በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ እንዳደረገው “ዲያብሎስን ተቃወሙት”

ኢየሱስ እንዳደረገው “ዲያብሎስን ተቃወሙት”

 ኢየሱስ እንዳደረገው “ዲያብሎስን ተቃወሙት”

“ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል።”—ያዕ. 4:7

1. ኢየሱስ በምድር ላይ ምን ዓይነት ተቃውሞ እንደሚያጋጥመው ያውቅ ነበር? የመጨረሻው ውጤትስ ምን ይሆናል?

ኢየሱስ ክርስቶስ ከዲያብሎስ ተቃውሞ እንደሚያጋጥመው ያውቅ ነበር። አምላክ ለእባቡ ይኸውም በእሱ ተጠቅሞ ለተናገረው ክፉና ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር “በአንተና በሴቲቱ [በይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል]፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” ብሎታል። (ዘፍ. 3:14, 15፤ ራእይ 12:9) ይህም ኢየሱስ ተቃውሞ እንደሚያጋጥመው በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ ኢየሱስን ለሰማያዊ ክብር ከሞት ስለሚያስነሳው የኢየሱስ ተረከዝ መቀጥቀጥ ወደ ምድር መጥቶ በሚሞትበት ጊዜ የሚደርስበትን ጊዜያዊ ጉዳት ያመለክታል። በአንጻሩ ደግሞ የእባቡ ራስ መቀጥቀጥ ዲያብሎስ ፈጽሞ ሊያንሰራራ በማይችልበት ሁኔታ ለሞት እንደሚዳረግ ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 2:31, 32ንና ዕብራውያን 2:14ን አንብብ።

2. ይሖዋ፣ ኢየሱስ የዲያብሎስን ተቃውሞ በተሳካ ሁኔታ እንደሚቋቋም እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው?

2 ይሖዋ፣ ኢየሱስ ምድር ላይ በሚያሳልፈው ሕይወት የተሰጠውን ሥራ በሚገባ እንደሚፈጽምና ዲያብሎስን እንደሚቃወም ሙሉ እምነት ነበረው። ይሖዋ ይህን ያህል እርግጠኛ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስን ከብዙ ዘመናት በፊት ስለፈጠረው፣ በሚገባ ስለሚያውቀው እንዲሁም “ዋና ባለሙያ” እና “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” የሆነው ይህ ልጁ ታዛዥና ታማኝ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። (ምሳሌ 8:22-31፤ ቈላ. 1:15) ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ምድር በተላከበትና ዲያብሎስ  እስከ ሞት ድረስ እንዲፈትነው በተፈቀደለት ጊዜ አምላክ አንድያ ልጁ ፈተናውን በድል አድራጊነት እንደሚወጣ እርግጠኛ ነበር።—ዮሐ. 3:16

ይሖዋ አገልጋዮቹን ይጠብቃል

3. ዲያብሎስ ለይሖዋ አገልጋዮች ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ዲያብሎስን ‘የዚህ ዓለም ገዥ’ ሲል የጠራው ሲሆን በእሱ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ደቀ መዛሙርቱም ስደት እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ዮሐ. 12:31፤ 15:20) በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም እውነተኛ ክርስቲያኖችን ይጠላቸዋል፤ ይህም የሆነው ይሖዋን ስለሚያገለግሉና ጽድቅን ስለሚሰብኩ ነው። (ማቴ. 24:9፤ 1 ዮሐ. 5:19) ዲያብሎስ በዋነኝነት የሚያነጣጥረው በመጨረሻ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ በሚገዙት ቅቡዓን ቀሪዎች ላይ ነው። በተጨማሪም ሰይጣን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የጥቃቱ ዒላማ ያደርጋል። የአምላክ ቃል “ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል” ሲል ያስጠነቅቀናል።—1 ጴጥ. 5:8

4. በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች ዲያብሎስን በተሳካ ሁኔታ እንደተቃወሙት የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

4 በድርጅት ደረጃ የይሖዋ አምላክ ድጋፍ ስላለን ዲያብሎስን በተሳካ ሁኔታ መቃወም እንችላለን። ቀጥሎ የቀረቡትን ማስረጃዎች እንመልከት፦ ባለፈው 100 ዓመት ውስጥ በታሪክ ዘመናት ከተነሱት እጅግ ጨካኝ የሆኑ አምባገነናዊ አገዛዞች አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮችን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ሞክረዋል። ይሁንና የምሥክሮቹ ቁጥር እየጨመረ መሄዱን የቀጠለ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ባሉ ከ100,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ወደ 7,000,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። ከምድር ገጽ የጠፉት የይሖዋን ሕዝቦች ያሳድዱ የነበሩት ጨካኝ አምባገነናዊ አገዛዞቹ ራሳቸው ናቸው!

5. ኢሳይያስ 54:17 በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

5 አምላክ ጥንት የነበረውን የእስራኤል ጉባኤ እንደ ሴት አድርጎ በመጥራት የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቶ ነበር፦ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው።” (ኢሳ. 54:11, 17) ይህ ተስፋ በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ በምድር ዙሪያ በሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል። (2 ጢሞ. 3:1-5, 13) ይሖዋ ከጎናችን ስለሆነ ዲያብሎስን መቃወማችንን እንቀጥላለን፤ ደግሞም የአምላክን ሕዝቦች ጠራርጎ ለማጥፋት የሚጠቀምበት ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል።—መዝ. 118:6, 7

6. የዳንኤል ትንቢት የዲያብሎስን አገዛዝ የወደፊት ዕጣ በተመለከተ ምን ይነግረናል?

6 በፍጥነት እየቀረበ ያለው የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ሲደርስ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት የሰይጣን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። ነቢዩ ዳንኤል በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በነዚያ [በእኛ ዘመን ባሉት] ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት [በሰማይ] ይመሠርታል፤ እነዚያን [አሁን ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳን. 2:44) ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ የሰይጣንም ሆነ ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች አገዛዝ ይወገዳል። ማንኛውም የሰይጣን ሥርዓት ክፍል ለዘላለም ይወገዳል፤ የአምላክ መንግሥት ደግሞ ያለምንም ተቀናቃኝ በመላው ምድር ላይ ይገዛል።—2 ጴጥሮስ 3:7, 13ን አንብብ።

7. የይሖዋ አገልጋዮች በግለሰብ ደረጃ ዲያብሎስን በተሳካ ሁኔታ መቃወም እንደሚችሉ እንዴት እናውቃለን?

7 የይሖዋ ድርጅት ጥበቃ እንደሚያገኝና በመንፈሳዊ እየበለጸገ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 125:1, 2ን አንብብ።) የእኛስ ሁኔታ እንዴት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ዲያብሎስን በመቃወም ረገድ ሊሳካልን እንደሚችል ይገልጻል። ክርስቶስ በሐዋርያው ዮሐንስ አማካኝነት የተናገረው ትንቢት እንደሚያሳየው የሰይጣን ተቃውሞ ቢኖርም ምድራዊ ተስፋ ያለው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ይተርፋል። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያመለክቱት እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ የአምላካችንና የበጉ [የኢየሱስ ክርስቶስ] ነው” በማለት ይጮኻሉ። (ራእይ 7:9-14) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰይጣንን ድል እንደሚያደርጉት የተነገረ ሲሆን ባልንጀሮቻቸው የሆኑት ‘ሌሎች  በጎችም’ ዲያብሎስን በተሳካ ሁኔታ ይቃወሙታል። (ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 12:10, 11) ሆኖም ዲያብሎስን ለመቃወም ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግና ‘ከክፉው ለመዳን’ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይጠይቃል።—ማቴ. 6:13

ዲያብሎስን በመቃወም ረገድ ፍጹም የሆነው ምሳሌ

8. ዲያብሎስ በምድረ በዳ ኢየሱስን ለማሳሳት ያቀረበው ተመዝግቦ የሚገኝ የመጀመሪያው ፈተና ምንድን ነው? ክርስቶስስ ምን ምላሽ ሰጠ?

8 ዲያብሎስ የኢየሱስን ንጹሕ አቋም ለማጉደፍ ሞክሮ ነበር። ሰይጣን፣ ኢየሱስ በምድረ በዳ ሳለ ለይሖዋ ታዛዥ እንዳይሆን ለማድረግ የተለያዩ ፈተናዎችን ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰይጣንን በመቃወም ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ከጾመ በኋላ በጣም እንደተራበና ምግብ ማግኘት እንደፈለገ የታወቀ ነው። ሰይጣን “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። ሆኖም ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ኃይል ለግል ጥቅሙ ለማዋል ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “‘ሰው ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት።—ማቴ. 4:1-4፤ ዘዳ. 8:3

9. ዲያብሎስ የተፈጥሮ ፍላጎታችንን ለመጠቀም የሚያደርገውን ጥረት መቋቋም ያለብን ለምንድን ነው?

9 በዛሬው ጊዜ ዲያብሎስ የይሖዋ አገልጋዮች ያላቸውን የተፈጥሮ ፍላጎት ለመጠቀም ይሞክራል። በመሆኑም በዚህ ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የጾታ ብልግና እንድንፈጽም የሚቀርብልንን ፈተና ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት አጠንክሮ ይናገራል፦ “ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮ. 6:9, 10) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት የሚመሩና ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች አምላክ በሚያዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም።

10. በማቴዎስ 4:5, 6 ላይ በተገለጸው መሠረት ሰይጣን የኢየሱስን ንጹሕ አቋም ለማጉደፍ የተጠቀመበት ሌላው ፈተና ምንድን ነው?

10 ቅዱሳን መጻሕፍት ኢየሱስ በምድረ በዳ ሳለ ከቀረቡለት ፈተናዎች መካከል ስለ አንዱ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፦ “ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣ በእጃቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል።”’” (ማቴ. 4:5, 6) ይህም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ማሳየት የሚችልበት ግሩም አጋጣሚ እንደሆነ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኢየሱስ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውና የእሱን ድጋፍ የማያስገኝ ተገቢ ያልሆነ የእብሪት ድርጊት ይሆን ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ በይሖዋ ዘንድ ያለውን ንጹሕ አቋም የጠበቀ ከመሆኑም ሌላ ጥቅስ በመጥቀስ መልስ  ሰጥቷል። እንዲህ ብሏል፦ “እንደዚሁም በመጻሕፍት፣ ‘እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ተጽፎአል።”—ማቴ. 4:7፤ ዘዳ. 6:16

11. ሰይጣን በምን መንገድ ሊፈትነን ይችላል? ውጤቱስ ምን ሊሆን ይችላል?

11 ሰይጣን በተለያዩ መንገዶች ክብር ለማግኘት እንድንፈልግ በማድረግ ሊፈትነን ይችላል። በአለባበስና በአበጣጠር ዓለማዊ ፋሽኖችን እንድንከተል ወይም አጠያያቂ በሆኑ መዝናኛዎች እንድንካፈል ይገፋፋን ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ችላ ብንልና ዓለምን ብንከተል መላእክት እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ከሚያስከትልብን መዘዝ ይጋርዱናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ ከፈጸማቸው ኃጢአቶች ንስሐ ቢገባም አድራጎቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ እንዲያመልጥ አልተደረገም። (2 ሳሙ. 12:9-12) ይሖዋን አግባብ ባልሆነ መንገድ አንፈትነው፤ ምናልባትም ይህን የምናደርገው ከዓለም ጋር ወዳጅነት በመመሥረት ሊሆን ይችላል።—ያዕቆብ 4:4ንና 1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።

12. በማቴዎስ 4:8, 9 ላይ የተጠቀሰው ፈተና ምንድን ነው? የአምላክ ልጅ ለፈተናው የሰጠውስ ምላሽ ምን ነበር?

12 ዲያብሎስ በምድረ በዳ የተጠቀመበት ሌላው ፈተና ለኢየሱስ የፖለቲካ ሥልጣን ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። ሰይጣን ለኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን ካሳየው በኋላ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። (ማቴ. 4:8, 9) ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ ለመውሰድና ኢየሱስ ለአምላክ ታማኝ እንዳይሆን ለማድረግ የታቀደ እንዴት ያለ መሠሪ ዘዴ ነው! በአንድ ወቅት ታማኝ የነበረው መልአክ ለመመለክ ባለው ፍላጎት ላይ በማውጠንጠኑ ኃጢአተኛ፣ ምቀኛ፣ ክፉና ፈታኝ በመሆኑ የሚታወቀው ሰይጣን ዲያብሎስ ሆነ። (ያዕ. 1:14, 15) ከዚህ በተቃራኒው ግን ኢየሱስ በሰማይ ላለው አባቱ ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል ቆርጦ ስለነበር “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” ሲል ተናግሯል። በመሆኑም ኢየሱስ ዲያብሎስን በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ በድጋሚ ተቃውሞታል። የአምላክ ልጅ የሰይጣን ዓለም ክፍል መሆን አልፈለገም፤ ደግሞም ለዚህ ክፉ መልአክ በምንም ዓይነት አምልኮ አያቀርብም!—ማቴ. 4:10፤ ዘዳ. 6:13፤ 10:20

“ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል”

13, 14. (ሀ) ዲያብሎስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ለኢየሱስ ባሳየው ጊዜ ምን ግብዣ እያቀረበለት ነበር? (ለ) ሰይጣን እኛን ለመበከል ጥረት የሚያደርገው እንዴት ነው?

13 ዲያብሎስ ለኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ሲያሳየው ከዚህ በፊት ማንም ሰው ያላገኘውን ሥልጣን ሊሰጠው እየጋበዘው ነበር። ሰይጣን፣ ኢየሱስ ያየው ነገር እንደሚያጓጓውና በምድር ላይ ተወዳዳሪ የሌለው የፖለቲካ መሪ መሆን እችላለሁ የሚል ትምክህት እንዲያድርበት እንደሚያደርገው ተማምኖ ነበር። በዛሬው ጊዜ ዲያብሎስ መንግሥታትን ሊሰጠን ግብዣ አያቀርብልንም፤ ሆኖም በምናየው፣ በምንሰማውና በምናስበው ነገር አማካኝነት ልባችንን ለመበከል ጥረት ያደርጋል።

14 ይህን ዓለም የሚቆጣጠረው ዲያብሎስ በመሆኑ በውስጡ ያለውን መገናኛ ብዙኃንም የሚቆጣጠረው እሱ ነው። ከዚህም የተነሳ ዓለም የሚያቀርባቸው የሚታዩ፣ የሚሰሙና የሚነበቡ ነገሮች በብልግናና በዓመፅ የተሞሉ መሆናቸው አያስደንቅም። ይህ ዓለም የሚያቀርባቸው ማስታወቂያዎች የግድ ለማያስፈልጉን ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ቁሳቁሶች ምኞት እንዲያድርብን ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው። በዚህ መንገድ ዲያብሎስ ዓይናችንን፣ ጆሯችንንና አስተሳሰባችንን ሊማርኩ በሚችሉ አጓጊ በሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ምንጊዜም ይፈትነናል። ይሁንና ቅዱስ ጽሑፉ የሚያወግዛቸውን ነገሮች ለማየት፣ ለመስማትና ለማንበብ ፈቃደኛ ሳንሆን ስንቀር በተዘዋዋሪ መንገድ “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ!” ያልን ያህል ነው። እንዲህ ስናደርግ የሰይጣንን ርኩስ ዓለም በማያሻማ ሁኔታና በጥብቅ በመቃወም ረገድ ኢየሱስን እንኮርጃለን። በተጨማሪም በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በምንኖርበት አካባቢ እንዲሁም በዘመዶቻችን ዘንድ የይሖዋ ምሥክሮችና የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን በድፍረት ማሳወቃችን የሰይጣን ዓለም ክፍል አለመሆናችንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ነው።—ማርቆስ 8:38ን አንብብ።

15. ሰይጣንን በመቃወም ረገድ ምንጊዜም ንቁ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

15 ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ ለአምላክ ያለውን ንጹሕ አቋም እንዲያላላ ለማድረግ ለሦስተኛ ጊዜ ያልተሳካ ሙከራ ካደረገ በኋላ “ትቶት ሄደ።” (ማቴ. 4:11) ይሁን እንጂ ሰይጣን ኢየሱስን መፈተኑን የማቆም ሐሳብ አልነበረውም፤ ምክንያቱም በሌላ ጥቅስ ላይ “ዲያብሎስም [በምድረ በዳ] ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ከእርሱ ተለየ” የሚል እናነባለን።  (ሉቃስ 4:13) ዲያብሎስን በመቃወም ረገድ ሲሳካልን ይሖዋን ልናመሰግነው ይገባል። ይሁንና ዲያብሎስ፣ የሚያመቸውን ሌላ አጋጣሚ ፈልጎ ሊፈትነን ተመልሶ ስለሚመጣ ከአምላክ የማያቋርጥ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ ሰይጣን ሊፈትነን የሚመጣው ፈተና ይገጥመናል ብለን ባሰብነው ጊዜ ላይሆን ይችላል። እንግዲያው የሚያጋጥመን ፈተና ምንም ይሁን ምን ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ረገድ በጽናት ለመቀጠል ዝግጁ በመሆን ምንጊዜም ንቁ ሆነን መኖር ይገባናል።

16. ይሖዋ የትኛውን ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ይሰጠናል? ይህን ለማግኘትስ መጸለይ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

16 ዲያብሎስን ለመቃወም በምናደርገው ጥረት እርዳታ ለማግኘት በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ይኸውም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል፤ ደግሞም ይሰጠናል። ይህ መንፈስ በራሳችን አቅም ማድረግ የማንችላቸውን ነገሮች እንድናደርግ ያስችለናል። ኢየሱስ የአምላክን መንፈስ ማግኘት እንደሚችሉ ለተከታዮቹ እንዲህ ሲል አረጋግጦላቸዋል፦ “እናንተ [ፍጹማን ባለመሆናችሁ የተነሳ በአንጻራዊ ሁኔታ] ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!” (ሉቃስ 11:13) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለያችንን እንቀጥል። ዲያብሎስን ለመቃወም ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ በዚህ ተወዳዳሪ በሌለው ኃይል እየታገዝን ድል አድራጊዎች መሆን እንችላለን። ዘወትር ልባዊ ጸሎት ከማቅረብ በተጨማሪ “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም” እንድንችል የአምላክን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ በሙሉ መልበስ ይኖርብናል።—ኤፌ. 6:11-18

17. ኢየሱስ ዲያብሎስን እንዲቃወም የረዳው የትኛው ደስታ ነው?

17 ኢየሱስ ዲያብሎስን እንዲቃወም የረዳው ሌላም ነገር አለ፤ ይህ ነገር እኛንም ሊረዳን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ [ኢየሱስ] በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” በማለት ይገልጻል። (ዕብ. 12:2) እኛም የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ፣ ቅዱስ ስሙን በማክበርና የዘላለም ሕይወት ሽልማታችንን ከፊታችን በማስቀመጥ ተመሳሳይ ደስታ ማግኘት እንችላለን። ሰይጣንና ሥራዎቹ በሙሉ ለዘላለም ሲወገዱ እንዲሁም ‘ገሮች ምድርን ወርሰው በታላቅ ሰላም ሐሤት ሲያደርጉ’ በምናይበት ጊዜ ከፍተኛ ደስታ እናገኛለን! (መዝ. 37:11) ስለዚህ ኢየሱስ እንዳደረገው ዲያብሎስን መቃወማችሁን ቀጥሉ።—ያዕቆብ 4:7, 8ን አንብብ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

• ኢየሱስ ሰይጣንን በመቃወም ረገድ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

• በምን መንገዶች ዲያብሎስን መቃወም ትችላላችሁ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዓለም ጋር ወዳጅነት መመሥረት የአምላክ ጠላት ያደርገናል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ፣ ሰይጣን የዓለምን መንግሥታት በሙሉ ሊሰጠው ያቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም