችው በበሽታ ትሠቃይ የነበረችው ሴት የደረሰባት ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። በማርቆስ 5:25, 26 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለ መድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር።” ኢየሱስ ይህችን ሴት የፈወሳት ከመሆኑም ሌላ ርኅራኄ አሳይቷታል። (ማር. 5:27-34) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመዳን ካላቸው ከፍተኛ ምኞት የተነሳ ንጹሕ የሆነው አምልኮ ከሚመራባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረኑ የምርመራ ወይም የሕክምና ዓይነቶችን ለመምረጥ ተፈትነዋል።

13, 14. (ሀ) ሰይጣን የምንመርጠውን የሕክምና ዓይነት በመጠቀም ንጹሕ አቋማችንን ሊያጎድፍ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ከምትሐታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ሊኖረው ከሚችል ማንኛውም ድርጊት መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

13 ሰይጣን እኛን ከእውነተኛው አምልኮ ለማራቅ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። አንዳንዶችን ለማሰናከል የጾታ ብልግናንና ፍቅረ ንዋይን እንደሚጠቀም ሁሉ በምትሐታዊና በመናፍስታዊ ኃይሎች ከሚከናወኑ ሕክምናዎች የማይለዩ አጠያያቂ ሕክምናዎችን እንዲከታተሉ በማድረግም የአንዳንዶችን ንጹሕ አቋም ለማጉደፍ ይሞክራል።  ይሖዋ “ከክፉው” እና ከማንኛውም ዓይነት “ክፋት” እንዲያድነን እንጸልያለን። ከምትሐታዊና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ሊኖረው ለሚችል ማንኛውም ድርጊት ራሳችንን በማጋለጥ በሰይጣን መዳፍ ውስጥ መውደቅ አይኖርብንም።—ማቴ. 6:13፤ ቲቶ 2:14

14 ይሖዋ እስራኤላውያንን ከሟርትና ከአስማት እንዲርቁ ነግሯቸው ነበር። (ዘዳ. 18:10-12) ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋ ሥራዎች” ብሎ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል “መናፍስታዊ ድርጊት” ይገኝበታል። (ገላ. 5:19, 20 NW) ከዚህም በላይ “አስማተኞች” ወይም መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች በይሖዋ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ቦታ አይኖራቸውም። (ራእይ 21:8) ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያለው ማንኛውም ነገር በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ እንደሆነ ግልጽ ነው።

‘ምክንያታዊነታችሁ የታወቀ ይሁን’

15, 16. ከሕክምና ምርጫ ጋር በተያያዘ ጥበብ ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካልስ ምን ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል?

15 ከላይ ከተጠቀሰው አንጻር ሲታይ አንዳንድ የምርመራ ወይም የሕክምና ዓይነቶች የሚከናወኑበትን መንገድ በተመለከተ አጠራጣሪ የሆነ ነገር ካለ ብንተወው ጥበብ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ አንድ የሕክምና ዘዴ እንዴት እንደሚሠራ ማስረዳት ስላልቻልን ብቻ ሕክምናው በሆነ መንገድ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ግንኙነት አለው ማለት አይደለም። ጤናን በመንከባከብ ረገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት ለመያዝ መለኮታዊ ጥበብና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዲኖረን ያስፈልጋል። በምሳሌ ምዕራፍ 3 ላይ የሚከተለውን ማሳሰቢያ እናገኛለን፦ ‘በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል። ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ።’—ምሳሌ 3:5, 6, 21, 22

16 በተቻለ መጠን ጤነኛ ሆነን ለመኖር አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ የምናደርግ ቢሆንም ሕመማችንን ወይም እርጅና የሚያስከትለውን ጣጣ ለመቋቋም በምናደርገው ጥረት የአምላክን ሞገስ ላለማጣት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በሌሎች ጉዳዮች እንደምናደርገው ሁሉ፣ ጤንነታችንን በመንከባከብ ረገድም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን በመኖር “ምክንያታዊነታች[ን] በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ” እንዲሆን ማድረግ ይገባናል። (ፊልጵ. 4:5 NW) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል በጻፈው እጅግ አስፈላጊ የሆነ ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ከጣዖት አምልኮ፣ ከደምና ከዝሙት እንዲርቁ መመሪያ አስተላልፎ ነበር። በደብዳቤው ላይ “ከእነዚህ ዐይነት ነገሮች ብትርቁ ለእናንተ መልካም ነው” የሚል ዋስትናም ታክሎበታል። (ሥራ 15:28, 29) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?

ፍጹም ጤንነት የምናገኝበትን ጊዜ በማሰብ ለራሳችን ሚዛናዊ እንክብካቤ ማድረግ

17. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ በመከተላችን በአካላዊ ሁኔታ የተጠቀምነው እንዴት ነው?

17 እያንዳንዳችን ‘መጽሐፍ ቅዱስ ደምና ዝሙትን በተመለከተ የያዘውን መሠረታዊ ሥርዓት በጥብቅ መከተሌ መልካም እንደሆነልኝ እገነዘባለሁ?’ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ነው። በተጨማሪም “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን” ለማንጻት ጥረት በማድረጋችን ያገኘናቸውን ጥቅሞች አስቡ። (2 ቆሮ. 7:1) መጽሐፍ ቅዱስ የግል ንጽሕና አጠባበቅን በሚመለከት የያዘውን መመሪያ በጥብቅ በመከተላችን ከብዙ በሽታዎች መዳን ችለናል። መንፈሳችንንና አካላችንን ከሚያረክሱ ከትንባሆና ከዕፆች መራቃችን መልካም ሆኖልናል። በተጨማሪም በመብልና በመጠጥ ረገድ ልከኞች በመሆናችን ከጤና አንጻር ያገኘነውን ጥቅም አስቡ። (ምሳሌ 23:20ንና ቲቶ 2:2, 3ን አንብብ።) ምንም እንኳ እንደ እረፍትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመሳሰሉ ነገሮች  በጥቅሉ ለጤንነታችን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ሊኖር ቢችልም በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ጥሩ ሁኔታ ላይ ልንገኝ የቻልነው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን በማክበራችን ነው።

18. በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው? ከጤና ጋር በተያያዘስ የትኛው ትንቢት ሲፈጸም ለማየት እንጓጓለን?

18 ከሁሉ በላይ ግን ለመንፈሳዊ ጤንነታችን እንክብካቤ ማድረግና የአሁኑ ሕይወታችንም ሆነ ተስፋ በተሰጠን አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘው ‘የሚመጣው ሕይወት’ ምንጭ ከሆነው በሰማይ ካለው አባታችን ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ማጠናከር ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 4:8፤ መዝ. 36:9) አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ፣ የኃጢአት ይቅርታ በሚያስገኘው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የተሟላ መንፈሳዊና አካላዊ ፈውስ እናገኛለን። የአምላክ በግ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭ” ይመራናል፤ እንዲሁም አምላክ እንባን ሁሉ ከዓይናችን ያብሳል። (ራእይ 7:14-17፤ 22:1, 2) በመቀጠል ደግሞ “በዚያም የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም” የሚለው አስደሳች ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢሳ. 33:24 የ1954 ትርጉም

19. ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጤንነታችንን ለመንከባከብ ጥረት ስናደርግ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

19 መዳናችን መቅረቡን በእርግጠኝነት እናምናለን፤ እንዲሁም ይሖዋ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ሕመምና ሞት የሚያስቆምበትን ቀን በናፍቆት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን፣ አፍቃሪ አባታችን ‘ስለ እኛ ስለሚያስብ’ ሕመምና ሥቃይ የሚያደርስብንን መከራ ችለን እንድንኖር እንደሚረዳን እርግጠኞች ነን። (1 ጴጥ. 5:7) ለጤናችን ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ይህን የምናደርገው ግን በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ከያዘው ግልጽ መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ መሆን ይኖርበታል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በመስከረም 1, 2003 የመጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 17 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ እንደነዚህ ካሉት ርዕሶች መካከል አንዳንዶቹ ተዘርዝረዋል።

ለክለሳ ያህል

• የሰው ልጆች ለበሽታ እንዲዳረጉ ያደረገው ማን ነው? ኃጢአት ካስከተለብን መዘዝ የሚገላግለንስ ማን ነው?

• ስለ ጤንነታችን ማሰባችን ያለ ነገር ቢሆንም ከምን ነገር መቆጠብ ይኖርብናል?

• የምንመርጠው የሕክምና ዓይነት ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንዴት ይነካብናል?

• ጤንነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ዘር የተፈጠረው ለሕመምና ለእርጅና አልነበረም

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ሕዝቦች የጤና እክል ቢኖርባቸውም ከአገልግሎት ደስታ ያገኛሉ