በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለተሰሎንቄ ሰዎችና ለጢሞቴዎስ የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

ለተሰሎንቄ ሰዎችና ለጢሞቴዎስ የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

 የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

ለተሰሎንቄ ሰዎችና ለጢሞቴዎስ የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

ጳውሎስ በተሰሎንቄ በነበረበት ወቅት የተቋቋመው በዚያ የሚገኘው አዲስ ጉባኤ ገና ከጅምሩ አንስቶ ስደት ሲደርስበት ቆይቷል። በዚህም የተነሳ ጢሞቴዎስ ከተሰሎንቄ መልካም ሪፖርት ይዞ ሲመጣ ጳውሎስ በመደሰቱ በዚያ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ለማመስገንና ለማበረታታት ደብዳቤ ጻፈላቸው፤ በዚህ ወቅት ጢሞቴዎስ በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የነበረ ይመስላል። በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ የሚገመተው ይህ ደብዳቤ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች መካከል የመጀመሪያው ነው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ሁለተኛውን ደብዳቤ ጻፈላቸው። በዚህኛው ደብዳቤው ላይ፣ አንዳንዶች የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ያረመ ከመሆኑም ሌላ ወንድሞች በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ አሳስቧቸዋል።

ጳውሎስ እነዚህን ደብዳቤዎች ከጻፈ ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ በመቄዶንያ የነበረ ሲሆን ጢሞቴዎስ ደግሞ በኤፌሶን ነበር። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን እንዲቆይ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር የሚያደርገውን መንፈሳዊ ውጊያ እንዲገፋበት የሚያበረታታ ደብዳቤ ጽፎለታል። በ64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሮም በእሳት መጋየቷን ተከትሎ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ የስደት ማዕበል ተነሳ፤ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ የጻፈው በዚህ ወቅት ነበር። ይህ ደብዳቤ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች የመጨረሻው ነው። በዛሬው ጊዜ እኛም ጳውሎስ በጻፋቸው በእነዚህ አራት ደብዳቤዎች ላይ ከሰፈረው ማበረታቻና ምክር ጥቅም እናገኛለን።—ዕብ. 4:12

“ነቅተን እንኑር”

(1 ተሰ. 1:1 እስከ 5:28)

ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ‘ከእምነት ለሆነው ሥራቸው፣ ከፍቅር ለመነጨው ድካማቸውና ለጽናታቸው’ አመስግኗቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ለእሱ ‘ተስፋውና ደስታው እንዲሁም አክሊሉ’ እንደሆኑ ነግሯቸዋል።—1 ተሰ. 1:3፤ 2:19

ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚገኙትን ክርስቲያኖች በትንሣኤ ተስፋ እርስ በርስ እንዲጽናኑ ካበረታታቸው በኋላ “ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ የጌታም ቀን እንዲሁ እንደሚመጣ” ነግሯቸዋል። ከዚያም ‘ነቅተው እንዲኖሩ’ እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲጠብቁ መክሯቸዋል።—1 ተሰ. 4:16-18፤ 5:2, 6 NW

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

4:15-17—‘ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል በደመና የሚነጠቁት’ እነማን ናቸው? ይህስ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ ጥቅስ የሚናገረው፣ ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት ስለሚኖሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች በማይታይ ሁኔታ በሰማይ ‘ጌታ ኢየሱስን ይቀበሉታል።’ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን መሞትና መንፈሳዊ ፍጥረት ሆነው መነሳት ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 6:3-5፤ 1 ቆሮ. 15:35, 44) በአሁኑ ወቅት ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ ስለተገኘ በዛሬው ጊዜ የሚሞቱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደሞቱ ‘ይነጠቃሉ’ ማለትም ወዲያውኑ ከሞት ይነሳሉ።—1 ቆሮ. 15:51, 52

5:23 NW—ጳውሎስ፣ የወንድሞች ‘መንፈስ፣ ነፍስና አካል ተጠብቆ እንዲቆይ’ ያቀረበው ጸሎት ምን ትርጉም አለው? ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚገኙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጨምሮ በርካታ አባላትን ስላቀፈው የክርስቲያን ጉባኤ መንፈስ፣ ነፍስና አካል መናገሩ ነበር። ጳውሎስ ጉባኤው ተጠብቆ እንዲቆይ በደፈናው ከመጸለይ ይልቅ የጉባኤው ‘መንፈስ’ ማለትም የጉባኤው አባላት አስተሳሰብ እንዲጠበቅ ጸልዮአል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ ጉባኤው ‘ነፍስ’ ወይም ሕልውና እንዲሁም ስለ ጉባኤው ‘አካል’ ማለትም እንደ አንድ አካል ስለሚቆጠረው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ጸልዮአል። (1 ቆሮ. 12:12, 13) ይህ ጸሎት ጳውሎስ ለጉባኤው በጥልቅ እንደሚያስብ ጎላ አድርጎ ያሳያል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:3, 7፤ 2:13፤ 4:1-12፤ 5:15:- ምክር በምንሰጥበት ጊዜ ሰዎች ላደረጉት ነገር ከልብ የመነጨ ምስጋና  ማቅረባችንና የበለጠ እንዲሠሩ ማበረታቻ መስጠታችን ምክሩ ተቀባይነት እንዲኖረው ይረዳል።

4:1, 9, 10:- የይሖዋ አምላኪዎች መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል።

5:1-3, 8, 20, 21:- የይሖዋ ቀን እየቀረበ ሲሄድ “እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር ለብሰን፣ የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቊር ደፍተን” እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን ጠብቀን መኖር ይገባናል። ከዚህም በላይ የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል።

“ጸንታችሁ ቁሙ”

(2 ተሰ. 1:1 እስከ 3:18)

በተሰሎንቄ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንዶች፣ ጳውሎስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ የጻፈውን ሐሳብ በማጣመም ‘የጌታችን መገኘት’ [NW] ደርሷል ብለው መከራከር የጀመሩ ይመስላል። ጳውሎስ ይህንን አመለካከት ለማረም ሲል ከጌታ መገኘት “አስቀድሞ” መምጣት ስላለበት ነገር ነግሯቸዋል።—2 ተሰ. 2:1-3

ጳውሎስ፣ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን “ጸንታችሁ ቁሙ፤ . . . ያስተላለፍንላችሁን ትምህርት አጥብቃችሁ ያዙ” በማለት መክሯቸዋል። እንዲሁም “ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ [እንዲለዩ]” አዟቸዋል።—2 ተሰ. 2:15፤ 3:6 የ1954 ትርጉም

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

2:3, 8—“የዐመፅ ሰው” የተባለው ማን ነው? የሚወገደውስ እንዴት ነው? ይህ “ሰው” የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት በቡድን ደረጃ ያመለክታል። አምላክ በክፉዎች ላይ የበየነውን ፍርድ የማወጅና ፍርዱ እንዲፈጸም ትእዛዝ የማስተላለፍ ሥልጣን የተሰጠው “ቃል” ተብሎ የተጠራውና የአምላክ ዋነኛ ቃል አቀባይ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐ. 1:1) በመሆኑም ኢየሱስ፣ የዐመፅ ሰውን “በአፉ መንፈስ” [የ1954 ትርጉም] ያስወግደዋል ሊባል ይችላል።

2:13, 14—ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ከመጀመሪያ አንሥቶ እንዲድኑ የተመረጡት’ እንዴት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ የተመረጡት ይሖዋ፣ የሴቲቱ ዘር የሰይጣንን ራስ እንዲቀጠቅጥ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ባሳወቀበት ጊዜ ነበር። (ዘፍ. 3:15) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ እነዚህ ክርስቲያኖች ማሟላት የሚገቧቸውን ብቃቶችና የሚያከናውኑትን ሥራ እንዲሁም የሚደርስባቸውን ፈተና ገልጿል። እነዚህን ክርስቲያኖች ‘ጠርቷቸዋል’ የሚባለው ለዚህ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:6-9:- ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽመው በክፉዎች ላይ ብቻ ነው።

3:8-12:- የይሖዋ ቀን መቅረቡ የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት እንዳንሠራ ሰበብ ሊሆነን አይገባም። ሥራ ፈት መሆናችን ሰነፎች እንዲሁም “በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ” እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል።—1 ጴጥ. 4:15

“በዐደራ የተቀበልኸውን ሁሉ ጠብቅ”

(1 ጢሞ. 1:1 እስከ 6:21)

ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ‘መልካሙን ገድል እንዲጋደል እንዲሁም እምነትና በጎ ኅሊና እንዲኖረው’ መመሪያ ሰጥቶታል። ሐዋርያው፣ በጉባኤ ውስጥ የሚሾሙ ወንዶች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን በዝርዝር አስፍሯል። ከዚህም በላይ ጳውሎስ “እግዚአብሔርን ከማያከብር ርባናቢስ አፈ ታሪክ [እንዲርቅ]” ለጢሞቴዎስ መመሪያ ሰጥቶታል።—1 ጢሞ. 1:18, 19፤ 3:1-10, 12, 13፤ 4:7

ጳውሎስ “አረጋዊውን ሰው . . . በኀይለ ቃል አትናገረው” በማለት ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል። አክሎም “በዐደራ የተቀበልኸውን ሁሉ ጠብቅ፤ እግዚአብሔርን ከማያስከብር ከከንቱ ልፍለፋና በውሸት ዕውቀት ከተባለ የተቃውሞ ፍልስፍና ራቅ” በማለት አሳስቦታል።—1 ጢሞ. 5:1፤ 6:20

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:18፤ 4:14—ጢሞቴዎስን በተመለከተ የተነገሩት ‘ትንቢቶች’ ምንድን ናቸው? ጳውሎስ በሁለተኛው የሚስዮናዊነት ጉዞው ወደ ልስጥራ በሄደበት ጊዜ ጢሞቴዎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ወደፊት ስለሚጫወተው ሚና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተነገሩ ትንቢቶች ሊሆኑ ይችላሉ። (ሥራ 16:1, 2) የጉባኤው ሽማግሌዎች እነዚህን ‘ትንቢቶች’ መሠረት በማድረግ በወጣቱ ጢሞቴዎስ ላይ ‘እጃቸውን ጭነው’ ለአንድ ልዩ አገልግሎት መርጠውታል።

2:15—ሴት “በመውለድ ትድናለች” ሲባል ምን ማለት ነው? አንዲት ሴት፣ ልጆች መውለዷና ልጆቿን መንከባከቧ እንዲሁም ቤቷን በአግባቡ ለመያዝ ጥረት ማድረጓ ‘ሥራ ፈት፣ ሐሜተኛና በሰው ጉዳይ ጣልቃ የምትገባ’ ከመሆን ‘ያድናታል።’—1 ጢሞ. 5:11-15

3:16 NW—ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር ምንድን ነው? የሰው ልጆች ለይሖዋ ሉዓላዊነት ፍጹም በሆነ መልኩ መታዘዝ መቻል አለመቻላቸው ለዘመናት ሚስጥር ሆኖ ነበር። ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ  ያለውን ታማኝነት ፍጹም በሆነ መንገድ በመጠበቅ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል።

6:15, 16 NW—ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ይሖዋ አምላክ ነው ወይስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ? ከዚህ ጥቅስ በፊት ያለው ቁጥር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ የሚናገር በመሆኑ ይህኛው ሐሳብም የሚገልጸው ስለ እሱ ነው። (1 ጢሞ. 6:14) ነገሥታትና ጌቶች ሆነው ከሚገዙ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ኢየሱስ “ብቸኛው ኃያል ገዥ” ከመሆኑም በላይ “ያለመሞትን ባሕርይ” የተላበሰው እሱ ብቻ ነው። (ዳን. 7:14፤ ሮሜ 6:9) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ በምድር ላይ ያለ ‘አንድም ሰው ሊያየው አይችልም።’

ምን ትምህርት እናገኛለን?

4:15:- ክርስቲያኖች የሆንነው በቅርብ ጊዜም ይሁን ከረጅም ጊዜ በፊት፣ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማጠናከር የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለብን።

6:2:- የእምነት ባልንጀራችን ዘንድ ተቀጥረን የምንሠራ ከሆነ ወንድማችንን በማንኛውም መንገድ መጠቀሚያ ከማድረግ ይልቅ ከጉባኤ ውጪ ላለ ሰው ከምናደርገው ይበልጥ በፈቃደኝነት ልናገለግለው ይገባል።

‘ቃሉን ስበክ፣ በጥድፊያ ስሜት አገልግል’

(2 ጢሞ. 1:1 እስከ 4:22)

ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን ከፊቱ ለሚጠብቀው አስቸጋሪ ጊዜ ለማዘጋጀት ሲል እንዲህ በማለት ጽፎለታል:- “እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንም።” ከዚህም በላይ ጢሞቴዎስን ሲመክረው “የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቃት ያለው . . . መሆን ይገባዋል” ብሎታል።—2 ጢሞ. 1:7፤ 2:24

ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን “አንተ ግን በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና” በማለት አሳስቦታል። የክህደት ትምህርቶች እየተስፋፉ ስለነበር ሐዋርያው ጳውሎስ በዕድሜ ከእሱ የሚያንሰውን የበላይ ተመልካች “ቃሉን ስበክ፣ . . . በጥድፊያ ስሜት አገልግል፤ . . . ገሥጽ፣ ውቀስ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር” ብሎታል።—2 ጢሞ. 3:14፤ 4:2 NW

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:13—“የጤናማ ትምህርት ምሳሌ” የተባለው ምንድን ነው? “ጤናማ ትምህርት” ወይም “ጤናማ ቃል” የተባሉት “ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ” የተገኙት እውነተኛ የክርስትና ትምህርቶች ናቸው። (1 ጢሞ. 6:3) የኢየሱስ ትምህርትም ሆነ ድርጊት ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ በመሆኑ “ጤናማ ትምህርት” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች በሙሉ ሊያመለክትም ይችላል። እነዚህ ትምህርቶች ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ እንድናስተውል ሊረዱን ይችላሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን ነገሮች በተግባር በማዋል ይህንን ምሳሌ ወይም ንድፍ ምንጊዜም አጥብቀን እንይዛለን።

4:13—‘የብራና መጻሕፍት’ የተባሉት ምንድን ናቸው? “ብራና” ከቆዳ የተዘጋጀ እንደ ወረቀት ያለ ለመጻፊያነት የሚያገለግል ነገር ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን የጠየቀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የተወሰኑ ክፍሎች እንዲያመጣለት ሊሆን ይችላል፤ ሐዋርያው እነዚህ ጥቅልሎች እንዲመጡለት የጠየቀው በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ለማጥናት ሲል ነው። ከእነዚህ ጥቅልሎች መካከል የተወሰኑት የተዘጋጁት በፓፒረስ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በብራና ሊሆን ይችላል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:5፤ 3:15:- ጢሞቴዎስ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ እምነት እንዲኖረው የረዳው ዋነኛ ነገር ቅዱሳን መጻሕፍትን ከልጅነቱ ጀምሮ ቤት ውስጥ መማሩ ነው፤ ይህ ወጣት የነበረው እምነት ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ወላጆች፣ ከልጆቻቸው ጋር በተያያዘ አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት እንዴት እየተወጡት እንዳሉ በቁም ነገር ማሰባቸው በጣም አስፈላጊ ነው!

1:16-18:- የእምነት ባልንጀሮቻችን ፈተና ሲያጋጥማቸው፣ ስደት ሲደርስባቸው ወይም ሲታሰሩ ስለ እነሱ እንጸልይ፤ እንዲሁም እነሱን ለመርዳት አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ እናድርግ።—ምሳሌ 3:27፤ 1 ተሰ. 5:25

2:22:- ክርስቲያኖች፣ በተለይም ወጣቶች ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ እስኪያጡ ድረስ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ በሙዚቃ፣ በመዝናኛ፣ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች፣ ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ፣ ቁም ነገር በሌላቸው ጭውውቶችና እነዚህን በመሳሰሉት ነገሮች መጠመድ አይኖርባቸውም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች መካከል የመጨረሻው የትኛው ነው?